Thursday, March 14, 2013

“በጣም በሚያሳዝንና በሚዘገንን ሁኔታ... ወሲብ...”

“በጣም በሚያሳዝንና በሚዘገንን ሁኔታ... ወሲብ...”
ባህል እንደኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር መዝገበ ቃላት 1993 የህብረተሰብ አኑዋኑዋር ዘዴ፣ ወግ ፣ልምድ ፣እምነትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የመግባብያ ቋንቋ ፣አመጋገብና አለባበስ ስርአት፣ የስራ ልምድና የአኗኗር ፍልስፍና ዘይቤዎች መስመራቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ የሚደረግበት የጋራ መግባባት ነው፡፡
ልማድ ማለት አንድ ሁኔታ ወይም ሁነት ሆን ተብሎም ይሁን በአጋጣሚ በተደጋጋሚ በአንድ ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ ሲከወን ወይም ሲነገር ለዚያ ሁኔታ የሚሰጥ ስያሜ ነው ፡፡ ልማድ በመነገር ፣በመደረግ ፣በመገለጽ እና በመከወን የሚተላለፍ በዘር ፣በቀዬ በክልል፣ በስራ ፣በሀይማኖት ፣በጾታ ወይንም በእድሜ ተለይተው ሊቆሙ ለሚችሉ ቡድኖች መታወቂያ ነው፡፡ ምንጭ - መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች ...በወጣቶችና ሰቶች ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ተጽእኖ/ህዳር2004/
የአዲስ አበባ ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ
ከሌሎች ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ባደረገው ጥናት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ወጣቶችና ሴቶች ከተለያዩ ልማዳዊ ድርጊቶችና ከሌሎች በተወረሱ መጤ ባህሎች ምክንያት ከተለያዩ ጉዳቶች ላይ መውደቃቸው አጠያያቂ አለመሆኑንና በተለይም ለስነተዋልዶ ጤና ችግር እንደሚጋለጡ ያሳያል፡፡ በአዲስ አበባ ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ ሂደት መሪ የሆኑት ወ/ሮ ብሩክታይት ውብሸት ጥናቱ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ለአምዱ አዘጋጅ ገልጸዋል፡፡

“ወጣቶችና ሴቶች ለሐገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አቅም ያላቸው ትኩስ ኃይሎች መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህን ኃይሎች ወደ ስራ አስገብቶ ሙሉ በሙሉ ሐገርን እንዲጠቅሙ ለማድረግ በሚያስችለው ሂደት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምንድናቸው? የሚለውን ማጥራት አስፈላጊ በመሆኑ ጥናቱን ማድረግ አስፈላጊ ሆኖአል፡፡ በህብረተሰቡ መካከል የሚነሱ ወጣቶችን ወይንም ሴቶችን ይጎዳሉ የሚባሉ ነገሮች መኖራቸውም እሙን በመሆኑ ይህንን በእንጭጩ ለመቅጨትና ሁኔታዎችን ወደ ትክክለኛው መስመር ለማስገባት እንዲቻል የሚመለከታቸውን መስሪያ ቤቶች ባካተተ መልኩ ሰፋ ያለ ጥናት ተደርጎአል፡፡ በጥናቱም የችግሩ ምንጭ ምንድነው? ችግሩን ለመፍታትስ ምን መደረግ አለበት? እነማን ምን ድርሻ አላቸው? ህብረተሰቡስ በምን መልክ የመፍትሔው አጋዥ ኃይል ይሆናል የሚለውን በስፋት ያጠነጠነ የጥናት ውጤት ነው”
አቶ ስንታየሁ ደመቀ በአዲስ አበባ ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ወጣቶችን የማሳተፍና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ መሪ እና የጥናቱ አስተባባሪ እንደሚገልጹት...
“በአዲስ አበባ 2739551 ሁለት ሚሊየን ሰባት መቶሰላሳ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ሀምሳ አንድያህል ነዋሪዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም 1161988 አንድ ሚሊየን አንድ መቶ ስድሳ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ስምንት ያህሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከ72 ኀ በላይ የሆኑት የከተማው ነዋሪዎች ሴቶችና ወጣቶች ቢሆኑም ከቁጥራቸው አንጻር ለሀገር እድገት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡
ለዚህም እንደምክንያት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ምክንያቶች መካከል ለሱስ አስያዥ እጾች እና የአልኮሆል መጠጦች ተጠቃሚነትና ለመጤ ባህል ተጋላጭ መሆን ነው፡፡ ሺሻ ማጨስ ፣ጫት መቃም ፣ቁማር ፣የህገወጥ ቪድዮ ማሳያ፣ የቀንና የሌሊት ጭፈራ፣ የራቁት ዳንስ፣ የግብረሰዶም ተመሳሳይ ጾታ ወሲብ መፈጸሚያና ጥንቃቄ የጎደለው ግልጽ ወሲብ መፈጸሚያ ቦታዎች መስፋፋት የወጣቱን ስነልቡና ከሚሰልቡት አስከፊ የአኑዋኑዋር ባህሪያት ናቸው፡፡ እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ በአስሩም ክፍለከተማዎች ወደ 3691 ሶስት ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና አንድ የሚደርሱ ቤቶች ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት ማከናወኛ ሆነው ይገኛሉ፡፡ የተገለጹት ልማዶች ወጣቶችን ለተለያዩ የጤና ችግሮች ሊዳርጉ የሚችሉ ሲሆን በተለይም ላልተፈለገ እርግዝና ለአባላዘር በሽታዎች እንዲሁም ለኤችአይቪ ኤይድስ ሊጋለጡ የሚችሉባቸው ባህሪያት መሆናቸውም ግልጽ ነው”
በጥናቱ ላይ እንደታየው ለመጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች የሚያጋልጡ ምክንያቶች ማህበራዊ የቤተሰብና የጉዋደኛ ተጽእኖ ፣የት/ቤትና የቤተሰብ የጋራ ቁጥጥር መላላት ስነልቡናዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና አለም አቀፋዊነት የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ መረቦች የአላስፈላጊ ድርጊቶች መፈጸሚያ ቦታዎች መስፋፋት ሲሆኑ ከዚህ ጋር በተያያዘም የፖሊስና የህግ ክፍተትና ተፈጻሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡
አቶ ስንታየሁ ደመቀ እንደሚያብራሩት-
“መጤ ከሚባሉት ባህሎች መካከል አለምአቀፋዊነት ሲባል በኢንተርኔት አማካኝነት የሚገኙ መረጃዎችን መቀባበል ይገኝበታል፡፡ አብዛኛው ወጣት በሚጠቀምበት (Facebook) ገና ጥናቱ ሲጀመር አንዲት ሴት በምናብ እንድትፈጠር ተደረገች፡፡ ከዚያች የፈጠራ ሴት ጋር የተለያዩ ሰዎች ውይይት እንዲያደርጉ መንገድ የተከፈተ ሲሆን ገና ሶስት ሳምንት ሳይሆነው ወደ ስምንት መቶ ሀምሳ የሚሆኑ ሰዎች ለጉዋደኝነት ጠይቀዋታል፡፡ አብዛኛዎቹ ሰዎችም ይልኩት የነበረው መልእክት ስለቁንጅናዋ፣ እንደሚወዱዋትና ጉዋደኛ እንዲሆኑዋት የሚገልጡ ሲሆን አንዳንዶች እንዲያውም በግልጽ የወሲብ ጥያቄ የሚያቀርቡበት ገጽ ሆኖ ነበር፡፡ አንዳንድ ጥያቄ አቅራቢዎች እራሳቸውን አጋልጠው ለዚህች የምናብ ሴት የስልክ ቁጥሮቻቸውንና የራሳቸውን ምስል ይልኩ ነበር፡፡እንደዚህ ያለውን መልእክት ይልኩ የነበሩት ሰዎች ማንነት ሲፈተሸ ትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ፣ጠቀም ያለ የወር ገቢ ያላቸው፣ በኃላፊነት ደረጃ የሚሰሩ ሰዎች ይገኙበት ነበር፡፡
ከዚህ ምላሽ የጥናት ቡድኑ የተረዳው ነገር ይህች የምናብ ሴት በዚህ በአጭር ጊዜ እንደዚህ ያለ ምላሽ ካገኘች እውነተኛዎቹ ሴት ወጣቶች ምን ያህል መሰናክል ይገጥማቸዋል የሚለውን ለመገመት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ የሚማሩ ተማሪዎችን አነጋግረን በዚህ መልክ ችግሩ እንደሚገጠማቸው ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ክኖሎጂውን በትክክለኛው መንገድ ባለመጠቀማችን ለችግር መዳረጉ ወይንም ባልተገባ መልኩ ተጠቃሚውን ወደአጉዋጉል መንገድ መክተቱ ስለማይቀር ይህም ከመጤ ባህሎች እንደ አንዱ ሊፈረጅ የሚችል ነው...”
ወጣቶችንና ሴቶችን ለችግር ይዳርጋሉ ከተባሉት መጤ ባህሎችና ልማዶች መካከል የጭፈራ ቤቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እንደ አቶ ስንታየሁ መረጃ...
“ጭፈራ ቤቶቹ የቀን የሌሊትና የራቁት በመባል ሊለዩ ይችላሉ፡፡ የቀን ጭፈራ ቤት የሚባሉት እድሜያቸው ከ18/አመት በታች የሆኑ ወንድና ሴት ሕጻናት የሚዝናኑበት ነው፡፡
የጥናት ቡድኑ በአዲስ አበባ አራት ክፍለ ከተሞች ላይ የሚገኙ የቀን ጭፈራ ቤቶችን ለመመልከት የበቃ ሲሆን ቦታዎቹም አራዳ ፣ቂርቆስ ፣ቦሌና የካ ክፍለከተማዎች ናቸው፡፡ በቦሌ ድልድይ ጀርባ እና በቦሌ ፊትለፊት ጎዳናዎች እንዲሁም በፒያሳ በቀድሞ ትግራይ ሆልና አካባቢው ፣ በንግድ ስራ ኮሌጅ ፣22 ማዞሪያ እና በራስ መኮንን ድልድይ አካባቢዎች በቡድኑ ይበልጥ ዳሰሳ የተደረገባቸው ናቸው፡፡ ድርጊቱ በጣም ዘግናኝ በሆነ መንገድ ሲፈጸም የታየው በኮሜርስ ፣በቦሌ ፣ዲኤች ገዳ ጀርባ በራስ መኮንን ድልድይ እና በትግራይ ቀድሞ ሆል አካባቢ ነው፡፡ ሴት እና ወንድ የግል ት/ቤት ተማሪዎች እየተቀጣጣሩ ከ8-12 ሰአት የሚጨፍሩበት ሲሆን በተለይም የቀን ምርጫቸው ቅዳሜ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል፡፡
እነዚህ ከአስራ ስድስት አመት የማይበልጣቸው ሴት ሕጻናት አለባበሳቸው በአብዛኛው እራቁት በሚያሰኝ ሁኔታ ሲሆን ደረት እና ጭናቸውን አካባቢ አጋልጠው ወደጭፈራ ቤቱ ይገባሉ፡፡ የጥናት ቡድኑ ወደ አስራ ሁለት የሚሆኑ የቀን ጭፈራ ቤቶችን ለመመልከት የበቃ ሲሆን ከጭፈራ በተጨማሪም ሲጋራ እየተቀባበሉ ማጨስ ፣ለረጅም ሰአት አላስፈላጊ በሆነ መልኩ መሳሳም የሚፈጽሙ ሲሆን በተለይም በቦሌ አካባቢ ሁለት ጭፈራ ቤቶች ከአስራ አንድ ሰአት በሁዋላ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደጉዋሮ በመውጣት ሌላ ክፍያ እየፈጸሙ ለወሲብ ክፍሎችን እንደሚከራዩ ቡድኑ ተመልክቶአል፡፡ ቦታውን በትክክል መጥቀስ ባያስፈልግም በሌላው ቦታ የጥናት ቡድኑ የተመለከተው ደግሞ ከመጨፈሪያው በታች ማረፊያ ክፍል ብሎ ቀስቱ ወደ ሚያመለክተው ግራውንድ ክፍል ጥንዶቹ እየተያያዙ በመግባት በወንበር ላይ ፣በአግዳሚ ወንበር፣ ሶፋ፣ መሬት ብቻ በአጠቃላይ ምንም ቦታ ሳይመርጡ እና ክፍል ይዘጋልን ሳይሉ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የየራሳቸውን ስሜት ለማርካት ወሲብ ይፈጽማሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጭፈራ ቤቶች አካባቢ መኪና ውስጥ ጫት ይዘው የሚቀመጡ ወንዶች ሴት ሕጻናቶቹ ከጭፈራው ቤት ሲወጡ ጠብቀው ለወሲብ አገልግሎት ይዘዋቸው ይሄዳሉ”
ሴት እና ወንድ ሕጻናቱ ወደቀን ጭፈራ ቤት ሲሄዱ የሚሰጡትን ምክንያት በተመለከተ ከትምህርት ቤቶቹ የተገኘው ምላሽ እንደሚያስረዳው በተለይም የግል ትምህርት ቤቶች አርብ ከሰአት በሁዋላ በጊዜ ተማሪዎችን ስለሚለቁና በተጨማሪም ቅዳሜ ላይብረሪና አፍተር ስኩል የሚባል ፕሮግራም ስላለ ተማሪዎች ይህንን ምክንያት እየሰጡ ወላጆቻቸው የማያውቁት ቦታ ይውላሉ፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች ግን ወደቀን ጭፈራ ቤት መሄድ በራሱ ስልጣኔ ወይንም ዘመናዊነት ነው ብለው ስለሚያምኑ ለልጆቻቸው ገንዘብና መኪና ሰጥተው የሚሸኙ መኖራቸውም እውቅ ነው፡፡ እነዚህ እድሜያቸው 16-18 የማይበልጥ ሴት ሕጻናት እና ከ20/ አመት የማይበልጡ ወንዶች ተማሪዎቹ ቅዳሜን እንዝናና በሚል ከተለያዩ ት/ቤቶች እየተጠራሩ ቢበዛ ከአስራ አምስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ እየደጋገሙ ይህንን ፕሮግራም እንደሚሳተፉና በጣም በሚያሳዝንና በሚዘገንን ሁኔታ ጠጥተው ሰክረው የሚሆኑትን ከማያውቁበት ደረጃ ደርሰው ከጭፈራው ቤት ሲወጡ በወንዶች እየተወሰዱ ልቅ የወሲብ ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው የጥናት ቡድኑ ታዝቦአል፡፡
ይቀጥላል

No comments: