ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣችው በ1966ቱ ድርቅ በበጎፈቃደኝነት ሲሆን አሁን በቋሚነት ኑሮዋ አፋር ነው፡፡ በልጅነቷ ቤተሰቦቿ ከእንግሊዝ ወደ አውስትራሊያ ሲሄዱ በመርከብ ቀይባህርን ማቋረጧን የምታስታውሰው ቫለሪ፤እጣ ክፍሌ እዚህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ፣ያኔውኑ ከመርከቧ እወርድ ነበር ትላለች፡፡ ቫለሪ ብራውኒንግ ስለ ህይወቷ የሚተርክ መፅሐፍ አሳትማለች፡፡
ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ጋር ሰመራ ላይ የተገናኘችው ቫለሪ፤ በአስገራሚ ታሪኮች ስለተሞላው ህይወቷ እንዲህ አውግታለች፡፡
ቫለሪ ማን ናት?
እኔ በትውልድ እንግሊዛዊት፣ በዜግነት አውስትራሊያዊ፣ በጋብቻ እና በኑሮ ኢትዮጵያዊት ነኝ፡፡ ሰባት ወንድሞች እና እህቶች አሉኝ። አውስትራሊያ ከሚገኝ ኮሌጅ በነርስነት እና በአዋላጅነት ሙያ ተመርቄያለሁ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት መጣሽ?