Monday, March 24, 2014

ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ አለማቀፍ የሳይንቲስቶች ሽልማት ተቀበሉ

                                                                               Written by  አንተነህ ይግዛው


የሎሬትነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል

         ኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ ዶ/ር ሰገነት ቀለሙ፣ በተለያዩ የምርምር መስኮች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ምርጥ የአለማችን ሴት ሳይንቲስቶች በየአመቱ የሚሰጠው የሎሪያል ፋውንዴሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አለማቀፍ የሴት ሳይንቲስቶች ሽልማት የ2014 ተሸላሚ ሆኑ፡፡
ተቀማጭነቱን  በናይሮቢ ኬኒያ ያደረገው ‘ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር ኢንሴክት ፊዚዮሎጂ ኤንድ ኢኮሎጂ’ የተባለ አለማቀፍ ተቋም ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሰገነት ቀለሙ፤ አፍሪካንና የአረቡን አለም በመወከል ተሸላሚ መሆናቸውን ሲስኮን ሚዲያ የተባለው የፈረንሳይ ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡  ዶ/ር ሰገነት ለ16ኛው የሎሪያል ፋውንዴሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አለማቀፍ የሴት ሳይንቲስቶች ሽልማት የበቁት፣ በእጽዋት ምርምር ዘርፍ ባደረጉት ጥናት በተለይ አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶአደሮች ዘንድ ስነ-ምህዳርን የማይጎዳ የሰብል አመራረት ዘዴ ለማስፋፋት ሁነኛ መፍትሄ የሚለግስ ተጨባጭ ውጤት በማግኘታቸው እንደሆነ
ተነግሯል፡፡
ሴቶች በሳይንስ ዘርፍ ለሚያደርጉት ምርምር እውቅና የመስጠትና የማበረታታት ዓላማ ያለው ይህ አመታዊ አለማቀፍ ሽልማት፤ ዘንድሮም ከተለያዩ አህጉራት ለተመረጡና በተለያዩ የምርምር ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አምስት የአለማችን ምርጥ ሴት ሳይንቲስቶች ባለፈው ረቡዕ ምሽት በፈረንሳይ ፓሪስ በተከናወነ ደማቅ ስነስርአት ላይ የተበረከተ ሲሆን ለተሸላሚዎችም የሎሬትነት ማዕረግ ተሰጥቷል።
የዘንድሮዎቹ አምስት ተሸላሚ ሴቶች፤ ልዩ ተሰጥኦ የታደሉ፣ በሙያቸው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነትና በትጋት የሰሩና አሁንም ድረስ በአብዛኛው ወንዶች በተያዘው የሳይንስና ምርምር መስክ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ በመሆናቸው ለሽልማቱ መመረጣቸውንም ዘገባው ያመለክታል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት ያተረፉ ሳይንቲስቶች በሰጡት ጥቆማ መሰረት፣ ራሱን የቻለ ገምጋሚ ቡድን ተቋቁሞ በተደጋጋሚ ዙር ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ከመዘነ በኋላ በሰጠው ውጤት ነው፣ አምስቱ ተሸላሚዎች ለመጨረሻው ዙር ደርሰው ለሽልማት የበቁት፡፡
ዶ/ር ሰገነት ቀለሙ ትምህርታቸውን በአሜሪካ ካጠናቀቁ በኋላ፣ በኮሎምቢያ ሲሰሩ መቆየታቸውንና ወደ አፍሪካ ተመልሰው፣ ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር ኢንሴክት ፊዚዮሎጂ ኤንድ ኢኮሎጂ በተባለውና ዘርፈ ብዙ ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነ በሚገኘው አለማቀፍ የሳይንሳዊ ምርምር ተቋም ውስጥ በሃላፊነትና በምርምር ዘርፍ በመስራት ላይ እንደሚገኙ ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡
ላለፉት 16 አመታት በየአመቱ ሲሰጥ የቆየውን ይህን አለማቀፍ ሽልማት፣ ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አገራት ሴት ሳይንቲስቶች የተቀበሉት ሲሆን፣ በዘንድሮው አመትም ከኢትዮጵያዊቷ ተመራማሪ ከዶ/ር ሰገነት ቀለሙ በተጨማሪ የአሜሪካ፣ የአርጀንቲናና የጃፓን ዜግነቶች ያሏቸው አራት ሴት ሳይንቲስቶች ሽልማቱን ተቀብለዋል፡፡

No comments: