Thursday, February 27, 2014

የአፍሪካ መሪዎችና አማፅያን በሩሲያዊው የክላሺንኮቭ ፈጣሪ ህልፈት አዝነዋል!




    ክላሺንኮቭ (AK-47) የተባለውን ለሁሉም ሥፍራ ተስማሚና ለአጠቃቀም ምቹ የሆነ  የጦር መሣሪያ በመፈልሰፍ፣ ለመላው ዓለም “እነሆ በረከት” ያሉት ሩሲያዊው “ጀግና” ሚካሄል ክላሺንኮቭ፤ ባለፈው ሰኞ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ስሰማ ማዘኔ አልቀረም፡፡ (የአፍሪካ መሪዎችና አማፅያን ባለውለታ መሆናቸውን እንዳትረሱት!) በነገራችሁ ላይ ሰውየው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልብ ችግር ሲሰቃዩ የቆዩ ሲሆን ለአንድ ወር ያህል በሆስፒታል ተኝተው የህክምና ክትትል ቢደረግላቸውም ከመሞት አልዳኑም፡፡ እሳቸውስ የእድሜ ባለፀጋ ናቸው - በ94 ዓመታቸው ነው የሞቱት፡፡ እሳቸው በሰሩት ክላሺንኮቭ ሲጠዛጠዙ በለጋ እድሜያቸው የተቀጩ አፍሪካውያንን ራሷ አፍሪካ ትቁጥረው!!  ሚኻኤል ክላሺንኮቭ በለጋ እድሜያቸው የእርሻ መሣሪያ የመሥራት ህልም ነበራቸው፡፡ (ህልሙ ነፍስ ሳይዘራ ቀረ እንጂ!) የማታ ማታም በዝነኛው ክላሺንኮቫቸው በዓለም ላይ እህል ሳይሆን ምስቅልቅል ቀውስ ዘሩበት፡፡ በህይወት ሳሉ የጦር መሣሪያ በመስራት ለህዝቦች ደም መፋሰስ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ሰላም ይነሳቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ የተጠየቁት ሚኻኤል ክላሺንኮቭ “እኔ እንቅልፌን ስለጥጥ ነው የማድረው፡፡ መስማማት አቅቷቸው የጦርነት አማራጭን የሚወስዱት ፖለቲከኞች ናቸው ተጠያቂዎቹ” በማለት ራሳቸውን ነፃ አድርገዋል (ከደሙ ንፁህ ነኝ እንደማለት!)

    የAk -47  አባት የሆኑትን ሩሲያዊ ዜና ህልፈት ቀድሞ በሞባይል ቴክስት ያቀበለኝ ሁነኛ ወዳጄ፤ ሳምንቱን መላ አፍሪካ የሃዘን ማቅ ለብሳ እንደምትሰነብት ጠቆም አድርጐኝ ነበር፡፡ ለምን ቢሉ? የአህጉሪቷ ህልውና ከክላሺንኮቭ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለውና፡፡ እንዴ … ለበርካታ ዘመናት አፍሪካውያን በጦር አበጋዞቻቸው ቀስቃሽነት እርስ በእርስ የተላለቁት እኮ በእኚህ ሰው ድንቅ የፈጠራ ሥራ (“ድንቅ የፈጠራ መጥፊያ” ይሻላል!) እኮ ነው። እስቲ አስቡት … አጠቃቀሙ ቀላል ነው፣ ብርድና ሙቀት ሳይል የትም አገር ይተኩሳል፣ ዋጋውም እርካሽ ነው (ዋጋው የማይቀመሰው አሜሪካ ሰራሽ የጦር መሣሪያ ተገዝቶማ አይቻልም ነበር!) AK-47 ባይኖር እኮ አፍሪካውያን በኋላ ቀር መሳሪያ ነበር የሚተላለቁት፡፡ ሌላው ቢቀር  ከአሰቃቂው “ገጀራ” ገላግሎናል (እርስ በእርስ መተላለቁማ አዕምሮ ሳይቀር ሊቀየር አይችልም!) ይኸው በ21ኛው ክ/ዘመን እንኳን --- የአዲሲቱ አገር ደቡብ ሱዳን መሪዎች በጎሳ ተቧድነው እልቂቱን ጀምረውት የለ! (እስካሁን 1000 ሰዎች ሞተዋል!)
     የኢንካርታ መዝገበ ቃላት፤ ክላሺንኮቭ የሚለውን ቃል ሲፈታው ምን ይላል መሰላችሁ? በአሸባሪዎች ወይም በሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል በከፊል አውቶማቲክ የሆነ ሩሲያ ሰራሽ ጠብመንጃ። መዝገበ ቃላቱ እንዲህ ይፍታው እንጂ በህዝብ ምርጫ ሥልጣን ላይ እንደወጡ በድፍረት የሚናገሩ የአፍሪካ መንግስታት ሳይቀሩ በስፋት ሲጠቀሙበት የኖረ የጦር መሳሪያ ነው፡፡ Ak -47!!
    እናም ሁነኛ ወዳጄ እንዳለው … ለአፍሪካ ታላቅ የሃዘን ሳምንት ነበር፡፡ ለምን ቢሉ … ድንገተኛ የሞት ዜናቸው የተሰማው ሩሲያዊ የ Ak -47 ፈጣሪ በእርግጥም የአፍሪካ ባለውለታ ነበሩና፡፡ በተለይ ለአፍሪካ መሪዎችና አማፅያን! ካላመናችሁኝ ደግሞ አፍሪካውያን ሽምጥ ተዋጊዎችንና ሥልጣን ላይ ያሉትን የአፍሪካ አምባገነን መንግስታት ልትጠይቁ ትችላላችሁ፡፡ የታሪክ ዶሴዎችም ከዚህ የተለየ ሃቅ አይነግሯችሁም፡፡ በሩሲያው “ጀግና” በተሰራው የጦር መሳሪያ ስንቶቹ ተቀናቃኞቻቸውን ዶግ አመድ አድርገው ስልጣን እንደተቆናጠጡ የየአገሩ ቤተመንግስት ይቁጠረው። እርግጥ ነው ቁጥራቸው የትየለሌ የሆኑ የአፍሪካ ንፁሃን ዜጎችም የAk -47 ሰለባ ከመሆን አላመለጡም። የሚገርመው ግን --- እስካሁን ማንም የጦር መሳሪያ ፈጣሪውን ሩሲያዊ ተጠያቂ ሲያደርግና ሲያማርር ሰምተን አናውቅም። (ባለውለታችን ናቸዋ!) የትኛውም የአፍሪካ አገር የቱንም ያህል መቶ ሺዎችና ከዚያም በላይ ህዝቦች ቢያልቁበትም መሳሪያውን ከመግዛትና ወደ አገሩ በገፍ ከማስገባት የታቀበበት ጊዜ የለም፡፡ (አፍሪካዊ መንግስት ክላሺንኮቭ ሳይንተራስ እንቅልፍ አይወስደውም እኮ!) እናም ---- በዚህ ሳምንት በሞት የተለዩት ሩሲያዊው ሜ.ቲ ክላሺንኮቭ ከማንኛውም የዓለም ክፍል ይልቅ የአፍሪካ ታላቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ (ለአፍሪካ ክላሺንኮቭ ኦክሲጂን ማለት እኮ ነው!) እንደውም ሰውየው ባለውለታ የሚለው ቃል ሳያንሳቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ እናላችሁ ---- “አፍሪካ ሌላ ታላቅ ልጇን በሞት ተነጠቀች” ብንል አላጋነንም (“መወለድ ቋንቋ ነው” አሉ!) ከሁለት ሳምንት በፊት የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት የነበረውን ታላቅ ልጇን ማንዴላን ያጣችው አፍሪካ፤ ይኸው አሁን ደግሞ ለህዝቦቿ እልቂት Ak -47ን ሰርተው ያበረከቱትን ታላቅ ባለውለታ ተነጠቀች፡፡ ዛሬ እንግዲህ የፈረንጆቹ ዓመት ማጠቃለያ ላይ ስለምንገኝ የፖለቲካ ወጋችን ዓለም አቀፍ ፖለቲካ ላይ ያነጣጥራል (ግሎባላይዜሽን እኮ ነው ዘመኑ!) እናም Toptens world.com የተሰኘ ድረ ገጽ፤ የዓመቱ Top 10 “የለየላቸው ቀሽም ፖለቲከኞች” በሚል ያወጣውን መረጃ እየቃኘን ዝነኛ ፖለቲከኞችን እንታዘባለን፡፡ ድረገፁ በመግቢያው ላይ እንደሚለው፤ በመላው ዓለም ከሚገኙ ፖለቲከኞች 10 የለየላቸውን ቀሽሞች ብቻ መምረጥ አስቸጋሪና ፈታኝ ነው፤ ምክንያቱም የዓለም ፖለቲከኞች ሁሉ ምድባቸው ከዚህ ውጭ አይደለም፡፡ የማታ ማታ ግን ከብዙ ጥናትና ምርምር በኋላ እንደምንም ቅሽምናው የከፋባቸውን ወይም የበረታባቸውን 10 ፖለቲከኞች መርጠናል - ይላል ድረገፁ፡፡
    “አብዛኞቹ ፈሪዎችና አጭበርባሪዎች፤ አንዳንዶቹ ስግብግቦችና ዋሾዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ አሳፋሪዎችና መሳቂያ መሳለቂያዎች ናቸው” ሲልም የዓለም ፖለቲከኞችን ዶግ አመድ ያደርጋቸዋል፡፡ (ሲያንሳቸው ነው!) እናላችሁ ----- ሁሉንም ባይሆን እንኳን የተወሰኑትን ቅሽምና የከፋባቸው ፖለቲከኞችና ለቅሽምና ያበቃቸውን ድርጊቶች አብረን እንቃኛለን (“ወዳጅህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ” አሉ!)
    የምንጀምረው የካናዳ ፖለቲከኛና የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ አባል ከሆነው ሮበርት አንደርስ ነው፡፡ አንደርስ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ላይ እንቅልፉን በመለጠጥ የሚታወቅ ፖለቲከኛ ነው(ያውም እያንኮራፈ!) ቀደም ሲል በዚሁ ክፉ ልማዱ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው አንደርስ፤ በቅርቡም እንቅልፉን ሲለጥጥ ተገኝቷል (እንቅልፎ አትሉትም!) እንቅልፉን ሲለጥጥ የነበረው የጡረተኞች ጉዳይ ኮሚቴ የሞቀ ስብሰባ ላይ ሲሆን ድንገት ከእንቅልፉ ባንኖ  ለተሰብሳቢው ድንገተኛ ሰላምታ በመስጠቱ ነው የተነቃበት ተብሏል (በእንቅልፍ ልቡ ማለት ነው!) ከእንቅልፉ በደንብ ሲነቃ ታዲያ ተሰብሳቢውን በአግባቡ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ነገር ግን ከኮሚቴው ከመባረር አላዳነውም፡፡ (በእንቅልፋምነት የኛዎቹ ባይብሱ ነው!) የሆነ ሆኖ የካናዳው ፖለቲከኛ፤ በቀሽም ፖለቲከኞች (Top 10) ዝርዝር ውስጥ 10ኛ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡
    ሮድ ታም ደግሞ በሃዋይ የሆኖሉሉ ከተማ ምክር ቤት አባል ነው፡፡ ታም በተለይ የሚታወቀው “ሆዳም የምክር ቤት አባል” በሚል ቅጽል ስሙ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ ሆዳም የተባለው? የምክር ቤቱን የወጪ ሂሳብ እና የምርጫ ዘመቻ ገንዘብ እየመዠረጠ ሆዱን ሲሞላ ስለከረመ ነው። የራሱ ሳያንስ ቤተሰቡን፣ ባልንጀሮቹን እና የምክር ቤት አባላትን እየሰበሰበ በከተማው ባሉ ምግብ ቤቶች ያበላ ነበርም ተብሏል፡፡ ሮድ ታም የማታ ማታ ክስ የተመሰረተበት ሲሆን በሦስተኛና አራተኛ ደረጃ የሌብነት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል፡፡ (እንደኛ አገር ሙሰኛ ፖለቲከኞች ማለት ነው!)
    በቶፕ 10 የቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር ውስጥ በ8ኛ ደረጃ የተቀመጡት አፍሪካዊ ፖለቲከኛ ናቸው - የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ኧርነስት ባይ ኮሮማ፡፡ ከ2007 እ.ኤ.አ ጀምሮ ሴራሊዮንን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ የሚገኙት ኮሮማ፤ የቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር ውስጥ የገቡት በጐሰኝነት አቀንቃኝነታቸው ነው፡፡ ይሄ ጐሰኝነታቸውም በሚያስተዳድሯት አገር ውስጥ ድህነትን አስፋፍቷል በሚል የሰላ ትችት ይሰነዘርባቸዋል፡፡ (ይሄ እንኳን ከኛ የተረፈ ነው!) ፕሬዚዳንቱ ከአገራቸው ሙስናን በቅጡ ለማጥፋት ተስኗቸዋል የሚለው መረጃው፤ የጐሳቸውን አባላት የሙስና ተግባራት ማጋለጥ ወይም ለህግ ማቅረብ አልቻሉም ይላል (የጐሳቸው ባህል አይፈቅድማ!) በዚህ የተነሳም መንግስታቸው ከመልካም አስተዳደር ጋር ተፋቷል ተብሏል። (መልካም አስተዳደርና ጐሰኝነት ውሃና ዘይት ናቸው!) ሲሲ ፓቲል ደግሞ የህንድ ፖለቲከኛ ናቸው። በደቡብ ህንድ የምትገኘው የካራታንካ ግዛት ህግ አውጭ ም/ቤት አባል የሆኑት ፓቲል፤ ቀደም ሲል የሴቶችና ህፃናት ልማት ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም የካራናታካ ግዛት የህግ አውጭ ም/ቤት ስብሰባ ላይ ከእሳቸው የማይጠበቅ ወራዳ ተግባር ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡ ይሄን ወራዳ ተግባራቸውን ያጋለጡት ደግሞ ስብሰባውን ለመዘገብ በም/ቤቱ የተገኙ የቴሌቪዥን የካሜራ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ም/ቤቱ በተጋጋለ ስብሰባ ላይ ሳለ ፓቲል በሞባይል ስልካቸው የወሲብ ፊልም (pornography) ሲኮመኩሙ በጋዜጠኞቹ የካሜራ ወጥመድ ውስጥ ገብተዋል ነው የተባለው፡፡ (የወከሉት ህዝብ እንዴት ያፍርባቸው!) ማፈር ብቻ አይደለም ብግን ብሎባቸዋል እንጂ! አንዳንዶች “እንዴት ይሄን የሚያመዛዝን አዕምሮ የላቸውም?” ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ “የምክር ቤቱን ቅድስና አጉድፈዋል” በማለት የውግዘት ናዳ አውርደውባቸዋል፡፡ በውግዘት ብቻ ግን አላበቃም። ፓርቲያቸው ባደረገባቸው ግፊት ከም/ቤቱ ወጥተዋል፡፡ እኚህ ቅሌታም “ፖለቲከኛ” በቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር ውስጥ በ6ኛነት ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
    ወደ አውሮፓ ደግሞ እንሻገር፡፡ ጣልያንን ለሦስት ጊዜ (ከ1994-2011 ዓ.ም) በጠ/ሚኒስትርነት የመሩት ሲልቪዮ በርሉስኮኒ በቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር የ2ኛነት ደረጃ ተሰጥቶአቸዋል፡፡  የቴሌቪዥን ቻናልን ጨምሮ ግዙፍ የሚዲያ ኩባንያ እንዳላቸው የሚነርላቸው በርሉስኮኒ፤ የጣልያን የእግር ኳስ ክለብ (ኤ.ሲ ሚላን) ባለቤትም ናቸው፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በርሉስኮኒ፤ በቅርቡ ታክስ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው የአንድ ዓመት እስር የተበየነባቸው ሲሆን ብይኑ ገና ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ለአቅመ ሄዋን ካልደረሰች ሴተኛ አዳሪ ጋር በክፍያ ወሲብ ፈፅመዋል በሚል ወንጀል ተከሰውም ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ በእርግጥ ታክስ ማጭበርበር ለሳቸው “ብርቅ” አይደለም፡፡ ሦስት ጊዜ ታክስ ባለመክፈል ክስ ተመስርቶባቸው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ እኚህ የለየላቸው ቀሽም ፖለቲከኛ፤ በአንድ ወቅት የG8 አገራት እምብርት የነበረችውን አገራቸውን ጣሊያንን፤ የ2 ትሪሊዮን ዩሮ ገደማ ዕዳ ውስጥ ከተዋታል ተብሏል፡፡ (የፖለቲከኛ ቅሽምና ለአገርም ይተርፋል!)
    በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ፍራንሶይስ ሆላንዴ፤ ከ1997 እስከ 2008 ዓ.ም  የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲ አንደኛ ፀሐፊ ነበሩ። በቅርቡ በተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት መሰረት፤ ለፍራንሶይስ ሆላንዴ ፕሬዚዳንትነት ቀና አመለካከት ያለው ከጠቅላላው ህዝብ መካከል  15 በመቶው ብቻ ነው ተብሏል፡፡ በእርግጥም ደግሞ ህዝቡ አይፈረድበትም፡፡ ለምን መሰላችሁ? በእሳቸው የአመራር ዘመን ሥራ አጥነት በከፍተኛ መጠን አሻቅቧል። በታክስ ህግ ላይ ያደረጉትን ለውጥ ተከትሎም በርካታ የፈረንሳይ ባለሀብቶች አገራቸውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል (ድሮስ ሶሻሊስት!) የአውሮፓ አህጉር ፈጠራ፣ አነስተኛ የመንግስት ባጀትና የተመጠነ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም የንግድ ሥራ ፈጠራና እድገት በምትፈልግበት በአሁኑ ሰዓት፤ ከአህጉሪቱ ቀንደኛ የሶሻሊዝም አቀንቃኞች አንዱ መሆናቸውም የፈረንሳዩን ፕሬዚዳንት ለትችትና ለወቀሳ ዳርጓቸዋል፡፡ በ2013 የቀሽም ፖለቲከኞች (Top 10 worst politician) ዝርዝር ውስጥ የአንደኝነት ደረጃ ይዘዋል - የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት፡፡
    እንግዲህ እኔም--- በነሐሴ ወር መጨረሻ አካባቢ ደህና ስፖንሰር ካገኘሁ የአገራችንን ቶፕ 10 ቀሽም ፖለቲከኞች ዝርዝር የማውጣት ራዕይ አለኝ። ብቻ ይቅናህ በሉኝ! (ደህና ስፖንሰር ለሚያመጣ ደህና ኮሚሽን ይከፈለዋል!)
                                                                        
    • Written by  ኤልያስ

    1 comment:

    Anonymous said...

    የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.