Friday, June 19, 2015

#‎ያንድ_አፈርአ_ፈሮች‬

-----------
ፍቅራችንን፤ ድንበር ወሰን ላይገድበው
ሁለት ክልል ላይመጥነው
መገዳደል ፍት ላይሆነው
በሽንፈትህ እሰይ ላልል
በሽንፈቴ እፎይ ላትል
ከቂም በቀል ፍቅር ላይበቅል
ልጅህ በጄ ለምን ይሙት
ልጄስ በጅህ ለምን ትሙት
እኔ እና አንተ እኮ:
ያንድ እናት ልጆች
ወንድማማቾች:
ያንድ አፈር አፈሮች።
ርስት አፈሩማ ይቅርም ወደዚ:
ይሂድም ወደዛ
ያው ነው የኢትዮጵያ:
ያንድ አፈር መጠሪያ
ወዲያ ካለው የቀድሞዋ:
ወዲህ ካለው የስካሁኗ
ግዳይ ጥዬ በልጅህ ደም፡ በጀግንነት ላልጠራ
ግዳይ ጥለህ በልጄ ደም: ላትፎክር ላታቅራራ
ወንድም ገለው ላይፎክሩ:
ጀብዱ ሰርተው ላይኩራሩ
ያዘን ሙሾ ሊዘምሩ


እንደማተብ የእምነት ክር: ፍቅር ድሩ ላይበጠስ
በሃዘናችን ላትዘፍኑ: በሞታችሁ ላንደንስ
ስውር አይሁን ነጭ ሴራው: ደስ አይበለው የጠላት ነፍስ
ልጅህ አይሙት በልጄ ጣት
ልጄም አይሙት በልጅህ ቀስት
እኔና አንተ እኮ ከዘመናት በፊት
በታሪክ በሃይማኖት በባህል በትውፊት
በደስታ በችግር: ስም የለሽ ስመ ጥር
በጋሻና በጦር: ጀብደኛ ባላገር
የአንድ አያቶች ዘር: የሁለት አፈር ሰፈር
ስም የለሹን ጥጋብ ስመጥር በረሃብ
እያሉ ሲተቹህ እያሉ ሲተቹን
በሙጫ ስድብ አጣብቀውን
ሲተቹን መተቸት ሲተቹህ መተቸት
እንዳለ ስናውቀው እንዳለ ስታውቁት
ካንድ እናት ተወልደህ: በሁለት አባት አድገን
ባንድ ውሃ ተራጭተን አንድ አፈር አቡክተን
ቃታ ስንሳሳብ እሺ ላይለው ልብህ: ደስ ላይለው ልቤን
እኮ እኔና አንት ዛሬ እንዲህ እንጫከን?
እኔና አንተ እኮ ያንድ እናት ልጆች
ወንድማማቾቸ ያንድ አፈር አፈሮች።
እናም ወንድም ስማኝ? ልስማህ!
ደስ አይበለው ነገር ሰሪ አንተን ከኔ ፀብ ሲያቃባ
እንዘምር ባንድ እንዝለል: ወሰን አይኑር የደም ካባ
በመሞትህ ደስ ላይለኝ: ውስጥ ልቤ እዥ ሊያነባ
የናቱ ልጅ ልጅን ገድሎ: ላያሰማ ጉሮ ወሸባ
ፍቅር እንጂ ግድባችን: ወሰን አይኑር የደም ካባ።
ይልቅስ ልንገርህ !
ኩራት ኩራቴ የሚያመፃድቀኝ የሚያመፃድቅህ
የኔም ያባቴ ነው ያንተም ያባትህ።
ከቢዘን ባስቀድስ
በጊሸን ብሰልስ
ባክሱም ብትኮራ
ብሸልል ባስመራ
ያንተ አባት አባቴ አባቴ አባትህ
የሚያመፃድቀኝ የሚያመፃድቅህ
ታሪኬ ታሪክህ
መሆኑን ስናውቀው መሆኑን ስታውቁት
በደምና ባጥንት
በስጋና ጅማት
በታሪክ በቱፌት
መንታ ናቸው ሲሉን
እኮ እንዴት ዛሬ እኔና አንተ እንዲህ እንጫከን??
በብቀላ ፀፀት በቀር
ወንድም ጥሎ ላይፎከር
ጀግና ተብሎ ሜዳይ ላይኖር
በናቴ ልጅ በመጨከን እሺ ላይለኝ የልቤ በር
ወንድ ልጄን ግዳጅ ጥለህ ላይፈታ የደም እስር
ካንድ ደብር አድገን
ባንድ አስቀድሰን
አንድ ዳዊት ደግመን
ባንድ መስኪድ ኖረን
ባንድ ሰላት አድገን
አንድ ቁርሀን ቀርተን
እኮ እንዴት ዛሬ እኔና እንተ እንዲህ እንጫከን?
ለጉዳት ተሰውቼ
ላንተ ክብር ብዙ ሞቼ
ስላንተ ነፃነት ካገርህ ደሜ አለ
በናቅፋ ተራሮች እቅፍ የታዘለ።
መጎዳቴን እንቢ ብለህ
ስለ ክብሬ ብዙ ሞተህ
የሰጠኸኝ ንፁህ ደምህ
ያንተም አፅም አድዋ አለ
ለጡቢያ ለፃነት ስለኔ የዋለ።
መንታ ናቸው ሲሊን
ፍቅር ናቸው ሲሉን
እያወቁት ልቡናቸን
ሁለት ክልል ላይመጥነን
ሁለት ወሰን ላይገድበን
መገዳደል ፍትህ ላይሆነን
በሽንፈት ስንዘምር በለው ያሉ
ሲታዘቡን ነጭ ሴራ መጣን ሊሉ
ስጋ ክንድህ ሲደማብን
ልቦናችን ሊያዝንብን
ባለም ዜና ድላችንን
ደም ጥማት ነው ብለው ሊሉን
ልጅህ በጄ ለምን ይሙት
ልጅህስ በጅህ ለምን ትሙት።
ስማኝ ወገን!
ደስ አይበለው ነገር ሰሪ አንተን ከኔ ፀብ ሲያቃባ
ስውር አይሁን ነጭ ሴራው የሸረበው የሞት ደባ
እንዘምር ባንድ እንዝከል ወሰን አይኑር የደም ካባ
እርስት አፈሩማ ይቅርም ወደዚ
ይሂድም ወደዛ
ያው ነው የኢትዮጵያ
ያንድ አፈር መጠሪያ
ወድያ ካለው የቀድሞዋ
ወዲህ ካለው የስካሁኑዋ
እናም በሞቱት ሞት
እናም በሞቱት ሞት
እኔና አንተ አንሙት
አኔና አንተማ ያንድ እናት ልጆች
አህትና ወንድሞች
ያንድ አፈር አፈሮች

ተፃፈ በገጣሚ ‪#‎ኤፍሬም_ስዮም‬

1 comment:

Anonymous said...

Coin Casino Online ᐈ 100+ Best Casinos List
Looking for septcasino a trustworthy online casino? Check out 인카지노 the list of top-rated 제왕 카지노 sites that use Coin Casino, with bonuses to play casino games. Rating: 3 · ‎Review by CasinoRewards