Tuesday, March 4, 2014

የአርሲ ጉዞዬ አስደናቂ ማስታወሻ 2

 

 Written by  ነቢይ መኮንን 

 

 የአርሲ ጉዞዬ አስደናቂ ማስታወሻ
(ካለፈው የቀጠለ)
ከ38 ዓመት በኋላ አስከሬናቸው የተገኘው የፊዚክስ ባለሙያው የዶክተር ሙሉጌታ በቀለ አባት የፊታውራሪ በቀለ ኦገቶ አስደማሚ የአስከሬን ማሳረፍ ሥነ ስርዓት በሳጉሬ ወረዳ/አርሲ/
የጉዳዩ ጭብጥ፤
ፊታውራሪ በቀለ ኦገቶ በደርግ መንግስት ከሌሎች 16 ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር በግፍ ተገድለው አስከሬናቸው ዘመድ ወዳጅ እንዳያውቅ፣ እንዳያገኝ ተደርጎ፤ በደርግ መንግስት አረመኔነት፤ የተጣሉበት ሳይታወቅ ለ38 ዓመታት ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ በልጆቻቸው በተለይም በዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ ጥንካሬና ፅናት፤ የተሞላበት የረጅም ጊዜ ፍለጋ፤ ታህሳስ 17/2006 ዓ.ም በአሰላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አፅማቸው ተቆፍሮ ተገኝቷል፡፡
ሁኔታው ለዘመድ ወዳጆቻቸው፣ ለአገር ሽማግሌዎችና አብረዋቸው ለተሰዉ ሰማእታት ቤተሰቦች ታህሳስ 28/2006 ዓ.ም ይፋ ተደረገ፡፡
አፅሙን በክብር ለማሳረፍ በዘመዶቻቸው፤ በወዳጆቻቸው፣ በሰማእታቱ
ቤተሰብ ታሪክ ለመዘከር ኮሚቴ ይቋቋም ተብሎ በተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ፤ መጽሄት ለማሳተም የሐውልት ስራ ለማሰራት እንዲሁም በእለቱ ለሚገኙ እንግዶች መስተንግዶ ለማድረግ ተስማሙ፡፡
በዝርዝር ስማቸው የተገኘ የአያትየው የኦገቶ ጉቱ ልጆች 31 ናቸው፡፡ የልጅ-ልጆቻቸው ቁጥር እጅግ በርካታ ነው፡፡
ከነዚህ መካከል ፊታውራሪ በቀለ ኦገቶ አንዱ ናቸው! የፊታውራሪ በቀለ ኦገቶ አሟሟት ምን መሳይ ነው? አሰቃቂ አሟሟት ነው የተባለው ለምንድነው? አስከሬናቸው እንዴት ተገኘ፡፡ ይህንን ዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ ከሰጡት ቃለ-ምልልስ እናገኘዋለን፡፡ በቀብሩ ሥነስርዓት ላይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲና አቶ ሽፈራው ጃርሶ ተገኝተው ነበር፡፡ ፊታውራሪ በቀለ ከአምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጋር ዝምድና እንዳላቸው ይነገራል፡፡
***
በአስከሬን ማሳረፉ ሥነ ስርዓት ላይ፤ የፕሮግራሙ መሪ፤ አራት ሰዎችንና ዶክተር ሙሉጌታ እንዲናገሩ ዕድል ሰጥቶ ነበር፡፡ አቶ ኢሊይ ሴማ፣ ሃጂዳውድ፣ ሼክ አማን ገዳ፣ አቶ ክፍሌ በቀለ ናቸው፡፡ አቶ ኢሊይ ሴማ ነዋሪነታቸው በዲገሉና ጢጂ ወረዳ የሆነና ፊታውራሪ በቀለ ኦገቶ በኖሩበት ዘመን የነበሩና በአሁኑ ወቅት የታወቁ የአካባቢው የሃገር ሽማግሌ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደተናገሩት፤
“ለዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ምን ያህል ሲደክሙና የህዝቡን አመለካከት ለመለወጥ በጽናት መታገላቸውን ዛሬም የምናስታውሰው ነው፡፡ ያ ጥረታቸው ተሳክቶ በአካባቢያችን ዘመናዊ ትምህርት ተስፋፍቶ ብዙ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ከአካባቢያችን በብዛት መፍለቃቸው የፊታውራሪ በቀለ ኦገቶ ጥረት ውጤት መሆኑን ዛሬም አንዘነጋም፡፡” ያሉ ሲሆን ቀጥለው የተናገሩት ሃጂ ዳውድ ደግሞ ፊታውራሪ በቀለ ኦገቶ በደርግ መንግሥት ከሌሎች 16 ሰዎች ጋር በግፍ ከተገደሉበት የሽርካ ወረዳ የመጡ የሃገር ሽማግሌና የሃይማኖት መሪ ናቸው፡፡ “ፊታውራሪ በቀለ ኦገቶንና አብረው የነበሩትን 16 ሰዎች ለመግደል የደርግ ወታደሮች በአካባቢው እንደደረሱ እሳቸውን የሚወዳቸውና የሚያከብራቸው የሽርካ ህዝብ ሽማግሌዎችን በመላክ የደርግ ወታደሮች በአካባቢው እንደደረሱና እሳቸው በፍጥነት አካባቢውን እንዲለቁ አሳስበዋቸው ነበር፡፡ ፊታውራሪ በቀለ ግን የደርግ ወታደሮችን ለመሸሽም ሆነ እጃቸውን ለወታደሮቹ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ከዚያ ይልቅ ወታደሮቹን ተጋፍጠው የማይቀረውን የሞት ጽዋ ለመጐንጨት በጽናት ሞትን ለመጋፈጥ የፀኑ ታላቅ የህዝብ ልጅ ነበሩ፡፡
“ሁሌም እንደሚታወቀው ጀግና በችግር ጊዜ የሚሞተው በቤተሰብ መሃከል በተመቻቸ አልጋ ላይ ሆኖ አይደለም፡፡ ጀግና በችግር ጊዜ የሚሞተው በመከራ ውስጥ ነው፡፡ ፊታውራሪም ሞታቸው የማይገርመው ለዚህ ነው፡፡ ዛሬ ከ38 ዓመት በኋላ እራሳቸው ባስገነቡት የሥላሴ ቤተክርስቲያን አፅማቸው ማረፍ መቻሉና ያኔ ሊያለቅስ ያልቻለው እስላምና ክርስቲያኑ ህዝብ በዚህ ሁኔታ ወጥቶ አጽማቸውን አጅቦ መጉረፍ ለህዝባቸው ትልቅ ዕፎይታ ሲሆን ትልቅ ተስፋና ተምሳሌት ነው!” ብለዋል፡፡
ሶስተኛው ተናጋሪ፤
ሼህ ኢማን ገዳ የአርሲ ዞን የኦህዴድ ጽ/ቤት ሃላፊና የዚህ ሥነ ሥርዓት የክብር እንግዳ ሲሆኑ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለታዳሚው ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት … “ከ38 ዓመታት በኋላ በዚህ ሁኔታ ህዝብ እንደ ንብ ከተለያየ ቦታ ተምሞ አፅሙ በክብር በሚያርፍበት ሥነ ሥርዓት ላይ እኛም መንግሥትንና ድርጅታችንን ወክለን መታደማችን የሚያስደስተን ከመሆኑም በላይ የመንግሥታችንንና የድርጅታችንንም የህዝብ ወገንተኝነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ፊታውራሪ በቀለ ኦገቶ ታሪካቸው ለህዝባቸውና ለሃገራቸው ዕድገት የታገሉት ትግልና የከፈሉት መሥዋዕትነት ለአዲሱ ትውልድ ብዙ ትምህርት የሚሰጥና አርአያነታቸው የማይዘነጋ በመሆኑ ታሪካቸዉ በቀላሉ እንዳይዘነጋ ለማድረግ እንዲያስችል ከዚህ ቀደም በዞኑ ውስጥ አርአያ ለሆኑና ለህዝባችን ትልቅ ውለታ ላበረከቱ እንደነ ዶ/ር ደምሱ ገመዳ ትምህርት ቤትን በስማቸው በሰየምነው መሠረት የፊታውራሪ በቀለ ኦገቶም በተመሣሣይ ሁኔታ ከህዝባችን ጋር በመመካከር በሥማቸው ትምህርት ቤትን ወይንም ተመሳሳይ ተቋምን በመሰየም አርአያነታቸውን ለትውልድ ለማስተላለፍ መንግሥትና ድርጅታችንን በመወከል ለዚህ ህዝብ ቃል መግባት እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡ ቀጥሎ የዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ ታላቅ ወንድም አቶ ክፍሌ በቀለ ናቸው የተናገሩት፡፡ እሳቸውም፤ “ይህ ፕሮግራም መፈፀሙ ጥቅሙ አሁን ዛሬ በህይወት ላለነውና እሳቸውን ለሚወዱና ለሚያከብሩ እንዲሁም አልቅሰው ሊቀብሩ ላልቻሉ የአካባቢው ተወላጅ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለመጪው ትውልድ ነው በስፋት ሲታይ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ትምህርት ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉጌታ የመጡትን ሰዎች በማመስገን ነው ያሳረጉት፡፡ ከሥነ ስርዓቱ በኋላ ከዶ/ር ሙሉጌታ ጋር ነቢይ መኰንን ቆይታ አድርጐ ነበር፡፡
ኢንተርቪው ከዶክተር ሙሉጌታ በቀለ ጋር
(ዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ ዕውቅ የፊዚክስ ምሁር ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የፊዚክስ ዕድገት ተስፋ የተጣለባቸው ትሁትና ያልተዘመረላቸው ምሁር ናቸው፡፡)
“የአባትህ ሌሎች ወንድሞች አሉ እንዴ?” አልኩት እንደመነሻ፡፡
“አቶ ተክሌ በእናት በአባት የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ ያባቴ ወንድም ነው፡፡ ግን የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ ሻሹ እምትባል እናት ነው ያላቸው፡፡ በቀለ፣ አሹ፣ ቶሶራ፣ ተክሌ፤ የአንድ እናት ልጆች መሆናቸው ነው፡፡ አያቴ ኦገቶ ግን ሚስት አግብቶ ወደ 80 ልጆች ሳይኖሩት አይቀርም! (ሳቅ)
ጅማ እርሻ ት/ቤት ነበር ዱሮ … ጅማ እርሻ ኮሌጅ ነው … እዚያ ከተማሩት ከመጀመሪያዎቹ ውስጥ ነው ተክሌ! … ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቤሩትም ነበር ከዚያ! እዚያ ተምሯል፡፡ ከዚያ ኤፒድ ኤክስቴንሽን ሰራተኛ ሆኖ ተቀጠረ፡፡ አልጣመውም፡፡ ትቶ ገበሬ ሆነ! ሜካናይዝድ ፋርሚንግ! እነ አቶ ተድላ አበበ ናቸው የጀመሩት-ታውቃቸዋለህ?”
“እንዴታ!”
“ተስፋዬ ረድኤ፣ አስረስ ዐባይ የሚባሉ?”
“እንዴ የናዝሬት ልጅ ነኝኮ! አሳምሬ አውቃቸዋለሁ!” አልኩት፡፡ አሰላ ለናዝሬት ቅርብ ከመሆኑም በላይ እነዚህ የተጠቀሱት ሀብታም ባለ እርሻዎች መኖሪያ ቤታቸው ናዝሬት ነው፡፡ የናዝሬት ሀብታም ናቸው፡፡”
“የአስረስ ዐባይ ልጅ ቀብር መጥቶ ነበር አይተኸዋል?”
“አላየሁትም! አውቀው ነበር ባየው ደስ ይለኝ ነበር”
“ተክሌ እንግዲህ ከእነ ተድላ በኋላ በእርሻ … እሱ ነው ግንባር ቀደሙ፡፡ በኋላ ደርግ ትራክተሩን በሙሉ ሲወርስ ቀወሰ! አበቃ! … ፒ ኤች ዲዬን ጨርሼ ከመምጣቴ ከ2 ሣምንት በፊት ሞተ! 90ዎቹ ውስጥ ነው … እና የአባትህን ነገር አደራ፤ አንድ ነገር መደረግ አለበት ይለኝ ነበር! …
“አሃ የተክሌን ነገር ለምን ታወሳልኛለህ ብዬ ነበር አሁን ገባኝ አመጣጥህ … የወንድሜን አስከሬን መፈለጉን ቸል አትበል ስላለህ ነው”
“አዎን … ተበሳጭቶ እኔ የምመኘው የወንድሜን ነገር አንድ ነገር ማድረግ ብንችል ነው ይል ነበር …የእስላም መፅሀፍ እየያዘ ሸከና ሁሴን ጋ ይሄድ ነበር … ቁርዓን የለየ ነው! ደምበኛ እስላም  ነው! … እስልምናውን አስትተውት … ት/ቤት ገብቶ … ተምሮ እዚህ ደረጃ ደረሰ! … ተክሌ ኦገቶ እንዳባቱ ነበር … ማለት ይቻላል፡፡ የመንግሥት ገንዘብ ያገኝ ነበረና እንዲህ ተብሎ ተገጠመለት፡-
“ተክሌ ኦገቶ
ደሞዙ 200መቶ
ይበላል ተኝቶ …”
ያኔ 200 ብር የትናየት! እሱን ትቶ ነው “መሬት ያለው ወንድሜ እያለ ምን ያለፋኛል?” ብሎ በግድ ብድር ተበደረ፡፡ “ብድር የሚባል ከባንክ መውሰድ ሲፈሩ እንደ ጉድ ነው!” እንደምንም አሳምኖ ትራክተር ገዝቶ የገባ ነው! ደህና አድርጎ ተግቶ ደህና ደረጃ ሲደርስ ነው በቃ ትራክተሮቹ ተበሉ በ1966 ዓ.ም! ዞረበት … ቀወሰ … ሰውነቱ ደከመ … በታይፈስ ነው የሞተው! በቀላል በሽታ ሞተ አሉ! ያኔ እንግዲህ የወንድሜን ነገር አደራ እያለ አጥብቆ ይነግረኝ ነበረ ብዬሃለሁ፡፡ ዕውነቱን ነው፤ አላፊነት መወጣት ነውኮ! … ያ ነገር እኔ ውስጥ ጐድሎ ይሰማኝ ነበር፡፡ ያባቴ ነገር ባለመሟላቱ! እኔ ገጠር እሄዳለሁ … በተለይ ለጥምቀት በዓመት  እሄዳለሁ … በተቻለኝ ህዝቡን አያለሁ … ዘመድ አዝማድ አያለሁ … አወራለሁ … አረቄም እጠጣለሁ … እንዳገሩ … እንዳገሬ! አንድ አሮጊት አለች .. ያን ቀን ቅዳሜ የነብር ቆዳ ለብሳ እየፎከረች ነበር አይታችኋት እንደሆነ አላውቅም! … ረጅም ቀጭን ነች! … የተክሌ ሚስት እናት ናት! ወንዳ ወንድ ናት ታዲያ! ጦቢያ ነው ስሟ! ቤተሰቧ የጥንት ናቸው! ከሸዋ የመጡ ናቸው! አቢቹዎች ሳይሆኑ አይቀሩም! …
ሽርካ እንግዴህ ቤተክርስቲያኑ ሥላሴ ሆነህ ወይም ወደ ምሥራቅ ስታይ ሰንሰላታማ ተራራ ይታያል፡፡ ጋላማ ተራራ የሚባል ነው፡፡ ጭላሎ ተራራንና ካካ ጋራን የሚያገናኝ ነው፡፡ ሠንሠለታማ ነው፡፡ ልክ ከሱ ጀርባ እዛው ዳገቱ ላይ ነው ጦርነቱ ተካሂዶ፤ 17ቱ የተገደሉት፡፡”
“ሽርካ ነበር ምሽጋቸው?”
“አዎ… ለነገሩማ ባሌ ሁሉ ሄደው ነበርኮ ተመልሰው መጡኮ… መውጣት ይችሉ ነበር፤ መዋጋት ፈለጉ፤ ተመለሱ፡፡ የተጠመዱትም እዚህ ነው! … ሽርካ የደምሱ አገር ነው”
“የዶ/ር ደምሱ - የሂሳብ ዲፓርትመንቱ?”
“አዎ!”
“ኤሌሜንታሪ የተማረው እዛ ነው!”
“ጢዮ ጢጆ አለ … ጢገሉና ጢጆ … ዱሮ ዋናው ወረዳ አሰላ ነበረ … በዱሮ ጊዜ … አሁን ግን መቀመጫው ሳጉሬ ሆኗል! ዲገሉና ጢጆ ተብሎ አሁን ዋናው ከተማ ሳጉሬ ነው፡፡ ሎሌ ወደ ቀርሳ ነው፡፡ ቆላ ማለት እስከ አዳሚ ቱሉ ድረስ ይሄዳል፡፡ ኮፊሌ፡፡ ኮፊሌ አካባቢ ሽሬ እምትባል አካባቢ ሠርተዋል፡፡ ጉምጉማ ማለት ባሊሜዳ የሚባል አካባቢ ነው፡፡ እዛም ሠርተዋል አባቴ በምስለኔነት! እንደውም መጀመሪያ የሠሩት እዛ ነው! … ከእናቴ ጋር ከመጋባታቸው በፊት ነው አባቴ እዛ የነበሩት፡፡ አሠላ ሠርተዋል፡፡ ጢቾ እስከ 66 ነበሩ፡፡ ያኔ ደርግ ገባ! የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ የዛሬ አርባ ዓመት መሆኑ ነውኮ!
“የአስከሬኑ አፈላለግ እንዴት ነበረ?”
“ፍቅረ ማሪያምን (የጋራ ጓደኛችን ነው) አዋራው ነበረ፡፡”
ይሄንን ቃለ-መጠይቅ ምሳ እየበላን ስናካሂድ ድንገት ስልኩ ጮኸ፡፡ ማን እንደሆነ ሲያውቅ በጣም ሳቀ፡፡
“ድካሙ ወጣልህ ወይ?” አለችው በስልክ-ባለቤቴ ናት፡፡
“ያን ሁሉ ደስታ አይቼ እንዴት አይወጣልኝም!...” አላት፡፡
“ባለቤትህ ቤት መጣች እኔጋ” አለችው፡፡
በጣም ሳቀ፡፡ እኔ ባለቤት ጋ የእሱ ባለቤት መምጣቷ ነው ያሳቀው፡፡
ወደኔ ዞሮ “እንዴት ያለ መቆላለፍ ነው ባክህ-በጣም የሚገርም ነው-Entanglement ይሉታል በፊዚክስ” አለኝና ተሳሳቅን፡፡
ከዚያ ቀጠለ፡፡ “ፍቅረማርያምን ነው ማማከር የጀመርኩት፡፡ ገና ቦታው ሊገኝ ይችል ይሆናል የተባለው በዚያን ጊዜ ገበሬ ማህበር ታጣቂ የነበረ ሁኔታውን የሚያውቅ አለ ስለተባለ ነው፡፡ ያባታችንን ሬሣ፤ 68 መስከረም አራት ነው እንግዲህ የሞቱት-ከተራራው ጀርባ አስከሬናቸውን ይዘው መጥተው በዕለቱ የጣውላ ርብራብ ላይ ሙሉ ልብስ እንደለበሱ አቆሙዋቸው …”
“ከገደሏቸው በኋላ አስከሬኑን ከጀርባው ርብራብ አድርገው አቆሙት ነው የምትለኝ?”
“አዎ፤ አስከሬኑን! … ህዝቡ ቀኑን ሙሉ እንዲመለከት አድርገው ነው ሌሊት ላይ የቀበሯቸው! … ያን የገበሬ ማህበር ታጣቂ ከአንድ ሶስት አራት ዓመት በፊት አገኘነው፡፡ ቀስ ተብሎ በዘመድ በኩል ተሄዶ በመከራ ነው የተገኘው፡፡ መጣ፡፡ ‘ቦታውን እናግኘው’ አለ፤ ሄድን፡፡ ያኔ አስከሬኑን ዘመድ ፈንቅሎ እንዳይወስድ ጠብቁ ተብለን ሶስት ሰዎች ተመድበን ነበር’ አለ፡፡ እኔ እንግዲህ በየለቅሶው፣ በየሠርጉ፣ በዓልም ሲሆን ወደ ሳጉሬ ስለምሄድ ተለምጃለሁ በቃ፡፡ የኛ ሰው ነው ብለውኛል፡፡ ይሄንን ጉዳይ መከታተሌን ስቀጥል፤ ጭምጭምታ ከመጣም ወደኔ የሚያመራ ሆነ! ታላቅ ወንድሜ አጠገባቸው ነው ክፍሌ፡፡ ግን ብዙ አያወሩትም - እንደማንኛውም እንደነሱው ነው እሱ፡፡ የእለት ችግር ነው እሚያወሩለት!
እኔ ግን በሄድኩ ጊዜ በበዓል በድግስ ላይ በጨዋታም ትዝታውን ያነሱልኛል! በዚሁ ነው ያገኘሁት፡፡ (ዘሪሁን የሚባል ልጅ አለው ክፍሌ፤ ሀውልቱን የሠራው እሱ ነው) እና እሱን አንድ መምሬ መኰንን መስቻ እሚባሉ ያባታችን ጓደኛ የቤተ ክህነት ሰው አሉ፡፡ የእሳቸው ልጅ አክሊሉ እሚባል አለ፡፡ እሱ ነው - ሰውዬውን የሚያውቅ - ታጣቂውን፡፡ አክሊሉ በዚያ ቤ/ክርስቲያን ውስጥ ይሠራል፡፡ አክሊሉን የጠቆመው አጐቴ ነው-ሙጀዲን የሚባል አጐቴ፡፡ አክሊሉ ሊረዳን ይችላል አለንና አጐቴ፣ ዘሪሁንና እኔ ሄድን፡፡ አክሊሉ የገበሬ ማህበሩን ሰውዬ ይዤ እመጣለሁ አለ፡፡ አንድ እሁድ ሰምበቴ ቀን ተቃጥረን ሄድን -አካባቢውን ለማየት፡፡ አሳየን፡፡ ታጣቂው ገበሬ በመሠረቱ የአምቦ ሰው ነው - ቤተሰቦቹ ያሉት እዛ ነው ግን እሱ እዚህ ነዋሪ ነው፡፡ ያኔ ጐረምሣ ሳይሆን አይቀርም-ያኔ በ1968 ዓ.ም፡፡ ዛሬ ግን ሽማግሌ ናቸው - አላየኋቸውም እንጂ የበዓሉ እለት መጥተው ነበር አሉ፡፡ አንተ እያልኩ ልቀጥልልህ፡፡ ደርግ - ማንም የበቀለ ኦገቶ ዘመድ የሆነ ድርሽ እንዳይል! ብሎ ተነግሯል፡፡ ሦስት ሰዎች ተመድበን ስንጠብቅ ነው የኖርነው አለ! ማንም እንዳይነካው ዘመድ አዝማድ ቆፍሮ እንዳያወጣው ምንም ዕድል እንዳይኖር” ማለቱ ነው፡፡
“የቀበረው ማነው ማለት ነው?”
“ደርግ ራሱ ነው፤ አለኝ”
“ሚካኤል ውሰጥ ነው የተቀበረው ሲባል ግር ይላል፡፡ ወይ ደርግ ኮሙኒዝሙ ጠፍቶበታል ማለት ነው?”
“ዕውነት ነው፡፡ የመጨረሻው የፍየል ወጠጤ የተባለው በእሳቸው ላይ ነበር”
ታጣቂው ያን እለት በቀጠሮው መሠረት መጣ፡፡ ሁለት አጐቶቼ፣ ሙጀዲን፣ ዘሪሁንና እኔ አለን፡፡ ሙጀዲን የሙስሊም ቆብ ስለሚያደርግ ግዴለም ይቅር አልን፡፡ ከቤተክርስቲያን ቅፅሩ ውጪ ቆየ፡፡ እኛ አየን የመቃብሩን ቦታ፡፡ አልተቆፈረም፡፡ ይሄ አምና ክረምት ከመግባቱ በፊት ነው - ግንቦት ግድም ነው፡፡ ከቤ/ክርስቲያን ውጪ ነበር በፊት - አሁን ግን አጥሩ በመስፋቱ ውስጥ ሆኗል … አየን፡፡ ሸለምጥማጥ አይነቶች ቆፍረው ያወጡት የራስ ቅል አጠገብ ነው፡፡ አካባቢውን ማተርን፡፡ ጥዶች አየን፡፡ ሌላም ሀውልት አለ፡፡ አስተዋልንና ሄድን፡፡ ከዛ መቆፈሪያው መቼ ይሁን አልን … በማህል ክረምት ገባ፡፡ ጥቅምት ማለፍ አለበት ጭቃ ነውና፡፡ … ህዳር … አሁን ታህሣሥ ግድም በአሁኑ ዓመት … በል አሳየን በትክክል እንቆፍር አልነው፡፡ መጣ፡፡ ሲያሳይ ሌላ ቦታ አሳየ-የተለየ ቦታ አሳየን፡፡ ይሄኛው ነው ትክክል አለን - ዞረበት … ተስፋ ቆረጥን! ሁለቱ ሌሎች ጠባቂዎች ሞተዋል … ገዳዮቹ፣ ፖሊሶቹ፣ ውጊያው ላይ የነበረ የተረፈ ሰው የለም፡፡ አልቀዋል፡፡ ለወሬ ነጋሪ እሱ ብቻ ነው፡፡ … እንሰብሰብ ተባለ፡፡ ጋሽ ክፍሌም ነበረ … እንዴት ይሁን? አልን … “ታጣቂውን አመስግነን በል ሂድ ብለን ሸኘነው፡፡
“ሁሉንም ቆፍረን እንሞክር አልን”
“አክሊሉ ይከብዳል፤ ግን፤ ካላችሁ ለማስፈቀድ ልሞክር አለ፡፡ ምሥክር ያስፈልጋል ለሰበካ ጉባዔው - ከዛ ነው የሚመራው - ቦታው ካልተለየ አይሆንም … ስለዚህ ምሥክር ፈልግ አልነው አክሊሉን፡፡ ሁሉንም በምሥክር ፊት ለመቆፈር ነው እንግዲህ … እንዴት ወደ ኋላ እንመለሳለን ብለን ተጨነቅን … ቢቀር ቢቀር ሳጥን ውስጥ አፈሩን ሞልተን እንቅበር አለ ዘሪሁን…”
“አላረገውም!” አለ ክፍሌ ባፅንዖት! ባዶ እጄን አፈር ብቻ  ይዤ ልሄድ ነው? አላረገውም” አለ ክፍሌ፡፡ … ቀጠሮ ይያዝ ተባባልን … በ13 ነው አሻሚው ስብሰባ … “ይሄንን በፀሎት ነው እንጂ በሌላ መፍታት አይቻልም!” አለ ክፍሌ … ልጅ አለችው፡፡ ምሥራቅ የምትባል በየገዳማቱ የምትዞር … እሷ ጋ ደወለ የዛኑ ጊዜ … እኛን መነኩሴ ታገኝልኛለሽ ወይ? አላት … “ኑ፤ አሉ” አለችና ደወለች -  ልሄድ ነው አለኝ ወደ መነኩሴው፡፡ አብሬህ ልሂድ አልኩት፡፡ ሄድን … እዛ ያለው ከርቸሌ ውስጥ ነው ኪዳነምህረት ቤ/ክርስቲያን ያለችው … አሰላ፡፡ የቆረቆሯት እሳቸው ናቸው፡፡ መኖሪያቸውም እዛው ደብር ግድም ነው፡፡ አገኘናቸው … ነገርናቸው … አባቴ ታላቅ ሰው መሆናቸውን ነገሩን … ተቸገርን አልናቸው … የመቃብሩ ቦታ እንዳወዛገበን አስረዳናቸው … ግራ ገብቶናል ፀልዩልን አልናቸው - ተዓምር ነውኮ ነቢይ!!”
“ምን አሉ? እንዴ በፀሎት ምን ሊፈጥሩ ይችላሉ?”
“ካሁን ጀምሮ ሱባዔ እገባለሁ” አሉ፡፡ “አንቺም ልጅ አንድ ሁለት ሰው ጨምሪልኝ አብረውኝ የሚፀልዩ” አሉ … “አንድ አሉ” አለች ምሥራቅ ከመድሃኒዓለም ቤ/ክ … ሌሎች አላገኝም … ግን እሺ እስቲ ልሞክር አለች፡፡ እኛ የመጀመሪያውን ጉድጓድ ልንቆፍር ወሰንን፡፡ ከዛ ዕሮብ ማታ ታህሥሣ 16 … አስረስ አባይ ሆቴል ነው ያደርነው … 11፡30 ደረስን ቁፋሮው አሥራ ሁለት ሳይሆን ይጀመር ተባለ …
“ሱባዔውስ?”
“ምንም ድምፃቸው አልተሰማም፡፡ የመጀመሪያው ቦታ ላይ ፀንተናል … ባይሆንስ? ብሎ ነበረ ዘሪሁን … የታሰበው ባይሆንስ አፅሙ! ‘ይሆናል ይሆናል ነው - ፀልየህ መጠራጠር የለም’ አለ ክፍሌ ‘ጥያቄ የለም’ አለ፡፡
ከየት ይጀመር ተባለ … ባትሪም ተዘጋጅቷል፡፡ ድንግዝግዝ ያለ ነው፡፡ የቤ/ክህነቱን ፈቃድ ለማግኘት የሰበካው ማመልከቻ እዚህ ነው መባሉ ተጠቅሷል … እንዳጋጣሚ የሰንበቴው አለቃ  ከአባታችን ጋር አንድ ሰንበቴ ይጠጡ የነበሩ ናቸው - ጌታቸው የሚባሉ አሰላ የሸማኔ ሥራ ይሠራሉ … ውጣ ውረዱ ብዙ ነበር፡፡ Hard Fact ነው የምነግርህ! ብቻ ተፈቅዷል፡፡ ዘሪሁን ከዚህ ይጀመር አለ፡፡ እኛ ቄስ አራት ወረቀት ተጠቅልሎ የፊታውራሪ ስም የወደቀበት ጋ ቆፍሩ ብለው ነበር፡፡ ያ ሊደረግ አልቻለም፡፡ ቀኗ ተቆርጣለች - ስንቀብራቸው 60 ሳንቲም ነው ብሏል፤ ፍንጭ ሰጪው “ሌሎች ደሆች ናቸው፡፡ አካባቢያቸው ላይ የሉም፡፡ እሳቸው ቀንደኛው የተባሉት ብቻ ናቸው እዚህ የተቀበሩት” ብሏል፡፡ ቁፋሮው ቀጠለ … ድም ይላል መቃብር አመላካች ድምፅ …አንድ ሜትር አለፈ፡፡ አክሊሉም ደንግጧል፡፡ ክፍሌ ጭራሽ ርቋል፡፡ … እኔና ዘሪሁን ብቻ ነን ያፈጠጥነው …አንድ ሰዓት ሆነ … ነጋ… ቆፋሪዎቹ ሲጋራ ያጨሳሉ … ቀጫጭኖች ናቸው … አይዟችሁ ጠላም አረቄም ይመጣል አለ ዘሪሁን ሊያበረታታቸው … አንድ ሜትር ተኩል ላይ የእግር አፅሞች ማግኘት ጀመርን!!
ዶ/ር ሙሉጌታ ሲናገር ከቃላቱ በፊት ትንፋሹና የስሜት ነፀብራቁ አስቀድሞ የማሳመን ኃይል አለው … ልዩ ባህርይ አለው-ንፁህ ላህይ አለው፡፡ … ከዚያ እያሰፋን እያሰፋን ቀጠለ ቀጠለና ሚሥማር ተገኘ። የእግር አጥንቶቹ ላይ ሚሥማርና እንጨት አገኘን። “ምንድን ነው? … እሱም ይሰብሰብ ብቻ” አልን፡፡ ጨርቅ … ይሄ ቆምጬዎች የሚለብሱት ጥለት ዓይነት አለ አደለ … የቆየ የወይን ጠጅ ቀለም ያለው? እስከላይ እስከ ራስ-ቅላቸው ድረስ አገኘን ክሮች ሱፍ ክር ዓይነት አገኘን … እሱንም ሰበሰብን …አጥንት ስንሰበስብ እንደገና ሚሥማሮች አገኘን …ይሄን ያህል ረጃጅምም አይደሉም … የተቆለመሙ ጣውላ እንጨት ላይ የተቸከሉ፤ ሽራፊዎች ናቸው … ብዙዎቹ ሟሙተው ተበትነዋል …
38 ዓመት መሆኑ ነው አየህ፡፡ ምንድነው ብለን ሰበሰብን … እንደገና እዚህ አካባቢ (ወደ ወገቡ፣ ደረቱ እያሳየኝ ነው) ስንደርስም እንደዚሁ ምሥማሮች አገኘን … ያኔ የተደገፉበት ርብራብ ላይ የተመታ ሚሥማር ይሆን ወይ? አልን፡፡ አንድ እሱ ነው - በእንጨት ድጋፍ ላይ ቆሞ ቆይቶ ኋላ የተቀበረ ሰውነት! ከዛ ጋር ያኔ አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ጋ (አሰላ ዛሬ ደራርቱ ሆቴል የተሠራበት ቦታ)፣ ሙሉ ልብሳቸውን እንደለበሱ ተቸንክረው ለህዝብ ሲታዩ፤ እንደነበረ ይታወቃልና ከሱ ጋር ተገጣጠመልን! ከዚያ ጥርሳቸው ነው ሌላ ማስረጃ፡፡ ነጫጭ ጥርሳቸው በሙሉ ነበሩ፡፡
አልተነኩም! አንዱ ግን ባዶ ሆኖ አገኘን! ጥርሳቸው ላይ አንድ ወርቅ እንዳላቸው አውቃለሁ! አንዱ ጥርሳቸው ወርቅ ነው፡፡ ወርቁን አላገኘንም፡፡ ግን ባዶ ሆኖ አየን! ተወስዷል ብለን አሰብን - ሁለት በል እንግዲህ! ሌላ ሦስተኛው - የራስ ቅላቸው ግንባራቸው ላይ ተመቶ ተቦድሷል! በጥይት ደብድበዋቸዋል፡፡ እና ያ ምልክት ነው።
ያኔም በጣውላ ቸንክረው ሲያሳዩዋቸው፤ ግንባራቸው መመታቱን ያዩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እዚህ ግንባር አካባቢ ከመመታታቸው በስተቀር ሌላ በሙሉ እንዳሉ ናቸው/ነበሩ ነው የተባለው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሦስቱን ማስረጃ ናቸው ብለን ጨረስን፡፡ እኚህ ሱባዔ የገቡ መነኩሴ “አብረን ማህበር እንጠጣ ነበረና የክርስትና ስማቸውን አውቃለሁ እኔ እነግራቸኋለሁ” አሉን ደውለው፡፡ ልክ ስንጨርስ ምሥራቅ ጋ ተደውሎ ገ/መድህን መሆኑ ተነገራት፡፡ እኛ ስንጨርስ የክርስትና ስማቸው ሲታወቅ አንድ ሆነ! እንግዲህ ለፍትሐቱ ለፀሎቱ ማናቸውንም ስም ልንሰጥ ነበር፡፡
“በቤተሰብ የክርስትና ስማቸው ገ/መድህን እንደሆነ ይታወቃል?”
“ማንም ረሳ፡፡ እናቴን ጠየኩ - አታውቅም … ጋሽ ክፍሌን ጠየኩ አያውቅም… እኚህ መነኩሴ ከቻሉ ለማወቅ ሞክሩ ብለን ነበር … ታወቀ፡፡ ግን አስከሬኑን በመፈለጉ ላይ እኛኑ በፀሎት መልዕክተኛ አድርገው ይሆን ይሆናል ማን ያውቃል…”
“አምላኬ ሆይ አሳካላቸው ብለው ፀልየው ይሆንም ይሆናል … ማለትህ ነው?”
“ብቻ እኛ አየህ በአቦ-ሰጥ ነው የሞከርነው -  ግን እላዩ ላይ ነው ያረፍነው! ማለት ይቻላል… ይሄ መቼም ተዓምር ነው!! … በየትም በኩል ይምጣ ያሳካልን ኃይል አለ፡፡ ባለፈው ሣምንት አክሊሉ ጋ ደወልኩ፡፡ በየእሁዱ ፍትሐት እንዲደረግላቸው ይሄንን አፅሙን ሰብስበን - ትንሽ ሳጥን ነች-እሱዋ ውስጥ አድርገናል … አንድ መቃብር ቤት ውስጥ እዚያው ሚካኤል አሳረፍን ከዛ ነው የተነሳው በኋላ … ፍትሐቱ መደረጉን ለማረጋገጥ ባለፈው እሁድ ደወልኩለት -  ለአክሊሉ፡፡ አሁን ጨርሰናል-በየእሁዱ ፍታት ተደርጐላቸዋል…አለ፡፡ “እንግዲህ አደራ የቀብሩ ሥነስርዓት ላይ እንድትገኝ” አልኩት፡፡ ‘አንድ ሠርግ አለብኝ’ አለ፡፡ ግን እሱን ብሠርዝ ይሻላል፡፡ ይሄን ዓይነት አጋጣሚ ሁለተኛ አላገኝም” አለ። (ሠርግና ቀብር ለምርጫ ሲቀርብ! አስገራሚ ነው - ስሜት የሚነካ ነገር ነው) 
“አዎ ፈታኝ ነው! አንዱ ካንዱ exclusive (የየራሱ) ዓይነት ነገር ነው’ …”
“ከ38 ዓመት በኋላ የተገኘ አስከሬን ይሻላል ወይስ የአሁን ሠርግ?!”
ሳቅን በጣም፡፡

No comments: