Monday, March 31, 2014

የፍትሕ ሚኒስቴር ታሪካዊ ዳራ

ፍትሕ ሚኒስቴር አሁን ያለውን ስያሜ ከመያዙ በፊት የተለያዩ መጠሪያዎችን በመያዝ አወቃቀሩም ሆነ አደረጃጀቱ በየጊዜው ለውጦች ሲካሄዱበት መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚኖረው አደረጃጀት ያለፈባቸውን ሥርዓተ ማህበራትና ቅርፀ መንግስታት አሠራርና ይዘት በሚያንፀባርቅ መልኩ የተደራጀ ሲሆን ይህም በተለይ ከዳኝነት ሥርዓቱ ጋር እስከ ቅርብ ጊዜያት የነበረው ቁርኝት ለዚህ አመላካች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ስለሆነም ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው ሁሉ ይህ ፅሁፍ የፍትሕ ሚኒስቴር ከየት ተነስቶ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደቻለ፣በየወቅቱ ሲከተላቸው  የነበሩ አሠራሮች ምን እንደሆኑ፣እንዲሁም አሁን ያለው አወቃቀርና የደረሰበት ደረጃ  ከዚህ ቀጥሎ ለማየት እንሞክራለን፡፡
ሀ. ፍትሕ ሚኒስቴር እስከ ደርግ ውድቀት

የፍትሕ ሚኒስቴር በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው በአፄ ሚኒሊክ ዘመነ-መንግስት ሲሆን ጊዜውም ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱም 12 የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተቋቋሙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የዳኝነት ሚኒስቴር ነበር፡፡ በወቅቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአገር ዳኞች ዋና አለቃ ፣የሚፈርደውን ፍርድ ሁሉ በፍትሐ-ነገስት[1] ቃል በትጋት የሚጠብቅ ፣የሚፈርደውንና ባገር ውስጥ የሚፈረደውን ፍርድ ሁሉ በመዝገብ የሚፅፍ መሆኑን የሚሉት ተግባርና ኃላፊነት የተሰጡት መሆኑን በዝክረ ነገር ገፅ 68 ላይ በግልፅ ሰፍሮ ይገኛል ፡፡
ከዚህ በኋላ በተደረገው ለውጥ ማለትም በ1914 አካባቢ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዳኝነት ሚኒስቴር መባሉ ቀርቶ የፍርድ ሚኒስቴር በሚል ስያሜ እንዲጠራ የተደረገው ሲሆን በዚህ የፍርድ ሚኒስቴርነት ሥልጣኑ የፍርድ ሥራ አካሄዱን ይመራ እንደነበር የተለያዩ ፅሁፎች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው የዳኝነት ሥርዓቱም ሆነ የፍርድ ሁኔታው በእጅጉ በነገስታቱ መልካም ፈቃድ ላይ መሠረቱን የጣለ ነበር፡፡
በመቀጠል በሥልጣን ላይ የወጣው የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስትም ቢሆን ቀደም ሲል ከነበረው ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡ በዚህ ወቅት በዋናነት ትኩረት የተሰጠው የኢትዮጵያን የተማከለና ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ዓላማ ያደረገ ሲሆን ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የዳኝነት ሥርዓቱን እንደገና ለማደራጀት የተወሰደው ሲሆን ለዚህም አጋዥ የሆኑ ሕግጋት ወጥተው በሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አንፃር የዳኝነት ሥራ አካሄድን በሚመለከት አዋጅ ቁጥር 2/1934 እና አዋጅ ቁጥር 29/1934 ወጥተው በሥራ ላይ ውለዋል፡፡ በእነዚህም የሕግ ድንጋጌዎች መሠረትም በወቅቱ የነበረው የፍርድ ሚኒስቴር ፍርድ ቤቶችንና የዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤትን በአንድ ላይ ሲያስተዳድር ቆይቷል፡፡
በቀጣይ ስለሚኒስትሮች ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው ትዕዛዝ ቁጥር 1/1935 ስያሜው ባይለወጥም ሥልጣንና ተግባሩ ተለይቶ በአዲስ መልክ እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን በዚህ ትዕዛዝ መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አግባብ ያላቸው ዳኞችን አቅርቦ በንጉሱ እንዲሾሙ የማድረግ፣አስፈላጊ ሲሆን ተጨማሪ ፍርድ ቤቶችን የማቋቋም፣የፍርድ ሥራን እንዲከናወን የማድረግ፣የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሠዎችንም ላይ ሆነ የምህረት ጥያቄ ላይ የራሱን ኃሳብና አስተያየት በመጨመር ለንጉሠ ነገሥቱ የማቅረብ፣ ለጠበቆች የሥራ ፈቃድ የመስጠት እንዲሁም የሕግ ኃሳቦችን አሰናድቶ የማቅረብ ሥልጣን ተሰጥተውት ነበር ፡፡ ይህም ከቀድሞው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥልጣን ለየት የሚያደረገው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕግ ተርጓሚውን ሥራ ከመምራት ባለፈ ራሱ ዳኛ ሆኖ እንዳይሰራ መሆኑ ሲሆን ይህም በተወሰነ መልኩ የሥራ ክፍፍል መጀመሩን አመላካች ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን የዳኝነት አካሉ ሙሉ በሙሉ ከተፅዕኖ ነፃ ያልነበረ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡
በእነዚህ ጊዜያት ዐቃቤ ሕግ በፍርድ ቤቶች ዘንድ ለሚቀርቡ ነገሮች ሕግን የሚያስከብር ጠበቃ ሲሆን ሥራውም በጠቅላላ የሕዝብን ፀጥታ የሚነኩትን ሕጎች እንዲከበሩ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እስከ 1954 / ማለትም የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ እስኪወጣ ድረስ/ በክስ አቤቱታ አቅራቢነት ከሚያስቀጡ ወንጀሎች በቀር በማናቸውም የወንጀል ጉዳይ መንግስትን ወክሎ በመከራከር ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በሌላ በኩል የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ከመከታተል አንፃር ለዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት የተሰጠው የሥራ ድርሻ የሌለ ሲሆን በ1952 የፍትሐብሔር ሕግን መውጣት ተከትሎ ግን
- በሕጉ በክብር መዝገብ አፃፃፍ ላይ ስህተቶች ሲኖሩ እንዲታረሙ የማድረግ  ( አንቀፅ 122)፣
- አካለ መጠን ያላደረሰም ሆነ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተከለከለ ሠው አሳዳሪ ወይም ሞግዚት እንዲሻር ለፍርድ አቤቱታ የማቅረብ( ቁጥር 234 ላይ እንደሰፈረው)፣
- ዕብድ ወይም ድውይ የሆነ ሠው እንዲከለከል ተገቢው አቤቱታ ለዳኞች የማቅረብ( በቁጥር 353/1/፣
- ዕብድ ወይም ድውይን በሚመለከት በዳኞች የተሠጠ የክልከላ ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ አቅርቦ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በሥር ፍ/ቤት የተሰጠውን የክልከላ ውሳኔውን እንዲያሻሽልለት ወይም እንዲሽርለት ተገቢውን አቤቱታ የማቅረብ( ቁጥር 355 እና 377/1/ ላይ እንደተደነገገው)፣
- በሕግ የተከለከለ ሠው ከሥልጣኑ በላይ የሆነ ሕጋዊ ተግባር ፈፅሞ ሲገኝ ተግባሩ ያስከተለው ሕጋዊ ውጤት ፈራሽ እንዲሆን ለፍርድ ቤት አቤቱታ የማቅረብ ኃላፊነት( ቁጥር 387/2/ ላይ እንደሰፈረው)፣
- ሕገ ወጥ የሆነ ጋብቻ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት አቤቱታ የማቅረብ( ቁጥር 592/2/ እንደተደነገገው) የሚሉት ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል፡፡ 
በተመሳሳይ በ1952 በታወጀው የኢትዮጵያ ንግድ ሕግ ቁጥር 975/ሐ/ በተደነገገው መሠረት የነጋዴ መክሰር እንዲወሰን ተገቢውን አቤቱታ የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በ1954 የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉን መውጣት ተከትሎም የዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ቀደም ሲል በወንጀል ጉዳዮች ላይ የነበረው የሥራ ድርሻ እንዲሰፋ ተደርጎ በክስ አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጡ ወንጀሎችንም የማየት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡  
የንጉሱ ሥርዓት አብቅቶ በምትኩ ወታደራዊ ደርግ በትረ ሥልጣኑን ቢይዝም ቀደም ሲል ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰጠው ስያሜ እንዳለ እንዲቀጥል የተደረገ ሲሆን በጥቅምት ወር 1968 በተላለፈ መመሪያ የሕግና የፍትሕ ሚኒስቴር በሚል ሥያሜ እንዲተካ ተደርጓል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ይህንኑ ስያሜ በመያዝ በአዋጅ ቁጥር 127/69 የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት ሲወጣ ቆይቷል፡፡ [2] ይህ አዋጅም እስከ 1979 መጨረሻ ድረስ ፍርድ ቤቶችንና የዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤቶችን በሚኒስትሩ ሥር ሆነው እንዲቆዩ አድርጓል፡፡
በ1980 ዓ.ም የኢሕዲሪ መንግስት ምስረታን ተከትሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 8/1980 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲጠራበት የነበረውን የሕግና የፍትሕ ሚኒስቴር በፍትሕ ሚኒስቴር እንዲተካ የተደረገ ሲሆን በዚሁ አደረጃጀት መሠረትም ቀደም ሲል በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥር የነበሩት ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለየብቻቸው ራሳቸውን ችለው እንደወጡ ተደርጎ ከፍተኛና አውራጃ ፍርድ ቤቶች ግን በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ሆነው እንዲቀጥሉ  ተደርጓል፡፡                               
ለ. ፍትሕ ሚኒስቴር ከደርግ ውድቀት በኋላ
ከደርግ ውድቀት በኋላ የተቋቋመው የሽግግር መንግስት የፍትሕ አስተዳደሩን አስመልክቶ ገንቢ የሆኑ እርምጃዎች የወሰደ ሲሆን ከዚህ አንፃር የዳኝነት አካሉ ከአስፈፃሚው አካል ነፃ ሆኖ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በዚሁም መሠረት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን የፌዴራል አወቃቀር መሰረት በማድረግ ፍርድ ቤቶች የማዕከላዊ መንግስት እና የክልል ፍርድ ቤቶች በኋላም የፌዴራል መንግስት እና የክልል ፍርድ ቤቶች በሚል በአዋጅ ተቀቁመውና ሕገ መንግስታዊ እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲዋቀሩ ተደርጓል፡፡
ከዚህ አኳያ የፍትሕ ሚኒስቴርም ከፍርድ ቤቶች ተለይቶ በአዋጅ ቁጥር 4/1987 መሠረት እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን ዝርዝር ተግባርና ኃላፊነቱ በአዋጁ በአንቀፅ 23 ላይ ሰፍሮ ይህንኑ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በመቀጠል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኢፌዲሪ አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 471/98 መሠረት ተሻሽሎ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኢፌዲሪ አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 መሠረት ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጁ አንቀፅ 16 የተሰጡትን ዝርዝር ተግባርና ኃላፊነት እና በአንቀፅ 10 ላይ የተሰጡትን የወል ሥልጣንና ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

No comments: