Tuesday, March 4, 2014

መብራት ሃይል የመ/ቤቴን “ኪራይ ሰብሳቢዎች” ታገሉልኝ እያለ ነው!

  • Written by  ኤልያስ 
  • ከኑሮ ውድነት ጋር እንታገል ወይስ ከ“ኪራይ ሰብሳቢዎች” ጋር?
  • መንግስት እኮ ታክሲ ተሳፍሮ አያውቅም--- (መንግስት መሆን አማረኝ!)
  • የጋዜጠኞች ማህበራቱ  “ፀረ-ነውጥ” ድርጅት ቢያቋቁሙ ይሻላቸዋል!

እኔ የምላችሁ … እነዚህ የጋዜጠኞች ማህበራት አሁንም እዚሁ ጦቢያ ናቸው እንዴ? እኔማ ባለፈው ጊዜ  በኢትዮጵያ “የፕሬስ ነፃነት ከየትኛውም የአፍሪካ አገር በተሻለ ተከብሯል፤ አንድም በሙያው የተነሳ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም” የሚል መግለጫ ከሰጡ በኋላ (ኢህአዴግ እኮ ይቀረናል ነው ያለው!) አንድ ስማርት የሆነች አይዲያ አቅርቤላቸው ነበር፡፡ (ኦሪጂናል እኮ ናት!) ማህበራቱ ጦቢያ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት በሽበሽ ነው ካሉ በኋላ እዚህ ምን ይሰራሉ አልኩና አዲስ ወደ ተቋቋሙ የአፍሪካ አገራት (እንደ ሶማሌና ደቡብ ሱዳን የመሳሰሉ) ሄደው የጋዜጠኞች ማህበራት ቢያቋቋሙና ለጋዜጠኞች መብት ቢታገሉ “አህጉራዊ የነፃነት ታጋይ” የሚል ማዕረግ ይቀዳጃሉ ብዬ እኮ ነው (የአፍሪካ ቼጉቬራ ሆኑ ማለት እኮ ነው!)
ከአህጉራዊ የጋዜጠኞች
ማህበርነት ቀጥሎ ወደ ዓለም አቀፋዊ ማህበርነትም ማደጋቸው አይቀርም (ጠባይ ግን የግድ ነው!) ከዚያም እነሲፒጄን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች ጋር ትውውቅና የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ፡፡ (ፈረንጅ ቂም አያውቅማ!)  እናላችሁ … እኔማ ድምፃቸው ጥፍት ሲልብኝ “የሰው ምክር ይሰማሉ” ብዬ ልመርቃቸው ዳድቶኝ ነበር (አንድዬ አወጣኝ!)
በዚህ መሃል ነው ድንገት ባለፈው ማክሰኞ ከመጀመሪያው የባሰ በጩኸትና በማስፈራራት የታጀበ  ሁለተኛ መግለጫቸውን የህዝብ ንብረት በሆነው ኢቴቪ የሰጡት፡፡ የአሁኑ መግለጫ ከመጀመርያው ጋር ሲነፃፀር ግን የመጀመርያው በስንት ጣዕሙ ያሰኛል፡፡ እኔ የምለው ግን … ማህበራቱ እኛ ሳንሰማ ፈቃዳቸውን ለወጡ እንዴ? አብዛኛው የሰማው ጋዜጠኛ እኮ የጋዜጠኞች ማህበር መግለጫ አልመሰለውም፡፡ “የፀረ-ነውጥ ግብረሃይል” የሚባል የማናውቀው አዲስ ተቋም ያወጣው ማስጠንቀቂያ እኮ ነው የመሰለው!
ከምሬ እኮ ነው የምላችሁ … የጋዜጠኞች ማህበራት የትም አለም ላይ ያሉት ---- ከጋዜጠኞች ሙያና ሥነምግባር፣ ከጋዜጠኞች መብትና የፕሬስ ነፃነት መከበር--- ጋር የተያያዙ መግለጫዎች ሲያወጡ እንጂ ድንገት ተነስተው ስለሽብርና ሽብርተኞች፣ስለነውጥና ነውጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ምናልባት ለአገራቸው በጣም ስለሚቆረቆሩ ነው ሊባል ይችላል፡፡ መቆርቆሩ ባልከፋ ግን አገራችን እኮ የሰለጠነች፣ህግና ሥርዓት ያላት፣ለአፍሪካ የሚተርፍ ዘመናዊ የፖሊስና የደህንነት ሃይል ያላት ናት፡፡ እርግጠኛ ነኝ---ከተቆረቆሩ ጥቂት ዓመታት ብቻ ባስቆጠሩት አዳዲስ የአፍሪካ አገራትም እንኳን   ስለሽብርተኞችና ሽብር ስጋት “የጋዜጠኞች ማህበር” አይደለም መግለጫ የሚሰጠው! (የቄሳርን ለቄሳር አሉ!)
ይታያችሁ----እኔ እንዲህ ከተናደድኩ ኢህአዴግ እንዴት እንደሚበግን?! በዚያ ላይ እኮ ኤምባሲዎችን ሁሉ ለማስፈራራት ዳድቷቸዋል (መንግስት እንኳን አድርጎት የማያውቀውን!) ለነገሩ በትእቢት ወይም በማንአለብኝነት አይመስለኝም እንዲህ ቅጥአምባሩ የጠፋ ድርጊት የፈፀሙት፡፡ ያውም እኮ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ነው! (ሪያሊቲ ሾው አደረጉት እኮ!) እናላችሁ የማህበራቱን ነገረ ሥራ ስመረምረው---  አንድም የአመለካከት መዛባት ገጥሟቸዋል አሊያም ደግሞ ወደ በሽታ ያደገ ፍርሃት ተጠናውቷቸዋል፡፡ ያለዚያማ በአገራቸው ተቀምጠው፣ መንግስት ባለበት አገር፣ አስተማማኝ የፖሊስና ደህንነት ኃይል እያለን----እንዴት የአሸባሪዎች ጉዳይ አስግቶኛል ብሎ የጋዜጠኛ ማህበር መግለጫ ይሰጣል? ጥርጣሬን ከእነመረጃው ለፖሊስ ወይ ለደህንነት መጠቆም እኮ የአባት ነው፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ … ሌላ አገር እኮ ቢሆን በፖሊስ ኮሚሽን ወይም በደህንነት ተቋም መከሰሳቸው አይቀርም! (እንዴ ያልታዘዙትን?!)
ሌላው ችግር ምን መሰላችሁ? እነዚህ የጋዜጠኞች ማህበራት መግለጫ የማውጣት ነገር ፈፅሞ ሆኖላቸው አያውቅም (ባለሙያ መቅጠር እኮ ነውር አይደለም!) ባለፈው በአፍሪካ ህብረት የሰጡትን መግለጫ መቼም ታስታውሱታላችሁ? (የባሰ አታምጣ አሉ!)
የማህበራቱን ጉዳይ በዚሁ እንቋጭና ወደ ሌላ አገራዊ አጀንዳ ደግሞ እንግባ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደመብራት ሃይልና ኢትዮ-ቴሌኮም የሚዲያ ትኩረትን የሳቡ የመንግስት ተቋማት አሉ ብትሉኝ አላምናችሁም፡፡ ከምሬ እኮ ነው … እንደሁለቱ በሚዲያ ስማቸው በተደጋጋሚ የሚጠቀስ ፈፅሞ አይገኝም!  በመደነቅ ግን አይደለም፤ በመነቀፍ እንጂ! በአገልግሎት ጥራትም አይደለም፤ በአገልግሎት ድክመት እንጂ! በቀልጣፋ መስተንግዶም አይደለም፤ በዳተኝነት እንጂ!
 ለነገሩ ይሄንንም ቢሆን ያላገኙ ስንት የመንግስት ተቋማት አሉና እነ ቴሌኮምን “ኮንግራ” ብያቸዋለሁ፡፡ ምናልባት “በሚዲያ ስማቸው በተደጋጋሚ የተነሳ የመንግስት ተቋማት” የሚል ዓመታዊ የሽልማት ዘርፍ የሚጀመር ከሆነ፤ እርግጠኛ ነኝ ሽልማቱ ከሁለቱ እጅ ፈፅሞ ሊወጣ አይችልም፡፡ ህብረተሰቡን ሲያማርሩ ከርመው እንዴት ይሸለማሉ ብለን ልንጨረጨር እንችላለን፡፡ ግን አንዳንዴ እንዲህ ነው (“ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” አሉ!)
እውነቴን እኮ ነው … እኔ ራሴ በዚህ ዓመት እንኳን ስንቴ ነው የሁለቱን ተቋማት ስም ሳልወድ በግድ ያነሳሁት፡፡ መብራት እየጠፋ በሻማ በፃፍኩና ኔትዎርክ “ኖ ዎርክ” እያለ ስራዬን ባስተጓጎለኝ ቁጥር  ስማቸውን እያነሳሁ እወቅሳቸው የለ! እኔማ እሮሮ ሳበዛ ቀልባቸው ቢቀር  ጆሮአቸውን እንኳን  ይሰጡኛል ብዬ ነበር (ለካስ የ“ባሉካው” ልጆች ናቸው!)
ሰሞኑን አንዱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነ ወዳጄ፤ስለ “የእድገቱ ምስቅልቅል” በተለይ ስለ ታክሲ እጥረትና የመብራት መጥፋት ችግር እያነሳ ሲያወጋኝ ነበር፤ እናም በመሃል
 “መንግስት እኮ አይፈረድበትም፤ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት አያውቀውም” አለኝ - በማሾፍ ቅላፄ፡፡
“እንዴት አያውቀውም? የህዝብ መንግስት ነኝ ይል የለ እንዴ?” ከምሬ ቱግ አልኩበት፤ ወዳጄ ላይ፡፡  “ትቀልዳለህ መንግስት እኮ በታክሲ ሄዶ አያውቅማ!” ሲል መለሰልኝ ዘና ብሎ፡፡ አሁን ዝም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ እውነትም እኮ ---- መንግስት በታክሲ ሄዶ አያውቅም፡፡ መብራትም ቢሆን ሊጠፋበት አይችልም፡፡ የውሃ መጥፋትም አይታሰብም፡፡ ኔትዎርክም ሊቆራረጥበት አይችልም፡፡ እንዲያ ከሆነማ ሊመሰገን ይገባል-አልኩኝ፡፡ እውነቴን እኮ ነው---- በታክሲ ሳይሄድ ሰልፉ እንዳስመረረን እንዲገባው እንጨቀጭቀዋለን፡፡ ቀላል ተሸወድኩ መሰላችሁ! እኔ እኮ እስከዛሬ መንግስት የኛን ችግሮች ባይበዛም እንኳ የሚያውቀው ይመስለኝ ነበር (“የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” አሉ!)
እኔ የምላችሁ በመስተዳድሩ ቲቪ… የመብራት ሃይሉ ኃላፊ ምን እንዳሉ ሰማችሁ? አንዳንድ የመብራት ኃይል ሰራተኞች፤ አገልግሎት ለመስጠት ህብረተሰቡን ገንዘብ ይጠይቃሉ (“ጉቦ” ማለት አሳፍሮኝ እኮ ነው!) የሚል ነገር ተነስቶላቸው ድንግጥም ሳይሉ የሰጡት ምላሽ ግርም ነው ያለኝ፡፡ የመ/ቤታቸውን “ኪራይ ሰብሳቢዎች” ህብረተሰቡ በመታገል እንዲያግዛቸው ኮስተር ብለው ጠይቀዋል፡፡ (ህዝብ ኪራይ ሰብሳቢን የመታገል ግዴታ ያለበት ይመስል!) እንዴ … ማን የፈጠረውን ኪራይ ሰብሳቢ ማን ይታገላል!? መብራት ሃይል ራሱ የፈጠራቸውን “ኪራይ ሰብሳቢዎች” ራሱ ታግሎ ያጥፋ እንጂ እኛ ምስኪኖቹ በምን ዕዳችን? ከኑሮ ውድነት ጋር እንታገል ወይስ ከመብራት ሃይል ኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር? ይኸውላችሁ … ሌላ አገር አሉ --- ህዝብ ነው መንግስትን ይህንን አድርግልኝ፤ ያንን ፈፅምልኝ እያለ የሚያስቸግረው፡፡ እኛ አገር ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ መንግስት እኛን ህዝቦችን ያስቸግረናል፡፡ ለልማት-ህዝብ! ለሰላምና ፀጥታ መከበር-ህዝብ! ወንጀለኞችን ለመከላከል -ህዝብ! እኛ እኮ ሌሊት ወጥተን ኢህአዴግን የመረጥነው ራሱን ችሎ ይመራናል ብለን እንጂ እኛ እያገዝነው እንዲመራን አይደለም፡፡ (ያውም ከ20 ዓመት በላይ ገዝቶን!) ያለበለዚያ ደግሞ ቦታ እንለዋወጥ (ህዝብ መንግስትን ይምራው!) እኔማ ቢያንስ ለትንሽ ጊዜ መንግስት ሆኜ ባየው እንዴት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ሥልጣን ከጅዬ እንዳይመስላችሁ፡፡ የሥልጣን አለርጂክ እኮ አለብኝ፡፡ መንግስት መሆን የምፈልገው ለአንድ ነገር ብቻ ነው (ከታክሲ ወረፋ ለመገላገል ነው!) መንግስት እኮ ታክሲ ተሳፍሮ አያውቅም!
ለነገሩ እቺ “ኪራይ ሰብሳቢ” የምትባል ቃል ለብዙዎች የኢህአዴግ ሹማምንቶች “የማርያም መንገድ” እየሆነች መጥታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ እኮ አብዛኛው ሹማምንት ስለ መ/ቤቱ ችግሮች ሲጠየቅ በ“ኪራይ ሰብሳቢዎች” አሳቦ ሸርተት ነው የሚለው፡፡ አያችሁ … ቃሏ አብስትራክት ነገር ስለሆነች ጋዜጠኛውም ማብራሪያ አይጠይቅም፡፡ ኃላፊው “ኪራይ ሰብሳቢዎች” የምትለዋን ቃል ከተነፈሰ በኋላ ቀጥ ይላል - ጋዜጠኛው፤ ኤሌክትሪክ እንደያዘው ሰው (ያውም እኮ ኤሌክትሪክ በሌለበት አገር ነው!) እስቲ ሁሌም ልብ ብላችሁ የኢህአዴግ ሹማምንትን ቃለመጠይቅ ተከታተሉ፡፡ ከባዱ ጥያቄ ሲመጣ ዕዳቸውን የሚያራግፉት “ኪራይ ሰብሳቢዎች” ላይ ነው! የትኛው ዲፓርትመንት ነው የሚሰሩት? አብስትራክት ነው! መኖራቸው ከታወቀ ለምን የማጥራት ዘመቻ አልተካሄደም? አብስትራክት ነው!
ከሁሉም የሚብሰው ደግሞ የእያንዳንዱን መ/ቤት ኪራይ ሰብሳቢዎች መዋጋት የህዝቡ ኃላፊነት እንደሆነ በድፍረት መነገሩ ነው፡፡ እንዴ … የቀጠራቸውም ሆነ ዕለት ተዕለት የሚቆጣጠራቸው፣ ደሞዝ የሚከፍላቸው፣ ዕድገት የሚሰጣቸው፣ባህሪያቸውን አብጠርጥሮ የሚያውቀው--- መ/ቤቱ  እያለ… ዕዳው ወደኛ የሚሻገረው በየትኛው ኃጥያታችን ነው? (ተበዳይም  ኃጥያተኛም ልንሆን አንችልም!) እውነቴን ነው የምላችሁ … መብራትና ኔትወርክ እንዲሁም ውሃ ማጣታችን ሳያንስ ስርአቱ ከፈጠራቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር ለምንድነው ታገሉ የምንባለው? (ያውም በባዶ እጃችን እኮ ነው!)
መቼም የዘመኑን ኪራይ ሰብሳቢዎች የቀድሞው አምባገነናዊ መንግስት አልፈጠራቸውም፤ ዘመኑ እንጂ! ዘመኑ ደግሞ ወደድንም ጠላንም የኢህአዴግ ነው፡፡ (ዘመኑ ማለት እኮ ገዢው ፓርቲ ነው!) እናም .. ራሱ ኢህአዴግ ታግሎ ያጥፋቸው ባይ ነን! (ያ ሁሉ ካድሬ ለመቼ ነው?!)
ይሄን የምለው ደግሞ በክፋት ወይም በጥላቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ህዝቡን ከማያውቀው “ኪራይ ሰብሳቢ” ጋር ታገል ማለት ስለማያዋጣ ነው፡፡ ይታያችሁ … እኛ ህዝቦች በየመንግስት መ/ቤቱ ያሉትን ኪራይ ሰብሳቢዎች ታግለን እናጥፋ ብንል 50 ዓመት እንኳን  አይበቃንም፡፡ ያውም ኑሮአችንን እርግፍ አድርገን ትተን እኮ ነው፡፡ (“በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” አሉ!!)
በነገራችሁ ላይ የኢህአዴግ ሹማምንቶች … ዋና ዋና ችግሮችን ሲጠየቁ በ“ኪራይ ሰብሳቢዎች” እያላከኩ መሰስ እንዳይሉ የሚከላከል ህግ ለማስወጣት የድጋፍ ፊርማ (petittion) እያሰባሰብኩ ስለሆነ ፊርማችሁን በመላክ እንድትተባበሩኝ እማጠናለሁ፡፡ (ከ“ኪራይ ሰብሳቢ” ሠራዊት ጋር ከመታገል ፊርማ ማዋጣት አይሻልም?!)   

No comments: