Thursday, February 27, 2014

“የህወኀት ዓላማ ግቡን አልመታም”

አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ፤ ከህወኀት መስራቾች አንዱ)
የካቲት 11 ይዛችሁ የተነሳችሁት አላማ ምን ነበር?
እኛ በዛን ወቅት ይዘነው የተነሳነው አላማ፣ ደርግን በሰላማዊ መንገድ መጣል ስለማይቻል፣ በትጥቅ ትግል ገርስሰን እንደ መሬት ላራሹ ያሉ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ ነበር፡፡ የመጀመሪያ አቋማችን የዘውዳዊውንና የደርግን ህገመንግስት መቀየር የሚል ሲሆን አቋሙ በማኒፌስቶ ፅንሰ ሀሳብ ላይ የተነደፈ አልነበረም፡፡ በቁርጥራጭ ወረቀትና በቃል ነበር የተያዘው፡፡ በሶስትና አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ስልሳ ሰባት ሰው ትግሉን ተቀላቀለ፡፡ መጀመሪያ ላይ ሃገራዊ፣ ብሄራዊና መደባዊ ትግል በማካሄድ ህዝባዊ መንግስት መመስረት የሚል ዓላማ የነበረ ሲሆን ከአመራሩ አካባቢ ደግሞ “እኛ የምንታገለው ከአማራ ቅኝ ገዢዎች ነፃ ለመውጣት ነው፤ ስለዚህ ዓላማችን ነፃ ሪፐብሊክ ትግራይን መመስረት ነው” የሚሉ ሀሳቦች መፍለቅ ጀመሩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ሃሳቡ በህወኀት መሪዎችና ለእነሱ ቅርበት በነበራቸው ታጋዮች ተረቀቀና በማኒፌስቶ ወጣ፡፡ አቶ ስዩም መስፍን ሱዳን ውስጥ አሳትመው አመጡት፡፡

አቶ ስዩም መስፍን የትግራይ ሪፐብሊክን በመመስረት ያምኑ ነበር?
አቶ ስዩምና አቶ አባይ ፀሃዬ ማኒፌስቶውን ከማርቀቅና ከማሳተም ጀምሮ እጃቸው ነበረበት። አቶ ስዩም መስፍን ስለሚያምንበት ሱዳን ወስዶ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በትግርኛ አሳትሞ አመጣው፡፡ ለታጋዮች እንዲሁም ወደ ከተማም ተሰራጨ፡፡ ማኒፌስቶው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ከባድ ቁጣንም ቀስቅሷል፡፡ በተለይ በታጋዮች ዘንድ  “እንዴት ተብሎ ትግራይ ነፃ ሪፐብሊክ ትሆናለች!?” የሚል ጥያቄ አስነሳ፡፡ “ከአማራ ቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት የሚባለው--- እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይ?!” የሚል ተቃውሞ ፈጠረ፡፡ ከዚያም የህወኀት አመራር “የነፃ ሪፐብሊክ ትግራይ” የሚለውን ነገር ሰርዣለሁ አልሰረዝኩም ሳይል ዝም ብሎ ተቀመጠ፡፡
በ1977 ዓ.ም በማሌሊት ጉባኤ፣ ከብአዴንና ከህወኀት ታጋዮች ጥያቄ ሲነሳ፣ ወዲያውኑ አስተካክለነዋል አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ  ይሄ ጉዳይ አልተነሳም፡፡ የመጀመሪያ አላማችን “ብሄራዊ መደባዊ ገዢዎችን በመገርሰስ ህዝባዊ መንግስት እንመሰርታለን” የሚለው ጠነከረና የትግራይ ሪፐብሊክ መመስረት የሚለውን እያድበሰበሱት ሄዱ፡፡
ህወኃት የተነሳለትን አላማ አሳክቷል ማለት ይቻላል?
ወታደራዊ ድል አግኝቷል፡፡ ፖለቲካዊ ድል ግን አላገኘም፡፡ ለምን ቢባል? ይዞት የተነሳው ዓላማ ሰብዓዊ መብትን ማስከበር፤ የብዙሃን ፓርቲ ሥርዓትን ማስፈን፣ ዲሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ማጽደቅ፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ነፃ ምርጫ፣ የዜጎችን ነፃና ሰብዓዊ መብት መጠበቅ የሚል ነበረ፡፡ ይሄ መቶ በመቶ ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ ህወሃት በትጥቅ ትግል ጊዜም ቢሆን ከራሱ አስተሳሰብ ውጪ ለሚተነፍስ ሁሉ (ልክ ደርግ እንደሚለው) “እምቢ ላለ ጥይት አጉርሰው” ይል እንደነበር ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ደርግ ከተደመሰሰ በኋላ ለስሙ የብዙሃን ፓርቲ ተባለ እንጂ በሀቀኛ መንገድ እውን አልተደረገም፡፡
በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች ቢቋቋሙም በ97 ዓ.ም እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል። አሁን ደግሞ ነገሩ ብሶበታል፡፡ የተለየ ፖለቲካዊ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙና የብዙሃን ፓርቲ ስርአት እንዳይጠናከር እያደረገ ነው፡፡ ለህወኀት የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸባሪዎችና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ናቸው፡፡
ጋዜጠኞችን ማሰሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ማሰቃየቱና ማፈኑ ህወሃት ብዙሃነትን እንደማያምን አመላካች ነው፡፡ የግለሰብ መብትን ከመጀመሪያውም አያምንበትም ነበር፡፡ አሁን የእኔ ጥያቄ  “ኢትዮጵያን እንዴት እናድናት?” ነው፡፡ ከህወሃት ውጪ ለዚች ሀገር ማንም የላትም የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ አጋር ድርጅቶች እና ወዳጅ ድርጅቶች የሚባሉት ከህብረተሰብ ፍላጎት በመነጨ የተፈጠሩ ሳይሆን የህወሃት መሪዎች እንደፈለጉ ሰርተው ያመጡዋቸው ናቸው፡፡
አንዳንድ ተቃዋሚዎች፤ ህወኀት አሁንም በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነት እንዳለው ይናገራሉ። የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? በትግሉ ወቅትስ እንዴት ነበር?
በመጀመሪያ እንደዚህ ዓይነት ነገር አልነበረም። መጀመሪያ መደባዊ ትግል  ይቅደም፤ የብሄር አደረጃጀት አሁን አያስፈልግም ተብሎ ነበር፡፡ የህወሃት መሪዎች ግን ብሄራዊ የትግል ታክቲክ ነው የሚያዋጣን ይሉ ነበር፡፡
የብሄር መብት ጥያቄን እንደ ታክቲክ ማለት ነው?
አዎ! የህወሃት የበላይነት ባይፈለግ ኖሮ ከኢህአፓ ጋር ምን ልዩነት ነበረው? ምንም ወደ ጦርነት የሚያመጣ ሁኔታ አልነበረም፡፡ የኢህአዴግ የመጨረሻው ውጤት ሲታይ ከፊውዳሊዝም የባሰ ካልሆነ በስተቀር የተቀየረ ስርዓት የለም፡፡ ያኔ ላቅ ያለ ንቃት የነበራቸው ምሁሮች ነበሩ፡፡ ትክክለኛ ዲሞክራሲ ፈላጊ ቢሆን ኖሮ ከኢህፓ፣ ከኦነግና ከሌሎችም ጋር እርቅ ወርዶ ለሁሉም ህዝቦች ትክክለኛ የሆነ ስርዓት በተፈጠረ ነበር፡፡
የእርስዎ መደምደሚያ ህወኀት ይዞት የተነሣው አላማ ከፖለቲካ አንፃር ግቡን አልመታም የሚል ነው?
ግቡን አልመታም ነው የምለው፡፡ ፓርቲዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግድ፣ የፕሬስ ነፃነት የሚዘጋ፣ ጋዜጠኞችን አሸባሪ እያለ የሚያፍን፣ የፖለቲካ መሪዎችን የሚያስርና የህዝብ ተቃውሞ የማይሰማ፣ የፓርቲዎችን ስብሰባ የሚያግድ፣ የራሱን መዋቅር በመዘርጋት ነፃ ምርጫ እንዳይካሄድ የሚያደርግ--- ስርዓት በመፈጠሩ የህወኃት ዓላማ ግቡን እንዳልመታ ያመለክታል፡፡
 አስራ አንዱ የህወኀት መስራቾች ስምና ቅፅል ስም
አምባዬ መስፍን (ስዩም)
አቶ ገሠሠ አየለ (ስኡል)
አቶ ንጉስ ታዬ (ቀለበት)
ወልደሚካኤል ገ/ስላሴ (አስገደ)
አረፋይኔ ካህሳይ (ፀሃዬ ካህሳይ)
ፋንታሁን ዘረፅዮን (ገዳይ ዘረፅዮን)
ሙሉጌታ ሀጎስ (አሰፋ ሀጎስ)
አብተው ታከለ (ሚካኤል)
ገሞሬ አምባዬ ወ/ጊዮርጊስ - (ገበሬ የነበረ)
አረጋዊ በርሄ (በሪሁን በርሄ)
ዘሩ ገሠሠ (አጋዚ ገሠሠ)

No comments: