Monday, March 31, 2014

እኔ የምጨነቀው ስለአፋር እንጂ ስለ ጎሳ አይደለም”


ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣችው በ1966ቱ ድርቅ በበጎፈቃደኝነት ሲሆን አሁን በቋሚነት ኑሮዋ አፋር ነው፡፡ በልጅነቷ ቤተሰቦቿ ከእንግሊዝ  ወደ አውስትራሊያ ሲሄዱ በመርከብ ቀይባህርን ማቋረጧን የምታስታውሰው ቫለሪ፤እጣ ክፍሌ እዚህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ፣ያኔውኑ ከመርከቧ እወርድ ነበር ትላለች፡፡ ቫለሪ ብራውኒንግ  ስለ ህይወቷ የሚተርክ መፅሐፍ አሳትማለች፡፡
ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ ጋር ሰመራ ላይ የተገናኘችው ቫለሪ፤ በአስገራሚ ታሪኮች ስለተሞላው ህይወቷ እንዲህ አውግታለች፡፡

ቫለሪ ማን ናት?
እኔ በትውልድ እንግሊዛዊት፣ በዜግነት አውስትራሊያዊ፣ በጋብቻ እና በኑሮ ኢትዮጵያዊት ነኝ፡፡ ሰባት ወንድሞች እና እህቶች አሉኝ። አውስትራሊያ ከሚገኝ ኮሌጅ በነርስነት እና በአዋላጅነት ሙያ ተመርቄያለሁ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት መጣሽ?  

የ22 አመት ወጣት ሳለሁ ኢትዮ­ጵያ ውስጥ የ1966ቱ ረሀብ ተከስቶ ስለነበር እኔና ጓደኛዬ በጎ ፈቃደኞች  ሊሆኑ ይችላሉ ተብለን ስማችን  ተላለፈ፡፡ ሁኔታው ለጊዜው ግር ቢለኝም  ፈቃደኛ ሆኜ መጣሁ፡፡ እናቴን ስነግራት ደስ ብሏት ስትሰማኝ፣ አባቴ ደግሞ  የአለምን ካርታ ፊቴ ዘረጋና “የምትሄጂው አፍሪካ ነው፣እዛ ደግሞ ሰው የሚበሉ አውሬዎች አሉ” በማለት ተቃወመ፡፡ ውሳኔዬን መለወጥ እንደማልችል ነገርኩት፡፡
አውሮፕላን ስትሳፈሩ ምን ተሰማሽ?
 አውሮፕላን ውስጥ ሆኜ ጓደኛዬን “የምንሄደው ጥቁሮች ወደሚኖሩበት አፍሪካ ነው” አልኳት
 “ምንም ችግር የለም፣ ገላችንን እጠቡን እንደማይሉን ተስፋ አደርጋለሁ“ ስትል መለሰችልኝ
 “ነርስ ስለሆንን ሊሉን ይችላሉ” አልኳት፡፡
ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚጠብቀን ነገር ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም፡፡ የመጣነው ለስድስት ወር ሲሆን የተመደብነው አላማጣ ነበር፡፡ በወቅቱ ያየሁት የሰዎች ስቃይ የሚረሳኝ አይደለም፡፡
ከዛስ
የአስር አመት ልጅ እያለች ቤተሰቧ ወደ አውስትራሊያ ሲሄድ በቀይ ባህር በኩል መሄዱን ስትነግረኝ እጣፈንታዬ እዚህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ ያኔ እወርድ ነበር በማለት አስቃኛለች፡፡
 አገልግሎቴን በስድስት ወር ጨርሼ አገሬ ብመለስም  ከስምንት ወር በኋላ ሱዳን በሚገኝ  የኤርትራ ተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ መስራት ጀመርኩ፡፡ ሱዳን ያመጣኝ ድርጅት የተደራጀ እንዳልሆነ ያወቅሁት ሱዳን ከመጣሁ በኋላ ነው። በአንድ ወቅት መድሀኒት አጥተን ስንጨነቅ አብሮኝ የሚሰራ ሰው “እናንተ የውጪ አገር ዜጎች ስለሆናችሁ ፓስፖርታችሁን አሳይታችሁ ዊስኪ መግዛት ትችላላችሁ፣ ያንን ሸጠን በምናገኘው ትርፍ መድሀኒት መግዛት እንችላላን” ሲለኝ ምክሩን ተቀብለን ውስኪ ብንገዛም በወቅቱ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኒሜሪ አዲስ ህግ  አውጥተው በተደረገ ፍተሻ ውስኪያችን ሲወረስ፣ እኔም ፍርድ ቤት ቀርቤ በነፃ ተለቀቅሁ፡፡ ውስኪያችንን የወሰዱት ፖሊሶች ሲጠጡት መክረማቸውን ሰማሁ፡፡
ከኤርትራ ነፃ አውጪ ድርጅት ሻእቢያ ጋር እንዴት ተገናኘሽ?
  በምሰራበት ክሊኒክ ውስጥ ድሬሰር የነበረው ኪሮስ፣ እሱን ለመጠየቅ ከኤርትራ  ከመጡ ካድሬዎች ጋር አስተዋወቀኝ፡፡ “ትግላችንን ክሊኒክ ውስጥ በመስራት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካም እንድትረጂን እንፈልጋለን” አሉኝ፡፡ ከጥያቄያቸው ጋር በማያያዝም “ስራው አደገኛ ስለሆነ ተጠንቀቂ” አሉኝ፡፡ ታሪክ ሲሰራ ለማየት ከነበረኝ ጉጉት የተነሳ ያለምንም ማመንታ እሺ አልኳቸው፡፡ ከአንድ ወር በኋላ እረፍት ወሰድኩና ከኪሮስ ጋር ፖርት ሱዳን በመሄድ፣ ከኢሳያስ አፈወርቂና ከረመዳን መሀመድ ኑር ጋር ተገናኘሁ፡፡ ከዛም በጉርምስና እድሜ ላይ ከሚገኙ ታጋዮች ጋር ኤርትራ ሄጄ ከደርግ ነፃ የወጡ አካባቢዎችን ጎበኘሁ፡፡ ብዙም ሳልቆይ የዋሽንግተን ፖስት፣ የቢቢሲ፣ የስዊድን ቴሌቪዥን እና ሌሎች ድርጅቶችን ከሚወክሉ ጋዜጠኞች ጋር ወደ ኤርትራ ተጓዝኩ፡፡ የኔ ስራ ጋዜጠኞቹን ደስተኛ እንዲሆኑ ማድረግ ነበር፡፡ የሱዳን ቆይታዬ ለስድስት ወር የነበረ ቢሆንም ወደ ሁለት አመት ተራዘመ፡፡ በዚህ ወቅት ሻዕቢያ የእርዳታ ድርጅት እንዳቋቁም ጠየቀኝ፡፡ እኔም ተስማማሁ፡፡ ወደ አገሬ ከመመለሴ በፊትም ኢትዮጵያ ገብቼ በደርግ ስለተፈፀሙ ግድያዎች መረጃ ሰብስቤ ስለነበር፣ ሲድኒ እንደደረስኩ ስለጉዳዩ ከቢቢሲ ጋር ቃለመጠይቅ አደረግሁ። ያንን ተከትሎ ካንቤራ ከሚገኘው የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተደውሎ “የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አገሩ እንዳትገቢ ማእቀብ ጥሏል፣ እዛ ብትሄጂ የሚጠብቅሽ ከባድ ችግር ነው፣የአውስትራሊያ መንግስት ሀላፊነቱን አይወስድም” ተባልኩ፡፡
ለሻእቢያ ያቋቋምሽው ድርጅት ምን ደረሰ ?
  በደርግ ስር ለነበሩት ሰዎች እርዳታ ማሰባሰብ ጀመርኩ፡፡ ስለጦርነቱ ለአውስትራሊያ መንግስትና  ለጋዜጠኞች ምን እየሆነ እንደሆነ መረጃ እስጥ ነበር፡፡ የአውስትራሊያ መንግስት ደርግ ለጦርነት የሚያውለውን ገንዘብ ከሚሰጥ ለኤርትራና ለትግራይ የእርዳታ ድርጅቶች ለምን አይሰጥም በሚል ተንቀሳቀስኩ፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1983 ከአውስትራሊያ ለኤርትራ ይሰጥ የነበረው እርዳታ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ በምሰጣቸው መረጃዎች ኢሳያስ አፈወርቂ ደስተኛ እንዳልሆነ እሰማ የነበረ ቢሆንም ከአመት በኋላ፣ ፖርት ሱዳን ስሄድ ከሱ ጋር ተገናኘንና ቅር መሰኘቱን ገለፀልኝ፡፡
“መናገር ያለብሽ ስለህዝባዊ ግንባር ብቻ ነው፣ ስለሌሎች ድርጅቶች ማውራት አትችይም” ሲለኝ  የፈለግሁትን መናገር መብቴ እንደሆነ ገለፅኩለት፡፡ “አንቺ የኛ ብቻ ነሽ፣እኛ ነን የፈጠረንሽ” አለኝ
“እኔ አውስትራሊያዊት ነኝ፣ለአገሬ መንግስት እደውላለሁ” ብዬው  በዛው ተለያየን፡፡
ከዚያ በኋላ ጋዜጠኛ ሆንሽ?
 ሳኡዲ አረቢያ በነርስነት ለተወሰኑ ጊዜያት ከሰራሁ በኋላ በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት እና ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ በመስጠት ሶማሊያ መኖር ጀመርኩ፡፡ የምልካቸው ሪፖርቶች በሙሉ በደርግ መንግስት ማስተባበያ ይቀርቡባቸው የነበረ ቢሆንም በአንድ ወቅት ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ሶማሊያ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ላይ በተፈጠረ ውዝግብ ሶማሊያዊው ጀነራል ሞርጋን፣ መረጃውን ከሌላ ወገን ካላረጋገጥኩ እንደምባረር ነገሩኝ፡፡ መረጃው ማጣራት የሚቻለው ደግሞ ኢትዮጵያ በመሄድ ቢሆንም እኔ ኢትዮጵያ መግባት ስለማልችል በጅቡቲ በኩል አድርጌ፣ በባቡር ድሬዳዋ ለመሄድ ያደረግሁት ጥረት  ብቻ ሳይሆን የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ተዋጊዎች በድንበር በኩል ሊያስገቡኝ ከተስማሙ በኋላ ከመንገድ በመመለሳቸው ሳይሳካ ቀረ፡፡ ወደ ሀርጌሳ ከተመለኩ በኋላ እዚህ የሚያቆየኝ ምንም ምክንያት የለም ብዬ ወደ አውስትራሊያ ተመለስኩ፡፡
ከዛ በኋላ እንዴት ተመልሰሽ መጣሽ?
በ1986 ሜልቦርን በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ መስራት ጀመርኩ፡፡ ሜልቦርን በአፍሪካውያን ስደተኞች ተመራጭ ከተማ ናት፡፡ በ1989 ከጅቡቲ የመጡ ስደተኞችን ለማየት የተዘጋጀ ስብሰባ ሄድኩ። አንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት መጣችና “አንቺ ቫለሪ ነሽ?” አለችኝ “አዎ” ስላት “ከጅቡቲ ከአንድ ሰው የተላከ ደብዳቤ አለሽ፣ ዛሬ እንደማገኝሽ ስለላወቅሁ ይዤው አልመጣሁም፣ አድራሻሽን ስጭኝና እልክልሻለሁ” አለችኝ፡፡ ላከችልኝ፡፡ ደብዳቤው የኢስማኤል ነው፡፡ በተደጋጋሚ ደብዳቤ እንደፃፈልኝና ከእኔ መልስ አለማግኘቱን በመጥቀስ ይህ የመጨረሻው እንደሆነ ያትታል፡፡ ሳነበው እጅግ አዘንኩ፡፡ እጅግ ታምሜ በነበረበት ወቅት እርዳታ ያደረገልኝን ሰው ቅር በማሰኘቴ አዘንኩ፡፡ ደብዳቤ ፅፌም አብዝቼ ይቅርታ ጠየቅሁት፡፡
በዚያው ሰሞን ለስራ ሱዳንና ሶማሊያ እሄድ ስለነበር ኢስማኤልን አግኝቼ “አመሰግናለሁ” ለማለት ጅቡቲንም የጉዞዬ አካል አደረግኋት፡፡ ጅቡቲ ስደርስ ኢስማኤልና ቤተሰቦቹ ተቀበሉኝ። አንድ ቀን ለብቻችን ቁጭ ብለን “መጋባት አለብን ብዬ አስባለሁ” ሲለኝ “ይቅርታ” አልኩት “እንጋባ” አለኝ፡፡  በጣም ተገርሜ “እጅግ በተሳሳተ መንገድ ነው የተረዳኸኝ፣እኔ ምንም ገንዘብ ባንክ የለኝም፣ለምን ታገባኛለህ?” ስለው “እኔ ያንቺን ገንዘብ አልፈልግም፣ እዚህ እንድትኖሪ ነው የምጠይቅሽ” አለኝ፡፡ “የምታውቀኝ ከሁለት አመት በፊት ለተወሰኑ ቀኖች ነው፣ አላውቅህም” ስለው “ፍቅር እንደዚህ ነው፣ ይልቅ ውሳኔሽን ንገሪኝ” አለኝ፡፡ በዛን ወቅት እድሜዬ 38 ነበር፡፡ ያኔ ምንም አይነት የፍቅር ግንኙነት አልነበረኝም፡፡ በቀጣዩ ቀን ስለ ኢስማኤል ሳስብ ዋልኩ፡፡ እሱ ጥሩ ሰው ነው፣ ጓደኞቹና ቤተሰቦቹም እንደዚያው፡፡ ነገር ግን ወጣም ወረደ እኔ የምእራቡ አለም ሴት ነኝ፣ ከአንድ ሴት በላይ ጋብቻ አልፈቅድም፣ እሱ የአራት አመት ታናሼ ነው፣ ሀይማኖታችን ሙስሊምና  ክርስትያን ነው፡፡ ከእኔ ሌላ ሴት እንደማያገባ ቃል ገባልኝ፡፡ ኃይማኖትም ችግር እንደማይፈጥር ነገረኝ፡፡  በጉዳዩ ላይ እግዚአብሄር መልስ እንዲሰጠኝ ፀለይኩ፡፡ ወላጆቼን ላማክር አሰብኩና ተውኩት፣ ከአንድ ወር በኋላ የጋብቻ ጥያቄውን ተቀበልኩት፡፡ ያለምንም ግርግር ተጋባን፡፡ ወደ አውስትራሊያ ተመልሼ ማግባቴን ለቤተሰቤ ተናገርኩ፡፡ ባለቤቴ ባይኖርም የሰርግ ግብዛዎች ካደረጉልኝ በኋላ ወደ ትዳሬ ተመለስኩ፣ ጅቡቲ፡፡ ኢስማኤል ስለ ሀይማኖት ሲጠየቅ የኔ ትክክል ከሆነ ገነት ይዛት እገባለሁ፣ የሷ ትክክል ከሆነ ደግሞ ይዛኝ ትገባለች ይላል፡፡
ኑሮአችሁ እንዴት ነበር?
ኑሯችን እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ ነበር፡፡ እሱ የኤሌክትሪክ እቃዎች መጠገኛ ሱቅ ቢኖረውም ስራውን የሚሰራው በአፋር መንገድ ነው፡፡ ሂሳብ የሚከፍሉት ገንዘብ ሲያገኙ ነው፡፡ ኑሮውን መልመድ ቀላል አልነበረም፡፡ ሙሉ በሙሉ ራሴን ወደ አፋር ሴት መለወጥ ነበረብኝ፡፡ ለዚህም ከአለባበሴ ጀመርኩ፡፡ አኗኗራቸው እርስ በእርስ በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፣ የግል ጊዜ  ወይም የግል ሀብት የሚባል ነገር የለም፡፡ ባለቤቴ በቂ ገንዘብ ባይሰጠኝም እንደሱ ለአፋር ነፃነት የሚታገሉ ጓዶቹን አብስዬ ማብላት ይጠበቅብኛል፡፡ እኔ ደግሞ ማብሰል ላይ እምብዛም ነኝ፡፡ አንድ ቀን እናቴ ያስተማረችኝን ቱና በማካሮኒና ቺዝ ሰርቼ ስሰጠው፣ “እንዴት ወተት አሳ እና ቺዝ ትቀላቅያለሽ? በህይወቴ እንዲህ አስቀያሚ ምግብ በልቼ አላውቅም” አለኝ፡፡
ሥራ ማግኘት አልቻልሽም ?
ጅቡቲ የሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ስራ ተገኝቶልኝ መስራት ብጀምርም ደሞዙን ግን ከአመት በኋላ ነበር ያገኘሁት፡፡ ፈተናው ሲበዛብኝ  አገሬ መመለስ አለብኝ ብዬ ወሰንኩና ኢስማኤልን ነገርኩት፡፡ ከአገሩ ባህል ጋር መላመድ እንዳልቻልኩና ለመግባቢያ የሚሆን ቋንቋም እንደማላውቅ አስረግጬ ስነግረው “እንዲህ ለማለት ጊዜው በጣም አጭር ነው፣ትንሽ ቆይተሽ ሞክሪው” ስላለኝ በዚህ ተስማማን። በመሀል አረገዝኩ፡፡ ምጤ ሲመጣ ኢስማኤልን ቀሰቀስኩትና “ሆስፒታል እንሂድ” ስለው “ምንም የሚያጣድፍ ነገር የለም ሲነጋ ትሄጃለሽ” አለኝ። ነግቶ ሆስፒታል ስደርስም ቀኑ አርብ ስለነበር ስራ የለም፡፡ ግብፃዊውን ሀኪም በቶሎ ኦፕራሲዮን እንዲያደርግ ብጠይቀውም “ዛሬ አልችልም” አለኝ፡፡ በነጋታው ወለድኩ፡፡ ስሟንም አይሻ አልኳት፡፡
“ፍሮንት ፎር ሪስቶሬሽን ኦፍ ዩኒቲ ኤንድ ዲሞክራሲ” (ፍሩድ) በመባል ከሚታወቀው የጅቡቲ አፋሮች ድርጅት ጋር ለመስራት እንዴት ወሰንሽ?
ጅቡቲ በአፋር አማፂ ቡድንና በኢሳ መራሹ መንግስት ውጥረት ላይ ነበረች፡፡ ኢስማኤል የቡድኑ አባል በመሆኑ “ነገሮች እየተበላሹ ስለሆነ እኔ ኢትዮጵያ እሄዳለሁ፣ አንቺ ትከተያለሽ” ብሎኝ ሄደ። አንድ ቀን በስልክ ኢትዮጵያ መምጣት እንዳለብኝ ነገረኝ፡፡ ብዙም ባይሆን ያለኝን ይዤ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡ ወደ አገሪቱ ለመግባት የተጣለበኝ እገዳ ተረስቷል፣አዲስ መንግስት መጥቷል፡፡ አዲስ አበባ ስደርስ ባለቤቴ ተቀበለኝ፡፡ አዲስ አበባ ከገባሁ በኋላ፣ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ የአፋር ታጋዮች ጋር ተገናኘሁ፡፡ ድርጅት እንዳቋቋም እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፡፡ ለፎረም ፎር ሪስቶሬሽን ፎር ዩኒቲ እና ዲሞክራሲ ሰብአዊ እርዳታ ካላገኘ ጦርነቱን መቀጠል አይችልም አንቺ ደግሞ ልምዱ አለሽ ሲሉኝ በውስጤ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩም ኢስማኤል ጣልቃ ገብቶ “እንደተስማማሽ ነግሬያቸዋለሁ” አለ። እርግጠኛ ባልሆንም እሺ አልኩ፡፡
ለአውሮፓ አገሮች ኤምባሲዎችና ለሌሎች ድርጅቶች የእርዳታ ጥያቄ አቀረብን፡፡ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚዋሰኑበት ቦታ ላይ የፍሩድ ተዋጊዎች የተገኙበትን ስብሰባ ተካፈልን፡፡ ከዛም የጅቡቲ የእርዳታ ማህበርን አቋቋምን፡፡ በወቅቱ ለእርዳታ ማስተላለፍ ስራችን ኢትዮጵያ ፈቃደኛ ስላልሆነች ከኤርትራ ፈቃድ ለማግኘት አስመራ ሄድን፡፡ በወቅቱ አንድ የሚመረቅ ፋብሪካ ዝግጅት ላይ ኢሳያስ አፈወርቂ እንደሚመጣ ስለሰማን እዛው ልናናግረው ወስነን ሄድን፡፡ ኢሳያስና ጠባቂውን አይቼ በፈገግታ ልጠጋቸው ስሞክር ጠባቂው ያለምንም ስሜት ራቅ አደረገኝ፡፡
ከለጋሽ ድርጅቶች ምላሽ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ስረዳ፣ቤተሰቦቼ አውስትራሊያ ውስጥ የገንዘብ ማሰባሰቢያ አድርገው በላኩት ገንዘብ አስር ግመሎችን ገዛን፡፡ እነሱን በመጠቀም መድሀኒትና ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ቦታዎች መድረስ ጀመርን፡፡ በዚህ ወቅት ነው የፍሩድ መሪ “ሀሚድ ማሊካ” በአረብኛ ንግስት የሚለው ስሜን ያወጣልኝ፡፡ ቀስ በቀስ የእርዳታ ድርጅቶቹ  እገዛ ቢያደርጉልንም  የፍሩድ አመራር በኢሳ መንግስት የተወሰኑ የሀላፊነት ቦታ ተሰጥቶት ለመስራት በመስማማቱ ኢስማኤል እጅግ ተበሳጨ፡፡ በ1996 ዓም  የኢትዮጵያ መንግስትም  በዚህ ስራ መቀጠል እንደማንችል አስረግጦ ስለነገረን፣ ድርጅቱን ወደ የአፋር አርብቶ አደሮች ልማት ማህበር ለወጥነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአፋርን ህዝብ በማስተማርና ጤና ላይ እየሰራን እንገኛለን፡፡
 አንቺ የየትኛው ጎሳ አባል ነሽ?
የጎሳ ስርአት ቢኖራቸውም እኔ ኢትዮጵያዊት ነኝ፡፡ ጎሳ የለኝም፡፡ ጎሳ በጣም ጠባብ ነው፡፡ የምሰራውም ለባለቤቴ ጎሳ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አፋሮች ነው፡፡ ሰዎች መጥተው ስለባለቤቴ ጎሳ ሲያወሩኝ አልቀበላቸውም፡፡ እኔ የምጨነቀው ስለአፋር እንጂ ስለ ጎሳ አይደለም፡፡
ሲጠሩሽ ምን ይሉሻል?
ያና ማሊካ፣ አክስቴ ማሊካ፣ ይና ማሊካ፣ እናቴ ማሊካ ይሉኛል፡፡
ከነሱ ጋር ስትኖሪ ምን ተማርሽ?
በምእራቡ አለም ለራሳችን ነው የምንኖረው፡፡ ፍላጎትሽንና ሌሎች አንቺን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በግልሽ ትወስኛለሽ፡፡ እዚህ ደግሞ ሁሉም ነገር የሚሰራው በማህበረሰብ ደረጃ ነው፡፡ የፀጉር ብሩሽ ካለኝ ሌሎች ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ መፅሀፍ ካለኝ ሌሎች ሊያነቡት መውሰድ ይችላሉ፡፡ ያለኝን ነገር መካፈል፣ ለሌሎች መስጠትን የተማርኩት ከአፋሮች ነው፡፡ ለቁሳቁስ ዋጋ እንዳልሰጥም አስተምረውኛል፡፡ ገንዘብ የለኝም ግን ምንም አይመስለኝም፡፡
ከብቶችስ  አሉሽ?
ከተማ ስለምኖር ከብቶች የሉኝም፣ ወተት ግን በጣም እወዳለሁ፡፡
ቫለሪ ብራውኒንግ ትባላለች፡፡ የአፋር አርብቶ አደሮች ልማት ማህበር ዳይሬክተር ናት፡፡  የአፋሮቹን ችግር ለጠየቃት አፋርኛውን ቅልጥፍ አድርጋ ስትናገር አፍ ታስከፍታለች፡፡

No comments: