Monday, March 31, 2014

ለኔትዎርኩና ለመብራቱ መጥፋት “አዋቂ” ጋ ብንሄድ ይሻላል!!

  • Written by  ኤልያስ 


  • ጐዳና የሚያፀዳ መኪና በማስመጣት ከአፍሪካ ቀዳሚ አይደለንም
  • ካሜሩን ከ11 ዓመት በፊት አስመጥቻለሁ ብላለች
  • ታንዛንያ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ነኝ ባይ ናት
      እናንተ… ያ የማሌዥያ (እየበረረ የጠፋ) አውሮፕላን እስካሁን እኮ አልተገኘም፡፡ እኔ የምለው---የዓለም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሁኔታ ጥርጣሬ አልፈጠረባችሁም? አንዴ ቻይና ትነሳና በሳተላይት ሦስት የአውሮፕላን ስብርባሪም ባህር ውስጥ ወድቆ አይቻለሁ…ትላለች፡፡ (እስካሁን አንዲትም ስባሪ አልተገኘም!) ቬትናምም እንዲሁ አንዳች ነገር ያየሁ ይመስለኛል ብላለች (ቅዥት ነው እንዴ?) አሁን ደግሞ አውስትራሊያ አካባቢ በሳተላይት ስብርባሪ እንደታየ ተሰምቷል፡፡ ነገርየው እኮ ግራ ያጋባል። የአውሮፕላኑ ባለቤት የማሌዥያ መንግስትም በሳይንስና ቴክኖሎጂው ግራ ቢገባው ጠንቋይ ጋ ሄዶ ስለአውሮፕላኑ ጠየቀ ተብሏል፡፡ (ከሳተላይት ጠንቋይ ይሻለኛል ማለት እኮ ነው!)
 እናላችሁ… የአገሪቱ ቱባ “ጠንቋይ” የወረቀት አውሮፕላን አሰርቶ (ምናቡን ወደጠፋው አውሮፕላን ለመመለስ ይሆን?) ጥንቆላውን ቀጠለ፡፡ (ይቅርታ ትንበያውን ማለቴ ነው!) ከዚያም ሁለት ምላሾችን ለመንግስት አቀረበ፡፡
አንደኛ - አውሮፕላኑ ወድቆ ጥልቅ ባህር ውስጥ ሰጥሟል!
ሁለተኛ - አውሮፕላኑ አሁንም እየበረረ ነው (በአስማት?)
እኔ የምለው…እንዴት ነው አውሮፕላኑ አሁንም ድረስ ሊበር የሚችለው? ቆይ ወዴት? በምኑ? (በነዳጅ መስሎኝ የሚበረው?) ወይስ ራሱ ጠንቋዩ በማጂክ እያበረረው ነው? ለነገሩ በክንፍም ሊያበረው ይችላል፡፡ የጠንቋዩ ምላሽ በሚዲያ ከተሰራጨ በኋላ ቻይና አራስ ነብር ሆና ነበር አሉ፡፡ ለምን መሰላችሁ? “የማሌዥያ መንግስት በማይቀለድ ጉዳይ እየቀለደ ነው” በማለት ነው፡፡ (ከ200 ተሳፋሪዎች 135 ያህሉ ቻይናውያን እንደሆኑ እንዳትዘነጉ!) የማሌዥያ መንግስት ግን “ጉዳት እኮ የለውም፤ ተሞክሮ ካልሆነ ይቀራል” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ (ጠንቋይ ጋ መሄዱን እኮ ነው!)
እኔ ግን ምን እንዳሰብኩ ታውቃላችሁ? የእኛንም የኔትዎርክ ችግር በጠንቋይ ለማስፈታት! መቼም በ“ጥንቆላ” ጥበብ ከማሌዥያ ብንበልጥ እንጂ ፈጽሞ አናንስም (በዕድሜም በዕውቀትም!) እናም…ባሉን “አዋቂዎቻችን” ተጠቅመን የኔትዎርክ ችግራችንን ለመፍታት ብንሞክር ምንም ጉዳት የለውም። (የማሌዥያ መንግስት እንዳለው ማለቴ ነው!) እውነቴን እኮ ነው… እኔ እንደሆነ በኢትዮ - ቴሌኮም ተስፋ የቆረጥኩት ገና ድሮ ነው፡፡ ይኼውላችሁ…የማሌዥያን መንግስት እያመሰገንን፣ይህቺን ድንገት ብልጭ ያለች ሃሳብ በፍጥነት ተግባራዊ ብናደርግ ያዋጣናል፡፡ ማን ያውቃል?…የቴሌኮም ኢንጂነሮች የተሰወረባቸውን የጦቢያ “አዋቂዎች” ይገለጥላቸው ይሆናል፡፡
አያችሁ…የኔትዎርክ ችግራችንን በ”አዋቂ” መፍትሔ ካገኘንለት----የመብራቱንም፣ የውሃውንም፣ የትራንስፖርቱንም ----- ለእሱ ወይም ለእነሱ አስረክበን እፎይ እንላለን! (የማሌዥያ መንግስት ወዶ መሰላችሁ!) ማን ያውቃል? “አዋቂው” ለእነዚህም ችግሮች መፈትሔ ከሰጠን፣ የኑሮ ውድነቱንና ፖለቲካዊ ችግሮቻችንንም እናቀብለዋለን፡፡ እነዚያን ችግሮች ከፈታ እኒህኞቹ አያስቸግሩትም፡፡ ከዛማ…ችግሮቻችንን በ “አዋቂ” በማስፈታት ከአፍሪካም ከአለምም አንደኛ መሆናችንን ለህዝበ አዳም ማወጅ ነው! (“አንደኛ ነን” ማለት እንወድ የለ!) ኧረ ይቅናን!!
ባለፈው ማክሰኞ ማታ ምን ሆነ መሰላችሁ? እንደ ልማዴ ከኢቴቪ ጋር ተፋጥጫለሁ፡፡ (ምን ዋጋ አለው እንዳሻው የሚናገር እሱ ብቻ!) ኢቴቪ ታክቶኝ ነው መሰለኝ ወደ አዲስ አበባ መስተዳደር  ለወጥኩት (“ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” አሉ!) በጥቅምት ወር መጥቶ ሥራ እንደጀመረ በሚነገርለት የአስፋልት ማጽጃ ዘመናዊ መኪና ላይ የተጠናቀረ ዘገባ እየቀረበ ነበር፡፡
ከምሬ ነው የምላችሁ…ቀያዮቹን ዘመናዊ የፅዳት መኪኖች ወደድኳቸው፡፡ ቢያንስ “እንግዶቹ” የሚመላለሱባቸው አውራ መንገዶች በአዛውንቶች ጉልበት ጠዋት ጠዋት መጽዳታቸው ቀርቶ፣ በዘመናዊ መኪና ሌሊት ሌሊት ጽድት ብለው ያድሩልናል ስል በኩራት ሰማይ ደረስኩ፡፡ “ግን ምነው አነሱ?” አልኩ - ለራሴ፡፡ መኪኖቹን እኮ ነው፡፡ (ይሄም በቻይና ብድር ነው እንዳትሉኝ ብቻ!) ኢህአዴግ 20 ዓመት ሙሉ ያሰራው መንገድ ቀልድ እንዳይመስላችሁ፡፡ የትየለሌ እኮ ነው! (እንደውም በየ5 ዓመት የሚመጣው ምርጫ ሥራ እያስፈታው ነው እንጂ እስከዛሬ ውስጥ ለውስጥ መንገድ ይጀምር ነበር! እናላችሁ…የጽዳት መኪኖቹ  3 ወይም 4 ቢሆኑ ነው፡፡  በቲቪ መስኮት ያየሁትን ማለቴ ነው! (ሰስቼ ይሆን እንዴ?) ግን እኮ እነዚያ መኪኖች ለአዲስ አበባ ቢያንሳት እንጂ አይበዛባትም (የአፍሪካ መዲና እኮ ናት!)
የሚገርማችሁ ---- ስለመኪናው አሰራር ተመስጬ እየተከታተልኩ ሳለ ጋዜጠኛው ድሮ ገና ወደ ፕሮፖጋንዳ ገብቶላችኋል፡፡ (የ “ልማታዊ ጋዜጠኛ ነገር አንዱ ጥሬ አንዱ ብስል አሉ!) ከዚያም መኪኖቹ ከሚሰሩት በላይ የሚደሰኩሩ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች”ና የመስተዳድሩ ተወካይ በየተራ ይቀርቡ ጀመር፡፡
ካድሬ ለመሆን ተስፋ የተሰጣቸው የሚመስሉ ነዋሪ እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ የጽዳት መኪኖች ትራንስፎርሜሽኑን ያፋጥኑታል!” እኔ የምለው…የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የከተማ ጽዳትን ያካትታል እንዴ? እኔን የበለጠ ግርም ያለኝ ግን የመስተዳድሩ ተወካይ ስለመኪኖቹ የተናገሩት ነገር ነው፡፡ ተወካዩ መኪኖቹን እተፈበረኩበት አገር ድረስ ሄደው ያስመጡ ነው የሚመስሉት፡፡ ግን አንድ ስህተት ፈፀሙ፡፡ የጽዳት መኪኖቹን በማስመጣት “ከአፍሪካ አንደኛ ነን” ሊሉ ምንም አልቀራቸው፡፡ “ምናልባት ደቡብ አፍሪካ ቢኖራት ነው…” አሉ በድፍረት! እንዴ…እኛ የተኛን እንደሆነ ዓለም አብሮን የሚተኛ መሰላቸው እንዴ?
ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? ይሄ ከጥንት ጀምሮ የተጠናወተን ራሳችንን አንደኛ የማድረግ አባዜ! (ፍርጃ እኮ ነው!) “መርካቶ በአፍሪካ ትልቁ ኦፕን ማርኬት ነው!”፣ “በአፍሪካ ኢህአዴግን የሚስተካከል ፓርቲ የለም!”…ወዘተ (አንደኝነትን የመውደድ አባዜያችን ያስቀባጥረናል!) ለነገሩ በአንዳንድ ክፉ ነገሮች እኮ አንደኛ ነን፡፡ ለምሳሌ በምቀኝነት፣ በጥላቻ ፖለቲካ፣ በአሉታዊነት፣ በመጠላለፍ፣ ተባብሮ ባለማደግ፣ ወዘተ--- ለምሳሌ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዛት ከአፍሪካ አይደለም ከዓለም ሳይቀር አንደኛ ልንሆን እንችላለን፡፡ ይሄ ማለት ግን በመድብለ ፓርቲ ስርዓትና በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ወይም በሰብዓዊ መብት አከባበር አንደኛ ነን ማለት አይደለም፡፡ (ይሄንንስ ኢህአዴግም አላለው!) እርግጥ ነው… በፓርላማ አንድ ተቃዋሚ ብቻ በመወከል አንደኛ ነን፡፡
ይኼውላችሁ…ጦቢያ በመልካም ነገሮች አንደኛ ወይም የመጀመሪያዋ ስትባል የሚጠላ ኢትዮጵያዊ የለም (ኢህአዴግም ባይሆን ማለቴ ነው!) የኢትዮጵያን ስኬት የሚጠላና አንደኝነቷን የሚያጣጥል ጠላቷ ብቻ ነው፡፡ እንዲያም ሲባል ታዲያ በስሜት ሳይሆን በምክንያታዊነት መመራት አለብን (ለጦቢያ ብሎ መዋሸት አይፈቀድም!)
የጽዳት መኪኖቹን በተመለከተ የመስተዳድሩ ተወካይ ወደሰጡት አስተያየት ልመልሳችሁ፡፡ “መኪኖቹን በማስመጣት ቀዳሚ ነን…ምናልባት ደቡብ አፍሪካ ቢኖራት ነው” ነው ያሉት ሃላፊው፡፡ አንድ ወዳጄ ግን ምን አለኝ መሰላችሁ? “ከ10 ዓመት በፊት ናምቢያን ስጐበኝ እነዚህ የጽዳት መኪኖች የከተማዋን ጐዳናዎች ሲያሳምሩ በዓይኔ በብሌኑ አይቻለሁ”፡፡
ከኢንተርኔት በተገኘ መረጃ መሰረት ደግሞ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም (የዛሬ 2 ዓመት ማለት ነው!) ታንዛንያ መኪኖቹን ወደ አገሯ ያስገባች ሲሆን “በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያዋ አገር” መሆኗም ተጠቅሷል፡፡ (እዚያም የአንደኝነት አባዜ አለ ማለት ነው!) ካሜሩን ግን ብዙ ትቀድማለች፡፡ በ2003 እ.ኤ.አ የጽዳት መኪኖቹ ወደ አገሬ ገብተው ሥራ ጀምረዋል ባይ ናት፡፡
ከ11 ዓመት በፊት ማለት እኮ ነው፡፡ ቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ይሰራ ከነበረ ጓደኛዬ ደግሞ ከ12 ዓመት በፊት የአየር መንገዱ አስፋልት (መንደርደርያው ሊሆን ይችላል) በመኪና ይፀዳ እንደነበር ነግሮኛል፡፡ (ለጠቅላላ እውቀት እኮ ነው!) የሆኖ ሆኖ ግን አዲስ አበባ መስተዳድርን ኮርቼበታለሁ፡፡ ዘግይቶም ቢሆን የጽዳት መኪኖቹን ማስመጣቱ ያስመሰግነዋል፡፡ “ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ እንዳታይ” ብየዋለሁ፡፡

No comments: