Thursday, March 14, 2013

ስትሠራ እንጂ ስታስብ መሳሳት የለብህም

“የማይሠራ ሰው አይሳሳትም” የሚለው አባባል የሰው ልጅ በስራ ላይ ሳለ ስህተት ቢፈጽም እንኳ ሰብዓዊ ባህርይ ነውና ከስህተቱ እንዲማር መምከር እንደሚገባ እንጂ በአግራሞት የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያስተምር ነው፡፡ ነገር ግን በስራው ላይ የተፈጠረው ስህተት ከተግባር ሳይሆን ከተሳሳተ አስተሳሰብ የመነጨ ከሆነ ነገሩ የከፋ ይሆናል፤ ምክንያቱም በአስተሳሰቡ ላይ ህጸጽ ያለበት ሰው የሚሰራው ወይም የሚናገረው ሁሉ ስህተት ስለሆነና ለእርሱ ለባለቤቱ ግን ስህተቱ ሁሉ ትክክል ስለሚመስለው በቀላሉ እውነት ላይ ለመድረስ ወይም ትክክለኛ ስራ ለመስራት እጅግ በጣም ከባድ ይሆንበታልና፡፡
የሚናገሩና የሚጽፉ ሰዎች ስለትክክለኛ አስተሳሰብ ምንነት ባለማወቅ ወይም እያወቁ ሌሎችን ለማታለል በማሰብ የአስተሳሰብ ህጸጾችን (ፋላሲ) ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ህጸጾች በቅዱሳት መጻህፍት አረዳድና አተናተን፣ በቴሌቪዥንና ሬዲዮ የማስታወቂያ ቋንቋ፣ በጥናትና ምርምር ስራዎች፣በፖሊስ ምርመራና በፍርድ ቤት ችሎት ሂደት፣ በታላላቅ ስብሰባዎችና ክርክር መድረኮች፣ በአሰሪና ሰራተኛ የስራ ምልልስ እንዲሁም በግለሰቦች የዕለት ተዕለት ተግባቦታዊ ምልልስና በመሳሰሉት ማናቸውም የህይወት መድረኮች ላይ ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡
አሪስጣጣሊስና ከእርሱ በኋላ የተነሱ የትክክለኛ አስተሳሰብ ጠበብት፣ የአስተሳሰብ ህጸጾችን በተለያዩ
ፈርጆች ከፋፍለው አቅርበዋል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም አንባብያን የአስተሳሰብ ህጸጾችን ምንነት እንዲሁም የሚፈጸሙበትን ምክንያት በዝርዝር በማጥናት የተሳሳተ ውሳኔ ከመስጠት ራሳቸውን እንዲቆጥቡና በሌሎች ከተሳሳተ አስተሳሰብ የመነጨ ንግግርና ጽሁፍ እንዳይታለሉ መታደግ ነው፡፡
የመጀመሪው የአስተሳሰብ ህጸጽ ከዕውቀት ማነስ (ignorance) የሚመነጭ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው “ስለ መላዕክት ህልውና በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም፡፡” ከሚል አንድ ማስረጃ ላይ ተነስቶ “በዓለም ላይ መላዕክት የሚባሉ ነገሮች የሉም” የሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርስ ስህተት ላይ ይወድቃል፤ ምክንያቱም አንድን ድምዳሜ ለመስጠት አለማወቅን እንደ አመክንዮ መጠቀም የአስተሳሰብ ህጸጽ ከመሆኑም ባሻገር ትክክለኛው የአስተሳሰብ መርህ ነገሩን አስከምናውቀው ድረስ ድምዳሜ ከመስጠት መቆጠብን ያስተምራልና፡፡
ሁለተኛው የአስተሳሰብ ህጸጽ አካላዊ ወይም ስነልቦናዊ ኃይልን በመጠቀም ወይም በማስፈራራት ለማሳመን በሚደረግ ሙከራ የሚፈጠር ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ግለሰብ ፈጸመ ስለተባለው ወንጀል ለማሳመን ልዩ ልዩ የድምጽ፣ የምስልና የሰው ማስረጃዎችን በማቅረብ ፈንታ ተጠርጣሪው ላይ አካላዊ ጥቃት (ድብደባ) በማድረስ ወይም በማስፈራራት ግለሰቡ ያልሰራውን ሰርቻለሁ፣ ያልፈጸመውን ፈጽሜያለሁ ብሎ የእምነት ቃሉን እንዲሰጥ በማስገደድ አሳምኖት ተጠርጣሪው ወንጀሉን እንደፈጸመ አምኗል የሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርስ በትክክለኛ አስተሳሰብ መርህ መሰረት ኃይልን መጠቀም (Appeal to Force) የተባለውን የአስተሳሰብ ህጸጽ ፈጽሟል ማለት ነው፡፡
በአድማጭ ወይም በአንባቢው ልብ ውስጥ የሐዘን ስሜትን በመጫር (Appeal to Pity) ለማሳመን የሚደረግ ሙከራ ሶስተኛው የአስተሳሰብ ህጸጽ መገለጫ ነው፡፡ አንድ ተማሪ በግል ኑሮው ላይ የገጠመውን ችግር እንባ በተቀላቀለበት ሁኔታ ዘርዝሮ ለመምህሩ በማስረዳት ምንም እንኳን የትምህርቱን ይዘት በሚፈለገው ደረጃ ባያውቀውም መምህሩ እንዲያዝንለትና ጥሩ ውጤት እንዲመዘግብለት አስተዛዝኖ ቢለምንና ቢሳካለት፣ተማሪው መምህሩን የአስተሳሰብ ህጸጽ ውስጥ ዘፍቆታል ማለት ነው፡፡
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ አብዛኞቹ የተማሪዎች የብሄር ግጭቶች የብዙሃኑን ስሜት በጅምላ ማነሳሳት (Mob mentality) በሚባል ለሚታወቀው የአስተሳሰብ ህጸጽ በአብነት የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ትክክለኛ አስተሳሰብ ከስሜታዊነትና ከቡድን መንፈስ የጸዳ፤ በአመክንዮና በተረጋጋ ግላዊ ተመስጦ የሚደረስበት መንገድ ነው፡፡ ሰዎች የበለጠ ስሜታዊ እየሆኑ በመጡ ቁጥር ይበልጡኑ ከአመክንዮ እየራቁ ይመጣሉ፤ ይበልጡኑ ከአመክንዮ በራቁ ቁጥር ይበልጡኑ የአስተሳሰብ ህጸጽ ውስጥ ይዘፈቃሉ፡፡ ለዚህም ነው የተለያየ ብሄረሰብ አባላት በሆኑ ሁለት ግለሰብ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረን ተራ ዕለታዊ ግጭት “የብሄራችን ልጅ ተነካ!” በሚል የቡድን (mob) ስሜት ተነሳስተው በማይመለከታቸው ጉዳይ በርካታ ተማሪዎች አላስፈላጊ የብሄር ግጭት ውስጥ ሲገቡና ራሳቸውን ችግር ላይ ሲጥሉ የምንመለከተው፡፡
በማስታወቂያ ቋንቋ ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ የአስተሳሰብ ህጸጾች አንድ ግለሰብ ራሱን ከብዙሃኑ ጋር በማነጻጸር የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት እንዲፈጠርበት በማድረግ እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን ከአንድ ምርት ወይም አገልግሎት ጋር በማቆራኘት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያውና (Bandwagon Argument) በመባል የሚታወቀው የአስተሳሰብ ህጸጽ ግለሰቡ ራሱን ከብዙሃኑ ጋር በማነጻጸር የበታችነት ስሜት እንዲሰማውና ከዚህ አሉታዊ ስሜትም ለመውጣት ሲል ብቻ ተገቢ ምክንያት ሳያገኝ በማሳመኛው መደምደሚያ ላይ የቀረበውን ዓረፍተ ነገር እውነትነት እንዲቀበል የሚገደድበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የፊልም ማስታወቂያ “በድፍን አዲስ አበባ መነጋገሪያ የሆነ ድንቅ ፊልም…” ወይም አንድ የቢራ ካምፓኒ “በመላ ሃገሪቱ ተወዳጅ የሆነ ድንቅ ቢራ…” የሚሉ ሃረጎችን በመጠቀም ምርቶቻቸውን ሲያስተዋዉቁ ሰምተው ይሆናል፡፡ “በድፍን” ወይም “በመላ” የሚሉትን የብዙሃን መገለጫ ቃላትን በመጠቀም አድማጩ ግለሰብ “እኔ ከብዙሃኑ ወደኋላ ቀርቻለሁ” የሚል ስሜት እንዲያጭርበትና ምርቱን ወይም አገልግሎቱን እንዲጠቀም የሚደረግበት ነው፡፡ ሁለተኛው አድማጩ ግለሰብ ራሱን ከሌሎች ጋር በማነጻጸር “እኔ እንደ ሌላው ተራ ተርታ ሰው አይደለሁም!” የሚል ስሜት እንዲፈጠርበትና ምርቱን ወይም አገልግሎቱን በመጠቀም ራሱን ከተራ ሰዎች እንደለየና ልዩ ክብር እንዳለው በማሰብ የሚኮፈስበት የአስተሳሰብ ህጸጽ (Appeal to Snobbery) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ለምሳሌ ልዩ ልዩ የሙዚቃ ኮንሰርቶች በሚዘጋጁበት ጊዜ በአንደኛ ማዕረግና በተራ የመግቢያ ትኬት መሃል ያለውን እጅግ በጣም የገዘፈን የዋጋ ልዩነት በርካታ ሰዎች እንደ ተገቢ (reasonable) የዋጋ ልዩነት የሚቀበሉት በዚህ የአስተሳሰብ ህጸጽ ተገፍተው ነው፡፡ ሶስተኛውና (Appeal to Vanity) በመባል የሚታወቀው የአስተሳሰብ ህጸጽ የሚፈጠረው ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ታዋቂና በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ካላቸው ስፖርተኞች፣ የፊልም ተዋናዮች፣የቁንጅና ንግስቶችና ሌሎች ዝነኛ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ጋር በማቆራኘት ህዝቡ ለግለሰቦቹ ወይም ለቡድኖቹ ያለውን አድናቆት ሳያስበው ወደሚተዋወቀው ምርትም እንዲያስተላልፍ በማድረግ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልናስተውል የሚገባው በትክክለኛ የአስተሳሰብ መርህ መሰረት አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ለመጠቀምም ሆነ ላለመጠቀም ከግምት ሊገባ የሚገባው የምርቱ ወይም የአገልግሎቱ የጥራት ደረጃና ለዚህም የሚቀርበው ዝርዝር ማሳመኛ እንጂ ራስን ከብዙሃኑ ህዝብ ጋር ማነጻጸር ወይም ምርትን ከዝነኛ ሰዎች ጋር በማቆራኘት የሚገኝ የስሜት እርካታ አለመሆኑን ነው፡፡
በፖለቲካዊ የክርክር መድረኮች በተደጋጋሚ የሚደመጠው የአስተሳሰብ ህጸጽ ደግሞ የተከራካሪውን ግለሰብ ሀሳብ በመቃወም ፈንታ ራሱን ተከራካሪውን ግለሰብ በመንቀፍ ወይም ስብዕናውን በልዩ ልዩ መንገድ በመንካት (against the person) የሚፈጸም ነው፡፡ ይህም በሦስት መንገድ ሊተገበር ይችላል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ክርክር ወቅት ፕሬዚደንት ኦባማ ተቃራኒያቸው የአቶ ሩምኒን የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ሲያጣጥሉ ካቀረቧቸው በርካታ ተገቢ ማሳመኛዎች በተጨማሪ አቶ ሩምኒ “በፖሊሲያቸው ላይ ወጥ አቋም የሌላቸው ባለ ሁለት ምላስ ሰው ናቸው” በሚል ዘለፋ የተቀላቀለበት ንግግር ተቃራኒያቸውን ሲያሸማቅቁ ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳ ይህ አቀራረብ በብዙዎች ዘንድ ትክክል መስሎ ቢታይም የተቃራኒን ሃሳብ እንጂ ተቃራኒውን ግለሰብ ራሱን በቀጥታ በመንቀፍ የሚቀርብ ማሳመኛ (Abusive) ለሚባለው መሰረታዊ የአስተሳሰብ ህጸጽ የተጋለጠ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል ሁለት ግለሰቦች በሃገራችን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የማስተማሪያ ቀንቋ “በአፍ መፍቻ ወይስ በሁለተኛ” በሚል ክርክር በሚያደርጉበት አንድ መድረክ ላይ “የአፍ መፍቻን የትምህርት ቋንቋ ማድረግ አይገባም” የሚል አቋም ይዞ የሚሟገተው ግለሰብ በተቃራኒው ላይ በማሳመኛነት ካነሳቸው ነጥቦች አንዱ “የአፍ መፍቻ ቋንቋን ደግፎ የቀረበው ተቃራኒው ግለሰብ እንዲህ ብሎ የሚከራከረው ‘ካድሬ’ ስለሆነ ነው እንጂ እውነታን ይዞ አይደለም!” የሚል ነበር፡፡ ከአመክንዮ ራቅ ብሎ ለሚያዳምጥ ሰው ጥሩ ማሳመኛ የቀረበ ቢመስለውም በትክክለኛ የአስተሳሰብ መርህ ሚዛን ግን (circumstantial) የሚባል ህጸጽ ተፈጽሟል እንላለን፤ ምክንያቱም የተገቢ አጸፋ ማሳመኛ (counter-argument) ዋና መገለጫ በቀጥታ ተቃራኒውን ግለሰብ ሃሳብ ውድቅ ማድረግ እንጂ ተቃራኒው ግለሰብ ስለሚገኝበት ሁኔታ በመተረክ አድማጭ ሃሳቡን እንዲያጣጥለው ማድረግ አይደለምና፡፡
በተለይ ከፍተኛ ማህበራዊና ሙያዊ ኃላፊነት ላይ የሚገኙና ለሌሎች አርአያ መሆን የሚገባቸው ግለሰቦች የሚያስተምሩትና የሚተገብሩት ድርጊት ተቃራኒ የሆነበትን አጋጣሚ ፈልፍሎ በማውጣት ይህንን ድክመታቸውን እንደ ምክንያት ለራሳቸው መልሰው በማቅረብ መልስ አልባ አድርጎ ለማሳመን የሚሞከርበት የተሳሳተ የአስተሳሰብ መንገድ (you too) ይባላል፡፡ ለምሳሌ አንድ የድርጅት መሪ ሙስና ወንጀል ነው ብሎ እያስተማረ በሆነ አጋጣሚ እርሱ ራሱ በሙስና ተዘፍቆ ቢገኝ ከግለሰቡ ድርጊት ተነስተው ከተከታዮቹ አንዳንዶቹ ሙስና ወንጀል አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ ቢደርሱ ግንዛቤያቸው (you too) በተባለው የአስተሳሰብ ህጸጽ የተቃኘ ስለሆነ የተሳሳተ ነው ማለት ነው፡፡
በተለምዶ ማስቀየስ (Red Herring) በመባል የሚታወቀው የአስተሳሰብ ስህተት በርካታ ሰዎች በየዕለቱ ሲጠቀሙበት የሚስተዋል ሲሆን ይህም ግለሰቡ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ተገቢ ማስረጃ አቅርቦ በማሳመን ፈንታ ሃሳብን በእጅጉ የሚሰርቅ አጓጊ ርዕስ በመፍጠር የአድማጭን ሃሳብ በመበታተን የሚፈጸም ነው፡፡
በማስረጃዎቹና በድምዳሜው መሃል የተፈጠረው ግንኙነት ምናባዊ በሆኑ የምክንያትና ውጤት ትስስር ላይ ተመስርቶ ከሆነ ወይም ለአንድ ድምዳሜ ምክንያት የሆነውን ነገር እንደ ውጤት፤ ውጤቱን ደግሞ እንደ ምክንያት አዟዙሮ በማሰብ፤ ወይም ለአንድ ውጤት በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩት እንደሚችል እየታወቀ አንድን ምክንያት ብቻ መርጦ በማቅረብ እንደ ዋናና ብቸኛ ምክንያት በማቅረብ ወይም አንድ ቀላል ኩነት (event) ሊያደርስ የሚችለውን ምናባዊ አደጋ ካለምንም ማስረጃ እጅግ በጣም አግዝፎ (አካብዶ) በማቅረብ አድማጭን አምታትቶ በምናባዊ ፍርሃት አሳቅቆ ለማሳመን በሚደረግ ሙከራ የሚፈጸም የአስተሳሰብ ስህተት የሀሰት ሰበብ (False cause) በመባል ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል በትክክለኛ ማሳመኛ ውስጥ የሚገኝ መደምደሚያ ከቀረቡት ማስረጃዎች መመንጨት እንዳለበት ይታወቃል፡፡
ይሁንና አንዳንድ ጀማሪ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች በጥናታቸው መደምደሚያ ላይ የሚያመጡትን ውጤት ጥናቱን ከመጀመራቸው በፊት በመገመት መላምታቸውን (hypothesis) በሚሰበስቡት መረጃዎች ላይ ተመስርተው በመፈተሽ ፈንታ ግምታቸውን በድምዳሜ ላይ በማስቀመጥ መረጃዎቻቸውን ጠምዝዘው የእነርሱን ሃሳብ በግድ እንዲደግፍ ለማድረግ በመሞከር የሚፈጠር ስህተት ፕሪዘምሽን ህጸጽ (Fallacy of Presumption) ይባላል፡፡ ይህ ህጸጽ በማሳመኛ ውስጥ የሚገኝንና መደምደሚያውን ሃሰት የማድረግ አቅም ያለውን አንድ ቁልፍ ማስረጃ በመሰወር ወይም በመደምደሚያው ላይ የተቀመጠውን ሃሳብ በማስረጃነት ደግሞ በማቅረብ ሊፈጸም ይችላል፡፡
በፍርድ ቤት ችሎት የምስክሮች አሰማም ሂደት ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የአስተሳሰብ ስህተቶች በመስቀለኛ ጥያቄ አቀራረብ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡
ይህም መስቀለኛ ጥያቄ የሚያቀርበው አካል ለመስካሪው አንድ ውስብስብ ጥያቄ (complex question) ያቀርብና ምስክሩ ለዚህ ጥያቄ አንድ “አዎ” ወይም “አይደለም” የሚል መልስ እንዲሰጥ ይጠየቃል፤ ይሁንና ግለሰቡ የሚሰጠው ማንኛውም መልስ በሁለት መንገድ ሊተነተን የሚችል በመሆኑ ምስክሩ ባላሰበበት መንገድ ድምዳሜ በመስጠት ከምስክሩ አፍ ማረጋገጫ እንደተገኘ አድርጎ በማቅረብ የሚፈጠር ህጸጽ ወይም ማደናገሪያ ነው፡፡
ለምሳሌ ከዚህ በፊት ከማንም ጋር ግንኙነት ላልነበረው ሰው “ከወንጀለኞቹ ጋር ማታ ማታ መገናኘት ትተሃል?” የሚል ጥያቄ ቢቀርብለትና ግለሰቡም “አዎ” የሚል መልስ ቢሰጥ አሁን ትቷል ነገር ግን ከዚህ በፊት ማታ ማታ ይገናኝ ነበር የሚል መደምደሚያ ይሰጥበታል፤ “አልተውኩም” ቢልም እንዲሁ ግንኙነት አለኝ የሚል እምነት ቃል እንደሰጠ ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው “አዎ” ወይም “አልተውኩም” ከሚል መልስ ተቆጥቦ ጥርት ባለ ቋንቋ “እስከ ዛሬ ከማንም ጋር ግንኙነት አልነበረኝም::” የሚል መልስ በመስጠት ራሱን መከላከል ይጠበቅበታል፡፡
በመጨረሻም በሰዋስው ምስስሎሽ (gramatical analogy) ባላቸው ቅርበት ሳቢያ የቡድንን መገለጫ ለነጠላ እንዲሁም ነገሮች በነጠላ ያላቸውን ባህርይ ለቡድን በማይገባ ሁኔታ በማስተላለፍ የሚፈጠር ህጸጽ እንገኛለን፡፡
ለምሳሌ “ኢትዮጵያውያን በጨዋነትና በእንግዳ ተቀባይነት የታወቁ ናቸው” ከሚለው የቡድን መገለጫ ተነስተን “ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጨዋና እንግዳ ተቀባይ ነው፡፡”
የሚል መደምደሚያ ላይ ብንደርስ ወይም “በዋልያዎቹ የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ የሚገኝ እንዳንዱ ተጨዋች ምርጥ ነው፡፡”
ከሚል የነጠላ ብቃት ተነስተን “ስለዚህ የዋልያዎቹ ቡድን ምርጥ የእግር ኳስ ቡድን ነው፡፡” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ስህተት ይሆናል፤ ምክንያቱም እንደ ቡድን ምርጥ ለመሆን ምርጥ ተጨዋቾችን ብቻ መያዝ በቂ ምክንያት አይደለምና፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጥንታዊ መጻህፍትን አንብቦ በትክክል የመተንተንና የመረዳት ሂደት (hermeunitics) ላይ የሚፈጠሩ በርካታ ህጸጾች (exegetical fallacies) የሚገኙ ሲሆን የጥንታዊ መጻህፍት ተመራማሪዎች (philologists) በተለይ የቅዱሳት መጻህፍት መምህራን፣ ሰባክያን ወይም የሥነ-መለኮት ምሁራን (theologians) በጥልቀት ሊያጠኗቸውና ራሳቸውን የተሳሳተ ትንታኔ ላይ ከመጣል ይጠብቁባቸው ዘንድ የትክክለኛ አስተሳሰብ ጠበብት ይመክራሉ፡፡

No comments: