Wednesday, March 13, 2013

ዶ/ር ቆንጂት ፈቃደ



‹‹እናትና አባቴ ድኸው ያደጉበት
ካያት ከቅድመ አያት የተረካከቡት
አፈር የፈጩበት ጥርስ የነቀሉበት
አገሬ ዓርማ ነው የነፃነት ዋንጫ
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ብጫ››

የሚለውን የስመ ጥሩው ገጣሚና ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥም ታኅሣሥ 23 ቀን 2003 ዓ.ም. የተስተጋባው፣ እንደ አዘቦቱ በጥበብ መናኸሪያ፣ በኪነት መዲና አልነበረም፡፡ በአዲስ አበባ በቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የታዋቂዋን ዶ/ር ቆንጂት ፈቃደ ቀብር ተከትሎ እንጂ፡፡

ዶ/ር ቆንጂት፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የቦርድ አባል፣ በሲቪል ማኅበረሰብ በተለይም በሴቶች መብት ተሟጋች፣ በፓኖስ ምሥራቅ አፍሪካ የምክር ቤት አባልና ተጠባባቂ ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡

የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሽመልስ ሀብቴና በመድኃኔ ዓለም ትምህርት ቤቶች የተከታተሉት ዶ/ር ቆንጂት፣ በምሕንድስና ትምህርት ከሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ በፒኤችዲ ከተመረቁ በኋላ፣ በሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በተመራማሪነትና አማካሪነት ሠርተዋል፡፡ በአሜሪካ ተማሪ በነበሩበት ጊዜም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ማቴሪያል ፊዚክስ አስተማሪ የነበሩት ዶ/ር ቆንጂት፣ በሚዲያ ውስጥ ከነበራቸው ሚና ባሻገር የግል ራዲዮ ጣቢያ ለመጀመር ተቋቁመው ከነበሩት አንዱ የነበረው አዲስ ብሮድካስቲንግ ኩባንያን ከመሠረቱት መካከል አንዷ ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ካለው ቤተሰብ (አያታቸው ነጋድራስ ወዳጆ አሊ፣ አጎታቸው አቶ ክፍሌ ወዳጆ) የወጡት ዶ/ር ቆንጂት፣ የተወለዱት ከወ/ሮ ዝማም ወዳጆና ኮሎኔል ፈቃደ መኩሪያ ረቡዕ፣ የካቲት 2 ቀን 1947 ዓ.ም. ነበር፡፡

ግንባር ቀደም የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የትምህርት ሰው (አካዴሚያዊት) የነበሩት ዶ/ር ቆንጂት ባደረባቸው የካንሰር ሕመም ምክንያት በአሜሪካ ያረፉት እሑድ፣ ታኅሣሥ 17 ቀን 2003 ዓ.ም. ነበር፡፡

ግብዓተ መሬት ከተፈጸመ በኋላ በቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ዐውደ ምሕረት ላይ እህታቸው ወ/ሮ ስንዱ ፈቃደ፣ የገብረ ክርስቶስ ደስታን ‹‹ሀገሬ›› ግጥም ሦስት አንጓዎች አንብበውታል፡፡

‹‹... መቅደስ ነው አገሬ አድባር ነው አገሬ
እሾህ ነው አገሬ
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ፡፡
አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት
ለምለም ነው አገሬ
ውበት ነው አገሬ
ገነት ነው አገሬ፡፡
ብሞት እሔዳለሁ ከመሬት ብገባ
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ፡፡››

No comments: