Thursday, March 14, 2013

ሥነ-ምግባር በሃይማኖት ወይስ በፍልስፍና?

ማህበረሰብ ከሌለ ወግና ስርዓት አይኖርም፡፡ ወግና ስርዓት ከሌለ ደግሞ ነውር ወይም ክብር አይኖርም፤ ሥነ-ምግባር ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውንና የሌለውን ድርጊት መለየትና ነውር የሆነውን ድርጊት የማስወገድ ሂደት ነው፤ ስለሆነም ለማህበረሰባዊ ስነ ምግባር (morality) መከሰት የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ የማህበረሰብ መገኘት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ባዶ ቤት ውስጥ ሙሉ ቀን ራቁቱን ቢዘዋወር ምንም ነውር የለውም፤ ነገር ግን ያው ግለሰብ ለአንድ ደቂቃ ያህል ከተማ ውስጥ እርቃኑን ቢዘዋወር እንደ “ነውረኛ” ወይም “እብድ” መቆጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በሌላ በኩል ታላቁ አትዮጵያዊ ጸሐፊ ከበደ ሚካኤል በግጥማቸው “ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” ብለዋል፡፡
ወግና ስርዓት፣ ነውርና ክብር ስለክፋትና ደግነት፣ ጥሩነትና መጥፎነት፣ እንዲሁም ስለ ስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ትክክለኝነትና ስህተትነት ምንነት፣መስፈርትና አስፈላጊነት የመሳሰሉትን ሃሳቦች የሚያጠና ዓቢይ የፍልስፍና ዘርፍ ሥነ-ምግባር (Ethics) ይባላል፡፡ ሥነ ምግባር “አንድን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለን የምንመዝነው ከምን አንጻር ነው?” የሚል መሰረታዊ

ስትሠራ እንጂ ስታስብ መሳሳት የለብህም

“የማይሠራ ሰው አይሳሳትም” የሚለው አባባል የሰው ልጅ በስራ ላይ ሳለ ስህተት ቢፈጽም እንኳ ሰብዓዊ ባህርይ ነውና ከስህተቱ እንዲማር መምከር እንደሚገባ እንጂ በአግራሞት የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያስተምር ነው፡፡ ነገር ግን በስራው ላይ የተፈጠረው ስህተት ከተግባር ሳይሆን ከተሳሳተ አስተሳሰብ የመነጨ ከሆነ ነገሩ የከፋ ይሆናል፤ ምክንያቱም በአስተሳሰቡ ላይ ህጸጽ ያለበት ሰው የሚሰራው ወይም የሚናገረው ሁሉ ስህተት ስለሆነና ለእርሱ ለባለቤቱ ግን ስህተቱ ሁሉ ትክክል ስለሚመስለው በቀላሉ እውነት ላይ ለመድረስ ወይም ትክክለኛ ስራ ለመስራት እጅግ በጣም ከባድ ይሆንበታልና፡፡
የሚናገሩና የሚጽፉ ሰዎች ስለትክክለኛ አስተሳሰብ ምንነት ባለማወቅ ወይም እያወቁ ሌሎችን ለማታለል በማሰብ የአስተሳሰብ ህጸጾችን (ፋላሲ) ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ህጸጾች በቅዱሳት መጻህፍት አረዳድና አተናተን፣ በቴሌቪዥንና ሬዲዮ የማስታወቂያ ቋንቋ፣ በጥናትና ምርምር ስራዎች፣በፖሊስ ምርመራና በፍርድ ቤት ችሎት ሂደት፣ በታላላቅ ስብሰባዎችና ክርክር መድረኮች፣ በአሰሪና ሰራተኛ የስራ ምልልስ እንዲሁም በግለሰቦች የዕለት ተዕለት ተግባቦታዊ ምልልስና በመሳሰሉት ማናቸውም የህይወት መድረኮች ላይ ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡
አሪስጣጣሊስና ከእርሱ በኋላ የተነሱ የትክክለኛ አስተሳሰብ ጠበብት፣ የአስተሳሰብ ህጸጾችን በተለያዩ

የአምላክን መኖር በፍልስፍና ማረጋገጥ ይቻላልን?

አንዱ መልካም ነገር ከሌላው መብለጡ ግድ ከሆነና ከላይ የተመለከትናቸው ነገሮች መልካምነት አንጻራዊ ነው ከተባለ ከመልካም ነገሮች ሁሉ የላቀ መልካም የሆነ፣ ለመልካምነቱ አቻ የሌለው መልካምነቱም ከራሱ የመነጨ (Intrisitic) አንድ አካል አለ ብሎ መደምደም አመክኗዊ ይሆናል፡፡ መልካም ነገሮች ሁሉ እንደሚወደዱ ሁሉ ይህ የመልካሞች ሁሉ መልካም (Supreme Good) የሆነ ታላቅ አካል ከመልካሞች ሁሉ የበለጠ ሊወደድ ይገባል ማለት ነው፡፡
የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም (universe) ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፣ የሚቆጣጠር፣ ከሰው ልጆች እውቀትና ኃይል በላይ የሆነ አምላክ (God) የሚባል ላዕላይ ነገር (Being) የመኖሩ ወይም ያለመኖሩ ጥያቄ የዓለም ጠቢባንን ለበርካታ ዘመናት ሲያስጨንቅ የሰነበተና ዛሬም ድረስ ብዙዎችን በማወዛገብ ላይ የሚገኝ ዓቢይ ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ አምላክ አለ? መኖሩን ወይም አለመኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል? እንዴት? በእምነት ብቻ? በፍልስፍና ? በሳይንስ? በእምነትና በፍልስፍና? መልሱ እንደየዘመናቱና እንደየመላሾቹ ግለሰቦች ማንነት ሃማኖታዊ፣ ሳይንሳዊ ወይም ፍልስፍናዊ መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡
ሃይማኖታዊው ምላሽ የአምላክን ህልውና በቅዱሳት መጻህፍት

ትክክለኛ አስተሳሰብ ሲኖርህ ትክክለኛ ሰው ትሆናለህ

ለቃላት ትክክለኛና ጥርት ያለ ትርጉም ለመስጠት ብሎም የቃላትን ብዥታና (vagueness) አሻሚነትን (ambiguity) ለማስወገድ ለእያንዳንዱ ቃል በተለያየ አውድ ውስጥ የሚኖረውን ብያኔ በትክክል መረዳትና እያንዳንዱንም ቃል በተገቢውና በትክክለኛ ቦታ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ የቋንቋ ፍልስፍና ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ “ደረቅ እንጀራ አለ” እና “ለምለም እንጀራ አለ” የሚሉትን በአዲስ አበባ እና በሐዋሳ ከተሞች የተለመዱ ሁለት የእንጀራ ሽያጭ ማስታወቂዎችን የቃላት አጠቃቀም ትክክለኝነትን ብናነጻጽር “ደረቅ እንጀራ” የሚለው ቃል “ድርቆሽ እንጀራ” የሚለውንም ትርጉም በውስጡ ስለሚይዝ የበለጠ አሻሚ (ambigious) ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የእስራኤሉ ንጉስ ዳዊት የሚሞትበት ቀን በቀረበ ጊዜ ልጁ ሰሎሞንን ያዘዘው ዋነኛ ትእዛዝ “ሰው ሁን” የሚል እንደነበር በመጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ እናነባለን፡፡ ሰው ሆኖ ከተፈጠረ በኋላ ሰው ሁን ተብሎ መታዘዙ ሰው መሆን በስጋና በደም ጸንቶ ከመንቀሳቀስ የዘለለ መለኪያ እንዳለው የሚያስረዳ ነው፡፡ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ “ማሰብ የሰውነት መገለጫ ነው” ሲል ደግሞ አንዱ መስፈሪያ ማሰብ (thinking) መሆኑን ይመሰክራል፡፡ “ማሰብ የሰውነት መገለጫ ነው” በሚለው ዓረፍተ ነገር የተስማማ ሰው “ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ትክክለኛ ሰው ነው” የሚለውን ዓረፍተ ነገር እውነትነትም በአመክንዮ መርህ መቀበል ይኖርበታል፡፡ በርግጥም ሁሉም ሰዎች ማሰባቸው እውነታ ቢሆንም ሁሉም ሰዎች በትክክል ማሰባቸው ግን በጥያቄ ምልክት መቀመጥ የሚገባው ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም በህጸጽ የተሞላ አስተሳሰብ ያላቸው በርካታ ሰዎች ህጸጾቻቸውንና የተሳሳተ ድምዳሜያቸውን በየደቂቃው በንግግራቸውም ሆነ በጽሁፋቸው ሲገልጹ ይስተዋላሉና፡፡ ለመሆኑ ትክክለኛ አስተሳሰብ ምንድን ነው?
ትክክለኛ አስተሳሰብ (correct thinking) በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ድምዳሜ የሚሰጥበት የአስተሳሰብ ስልት ነው፡፡ በእንግሊዝኛው (Logic) የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሃሳብ ሎጎስ (logos) ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን የትክክለኛ አስተሳሰብ ጥበብ የሚል ትርጉም ያዘለ ነው፡፡
ትክክለኛ አስተሳሰብ የሚከተለው የራሱ የሆነ ቀመር አለው፡፡ የመጀመሪያው መሰረታዊ የትክክለኛ አስተሳሰብ ቀመር ማሳመኛ አንቀጽ (argumnet) ይባላል፡፡ አንድ ማሳመኛ አንቀጽ እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ አንድ ወይም ከአንድ በላይ እውነት ወይም ሀሰት ሊባሉ የሚችሉ ዓረፍተ ነገሮችን ወይም ማስረጃዎችን (premises)፤ እንዲሁም ከእነዚህ ማስረጃዎች የመነጨ አንድ መደምደሚያ ዓረፍተ ነገር (conclusion) ሊኖረው ይገባል፡፡
ትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር ማንኛውንም ፍልስፍና ለመረዳትም ሆነ ለመስራት የምንገለገልበት የፍልስፍና ቋንቋ ነው፡፡ በዚህ ቀመር የሚመነጨው ድምዳሜ ፍጹማዊ (deductive) ወይም ምናልባታዊ (inductive) መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡
ፍጹማዊ የሚባለው ቀመር የማሳመኛ አንቀጹ ድምዳሜ ከቀረበው ማስረጃ በፍጹም እርግጠኝነት (certainity) የመነጨ ሲሆን ነው፡፡ ይህም አንድ ሰው ባቀረበው ማሳመኛ ውስጥ የዘረዘራቸው ማስረጃዎች በሙሉ እውነት ከሆኑ ከዚህ የመነጨው ድምዳሜ በምንም መንገድ ሀሰት ሊሆን አይችልም፡፡ በሂሳብ ስሌት፣ በብያኔ ወይም በሲሎጂዝም ላይ ተመስርቶ የሚሰጡ ድምዳሜዎች የፍጹማዊ ድምዳሜ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ “ኢትዮጵያውን በሙሉ ብርቱ የሀገር ፍቅር ስሜት አላቸው”፤ እና “አቶ ኦንጋዬ ኢትዮጵያዊ ናቸው”፤ የሚሉት ሁለት የማስረጃ ዓረፍተ ነገሮች “እውነት” መሆናቸውን ካረጋገጥንና ከዚህም “አቶ ኦንጋዬ ብርቱ የሀገር ፍቅር ስሜት አላቸው” የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ በመደምደሚያ ስለቀረበው ዓረፍተ ነገር እውነትነት መናገር ያለብን በፍጹም እርግጠኝነት እንጂ በምናልባት አይደለም ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል በማሳመኛ አንቀጹ መደምደሚያ ላይ የተቀመጠው ዓረፍተ ነገር ከቀረቡት ማስረጃዎች በምናልባት (probability) የመነጨ ማሳመኛ ምናልባታዊ (Inductive) ቀመር ተከትሏል ይባላል፡፡
ይህም ማለት በማሳመኛው አንቀጽ ውስጥ በማስረጃነት የቀረቡት ዓረፍተ ነገሮች በሙሉ እውነት መሆናቸውን ብናረጋግጥ እንኳን ከማስረጃዎቹ የመነጨው መደምደሚያ እውነት ወይም ሀሰት የመሆኑ ጉዳይ በምናልባት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
በትንበያ፣ በምስስሎሽ፣ በምልክት፣ እንዲሁም በምክንያትና በውጤት ትስስር ላይ ተመስርተው የሚቀርቡ ማሳመኛዎች የምናልባታዊ አስተሳሰብ ቀመርን መርህ የተከተሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ “አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አስር ክፍለ ከተማዎች ይገኛሉ፡፡” እና “በየካ፣ በቦሌ ፣በጉለሌ፣ በኮልፌ ቀራንዮና በአቃቂ-ቃሊቲ ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ተፈጥሯዊ የመናፈሻ ስፍራዎች (Parks) ይገኛሉ” የሚሉት በማስረጃነት የቀረቡ ዓረፍተ ነገሮች እውነት እንደሆኑ ካረጋገጥንና ከዚህም ተነስተን “በተቀሩት አምስት ክፍለ ከተማዎች ውስጥም እንዲሁ ተፈጥሯዊ የመናፈሻ ስፍራዎች (Parks) ይገኛሉ” የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ በመደምደሚያ ስለቀረበው ዓረፍተ ነገር እውነትነት መናገር ያለብን በምናልባት እንጂ በፍጹም እርግጠኝነት አይደለም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ስለቀሩት አምስት ክፍለ ከተማዎች ይዞታ በማሳመኛ አንቀጹ የቀረበ ግልጽ ማስረጃ ስለሌለና ድምዳሜውን የምናመነጨው በይሆናል ስለሆነ ነው፡፡
ከህጸጽ የጸዳና ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ጥርት አድርጎ የማሰብ አቅም ይኖረዋል፡፡ ጥርት አድርጎ የሚያስብ ሰው ደግሞ ጥርት ያለና ትክክለኛ ቋንቋ ይናገራል፡፡ ትክክለኛ ቋንቋና ትክክለኛ አስተሳሰብ የተቆራኙ ናቸው፡፡ ማለትም ፍልስፍና ያለ ቋንቋ ሊገለጽ አይችልም፤ ቋንቋም በፍልስፍና ካልተቃኘ ጥርት ያለና ትክክለኛ ሊሆን አይችልም፡፡
ትክክለኛ አስተሳሰብ ሊመጣ የሚችለው በማንኛውም ቋንቋ ውስጥ የሚገኙ ቃላትን ትክክለኛ ፍቺና ብያኔ አውቆ በተገቢው ቦታ ላይ ብቻ መጠቀም ሲቻል ነው፡፡ ቀደምት የግሪክ ፈላስፎች ፍልስፍናቸውን የጀመሩትም በዚሁ የቃላት ፍቺ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአፍላጦን መምህር ሶቅራጥስ (dialectic) ተብሎ በሚታወቀው የፍልስፍና ዘዴው በጥያቄና መልስ ከበርካታ ሰዎች ጋር በሚያደርገው ምልልስ የሥነ-ምግባር ጽንሰ ሃሳቦችን ትክክለኛ ብያኔና ምንነት ጥርት አድርጎ ለማወቅና ለማሳወቅ ከፍተኛ ትግል ያደርግ እንደነበር ከምዕራባውያን የፍልስፍና ታሪክ እንማራለን፡፡ ሶቅራጥስ ተማሪዎቹ ፍትህ፣ ፍቅር፣ ጀግንነት፣ ትዕግስት የመሳሰሉት የስነምግባር ቃላት ትርጉም በራሳቸው ተመራምረው እንዲደርሱበት በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር የቃላቱ ፍቺ ነው ብለው የሚሰነዝሩትን ምላሽ ጎዶሎነት ወይም ስህተት በአመክንዮ ያሳያቸውና የተሻለና የመጨረሻውን ትክክለኛ ብያኔ እንዲፈልጉ ያበረታታቸው ነበር፡፡
ከዚህም ባሻገር የጥያቄና መልስ ተሳታፊዎቹ የሶቅራጥስን ተቋቁሞ (defense) መከላከል ሲያቅታቸውና ለቀረበው ቃል አንድ የተለመደ ፍቺ እንዲነግራቸው ሲጠይቁት በማህበረሰብ አስተሳሰብ (communal thinking) ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑና በግል ፍልስፍና (individual thinking) መኖርን እንዲማሩ “የማውቀው አለማወቄን ብቻ ነው” የሚል መልስ ይሰጣቸው ነበር፡፡
ለቃላት ትክክለኛና ጥርት ያለ ትርጉም ለመስጠት ብሎም የቃላትን ብዥታና (vagueness) አሻሚነትን (ambiguity) ለማስወገድ ለእያንዳንዱ ቃል በተለያየ አውድ ውስጥ የሚኖረውን ብያኔ በትክክል መረዳትና እያንዳንዱንም ቃል በተገቢውና በትክክለኛ ቦታ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ የቋንቋ ፍልስፍና ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ “ደረቅ እንጀራ አለ” እና “ለምለም እንጀራ አለ” የሚሉትን በአዲስ አበባ እና በሐዋሳ ከተሞች የተለመዱ ሁለት የእንጀራ ሽያጭ ማስታወቂዎችን የቃላት አጠቃቀም ትክክለኝነትን ብናነጻጽር “ደረቅ እንጀራ” የሚለው ቃል “ድርቆሽ እንጀራ” የሚለውንም ትርጉም በውስጡ ስለሚይዝ የበለጠ አሻሚ (ambigious) ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ይህም ሲባል በዚህ ሐረግ ሰዎች አይግባቡበትም ማለት ሳይሆን ትክክለኛና ጥርት ያለ አስተሳሰብ ባለው ሰው የተጻፈ የጽሁፍ ሥራ መለኪያ አንባቢያን ጽሁፉን ብቻ አንብበው በቀጥታና በትክክል እንዲረዱ እንጂ በጸሐፊው አእምሮ ውስጥ የሚመላለሰውን ወይም ጸሐፊው ለመግለጽ የፈለገውን በመገመት ሞልተው እንዲገነዘቡ የማይጋብዝ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡
ትክክለኛ አስተሳሰብ (ሎጂክ) ወደ አንድ እውነት ወይም እውቀት ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጉዞ ላይ ቁልፍ ቦታ አለው፡፡ ለምሳሌ በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ሂደት ውስጥ ተመራማሪው የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህን በሚገባ ካልተከተለ አንድ አዲስ ግኝት ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አይችልም፡፡
አንድ ሃኪምም የታካሚውን ትክክለኛ በሽታ ለማወቅ መጀመሪያ ለግለሰቡ ከሚያቀርበው ቃለ መጠይቅ፣ኋላም ከቤተ ሙከራ በግለሰቡ የጤና ችግር ዙሪያ ከሚሰበስባቸው ልዩ ልዩ መረጃዎች ላይ በመንተራስ ስለታካሚው የበሽታ ምንነት አንድ ትክክለኛ እውቀት ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መቻሉ የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህን ጉልህ ሚና የሚያመላክት ነው፡፡
አንድ ሰው አንድን አዲስ ግኝት ወይም እውቀት እውነት ነው ብሎ ከመቀበሉ በፊት በትክክለኛ አስተሳሰብ ቀመር መነጽር በጥልቀት መመርመር ይገባዋል፡፡ አንድን ድምዳሜ እውነት ወይም ሀሰት ነው ብሎ ከመደምደሙ በፊትም እንዲሁ ስለእውነት ምንነት እውነተኛ እውቀትና ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተመራማሪው የዓለም የሳይንስ ፍልስፍና (Philosophy of Science) ሊቃውንት ስለ እውነት ምንነትና ባህርይ ያቀረቧቸውን ዘርፈ ብዙ አመለካከቶች በስፋት ሊመረምርና ከእነዚህ ውስጥም እርሱ ከተሰማራበት አውድ ጋር የሚስማማ አንድ ጥርት ያለ አመክኗዊ አቋም እንደያዘ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ “እውነት አንድ ነች ወይስ ብዙ? እውነት አንጻራዊ ነች ወይስ ፍጹማዊ?፤ እውነት ጊዜያዊ ነች ወይስ ዘለዓለማዊ? እውነተኛ እውቀት ሳይንሳዊ ነው ወይስ ሃማኖታዊና ባህላዊ? ሁሉንም እውቀት የምናገኘው ከተወለድን በኋላ በስሜት ህዋሶቻች አማካኝነት በምናካብተው ገጠመኝ ነው ወይስ አብሮን የሚወለድ እውቀት አለ? እውቀት በአመክንዮና በሰብአዊ ምልከታ ይገኛል ወይስ በመለኮታዊ ኃይል ይገለጻል?” ወዘተ የሚሉትን አወዛጋቢ ሃሳቦች በአጽንኦት መርምሮ አንድ ትክክለኛ አቋም ላይ መድረስ ይኖርበታል፤ይህም ከትክክለኛ አስተሳሰብ (Logic) ውጪ የሚቻል አይሆንም፡፡
የራሳችንን ወይም የሌላን ሰው አስተሳሰብ በመገምገም ጥሩ ወይም መጥፎ አስተሳሰብ በማለት ልንፈርጀው እንችላለን፡፡ አንድን አስተሳሰብ ትክክለኛ ወይም ህጸጽ ያለበት ብሎ ለመፈረጅ ከማሳመኛ አንቀጹ (argumnet) አወቃቀርና በማስረጃነት ከቀረቡት ዓረፍተ ነገሮች የእውነታ እሴት (truth value) አንጻር በጥንቃቄ መገምገምን ይሻል፡፡ ማሳመኛ አንቀጹ ተገቢ (valid) ወይም እውነተኛ (sound) ከሆነ በድምዳሜው የተመለከተው አስተሳሰብ ትክክለኛ አስተሳሰብ ይባላል፡፡ ይሁንና ማሳመኛ አንቀጹ የማይገባ (Invalid) ከሆነ ህጸጽ ያለበት (fallacious) መሆኑ ይረጋገጣል ማለት ነው፡፡ አንድ ማሳመኛ አንቀጽ ተገቢ ነው የሚባለው ድምዳሜው ከማስረጃው ከማስረጃው(ዎቹ) በትክክል የመነጨ ከሆነ፤ ወይም የቀረቡት ማስረጃዎች በመደምደሚያው የቀረበውን ሃሳብ በትክክል ለመደገፍ የቀረቡ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይሁንና ይህ ካልሆነ ወይም በአንቀጹ ውስጥ የሚገኙ ዓረፍተ ነገሮች በትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር መሰረት በአመክንዮ ካልተሳሰሩ በማሳመኛ አንቀጹ የተመለከተው መደምደሚያ የተሳሳተ፤አስተሳሰቡም ህጸጽ (Fallacy) ያለበት ነው እንላለን፡
የአስተሳሰብ ህጸጽ (Logical fallacy) የሚከሰተው በማሳመኛ አንቀጽ ላይ የቀረበው መደምደሚያ ከቀረቡት ማስረጃዎች በተገቢ (valid) መንገድ ያልወጣ ከሆነ ነው፡፡ አንድ መደመደሚያ ከማስረጃው በተገቢ መንገድ አልወጣም የሚባለው ግለሰቡ ድምዳሜውን ለመስጠት ያቀረባቸው ማስረጃዎች በመደምደሚያው ላይ ለቀረበው ይዘት አመክኖያዊ አስፈላጊነት የሌላቸው ከሆኑ፣በማሳመኛነት የቀረበው ምስስሎሽ (Analogy) ደካማ ከሆነ፣ ማሳመኛው ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ አሻሚ (ambigious) ቃላትን በመጠቀም የተገነባ ከሆነ፣ በማሳመኛው የቀረበው ድምዳሜ በቀጥታ ከማስረጃዎቹ የመነጨ ሳይሆን የግለሰቡን አመለካከትና ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ከሆነ እንዲሁም በጽሁፍ ውስጥ በስዋስው የትርጉም ምስስሎሽ ስህተት የተሳሳተ ድምዳሜ ከተሰጠ ነው፡፡

Wednesday, March 13, 2013

ዶ/ር ቆንጂት ፈቃደ



‹‹እናትና አባቴ ድኸው ያደጉበት
ካያት ከቅድመ አያት የተረካከቡት
አፈር የፈጩበት ጥርስ የነቀሉበት
አገሬ ዓርማ ነው የነፃነት ዋንጫ
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ብጫ››

የሚለውን የስመ ጥሩው ገጣሚና ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥም ታኅሣሥ 23 ቀን 2003 ዓ.ም. የተስተጋባው፣ እንደ አዘቦቱ በጥበብ መናኸሪያ፣ በኪነት መዲና አልነበረም፡፡ በአዲስ አበባ በቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የታዋቂዋን ዶ/ር ቆንጂት ፈቃደ ቀብር ተከትሎ እንጂ፡፡

ዶ/ር ቆንጂት፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የቦርድ አባል፣ በሲቪል ማኅበረሰብ በተለይም በሴቶች መብት ተሟጋች፣ በፓኖስ ምሥራቅ አፍሪካ የምክር ቤት አባልና ተጠባባቂ ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡

የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሽመልስ ሀብቴና በመድኃኔ ዓለም ትምህርት ቤቶች የተከታተሉት ዶ/ር ቆንጂት፣ በምሕንድስና ትምህርት ከሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ በፒኤችዲ ከተመረቁ በኋላ፣ በሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በተመራማሪነትና አማካሪነት ሠርተዋል፡፡ በአሜሪካ ተማሪ በነበሩበት ጊዜም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ማቴሪያል ፊዚክስ አስተማሪ የነበሩት ዶ/ር ቆንጂት፣ በሚዲያ ውስጥ ከነበራቸው ሚና ባሻገር የግል ራዲዮ ጣቢያ ለመጀመር ተቋቁመው ከነበሩት አንዱ የነበረው አዲስ ብሮድካስቲንግ ኩባንያን ከመሠረቱት መካከል አንዷ ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ካለው ቤተሰብ (አያታቸው ነጋድራስ ወዳጆ አሊ፣ አጎታቸው አቶ ክፍሌ ወዳጆ) የወጡት ዶ/ር ቆንጂት፣ የተወለዱት ከወ/ሮ ዝማም ወዳጆና ኮሎኔል ፈቃደ መኩሪያ ረቡዕ፣ የካቲት 2 ቀን 1947 ዓ.ም. ነበር፡፡

ግንባር ቀደም የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የትምህርት ሰው (አካዴሚያዊት) የነበሩት ዶ/ር ቆንጂት ባደረባቸው የካንሰር ሕመም ምክንያት በአሜሪካ ያረፉት እሑድ፣ ታኅሣሥ 17 ቀን 2003 ዓ.ም. ነበር፡፡

ግብዓተ መሬት ከተፈጸመ በኋላ በቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ዐውደ ምሕረት ላይ እህታቸው ወ/ሮ ስንዱ ፈቃደ፣ የገብረ ክርስቶስ ደስታን ‹‹ሀገሬ›› ግጥም ሦስት አንጓዎች አንብበውታል፡፡

‹‹... መቅደስ ነው አገሬ አድባር ነው አገሬ
እሾህ ነው አገሬ
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ፡፡
አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት
ለምለም ነው አገሬ
ውበት ነው አገሬ
ገነት ነው አገሬ፡፡
ብሞት እሔዳለሁ ከመሬት ብገባ
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ፡፡››

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምሥረታ

ለብዙ ሺ ዓመታት ኢትዮጵያ ብቻዋን በአኅጉሩ ውስጥ ከአውሮፓውያኖች የቅኝ ግዛት ቀንበር ውጪ ቆይታ የሙሶሊኒ ፋሺስት ኢጣልያ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ወርራት በነበረ ጊዜ አርበኞች ልጆቿ ውድ አገራቸውንና ነጻነታቸውን አሳልፈው ላለመስጠት አምስት ዓመታት ሙሉ ተዋጉ። ንጉሠ ነገሥታቸውም የእዚህን የግፍ ወረራ ለማጋፈጥ በዓለም መንግሥታት ማኅበር መድረክ ላይ ሲቀርቡ፣ ከአፍሪቃ አኅጉር ብቸኛዋ አባል ኢትዮጵያ ማንም አጋዥ አገር አልነበራትም።
ለአኅጉሩ ነጻነት በቅኝ ግዛት ሥርም የነበሩት ሕዝቦች፤ በነጻነትም ላይ የነበሩት አገራት የአውሮፓውያንን መዥገራዊ ልጥፍነት ለማላቀቅ ብዙ ከታገሉ በኋላ በሰሐራዊ አፍሪቃ የካቲት ፳፯ ቀን ፲፱፻፵፱ ዓ/ም ጋና ነጻ ሆነች። ከዚያ አስከትሎ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት እስከተመሠረተ ድረስ በ፲፱፻፶፩ ዓ/ም ጊኒ ነጻ ስትሆን በ ፲፱፻፶፪ ዓ/ም አሥራ አምስት አገራት፤ በ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ሦሥት አገራት፤ በ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ደግሞ አራት አገራት ነጻነታቸውን ተቀዳጁ።
የአኅጉሩ መሪዎች በዓለም መድረክ ላይ ለበለጠ ተሰሚነት የትብብርን ግንባር ማሳየት እንደነበረባቸው በመገንዘብና ገና ነጻ ላልወጡትም ወንድም አገሮች ሉዐላዊነት መታገል ስለነበረባቸው ዓላማቸውን ግብ ለማድረስ በሁለት ቡድን ተከፍለው ፣ ባንድ በኩል እራሱን “የዘመናዊ ተራማጅ” ብሎ የሚጠራው፣ በጋናው ፕሬዚደንት ክዋሜ ንክሩማ የሚመራው የ “ካዛብላንካ ቡድን” በ ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ተመሠረተ። ይሄ ቡድን የአኅጉሩን መንግሥታት በኅብረት ለማዋሃድ ዓላማ የያዘ ሲሆን አባላቱ ጋናአልጄሪያጊኒሞሮኮግብጽማሊ እና ሊቢያ ነበሩ።
ሁለተኛው ቡድን የ”ሞንሮቪያ ቡድን” ሲሆን የተመራው በ ሴኔጋል ፕሬዚደንት ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንግሆር ነበር። አባላቱ ሴኔጋልናይጄሪያላይቤሪያ እና ኢትዮጵያ ሲሆኑ የነሱ የኅብረት አስተያየት ደግሞ የዱኛ ኅብረት ሳይሆን ፍላጎታቸው ረጋ ባለ ሁኔታ የዱኛኪን ኅብረት አንድነትን ያስከትላል የሚል ነበር።
መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ታላቅ ጥረትና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ ሁለቱም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ እንዲገናኙ በተደረገው ጥሪ መሠረት ተሰባስበው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን የስምምነት ውል ፴፪ ነጻ ሀገሮች ሲፈርሙ ድርጅቱ ተመሠረተ።

፴፪ቱ መሥራች መሪዎች

የካዛብላንካ ቡድን

ጋና

ክዋሜ ንክሩማ
Flag of Ghana.svg
የካቲት ፳፯ ቀን ፲፱፻፵፱ ዓ/ም ነጻነቷን በዶክቶር ክዋሜ ንክሩማ መሪነት ከብሪታንያ የተቀዳጀችው ጋና በዚህ በመጀመሪያው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የምሥረታ ስብሰባም የተወከለችው በኒህ ታላቅ መሪ ነበር።
ዶክቶር ንክሩማ የ”ካዛብላንካ ቡድን” መሪ ሲሆኑ በሽከታ ኅብረት (pan-Africanism) የሚባለው ፍልስፍና ምንጭ እንደነበሩ ይገመታል።

ሞሮኮ

ንጉሥ ሀሰን
Flag of Morocco.svg
ሞሮኮእስከ መጋቢት ፳፱ ቀን ፲፱፻፵፰ ዓ/ም ድረስ በፈረንሳይ ሥር ነበረች። ከነጻነት ወዲህ መሪዋ ግርማዊ ዳግማዊ ሀሰን የሞሮኮ ንጉሥ በጋናው ፕሬዚደንት ክዋሜ ንክሩማ የሚመራው የ “ካዛብላንካ ቡድን” በ ፲፱፻፶፬ ዓ/ም በካዛብላንካ ከተማቸው እንዲመሠረትና
በዓላማው እንዲገፋበት ጥረዋል። ወደፊትም በ ሞሮኮ ሥር በምትገኘው ሰሐራዊ የአረብ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ነጻነት ምክንያት ከድርጅቱ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት አግራቸውን ከአባልነት አስወግደዋል።

አልጄሪያ

አህመድ ቤንቤላ
Flag of Algeria.svg
አልጄሪያ የነጻነት ትግል ፲፱፻፵፮ ዓ/ም በጦርነት ሲጀመር የነጻነት አውጪ ግንባር ዓባል የነበሩት አህመድ ቤንቤላ አገሪቱ ነጻነቷን ከፈረንሳይ ሰኔ ፳፮ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ስትቀዳጅ በመሪነት የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን ጨበጡ።

ግብጽ

ጋማል አብደል ናስር
Flag of Egypt.svg
ጋማል አብደል ናስር ከመጀመሪያው የግብጽ ፕሬዚደንት ሙሐመድ ናጊብ ጋር በ፲፱፻፵፬ ዓ/ም የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ንጉሡን ቀዳማዊ ፋሩክን ገለበጡ።
ናሰር የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን በ፲፱፻፵፰ ዓ/ም ሲጨብጡ የአገሪቱ ሁለተኛው ፕሬዚደንት በመሆን እስከ ዕለተ ሞታቸው፣ መስከረም ፲፰ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ/ም ድረስ አገልግለዋል።

ማሊ

ሞዲቦ ኬይታ
Flag of Mali.svg
ባማኮ ከተማ ላይ ግንቦት ፳፯ ቀን ፲፱፻፯ ዓ/ም የተወለዱት ሞዲቦ ኬይታ አገራቸው ማሊ ነጻነቷን ከፈረንሳይ ሰኔ ፲፫ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ስትቀዳጅ የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን ጨብጠው እስከ ፲፱፻፷ ዓ/ም አገልግለዋል።

ሊቢያ

ንጉሥ ኢድሪስ
Flag of Libya.svg
ሊቢያ ሉዓላዊ እና ነጻ፣ በሕገ መንግሥት የሚተዳደር የዘውድ ሥርዐተ መንግሥት ታኅሣሥ ፲፬ ቀን ፲፱፻፵፬ ዓ/ም ላይ ስታውጅ በንጉሥ ኢድሪስ መሪነት ነበር። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትም ሲመሠረት አዲስ አበባ ላይ በመሳተፍ ውሉን የፈረሙት እኒሁ ንጉሥ ኢድሪስ ነበሩ።
በኋላ በነሐሴ ፳፮ ቀን ፲፱፻፷፩ ዓ/ም በሀያ ሰባት ዓመቱ ወጣት መኮንን፣ ሙአማር ጋዳፊ የተመራ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ንጉሡን ቱርክ አገር በህክምና ላይ እንዳሉ ከሥልጣን አወረዳቸው። ንጉሥ ኢድሪስ በግንቦት ፲፱፻፸፭ ዓ/ም ካይሮ ላይ አረፉ።

ጊኒ

ሴኩ ቱሬ
Flag of Guinea.svg
ጊኒ ነጻነቷን ከፈረንሳይ መስከረም ፳፪ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ/ም ተቀዳጀች። የአገሪቷ የመጀመሪያ ፕሬዚደንት ሴኩ ቱሬ ሲሆኑ በ ፲፱፻፸፮ ዓ/ም እስከሞቱ ድረስ በዚሁ ሥልጣን ቆይተዋል።

የሞንሮቪያ ቡድን

ኢትዮጵያ

ቀ. ኃ. ሥ.
Flag of Ethiopia (1897).png
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት : የስብሰባው አስተናጋጅና የተከፋፈሉትን ሁለት ቡድኖች በማስተባበር አንድ ድርጅት እንዲመሠረት ያደረጉ መሪ ሲሆኑ፤ የማኅበሩም የውል
ረቂቅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በአቶ ከተማ ይፍሩ ትጋትና ድካም ተዘጋጅቶ እንዲፈረም አድርገዋል። በአብዝኛው ዓለም አቀፍ አስተያየት “የአፍሪቃ አባት” የሚል ስምም አትርፎላቸዋል።

ላይቤሪያ

ዊልያም ተብማን
Flag of Liberia.svg
ክቡር ፕሬዚደንት ዶክቶር ዊሊያም ተብማን፦ የላይቤሪያ ፕሬዚደንት እና ሁለተናውን በ ሴኔጋል ፕሬዚደንት ሊዮፖልድ ሴዳር ሴንግሆር የሚመራውን “የሞንሮቪያ ቡድን” መሥራች ሲሆኑ
አገራቸው ደግሞ ሐምሌ ፳ ቀን ፲፰፻፴፱ ዓ/ም በአሜሪካ ነጻ በወጡ የቀድሞ ግሎሌዎች (የግድ ሎሌ) ወይም ‘ባርያዎች’ ከተመሠረተች በኋላ በአፍሪቃ አኅጉር በነጻነት ዕድሜ ከኢትዮጵያ ተከትላ ሁለተኛዋ አገር ናት።

ሴኔጋል

ሊዮፖልድ ሴንግሆር
Flag of Senegal.svg
ሴኔጋል እስከ መጋቢት ፳፮ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነበረች። በዚያን ዕለት ነጽ ስትወጣ፣ በሥነ ጽሁፍ እና ቅኔ ባለሙያነታቸው የሚታወቁት መሪ እና “የሞንሮቪያ ቡድን” የሚባለውን ሁለተኛውን ቡድን የመሩት ሊዮፖልድ ሴጋር ሴንግሆር ነበሩ።

ናይጄሪያ

ታፌዋ ባሌዋ
Flag of Nigeria.svg
የቀድሞዋ የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ናይጄሪያ መስከረም ፳፩ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ነጻነቷን ስትቀዳጅ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት አል ሃጅ አቡባካ ታፌዋ ባሌዋ ነበሩ። ባሌዋ በአስተማሪነት የሠለጠኑ ሲሆን በሥልጣን ጊዜያቸው ደግሞ ስለአፍሪቃ ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት ብዙ የታገሉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ብዙ ጥረት አድርገዋል። በፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛተናጋሪ አገሮች መሃል ስምምነትና ወዳጅነት እንዲፈጠርም አመቻችተዋል።
መጨረሻ ላይ በአገራቸው በተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ጥር ፯ ቀን ፲፱፻፶፰ ዓ/ም ተገደሉ። እሬሳቸውም በተገደሉ በስድስተኛው ቀን በሌጎስ ከተማ መንገድ ዳር ላይ ተጥሎ ተገኘ።

ቡድን ያልለዩ ዓባላት

ዳሆሜ

ሁበርት ማጋ
Flag of Benin.svg
የቀድሞዋ ዳሆሜ (አሁን ቤኒን) ነጻነቷን ሐምሌ ፳፭ ቀን ፲፱፻፶፪ፈረንሳይ ስትቀዳጅ ሁበርት ማጋ የአገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዚደንትነትን ሥልጣን ይዘው ወዲያው በታኅሣሥ ወር ላይ በተካሄደ ምርጫ ጸደቀላቸው።

ቱኒዚያ

ሀቢብ ቡርጊባ
Flag of Tunisia.svg
ቱኒዚያን ሪፑብሊክ መጋቢት ፲፩ ቀን ፲፱፻፵፰ ዓ/ም በነጻነት የመሠረቱትና ከ ሐምሌ ፲፱ ቀን ፲፱፻፵፱ ዓ/ም ጀምሮ ለሠላሳ ዓመታት እስከ ጥቅምት ፴ ቀን ፲፱፻፹ ዓ/ም ድረስ በፕሬዚደንትነት ያገለገሉት ሀቢብ ቡርጊባ ነበሩ።

ካሜሩን

አማዱ አሂጆ
Flag of Cameroon.svg
ከነጻነት [[ታኅሣሥ ፳፪] ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ጀምሮ ለሀያ ሁለት ዓመታት እስከ ኅዳር ፳፩ ቀን ፲፱፻፹፪ ዓ/ም አገራቸውን ካሜሩንን በፕሬዚደንትነት የመሩት አማዱ ባባቱራ አሂጆ ነበሩ።

ቻድ

ፍራንስዋ ቶምቦልባይ
Flag of Chad.svg
አስተማሪና የሠራተኞች ማኅበር ቀስቃሽ የነበሩት ፍራንስዋ ቶምቦልባይ መጀመሪያ በቅኝ ግዛት ሥር የአስተዳደሩ ርዕስ በመሆን ቻድ ነሐሴ ፭ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ከፈረንሳይ ነጻነቷን ስትቀዳጅ የአገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ሆኑ። ቶምቦልባይ በተወለዱ በ፶፯ ዓመታቸው ሚያዝያ ፭ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ/ም አረፉ።

ቶጎ

ሲልቫኑስ ኦሊምፒዮ
Flag of Togo.svg
የምዕራብ አፍሪቃቶጎፈረንሳይ የቅኝ ግዛትነት ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ነጻ ስትወጣ ሲልቫኑስ ኦሊምፒዮ መጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከዚያም በፕሬዚደንትነት አገልግለዋል። ጥር ፭ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ/ም በተነሳ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በጥይት ተገደሉ።

ሶማሊያ

አብዲራሺድ ሸርማርክ
Flag of Somalia.svg
ሶማልያ ሪፑብሊክ በብሪታንያ ስር በሙሀመድ ሃጂ ኢብራሂም ኤጋል ይተዳደር የነበረውን ክፍልና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስም በኢጣልያ ስር በአደን አብዱላ ኦስማን ዳር መሪነት ይተዳደር የነበረውን ክፍል በማዋሃድ ሰኔ ፳፫ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ተመሠረተ። በቀድሞው የኢጣልያ የቅኝ ግዛት በመንግሥት ሠራተኛነት ሲያገለግሉ የነበሩት ክቡር ዶክቶር አብዲራሺድ አሊ ሸርማርክ የአገሪቱ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ።

አይቮሪ ኮስት (ኮት ዲቯር)

ፌሊክስ ሁፍዌ ቧኝ
Flag of Cote d'Ivoire.svg
ሕዝባቸው ባቆላማጭ መንፈስ “አባባ ሁፍዌ” ይላቸው የነበሩት አንጋፋው ፌሊክስ ሁፍዌ ቧኝ በ፲፰፻፺፯ ዓ/ም ተወለዱ። በፈረንሳይ የሕግ ምክር ቤት አባልነት ከመረጣቸው በፊት በልዩ ልዩ ግዜያት የመንደር ዓለቃ፣ የህክምና ዶክቶር፣ የእርሻ አስተዳዳሪ እና የሠራተኞች ማኅበር ዓለቃ በመሆን አገልግለዋል። በፈረንሳይ መንግሥትም በልዩ ልዩ ክፍሎች በሚኒስትርነት አገልግለዋል።
አገራቸው ከፈረንሳይ ግዛትነት ነሐሴ ፩ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ነጻ ከወጣች በኋላ በፖሊቲካ ዘመናቸው የአፍሪቃ አኅጉርን የቅኝ ግዛትነት ቀንበር ለማስለቀቅ ብዙ የደከሙ ሲሆን አገራቸውንም በፕሬዚደንትንት በመሩባቸው ዘመናት ራዕያዊ ዕቅዶችን በመተመንና የአገሪቱን ዋና ምርቶች የሆኑትን ኮኮ እና ቡና በማዳበር በምዕራብ አፍሪቃ የላቀ እድገትን አስገኝተዋል። ከምዕራባውያን ጋር የነበራቸው መልካም ግንኙነት እና ለኮሙኒስት ዓላማ የነበራቸው ጥላቻ በሌሎች የጎረቤት አገር መሪዎች ላይ የተነሱ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራዎችን ይደግፉ ነበር እየተባሉ ይታማሉ።

ኬንያ

ጆሞ ኬንያታ
Flag of Kenya.svg
ሲወለዱ የተሰጣቸው ስም “ካማው ዋ ንጌንጊ” ሲሆን በክርስትና ሲጠመቁ “ዮሐንስ ጴጥሮስ” ተብለው ነበር። በኋላ መጠሪያ ስማቸውን ጆሞ ኬንያታ ብለው ሰየሙ። ኬንያታ አገራቸው ኬንያ ለነጻነት በምትታገልበት ጊዜ ከ፲፱፻፵፭ ዓ/ም እስከ ፲፱፻፶፩ ዓ/ም ድረስ የተካሄደውን “ማው ማው” የተባለውን የአርበኝነት ግንባር መርተዋል። በዚህም ምክንይት በብሪታንያ አስተዳደር ታስረው ነበር።
“ምዚ” (አዛውንቱ) ጆሞ ኬንያታ በ፲፱፻፴፰ ዓ/ም ሎንዶን በነበሩ ጊዜ ከጋናክዋሜ ንክሩማ ጋር “የአፍሪቃ አኅጉር የሽከታ ኅብረት” (pan-Africanism) የተባለውን ፍልስፍና መሥርተው ያራምዱ ነበር። ከዘመናት በኋላ አገራቸው ኬንያታኅሣሥ ፪ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ/ም በአፍሪቃ ሠላሣ ሁለተኛዋ ነጻ አገር ሆና ሉዓላዊ ስትሆን፣ ኬንያታ መጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በፕሬዚደንትነት እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አገልግለዋል።

ኮንጎ ብራዛቪል

አቤ ፉልበርት ያውሉ
Flag of the Republic of the Congo.svg
አሁን ኮንጎ ሪፑብሊክ የምትባለው ኮንጎ ብራዛቪል ነሐሴ ፱ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ከፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ቀንበር ተላቃ ነጻ ሉዐላዊ አገር ሆነች። በነጻነት ጊዜ አገሪቷን በመሪነት ሥልጣን ይመሩ የነበሩት ቀድሞ የካቶሊክ እምነት ቄስ የነበሩት አቤ ፉልበርት ያውሉ ነበሩ። ያውሉ በ፲፱፻፶፭ ዓ/ም መሪውን ፓርቲያቸውን ብቻ ሕጋዊ ፓርቲ ለማድረግ ሲነሳሱ ሕዝባቸው ይሄንን በመቃወም በነሐሴ ወር ላይ ባካሄደው የሦስት ቀን የተቃውሞ ሁከት ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዱ።

ጋቦን

ገብርኤል እምባ
Flag of Gabon.svg
የቀድሞዋ የፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ጋቦን ነጻነቷን ነሐሴ ፲፩ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም አገኘች። በሽግግሩ ጊዜ በጠቅላይ ሚንስትርነት ከነጻነት በኋላ ደግሞ የአገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት በመሆን ያገለገሉት ገብርኤል እምባ ነበሩ።
ጋቦን ሽከታ ተዋናይነትን በ ፲፱፻፴፰ ዓ/ም የጀመሩት ፕሬዚደንት እምባ በ፲፱፻፶፮ ዓ/ም በዱኛ ባላጋራቸው ጃን ሂሌይር ኦባም ቀስቃችነት የተነሳውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በፈረንሳይ እርዳታ ካከሸፉ በኋላ በ፲፱፻፶፱ ዓ/ም በፕሬዚደንትነት ተመርጠው ነበር። ዳሩ ግን በነበረባቸው የነቀርሳ በሽታ ምክንያት በኅዳር ወር በሞት ተለዩ።

ማዳጋስካር

ፊሊበርት ጺራናና
Flag of Madagascar.svg
ፊሊበርት ጺራናና በ፲፱፻፬ ዓ/ም የተወለዱ የማዳጋስካር ሽከተኛ ነበሩ። አገራቸውን በመሪነት ሰኔ ፲፱ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ለነጻነት ካበቁ በኋላ በፕሬዚደንትነት እስከ ፲፱፻፷፬ ዓ/ም ድረስ መርተዋል። በመሪነታቸው የ”ማዳጋስካር ሕብረተ-ሰብዓዊ ሽከታ” ("Malagasy socialism") በሚሉት የአስተዳደራቸው መመሪያ ብዙ ስህተቶችን እንደሠሩ ይዘገባል። ሆኖም በአገራቸው ስማቸው የተከበረ፣ እስካሁንም “የነጻነት አባት” የሚል ቅጽል ስም አስጥቷቸዋል።
ፕሬዚደንት ፊሊበርት ጺራናና በሚያዝያ ፰ ቀን ፲፱፻፸ ዓ/ም አረፉ።

ሞሪታንያ

ሙክታር ኡልድ ዳዳ
Flag of Mauritania.svg
ሞሪታንያ ነጻነቷን ኅዳር ፲፱ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ከፈረንሳይ ተቀዳጀች። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በ፲፱፻፸ ዓ/ም በተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እስከተገለበጡ ድረስ ሞክታር ኡልድ ዳዳ አገራቸውን በፕሬዚደንትነት አገልግለዋል።
ፕሬዚደንት ኡልድ ዳዳ የአንድ ፓርቲ ሽከታን ብቻ ሕጋዊ አድርገው ተቃራኒ በሌለባቸው ሦሥት ምርጫዎች አሸንፌያለሁ ብለዋል። በ፲፱፻፷፫ ዓ/ም የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት (አ. አ. ድ.) ፕሬዚደንት ሆነው ነበር። ጥቅምት ፬ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ/ም አረፉ።

የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ

ዴቪድ ዳኮ
Flag of the Central African Republic.svg
የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የመጀመሪያውና ሦሥተኛው ፕሬዚደንት፣ በ፲፱፻፳፪ ዓ/ም የተወለዱት ዴቪድ ዳኮ ናቸው። ከፕሬዚደንትነቱ ሥልጣን ሁለቴም የወረዱት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሲሆን፤ በአገራቸው ሽከታ ለግማሽ ምዕት ዓመት ተሳትፈዋል።
የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ነጻነቷን ነሐሴ ፯ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ስትቀዳጅ፣ ጊዜያዊ ፕሬዚደንት ከሆኑ በኋላ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ እስከ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፱፻፶፯ ዓ/ም ድረስ በፕሬዚደንትነት ሲመሩ ቆይተው ጄኔራል ጃን ቢዴል ቦካሳ (በኋላ ንጉሠ ነገሥት) ስኬታም ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ዳኮን ከሥልጣን አወረዷቸው።
ከአሥራ አምስት ዓመት አምባ ገነናዊ ግዛት በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቦካሳ በፈረንሳይ ምርጥ ወታደሮች ኃይል ከሥልጣን ሲወርዱ ዴቪድ ዳኮ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን ጨበጡ። ሁለተኛው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በመስከረም ፲ ቀን ፲፱፻፸፬ ዓ/ም ተካሂዶ ዳኮን ለሁለተኛና መጨረሻ ጊዜ ከሥልጣን አወረዳቸው።

አፐር ቮልታ

ሞሪስ ያሜዎጎ
Flag of Burkina Faso.svg
ሐምሌ ፳፱ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ነጻነቷን ከፈረንሳይ የተቀዳጀችው አፐር ቮልታ (አሁን ቡርኪና ፋሶ) የመጀመሪያ ፕሬዚደንትነትን ሥልጣን የሰጠችው ለሞሪስ ያሜዎጎ ነበር።
ያሜዎጎ የአይቮሪ ኮስትን ፕሬዚደንት ፌሊሽ ሁፌ ቧኝ የቅርብ ወዳጅ እና በዕድሜያቸው እንደታላቅ ወንድም የሚያይዋቸው፣ መካሪያቸው እንደነበሩ ይነገራል። ያሜዎጎ መጀመሪያ በአይቮሪ ኮስት እና በአፐር ቮልታ መሃል የተዋህዶ መንግሥት ለመመሥረት ጥረው ስከታማ ሳይሆን ቀረ። በኋላ ደግሞ ይሄንን ዓላማ ለማራመድ በሴኔጋልማሊዳሆሚ እና አፐር ቮልታ መሃል በአንድ መንግሥት የሚመራ የኅብረት ውህደትን ለማግኘት ይለፉ ነበር። ዳሩ ግን በፕሬዚደንት ቧኝ እና በፈረንሳይ መንግሥት ተቃዋሚነት ይህን አሳብ ለመተው ተገደዋል።
ያሜዎጎ ከሥልጣን እስከወረዱበት ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ፲፱፻፶፰ ዓ/ም ድረስ ከቧኝ ጋር የሁለቱን አገር ሕዝቦች በመንታ ዜግነት ማስተዳደር የሚያስችል አሳብ ያራምዱ ነበር። እሳቸው ከሥልጣን ሲወገዱ ይሄም አሳብ አብሮ ወደቅ።

ሲዬራ ሊዮን

ሚልተን ማርጋይ
Flag of Sierra Leone.svg
ሲዬራ ሊዮን የመጀመሪያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር “ሰር” (SIR) ሚልተን ማርጋይ አገራቸው የብሪታንያ ቅኝ ግዛት በነበረች ጊዜ የህክምና ዶክቶር በመሆን ከመመረቃቸውም ባሻገር በግዛቱ ላይ በተገዢው ሕዝብ ቁጥጥር ሥር የሆነውን የመጀመሪያ ጋዜጣ ያቋቋሙ ናቸው።
አገሪቷ ነጻነቷን ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፶፫ ዓ/ም ተቀዳጀች። እስከዚያም ጊዜ በቅኝ አስተዳደር ውስጥ በዋና ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩት እና አገራቸውንም ወደነጻነት የመሩት ማርጋይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ። በዚህ ሥልጣን ላይ እንዳሉ በ፲፱፻፶፮ ዓ/ም በሞት ሲለዩ የተቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን ወንድማቸው ወረሱ።

ታንጋኒካ

ጁልዬስ ኒዬሬሬ
Flag of Tanzania.svg
“የምንገነባት አፍሪቃ ሌላው ዓለም አይቷት “ስለሕብረተ ሰብ ያላቸውን ህልም ግብ ያደረሱ ነጻ ሕዝቦችን ማየት ከፈለጋችሁ አፍሪቃ ሂዱ!” የሚሉላት መሆን አለባት። ለመላው የሰው ልጅ ሁሉ የተስፋ አኅጉር ማለት ይቺ ናት።”
መምህር ጁሊዬስ ኒዬሬሬ (፲፱፻፶፪ ዓ/ም)
ጁሊዬስ ካምባራጌ ኒዬሬሬ የብሪታንያን ጭቆና፣ የአገር ውስጥ መከፋፈልን እና የጊዜውን የ”ቀዝቃዛ ጦርነት” ሽከታ ተቋቁመው ኅዳር ፴ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓ/ም አገራቸውን ታንጋኒካን በሰላም ወደነጻነት የመሩ ሲሆኑ የአገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ነበሩ። ከዚህም ሌላ፣ አብላጫነት በሌላቸው ነጮች የሚተዳደሩትን የደቡባዊ አፍሪቃ አገሮችን የነጻነት ትግል በመደገፍ ግንባር ቀደም ነበሩ።
ኒዬሬሬ በ፲፱፻፲፬ ዓ/ም ተወለዱ። በትምህርት ስጦታ የነበራቸው ምሁር ሲሆኑ በከፍተኛ ትምህርት ከተመረቁ በኋላ በመምህርነት አገልግለዋል። የስዋሂሊ ቋንቋ ለአንድነት ጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት የሼክስፒርን “ጁሊዬስ ቄሳር” ወደዚህ የአፍሪቃ ቋንቋ ተርጉመው አሳትመዋል። ኒዬሬሬ፣ ያልተሳካላቸው ትልቅ ህልም የምሥራቅ አፍሪቃን አገሮች በኅብረት መንግሥት ማዋሃድ ቢሆንም ታንጋኒካን እና የዛንዚባርን ደሴት በማዋሃድ አዲሷን ታንዛኒያን በ፲፱፻፶፮ ዓ/ም ስኬታማ አድርገዋል።
በኚህ ታላቅ መሪ የሥልጣን ዘመናት ጠቅላላው ሕዝባቸውን ከሞላ ጎደል የማንበበ እና መጻፍ ችሎታ ሰጥተውታል። ፕሬዚደንት ኒዬሬሬ በጊዜውም ሆነ እስካሁን በአፍሪቃ ሽከታ ተሰምቶም ተደርጎም የማይታወቅ በፈቃዳቸው በ፲፱፻፸፯ ዓ/ም ሥልጣናቸውን ሲለቁ አገራቸው በዴሞክራሲ የዳበረች ሰላምና አንድነትን ያቀፈች አገር ነበረች።
መምህር ጁሊዬስ ኒዬሬሬ ባደርባቸው የደም ነቀርሳ (leukaemia) በሽታ በተወለዱ በ፸፰ ዓመታቸው ጥቅምት ፬ ቀን ፲፱፻፺፪ ዓ/ም ሎንዶን ላይ አረፉ። በ፳፻፩ ዓ/ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ “ዓለም አቀፍ የፍትሐዊ ሕብረተ ሰብ ጀግና” ብሎ ሰይሟቸዋል።

ቡሩንዲ

ንጉሥ ምዋምቡትሳ ፬ኛ
Flag of Burundi.svg
ቡሩንዲ የቀድሞ ቅኝ ገዥ የነበረችው አለማኛአንደኛው የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ በዚያን ጊዜ የጀርመን ምሥራቅ አፍሪቃ (አሁን ቡሩንዲ እና ርዋንዳ) የሚባለውን ግዛት ጥቅምት ፲ ቀን ፲፱፻፲፯ ዓ/ም ለቤልጅግ መንግሥት አስረከበች።
ቤልጅግ ይችን ግዛት በነጻነት ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ስታስረክብ በመሪነት የተረከቡት ንጉሥ ግርማዊ ምዋሚ ምዋምቡትሳ ፬ኛ ነበሩ። ንጉሡ ለአራት ዓመታት አገራቸውን ካስተዳደሩ በኋላ መጋቢት ፲፭ ቀን ፲፱፻፶፰ ዓ/ም ልጃቸውን እንደራሴ አድርገው ሾመው ኑሯቸውን ስዊስ አገር አደረጉ። ከሦሥት ወራት በኋላ ግን ሐምሌ ፩ ቀን በጄኔራል ሚኮምቤሮ መሪነት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ ንጉሥ ምዋሚ ምዋምቡትሳ ፬ኛ ተገለበጡ። ንጉሡ እዚያው መኖሪያቸው አገር ዠኔቭ ከተማ ላይ ሚያዝያ ፳፫ ቀን ፲፱፻፷፱ ዓ/ም አረፉ።

ኡጋንዳ

ሚልተን ኦቦቴ
Flag of Uganda.svg
ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፲፱፻፲፰ ዓ/ም የተወለዱት የኡጋንዳ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመጀመሪያ ፕሬዚደንት አፖሎ ሚልተን ኦቦቴ ለዚህ ሥልጣን የበቁት ከነጻነት በፊት በብሪታንያ የቅኝ አስተዳደር በተካሄደ ምርጫ ከቡጋንዳ የዘውድ ቡድን ጋር የሽከታ ኅብረት በመፍጠር ነበር። ይሄ የሽከታ ኅብረት በኡጋንዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብዙኃን ነትን ሲያገኝ ኦቦቴ ሚያዝያ ፲፯ ቀን ፲፱፻፶፬ ዓ/ም የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ።ወዲያው አገሪቷ መስከረም ፳፱ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ/ም ነጻነቷን ተቀዳጀች።
፲፱፻፶፰ ዓ/ም በጠቅላይ ሚንስትር ኦቦቴ እና በቡጋንዳው ንጉሥ ሙቲሳ መሃል የተከሰተውን የሥልጣን ፉክክር ምክንያት በማድረግ ኦቦቴ ሕገ መንግሥቱን ለውጠው በዓመቱ እራሳቸውን ፕሬዚደንት አደረጉ። ሆኖም ጥር ፲፯ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ/ም ፕሬዚደንት ኦቦቴ ሲንጋፖር ላይ ይካሄድ በነበረው የ”ኮመን ዌልዝ” ርዕሰ መንግሥታት ስብሰባ ላይ ሲሳተፉ በጄኔራል ኢዲ አሚን የተመራ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን አስወገዳቸው። የታንዛንያ ሠራዊት ኢዲ አሚንን ሚያዝያ ፭ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ/ም ከሥልጣን ካወረደ በኋላ ኦቦቴ አገራቸው ተመልሰው ታኅሣሥ ፰ ቀን ፲፱፻፸፫ በሰፊው የትጭበረበረ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዚደንት ሆኑ። ይሄ ምርጫ እና የኦቦቴ አምባ ገነንነት ያስከተለው የጦርነት ትግል ለሁለተኛው የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት ሆኖ ሐምሌ ፳ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ/ም ለሁለተኛና ለመጨረሻ ጊዜ ሥልጣናቸውን ለቀው ተሰደዱ። ሚልተን ኦቦቴ ባደረባቸው የኩላሊት በሽታ በደቡብ አፍሪቃ ከተማ ጆሃንስበርግ ላይ በተወለዱ በ ፹ ዓመታቸው መስከረም ፴ ቀን ፲፱፻፺፰ ዓ/ም አረፉ።

ሱዳን

ኢብራሂም አቡድ
Flag of Sudan.svg
ሱዳን ነጻነቷን ከብሪታንያ የተቀዳጀችው ታኅሣሥ ፳፪ቀን ፲፱፻፵፰ ዓ/ም ነው። ማርሻል ፋሪቅ ኢብራሂም አቡድ ጥቅምት ፲፮ ቀን ፲፰፻፺፫ ዓ/ም በቀይ ባሕር አጠገብ ሞሐመድ ጋል በተባለች ሥፍራ ተወለዱ። ካርቱም በሚገኘው የ’ጎርዶን መታሰቢያ ኮሌጅ” እና በብሪታንያ በምሕንድስና የተመረቁት አቡድ፣ በውትድርና ምክትል መቶ ዓለቃ ሆነው በግብጽ ሠራዊት ውስጥ አገልግለዋል።
ወደ ሽከታ ዓለም ከመዛወራቸው በፊት በጦር መሐንዲስነት እና በተለያዩ ወታደራዊ ሥልጣኖች ተመድበው ይሠሩ ነበር። የሱዳንንም ጠቅላላ ሠራዊት አዛዥ በመሆን የመጀመሪያው ሱዳናዊ ነበሩ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ኢጣልያን ከአፍሪቃ ለማስወገድ በተካሄዱት ጦርነቶች ላይ በሊቢያ እና በኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ ተሰልፈው በታላቅ ጀብድ እንደተዋጉ ተመዝግቦላቸዋል። [1]
፲፱፻፶ ዓ/ም የሱዳንን ርዕሰ ብሔር ሥልጣን የጨበጡት አቡድ፣ የደቡብ ሱዳንን የመገንጠል ዓላማ ወኮሎቹን በማሰር፣ በመግደል ወይም በማሰደድ እና በመላ አገሪቱም ላይ የእስላምን የሻሪያ ሕግ በመጠቀም፣ አገሪቱን ወደ አረባዊው ዓለም በመምራትና የውጭ የክርስትና ኃይማኖት ሰባኪዎችን በማባረር እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የነበሩትን አብያተ ክርስቲያናት በመዝጋት የሕዝባቸውን ሰብዓዊ መብት የጨቆኑ መሪ ነበሩ። አቡድ በ፲፱፻፷፬ ዓ/ም በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀው ለብዙ ዓመታት በስደተኝነት ብሪታንያ ኖረዋል። በመጨረሻ ዘመናቸው ወደአገራቸው ተመልሰው ጳጉሜ ፫ ቀን ፲፱፻፸፭ ዓ/ም፣ በተወለዱ በ፹፪ ዓመታቸው ካርቱም ላይ አረፉ።

ኒጄር

ሀማኒ ዲዮሪ
Flag of Niger.svgኒጄር የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና ፕሬዚደንት ሀማኒ ዲዮሪ ሱዱሬ በሚባል የምዕራብ ኒዤር ክፍል በ1908 ዓ/ም ተወለዱ።
በትምህርት ከተመረቁ በኋላ በ[ናያሚ]]፣ ማራዲ እና ፓሪስ ውስጥ በአስተማሪነትም በትምህርት ቤት አስተዳዳሪነትም አገልግለዋል። ከዚህም ሌላ የኒዤር ተራማጅ ቡድን ከመሠረቱት አንዱ ናቸው።
፲፱፻፶ ዓ/ም ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ኒዤር እራሷን እንድታስተዳድር ተፈቀደ። ዲዮሪ ፕሬዚደንት ሆነው ነጻነት [ሐምሌ ፳፯]] ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ሲታወጅ የአዲሷ ሪፑብሊክ ፕሬዚደንት ሆኑ። ሀማኒ ዲዮሪ እና መንግሥታቸው በአኅጉሩ በአስታራቂነት ቢመሰገኑም እንኳ በአገር ውስጥ ግን በሙሰኝነት ይወነጀላሉ። በመጨረሻው በሌፍተናንት ኮሎኔል ሴይኒ ኩንቼ የተመራ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሚያዝያ ፯ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም ዲዮሪን ከሥልጣን አውርዶ ለስደስት ዓመታት በእስር ተቆጣጠራቸው። ሲፈቱም በቁም እስር እስከ ፲፱፻፸፱ ዓ/ም ቆይተው ኑሯቸውን በስደት ሞሮኮ ላይ መሥርተው ሲኖሩ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፲፱፻፹፩ ዓ/ም በተወለዱ በ ፸፪ ዓመታቸው እዚያው ሞሮኮ ውስጥ አረፉ።

=ኮንጎ ሊዮፖልድቪል

ዮሴፍ ካዛቩቡ
Flag of the Democratic Republic of the Congo.svg
ኮንጎ ደሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መጀመሪያ ፕሬዚደንት ዮሰፍ ካዛቩቡ ነበሩ። በወጣትነት ዘመናቸው በአስተማሪነት እና በሒሳብ ተቆጣጣሪነት ሠርተዋል። በ፲፱፻፴፰ ዓ/ም የሙግት ማኅበር አባል ሲሆኑ የሽከታ ሕይወታቸው ተጀምሮ ቀስ በቀስ ዝናቸው እየታወቀ እስከ ነጻነት ዘመን ቆዩ። በሽከታ ዓለም ካዛቩቡን ስኬታማ ያደረጓቸው በተፈጥሮ ጠባያቸው አሰላሳይነታቸውና በጥፋት ጊዜ ሌሎችን የማጋፈጥ ችሎታቸው ናቸው። በ ፲፱፻፶፪ ዓ/ም መግቢያ ወራት በቀድሞዋ ኮንጎ ሊዮፖልድቪል (አሁን ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ) በተከሰተው የሕዝብ ሽብር እና ሁከት መነሻነት፣ የቅኝ ገዥዎቿ የቤልጂግ ባለ ሥልጣናት አገሪቱን በስድስት ወራት እንደሚለቁና ነጻነቷን እንደሚሰጧት ጥር ፲፰ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም አስታወቁ። በዚህ መሠረት አገሪቷ ሰኔ ፳፫ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ስሟን ወደኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ለውጣ ነጻ ወጣች።
ወዲያው የሕዝብ ምርጫ ተካሂዶ በጠቅላይ ሚንስትርነት ብሔራዊው ፓትሪስ ሉሙምባን ሲመረጡ በፕሬዚደንትነት ደግሞ የምዕራባውያን ደጋፊ የነበሩት ዮሴፍ ካዛቩቡ ተመረጡ። ይሄ በሆነ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ሽብር ሲነሳ በተፈጥሮ ሀብት ባለጸጋ የሆነችው የካታንጋ ግዛት በሞይስ ቾምቤ መሪነት ከሪፑብሊኩ ተገነጠለች። የአገሪቱን ጸጥታ ለማስከበርና በሁለቱ ወገኖች (ሉሙምባ እና ካዛቩቡ) የተከሰተውን ጦርነት ለማብረድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሀያ ሺ ወታደሮች ላከ። በታኅሣሥ ወር አሜሪካ ካዛቩቡን በመደገፍ የላኩት መሣሪያና የ “ሲ አይ ኤ” (CIA) ሰላዮች ከካዛቩቡ ጋር በመረዳዳት ሉሙምባን ገድለው የካዛቩቡን ሥልጣን አጠናከሩ።
ካዛቩቡ ኅዳር ፲፮ ቀን ፲፱፻፶፰ ዓ/ም፣ እስከዚያ ድረስ ታማኝ በነበረው መኮንን፣ ኮሎነል ሞቡቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ተወገዱ። በፕሬዚደንትነት ዘመናቸው ለአገራቸውና ሕዝባቸው እድገትና ለውጥ እምብዛም አመጡ የሚባልላቸው ነገር ባይኖርም በዚያ በነጻነት ማግስት በተከሰተው ጭፍጨፋ እና ሁከት ጊዜ በአሰላሳይነታቸው እራሳቸውን የአንድነት አርማ አስደርገው ማሳያታቸው ይጠቀሳል። ዮሴፍ ካዛቩቡ መጋቢት ፲፭ ቀን ፲፱፻፷፩ ዓ/ም አረፉ።

ማላዊ

ዶክቶር ካሙዙ ባንዳ
Flag of Malawi.svg
ሄስቲንግስ ካሙዙ ባንዳ ግንቦት ፯ ቀን ፲፰፻፺ ዓ/ም ተወለዱ። ባንዳ አገራቸውን ማላዊን ለሰላሳ ዓመታት ያስተዳደሩ ሲሆን በትምህርታቸው ጤና ጥበቃ አጥንተው በእንግሊዝ አገር ውስጥ በሕክምና ዶክቶርነት በሊቨርፑል፣ ኒውካስትል እና ሃርልስደን ሲያገለግሉ በታካሚዎቻቸው ዘንድ በጣም ተወዳጅ እንደነበሩ ይዘገባል።
ባንዳ ለ፵፫ ዓመታት በስደት ከኖሩ በኋላ ያኔ በቅኝ ግዛትነት ሥር ወደነበረችው አገራቸው ኒያሳላንድ (አሁን ማላዊ) ሲመለሱ የአገራቸውን ቋንቋ ረስተው፣ ሁኔታቸው ሁሉ ከአውሮፓውያን የበለጡ አውሮፓዊ ነበሩ። ይሄም ሁኔታ ለሽከታ ዓላማቸው እንቅፋት ሳይሆንባቸው አልቀረም። አማካሪም ሲያስፈልጋቸው የበለጠውን ዕምነት የጫኑባቸው የለመዷቸው የብሪታንያ ዜጎችን ነበር። ሆኖም በምሁርነታቸው እና የእንግሊዞች ተደጋፊ በመሆናቸው መጀመሪያ የኒያሳላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተሾሙ።
ኒያሳላንድ በአዲስ ስሟ ማላዊ ተብላ ሰኔ ፳፱ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ/ም ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ በተካሄደው የሕዝብ ምርጫ በትልቅ ድምጽ ብዛት ለፕሬዚደንትነት ሲመረጡ የአምባ ገነንነት ባህሪያቸው ይፋ እየሆነ መጣ። በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች “እንግዋዚ” (Ngwazi) ወይም “ድል አድራጊ” እየተባሉ እንዲጠሩ አዘዙ። ከጥቂት ዓመታትም በኋላ “የዘላለም ፕሬዚደንት” ነኝ አሉ።
ለ፴ ዓመታት በፈላጭ ቆራጭነት ማላዊን ከገዙ በኋላ በምዕራባውያን ለጋሽ አገሮች ተጽዕኖ ማላዊ የአንድ ፓርቲ አገር ወይስ የብዙኀን ፓርቲዎች ትሁን የሚል “ውሳኔ ሕዝብ” አካሂደው በተገኘው ውጤት መሠረት በግንቦት ወር ፲፱፻፹፮ ዓ/ም የፕሬዚደንት ምርጫ ተደርጎ ባንዳ በመሸነፋቸው ሥልጣን ለቀቁ። ካሙዙ ሄስቲንግስ ባንዳ በተወለዱ በ፻ ዓመታቸው በደቡብ አፍሪቃ ከተማ ጆሃንስበርግ ላይ ኅዳር ፲፮ ቀን ፲፱፻፺ ዓ/ም አረፉ።

የ አ. አ. ድ. ዓላማዎች

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት (አ. አ. ድ.) ሲመሠረት ሁለት ዐቢይ ዓላማዎችን ተመርኩዞ ነበር። እነኚህም፦
  • ለአኅጉሩ የሽከታና የዱኛኪን እርምጃዎች ወሳኝ ጉዳይ የነበረው ጉዳይ ድርጅቱ የአኅጉሩን አንድነትና ትብብር ለማራመድና የጋራ ልሣን እንዲሆን።

  • ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ በዚያን ጊዜ ከቅኝነት ቀንበር ያልወጡ ብዙ የአፍሪቃ አገሮች ስለነበሩ የእነሱን ነጻነት ዐቢይ ዓላማ አድርጎ መታገል ሲሆን፤ ማኅበረተኞቹ እንደቀድሞው በውጭ ኃያላን ቁጥጥር ሥር እንዳይሆኑ በዓለም ዓቀፍ የሽከታ ጉዳዮች አባላቱ ገለልተኞች እንዲሆኑ ነው።
ከነኚህ ዐቢይ ዓላማዎች ሌላ፣ ማኅበሩ
  • ሁሉም አፍሪቃውያን ሰብዓዊ መብታቸው የተከበር እንዲሆን
  • የሁሉም አፍሪቃውያን የኑሮ ደረጃ የተሻሻለ እንዲሆን
  • የእርስ በእርስ ግጭቶችንና አለመግባባት በኃይል ሳይሆን በሰላማዊና ሚዛናዊ ሽምግልና መፍታት
የተስማማባቸውና የያዛቸው ዓላማዎች ነበሩ።
ሆኖም በርስ በርስ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ገብነትነት የማይፈልግ ማኅበርም በመሆኑ እና በሽምግልና የማይፈቱ ቅራኔዎች በተፈጠሩም ጊዜ ሰላምን የሚያስክብርበት መሣሪያ የሌለው ጥርስ የለሽ መንጋጋ ብቻ የነበር ድርጅት በመሆኑ የአኅጉሩ ሕዝቦች የጓጉበትን የሰብዓዊ መብት መከበርም ሆነ እንደናይጄሪያ እና አንጎላ ላይ የተካሄዱትንም ብሔራዊ እልቂቶች ለመግታት ያልቻለ ድርጅት ነበር። ስለዚህም በአብዛኛ አፍሪቃውያኖች እና በሰፊውም ዓለም አስተያየት ይሄ ድርጅት ውጤተ ቢስ የወሬ ማኅበር በመባል በይፋ ይተች ነበር።

የድርጅቱ ዋና ጸሐፊዎች

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት በ፲፱፻፶፭ ዓ/ም ተመሥርቶ የአፍሪቃ ሕብረት ሐምሌ ፪ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም እስከተካው ድረስ በየጊዜው ከአባል አገራት የተመረጡ ዘጠኝ ቋሚ ዋና ጸሐፊዎች አገልግለውታል። በድርጅቱ መመሪያ ውል (OAU Charter) መሠረት ዋና ጸሐፊው ለአራት ዓመታት እንዲያገለግል ይመረጣል።

የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ

Flag of Ethiopia (1897).png
አቶ ክፍሌ ወዳጆ
ድርጅቱ አዲስ አበባ ላይ በተመሠረተ ጊዜ ለስብሰባው ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉት በጊዜው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትኢትዮጵያ ልዑካን መሪ የነበሩት ዶክቶር ተስፋዬ ገብረ እዝጊ ነበሩ። በዚያው ስብሰባ ላይ ቋሚ ዋና ጸሐፊ እስኪገኝ ድረስ ተመርጠው ከ ግንቦት ፲፯ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ/ም እስከ ሐምሌ ፲፬ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ/ም ድረስ ያገለገሉት ኢትዮጵያዊው አቶ ክፍሌ ወዳጆ ነበሩ።

ሁለተኛው ዋና ጸሐፊ

Flag of Guinea.svg
ዲያሎ ቴሊ
ከድርጅቱ ምሥረታ በኋላ ዋና ጽሕፈት ቤቱ የሚቋቋምበትን ከተማ ለመምረጥ ያስከተለውን እሽቅድምድም እና ፉክክር ለማክሸፍና አዲስ አበባን ለማስመረጥ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩጊኒው መሪ ሴኩ ቱሬ ጋር ባደረጉት ውል መሠረት፤ ጊኒአዲስ አበባን መመረጥ ልትደግፍ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ለድርጅቱ ዋና ጸሐፊነት የጊኒውን ተወላጅ ቡባካር ዲያሎ ቴሊን ለማሳጨት እና ለማስመረጥ እንደተስማሙ የአቶ ከተማ ልጅ መኮንን ከተማ The Creation of the OAU በሚል ርዕስ ላይ አስፍረውታል።[2]
ቴሊ ከ ሐምሌ ፲፬ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ/ም ጀምሮ እስከ ሰኔ ፰ ቀን ፲፱፻፷፬ ዓ/ም ድረስ ሁለት ጊዜ ተመርጠው በድርጅቱ ዋና ጸሀፊነት አገልግለዋል። ዲያሎ ቴሊ በሴኩ ቱሬ ትዕዛዝ ታስረው የካቲት ፳፪ ቀን ፲፱፻፷፱ ዓ/ም በረሀብ ሞተዋል።

ሦሥተኛው ዋና ጸሐፊ

Flag of Cameroon.svg
እንዞ ኤካንጋኪ
ሰኔ ፰ ቀን ፲፱፻፷፬ ዓ/ም ሥራቸውን የጀመሩት ሦሥተኛው ጸሐፊ የካሜሩን ተወላጁ እንዞ ኤካንጋኪ ነበሩ። በአለማኛ የተማሩት ኤካንጋኪ ከአገራቸው ነጻነት በኋላ በውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርነትና የሥራ ሚኒስትር ሆነው ካለገሉ በኋላ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሆነው ተመረጡ።
የተመረጡበትን የሥልጣን ጊዜ ሳይጨርሱ በሁለት ዓመቱ ድርጅቱ በአኅጉሩ ውስጥ የተፈጥሮ ነዳጅ ምርምር እንዲያካሂድ ከመረጠው የ”ሎንሮ” (Lonrho Group) ድርጅት ሙስና ተቀብለዋል ተብለው ሲታሙ ሰኔ ፱ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ። [3]

አራተኛው ዋና ጸሐፊ

Flag of Cameroon.svg
ዊሊያም እቴኪ
የካሜሩኑ ዜጋ እንዞ ኤካንጋኪ ሥልጣናቸውን ሲለቁ የካሜሩን ፕሬዚደንት አህማዱ አሂጆ የአገራቸውን ሰው ዊሊያም ኦሬሊዬን እቴኪ እምቡሙዋን በተተኪነት አጭተው አቀረቡ። በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ ላይ በተካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ላይ የቀረቡት የሶማሌ እና የዛምቢያ እጩዎች የሚያስፈልገውን ከሦሥት ሁለት እጅ የድምጽ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ስብሰባው በሦሥተኛ አማራጭነት እቴኪን በሙሉ ድምጽ መረጠ።
ዊሊያም እቴኪ እስከ ሐምሌ ፲፬ ቀን ፲፱፻፸ ዓ/ም አገልግለዋል።

አምስተኛው ዋና ጸሐፊ

Flag of Togo.svg
ኤደም ኮጆ
ሐምሌ ፲፬ ቀን ፲፱፻፸ ዓ/ም እስከ ሰኔ ፭ ቀን ፲፱፻፸፭ ዓ/ም ድረስ ያገለገሉት አምስተኛው ዋና ጸሐፊ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ላይ በተካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ላይ የተመረጡት የቶጎው ተወላጅ፣ ኤድዋርድ ኮጆ (ኤደም ኮጆ) ናቸው።
በኮጆ የሥልጣን ዘመን በሞሮኮ አስተዳደር ሥር ያለችው የሰሐራዊ የአረብ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ጉዳይ እና እሷንም በተመለከተ የሳቸው አቋም የድርጅቱን አባላት አቃቅሮ ነበር። ኮጆ የካቲት ፳፩ ቀን ፲፱፻፸፬ ዓ/ም በተካሄደ ስብሰባ ላይ የዚችን ግዛት ልዑካን እንደ አባል መቀመጫ እንዲይዙ ማድረጋቸውን በመቃወም ሞሮኮ እና እሷን የሚደግፉ አገራት የድርጅቱ ስብሰባዎች ላይ ላለመሳተፍ ወስነው ነበር። በዚህ ጉዳይ የተነሳ የሴኔጋል ፕሬዚደንት አብዱ ዲዩፍ ኮጆን “ነገር አማሳይ/በጥባጭ” ብለዋቸዋል።

ስድስተኛው ዋና ጸሐፊ

ፒተር ኦኑ
Flag of Nigeria.svg
ሰኔ ፭ ቀን ፲፱፻፸፭ ዓ/ም የዋና ጸሐፊነቱን ሥልጣን በስድስተኛነት ተራ የተረከቡት ናይጄሪያዊው ዶክቶር ፒተር ኦኑ ናቸው። ዶክቶር ኦኑ ለሁለት ዓመታት ብቻ አገልግለው ሐምሌ ፲፫ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ/ም ለቀቁ።

ሰባተኛው ዋና ጸሐፊ

ኢዴ ኡማሩ
Flag of Niger.svg
ከዶክቶር ኦኑ በተከታይነት ሰባተኛ ዋና ጸሐፊ ሆነው ሐምሌ ፲፫ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ/ም የተሾሙት የኒጄር ተወላጁ ኢዴ ኡማሩ ናቸው።
ዳካር እና በፓሪስ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ኡማሩ፣ በአገራቸው በጋዜጠኝነት፣ አምባሳዶርነት እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት የሠሩ ሲሆን በ፲፱፻፷፰ ዓ/ም አገራቸው ላይ ከተካሄደውመፈንቅለ መንግሥት በኋላ ለወታደራዊ ርዕሰ መንግሥቱ ሴይኒ ኩንቼ የቅርብ አማካሪ ሆነውም ሠርተዋል።
ኡማሩ የመጀመሪያውን የጸሐፊነት አራት ዓመታት መስከረም ፱ ቀን ፲፱፻፹፪ ዓ/ም ሲያጠናቅቁ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲያገለግሉ ታጭተው ነበር። ዳር ግን በውድድሩ የታንዛንያው ሳሊም አህመድ ሳሊም አሸንፈው ሥልጣኑን ተቀበሉ።

ስምንተኛው ዋና ጸሐፊ

Flag of Tanzania.svg
ሳሊም አህመድ ሳሊም
ስምንተኛው ተረኛ ዋና ጸሐፊ ዛንዚባር ደሠት ላይ የተወለዱት የታንዛንያው ዜጋ ሳሊም አህመድ ሳሊም ሲሆኑ፣ ሥልጣኑን ከ ኤዲ ኡማሩ መስከረም ፱ ቀን ፲፱፻፹፪ ዓ/ም ተቀበሉ።
ጥር ፲፭ ቀን ፲፱፻፴፬ ዓ/ም የተወለዱት ሳሊም አገራቸውን በዲፕሎማትነት ለብዙ ዘመናት ያገለገሉ ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት፤ በመከላከያ ሚንስትርነት፤ በምክትል እና ጠቅላይ ሚንስትርነትም አገልግለዋል። ሳሊም የጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የዛንዚባር ጋዜጠኞች ማኅበር ዋና ጸሐፊም ነበሩ።
ሳሊም አህመድ ሳሊም እስከ መስከረም ፯ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም ድረስ ካገለገሉ በኋላ ሥልጣናቸውን አስረክበዋል።

ዘጠነኛውና የመጨረሻው ዋና ጸሐፊ

Flag of Cote d'Ivoire.svg
አማራ ኤሲ
ሐምሌ ፪ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ/ም በዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ ላይ የተካሄደው የድርጅቱ ስብሰባ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን በአንድ ዓመት ውስጥ በአፍሪቃ ኅብረት ለመተካት የተስማማበትን ዓላማ ግብ የሚያደርስ ዋና ጸሐፊ ሲመርጥ ዘጠነኛውና የመጨረሻው ዋና ጸሐፊ ሆነው የተመረጡት የኮት ዲቯር ተወላጁ አማራ ኤሲ ናቸው።
አማራ ኤሲ ሥልጣኑን መስከረም ፯ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም ተረክበው፣ የአፍሪቃ ኅብረት እስከተመሠረተበት ሐምሌ ፪ ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ/ም ድረስ ካገለገሉ በኋላ ለአዲሱ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሲዮንም ጊዜያዊ ሊቀ መንበር ሆነው ተሹመው ነበር።