Saturday, September 28, 2013

ከአስር ሺ ካድሬዎች አንድ ጀግና አትሌት ይሻለኛል!

የፌዴሬሽን ነገር አልተሳካልንም!
ሩጫ እንደ አፍ አይቀናም (ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን!)
.የዛሬውን ፖለቲካዊ ወጌን የምጀምረው በአትሌቲክስ ነው፡፡ አትሌቲክስና ፖለቲካ ምን አገናኛቸው እንዳትሉኝ ብቻ! (ቀላል ይገናኛሉ!) ወዳጆቼ … አትሌቲክስ ስፖርትነቱ ለጀግኖች አትሌቶቻችን ነው እንጂ ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሲገባ መልኩን ይቀይራል፡፡ (የቀለጠ ፖለቲካ ይሆናል!) ይሄ እኮ ሃሜት አይደለም፡፡ በመረጃም በማስረጃም የተደገፈ ሃቅ ነው (ፍ/ቤት የመሄድ ፍላጐት ግን የለኝም!) ለነገሩ ፍ/ቤትም ለካ እረፍት ላይ ነው፡፡ እናንተዬ … ፍ/ቤት በክረምት የሚዘጋው (የሚያርፈው) ድሮ ወንዝ እየሞላ መሻገሪያ ስለሚጠፋ ነው የሚባለው እውነት ነው እንዴ? አሁን ታዲያ የትኛው ወንዝ አስቸግሮን ይሆን? (የልማድ እስረኞች እኮ ነን!) 
ይሄውላችሁ … ስለ ፌዴሬሽኑ ፖለቲካ ከማውጋታችን በፊት ትንሽ “ሰለብሬት” ማድረግ አለብን - ስለ አትሌቶቻችን ድል!! እናንተ … የጦቢያ አትሌቶች እንዴት አንጀት አርስ ናቸው ባካችሁ! (ኧረ ሺ ጊዜ ይመቻቸው!) ለዓለማችን ኮከብ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ (እውነትም ነገር የገባት ሰጐን!) እጅ ነስቻለሁ! ለ800 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ባለድሉ ለመሃመድ አማንም እጅ ነስቼአለሁ - በአዲስ ርቀት ላስመዘገበው ድንቅ ውጤት! ነሐስን ጨምሮ ሌሎች ድሎችን (ከ4-10 ለወጡትም) ላገኙም እጅ ነስቼአለሁ፡፡ ለደረጃ ባይበቁም ጦቢያን አደባባይ ወክለው ለሮጡልን ምርጥ የአገሬ ልጆችም እጅ ነስቼአለሁ፡፡ በሴቶች ማራቶን በገጠማቸው አንዳንድ እክሎች ውድድሩን አቋርጠው ለወጡት የጦቢያ ጀግና አትሌቶችም እጅ ነስቼአለሁ (ፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ፃፉ ቢልም) አንዳንዴ ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ? ኢትዮጵያን የሚመሯት ምነው አትሌቶች በሆኑ እላለሁ (የድል አርማ ናቸዋ!)

እናላችሁ … በብዙ ጉዳዮች “ኮንሰንሰስ” ላይ የማይደርሰው የአበሻ ልጅ፣ በጥሩነሽ ድል እኩል ሲቦርቅ፣ እኩል ሲፈነድቅ፣ እኩል ሲቀኝ፣ እኩል ሲያደንቅና ሲያሞግስ አስተውዬ “ይሄ ህዝብ ጀግና ይወዳል” አልኩኝ (ጀግና ነው የጠፋው ማለት ነው?) እናላችሁ… ለወትሮው የፌዝ መድረክ የነበረው ፌስቡክ እንኳን አትሌቷን በማወዳደስ ሲባትል ነው የሰነበተላችሁ እውነትም ጀግና ይወዳል!
ኤፍሬም አማረ የተባለ ፀሐፊ ምን አለ መሰላችሁ? “የወርቅ እርግቢቷ ሞስኮም ላይ በረረች” (እሷ ማርስም ቢሆን ትበራለች!) እዚያው ፌስ ቡክ ላይ የሰፈረው ሌላው አስተያየት ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮምን በሾርኒ ወጋ ያደርጋል - አትሌቷን እያደነቀ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“እቺ ጥሩዬ የሚሏት እንዴት ታድላለች
የኢትዮጵያን ኔትዎርክ በፍጥነት በልጣለች፡፡”
ግጥሟ ዘና ብታደርገኝም ንፅፅሩ ብዙም አልተዋጠልኝም፡፡ እንዴ… ሮኬትና ጋሪ እኮ ነው የተወዳደረው! አንድ የፌስቡክ ውዳሴ ደግሞ እነሆ (ለሰጐኒቷ!) “አሳፍራን የማታውቀው የወርቅ መአድኗ (አዶላ ማለት ይቻላል) ኢትዮጵያዊቷ ጥሩነሽ ዲባባ፤ አሁንም ህዝቦቿን ተሸክማ ሞስኮ ላይ በረረች (ከ85 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተሸክሞ መብረር በጣም ከባድ ነው!)” አያችሁልኝ… የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች “እኛ ነን የተሸከምናችሁ” እያሉ ውለታ ለማስቆጠር ይሽቀዳደማሉ እንጂ እውነቱስ ሌላ ነው! እኔ የምላችሁ … ኢህአዴግ ስንት ሺ ካድሬ ሰብስቦ ስንት ዘመን “የአገር ገፅ ግንባታ” ሲለን የከረመውን አትሌቷ በ10 ሺ ሜትር ብቻ ገነባብታው መጣች አይደል! - ያውም በእግሯ! ወርቅ ማጥለቅ በለመደ የአቦ ሸማኔ እግሯ!! (ከአስር ሺ ካድሬ አንድ ጀግና አትሌት ይሏል ይሄ ነው!!)
ለአፍታ ወደ ሌላ አገራዊ አጀንዳ ልውሰዳችሁና ወደ አትሌቲክሱ እንመለስበታለን (አምዴ እንደ ኢቴቪ ማስታወቂያ የለውም!) በቅርቡ በኢቴቪ አንድ ውይይት (ግምገማ ቢባል ይሻላል) ተላልፎ ነበር - በህዳሴ ግድብ መዋጮና የቦንድ ግዢ ዙርያ፡፡ የቀድሞው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር በነበሩት አቶ በረከት ስዩም የመድረክ መሪነት በተካሄደው ውይይት፣ ባለሀብቱ ለህዳሴው ግድብ ቃል የገባውን በመፈፀም ረገድ “ዳተኝነት” አሳይቷል ተብሏል፡፡ (በአጭሩ ቃሉን አልፈፀመም!) ባለሃብቱ በንፅፅር የቀረበው ደግሞ “ኑሮ ዳገት ሆኖበታል” ከሚባለው የመንግሥት ደሞዝተኛ ጋር መሆኑ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ እናም የደሞዝተኛውን ያህል እንኳን አስተዋፅኦ አላበረከተም የሚል ለዘብ ያለ ትችት ከመንግስት ወገን ተሰንዝሮበታል፡፡
ከዳያስፖራ ባለሃብት ጋር ቢወዳደርማ አለቀለት፡፡ አንዳንዱ ዳያስፖራ ሳልዘጋጅ ስለመጣሁ ነው እያለ ስንት እንደሚመዝ አይታችኋል? “ለጊዜው የ100ሺ ዶላር ቦንድ ገዝቻለሁ” እኮ ነው የሚለው! (ኢህአዴግ ዳያስፖራውን ጠበቅ ያድርግ!) በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ባለሀብቶች የኢህአዴግ አባላት ስለመሆናቸው መረጃ የለኝም እንጂ … ከሆኑ እኮ የሰላ ግምገማ የግድ ነበር (ሂሳቸውን መዋጥ አለባቸዋ!) ምናልባት አድርባይነት ይሆን? ወይስ አፈንጋጭነት? የፈረደበት ኮንሰንሰስ ላይ ያለመድረስ (አገራዊ መግባባት ነው የሚሉት) ሊሆንም ይችላል፡፡ እኔ የምለው ግን … በ97 ምርጫ ማግስት የተቋቋመው “የኢህአዴግ ደጋፊዎች ነጋዴ ፎረም” የት ደረሰ? ወደ ሊግነት ተቀየረ እንዴ? (“የአርቲስቶች ሊግ” ተቋቋመ ሲባል ሰማሁ ልበል?) ባለሃብቶችና ያልተፈፀመ የህዳሴ ግድብ ቃላቸውን እያሰላሰልኩ ሳለ አንድ ድንገተኛ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ (የፈጠራ እንዳይመስላችሁ!) እነዚህ በሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ለግድቡ አዋጥተዋል እንዴ? (ለጠቅላላ ዕውቀት ያህል ነው!) ምናልባት እኮ የ100ሺ ዶላር ባይሆን እንኳን የ100ሺ ብር ቦንድ ሸምተው ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ድንገት ጥፋተኛ ከተባሉ ለብይን ማቅለያ ሳይጠቅማቸው አይቀርም (የአገር ፍቅር መገለጫ እኮ ነው!)
አሁን ወደ አትሌቲክስ እንመለስ፡፡
ወደ ስፖርቱ ሳይሆን ወደ ፖለቲካው አትሌቲክስ፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ማንን መሰላችሁ? የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ነው - እሱ ነዋ የቀለጠ ፖለቲካ አድርጐት ቁጭ ያለው፡፡ ስፖርት ነው ያሉትማ ወርቅ አጥልቀው የአገራቸውን ባንዲራ በስንት ሺ ኪ.ሜትሮች ርቀት ላይ እንዲውለበለብ አድርገዋል-በድላቸው!
እንደኔ ሰምታችሁ እንደሆነ ባላውቅም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አንድ በዓይነቱ ለየት ያለ ማስፈራርያም ማስጠንቀቂያም የሚመስል መግለጫ አውጥቷል - በሞስኮው የሴቶች ማራቶን ውድድር አቋርጠው ለወጡት አትሌቶቻችንን! ውድድሩን አቋርጠው የወጡት አትሌቶች ምክንያታቸውን በፅሁፍ (በደብዳቤ) ለፌዴሬሽኑ እንዲገልፁ ተጠይቀዋል (ውድድር ማቋረጥ ወንጀል ሆነ እንዴ?) አይገርማችሁም … አትሌቶች ውድድር አቋርጠው የሚወጡት ለምን እንደሆነ የማያውቅ ፌዴሬሽን ነው ያለን (ፌዴሬሽን አይዋጣልንም ልበል?) እኔማ በጣም ስለገረመኝ ጥያቄውን መልሼ ለራሱ አቀረብኩለት - ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ፡፡ (ለአመራሩ ማለቴ ነው!) “እስቲ ገምቱ እነ ቲኪ ገላና ለምንድነው የሞስኮውን ውድድር አቋርጠው የወጡት?” ምናልባት ይሄ ጥያቄ ለፌዴሬሽኑ አመራሮች ጠጠር እንዳይልባቸው ፈራሁ (መጠየቅና መመለስ ለየቅል ናቸዋ!) እናም እስቲ ምርጫ ልስጣቸው (እንደ ት/ቤት ፈተና!)
ሀ- የአገር ፍቅር ስሜት በማጣት (ለግል ጥቅም በማድላት!)
ለ- ፌዴሬሽኑን ለማሳጣት (መልካም ስሙን ጥላሸት ለመቀባት)
ሐ- አገሪቱን ለማተረማመስ ከሚያስቡ ኃይሎች ጋር በማበር
መ- ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ካላቸው ኃይሎች ጋር “ጋብቻ” በመፈፀም
ሠ. መንግስትና ህዝብ ደስ እንዳይለው በማድረግ የግል ፍላጐታቸውን ለማርካት
ረ. ሁሉም መልስ ይሆናሉ
እርግጠኛ ነኝ በኢትዮጵያ የፈተና ታሪክ ብዙ ምርጫዎች የቀረቡበት ጥያቄ ይሄኛው ነው፡፡ ለነገሩ እኮ ደብዳቤ መፃፍ ቁም ነገር ሆኖ አይደለም (የፍቅር ደብዳቤ አይሁን እንጂ!) ግን ለምን እንዲህ በጥድፊያ አደረጉት? አንዱ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ? “ያጣደፉትማ አትሌቶቹ ያቋረጡበትን ምክንያት እንዳይረሱት ብለው ነው” (ወረቀት የያዘው … ይባል የለ!) “ምን መሰለህ …” ብሎ ቀጠለ ወዳጄ “አየህ … ህመምና ስቃዩን ሳይረሱት በትኩሱ እንዲገልፁትም ብለው ነው” አለኝ፡፡ (የፌዴሬሽኑ ቃል አቀባይ የሆነ መሰለኝ!) በደርግ ዘመንም እንዲሁ ጀግናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር፤ በአንድ ውድድር ላይ ወርቅ ሳይሆን ብር አምጥቶ ወደ አገሩ ሲመለስ በመንግስት ባለስልጣን ተጠርቶ (ካድሬ በሉት!) ተግሳፅ ነገር ደርሶበታል የሚባል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ (የደርግ ርዝራዦች ፌዴሬሽኑ ውስጥ አሉ ማለት ነው?) በእርግጥ የፌዴሬሽኑ አመራር የመላዕክት ስብስብ ነው ብዬ አላስብም (የአምባገነኖች መፈንጪያ ነውም አልወጣኝም!) ግን ፌዴሬሽኑ የስፖርት ሳይሆን የፖለቲካ ፓሽን ባላቸው ግለሰቦች ሳይሞላ አልቀረም፡፡
የፌዴሬሽኑ ፖለቲካ ግን ይሄ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ በ10ሺ ከዓለም በአንደኝነት ደረጃ ላይ የምትገኘውና በ5ሺ ደግሞ በሁለተኝነት ላይ ያለችው ጀግናዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ5ሺ ውድድር እንዳትካፈል ተደርጋለች - የማሸነፍ ብቃት እንዳላት እየታወቀ! ለምን አትሉም? ለተተኪዎች እድል ለመስጠት በሚል ተልካሻ ምክንያት!! እንዴ… ተተኪዎች እሷ የደረሰችበት ደረጃ ላይ መድረስ ያለባቸው በኮታ ነው በብቃት? ጥሩነሽ እኮ ለዚህ የበቃችው አርአያ የሆኗት እነደራርቱ “ተተኪ ነሽ” ብለው እድል ስለሰጡዋት አይደለም፡፡ በብቃቷ አሸንፋና ልቃ ነው!! ቀነኒሳም አርአያዬ የሚለውን አትሌት ኃይሌን አሸንፎ ነው ለዛሬው ስኬት የበቃው፡፡ እናም ስፖርት እንደ ፖለቲካ አይደለም - በችሮታና በምፅዋት አይገኝም (ብቃትና ልቀት ነጥሮ የሚወጣበት ነው!) ምናልባት የምፈራው ምን መሰላችሁ? የፌዴሬሽኑ አመራር የኢህአዴግን የመተካካት ስትራቴጂ በቀጥታ ቀድቶ እየተገበረ እንዳይሆን? (ጥርጣሬ እኮ ነው!) ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቃላችሁ? የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና) አንዴ ወጣቶችን ሰብስበው ሲያወያዩ “ሥልጣን ማንም የሚሰጣችሁ የለም! ራሳችሁ ናችሁ መውሰድ ያለባችሁ!” ብለው ነበር (ፌዴሬሽኑ አልተዋጠለት ይሆን?) ወጋችንን ከፌስ ቡክ ላይ በተገኘ የሳምንቱ ምርጥ ጥቅስ እንቋጭ፡-
“ሥራችሁን በፍፅምና ስታከናውኑ ያኔ ጥሩነሽ ዲባባ ትባላላችሁ” ከዚህ በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ (እቺኛዋ የእኔ ናት!) የኢትየጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ሆናችሁ ማለት ነው፡፡

No comments: