Monday, March 31, 2014

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋብቻና ፍቺ አልተጣጣመም!

  • Written by  ኤልያስ 


  • ኢትዮ-ቴሌኮም በኖኪያ ቁጥጥር ስር የነበሩ የኔትዎርክ ወረዳዎችን ነፃ አወጣ!
  • አንድነት እና መኢአድ ሳይጋቡ በመፋታት ሪከርድ ሰብረዋል
  • “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ትዝ የሚላቸው ምርጫ ሲቃረብ ነው

        የአፍሪካ አንድነት የሰላም አስከባሪ ኃይልን የተቀላቀለው የአገራችን መከላከያ ኃይል ሶማሊያ ውስጥ አልሻባብ ተቆጣጥሯቸው የነበሩትን ቦታዎች ማስለቀቁን በኢቴቪ ዜና እወጃ ላይ ሰምቼ ደስ ብሎኝ ነበር (ኢትዮጵያዊ ሆኖ ድል የማይወድ አለ እንዴ?) በነጋታው ነው መሰለኝ … ሌላ የምስራች ደግሞ ሰማሁ፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም በኖኪያ ቁጥጥር ስር የነበሩትን አየር ጤና፣ ቄራና ዓለም ባንክ አካባቢዎች ነፃ ማውጣቱ ተነገረ-በዜና ሳይሆን በተባባሪ ወሬ፡፡ እናላችሁ …. ሁለቱ አካባቢዎች አሁን ኔትዎርካቸው ያለመቆራረጥ እየሰራ ነው፤ ተብሏል (ኢንተርኔትና ፌስቡክም ያለችግር ማግኘት ችለዋል) ኢትዮ-ቴሌኮምን የማሳስበው ግን በዚህ የድል ብስራት ተኩራርቶ ሌሎቹን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የኔትዎርክ ወረዳዎች ነፃ ከማውጣት እንዳይዘናጋ ነው። ያለዚያ እኮ የሦስቱ አካባቢዎች ነፃ መውጣት ትርጉም የለውም (ተመልሰው በ“ጠላት እጅ” ሊወድቁም ይችላሉ!) እናላችሁ … ሌሎች የመዲናዋ አካባቢዎችም ከ “ባዕድ እጅ” ነፃ ሲወጡ ነው እነ ዓለም ባንክ ነፃነታቸውን በቅጡ የሚያጣጥሙት፡፡ እስከዛ እኮ እርስ በርስ ብቻ ነው ኮሙኒኬሽኑ!

አሁን ደግሞ እስቲ ወደ ዓለም አቀፉ የትዳር ወሬ እንግባ፡፡ በአሜሪካ በየ36 ሰኮንዶች አንድ ፍቺ እንደሚፈፀም ታውቃላችሁ? (በጦቢያ ስንት ይሆን?) ይሄ ማለት በቀን 2ሺ 400 ገደማ ፍቺዎች እንደ ማለት ነው፡፡ በሳምንት ሲሰላ 16ሺ 800 ፍቺዎች ይሆናል፡፡ በዓመት ደግሞ 8ሺ ፍቺዎች! (ጉድ አትሉም!) የአገራችንን ጋብቻና ፍቺ የተመለከቱ መረጃዎች በቅጡ የተደራጁ ስላልሆነ ነው እንጂ ከአሜሪካኖቹ ላይተናነስ ሁሉ ይችላል እኮ! (አደራ ከፍቺ  የሚደመሩ ትዳሮች እንዳይዘነጉ!) የመረጃ እጥረታችንን እስክንደፍን ድረስ በአሜሪካውያኑ መረጃ እንጠቀማ!፡፡ (“ምስጋና ለስልጣኔያቸው” እያልን!)
በነገራችን ላይ ብዙ በማግባትና በመፍታት ከተራ ተርታው አሜሪካዊያን ይልቅ ዝነኞቹ ይበልጥ ይታወቃሉ፡፡ ከዝነኞችም ደግሞ ዘፋኞችና የሆሊውድ አርቲስቶችን የሚወዳደራቸው የለም ነው የሚባለው፡፡ ብሪትኒ ስፒርስ የተባለችው ዝነኛ አቀንቃኝ ለምሳሌ በአጭር የጋብቻ ህይወት ሪከርድ ሰብራለች፡፡ ጃሶን አሌክሳንደር ከተባለው ፍቅረኛዋ ጋር የመሰረተችው ጋብቻ የዘለቀው ለ55 ሰዓታት (2 ቀን ተኩል ገደማ) ብቻ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ብዙ ጊዜ በማግባትና በመፍታት ደግሞ Zsa zsa Gabor የተባለች የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ሪከርዱን ይዛለች፡፡ እቺ ተዋናይ ዘጠኝ ጊዜ አግብታ መፍታቷ ተዘግቧል፡፡ (ህይወቷንም ተወነችው እንዴ?) በዝነኞች የፍቺ ታሪክ ለቀድሞ የትዳር አጋሩ ከፍተኛ ክፍያ በመፈፀም (የሃብት ክፍፍል መሆኑ ነው!) እስካሁን የፊልም ባለሙያውን ሜል ጊብሰንን የሚወዳደር አልተገኘም፡፡ በ2009 ዓ.ም  በፈፀመው ፍቺ ለቀድሞ ሚስቱ 425 ሚ. ዶላር ነው የከፈለው። (ሴትየዋ በፍቺ ከበረች እኮ!)
በእኛም አገር (የዝነኞች አይደለም እንጂ) በአስደናቂ ፍጥነት ለፍቺ የበቃ ጋብቻ መኖሩን ሰምቻለሁ፡፡ ለነገሩ ጋብቻ እንኳን አይባልም፡፡ እንደ አንዳንድ የአገራችን ፓርቲዎች ከጋብቻው በፊት ነው ፍቺው የተፈፀመው፡፡ ጥንዶቹ ዝነኞች ባይሆኑም ለሰርጋቸው ያወጡት ወጪ ግን ከዝነኞች ተርታ የሚያስመድባቸው ነው (አሉ!) ለሰርጋቸው የተከራዩት ሊሞዚን ለአንድ ቀን 45 ሺ ብር ነው የተከፈለበት፡፡ ግን ምን ያደርጋል … እዚያው ሊሞዚን ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ጥንዶቹ ለመለያየት በቅተዋል፡፡ (ገና ሳይጋቡ ማለት ነው!) እነዚህስ እንኳንም አልተጋቡ ያሰኛል። (እንደማይዛለቁ ያስታውቃሉዋ!) ለዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ መጠባበቂያ ሙሽራ ወይም ሙሽሪት የሚያዘጋጁ ማህበረሰቦች መኖራቸውን ሰምቼ “የገባቸው” ብያቸዋለሁ፡፡ እነዚህን ሁሉ የጋብቻና ፍቺ መረጃዎች ያመጣሁት ግን የባልና ሚስት ትዳር አሳስቦኝ እንዳይመስላችሁ። (ቢያንስ ለዛሬ ያሳሰበኝ ሌላ ነው!) ጉዳዩ ምን መሰላችሁ? የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋብቻና ፍቺ ነው፡፡ መነሻ የሆነኝ ደግሞ ባለፈው ሳምንት በሰርጋቸው ዕለት የከሸፈው የአንድነት እና የመኢአድ ጋብቻ ነው፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች የሰርጋቸው ዕለት ነው ፍቺያቸውን ያወጁት፡፡ እርግጥ ነው እነሱ “ለጊዜው …ትተነዋል” ነው ያሉት፡፡ በአገራችን የጋብቻ ባህልና ልማድ ደግሞ የሰርጉ ቀን ይፋ ተደርጎ፣ “ልንጋባ ነው እወቁልን” ከተባለ በኋላ የሰርጉ ዕለት ድንገት ተነስቶ “ለሌላ ጊዜ አስተላልፈነዋል” አይባልም፡፡ (“የመጀመርያውን ለምን ይፈቱታል፤ ሁለተኛውን ለምን ያገቡታል፤ ሶስተኛውን …” አለች አስቱ!) እንዴ … ይሄ እኮ ቤተሰብን ማሳፈር ነው፡፡ ፓርቲዎች ሲሆኑ ደግሞ ህዝብን ያሳፍራሉ (የአገርም ማፈሪያዎች መሆናቸው ሳይረሳ!) በአንድ በኩል ግን እንኳንም “ሙሽራው ቀረ” ብያለሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ለመጋባት እንኳን አልተማመኑም እኮ!! (“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” አሉ!) አንዱ በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አንጀቱ የሚበግን ወዳጄ ስለ እነ አንድነት ጋብቻ መክሸፍ ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? “ጋብቻው የፈረሰው ሁለቱም ሙሽራ ካልሆንን ብለው ነው!!”፡፡ (ሁለቱም “ወንዶች” ነን ሲሉ ተፈጠሙ ማለቱ ነው!) አያችሁ … ጋብቻ የሚፈፀመው ደግሞ በሙሽራና ሙሽሪት መካከል ነው፡፡ ሙሽሪትን የሚሆን ሳይሆን ሆኖ የሚተውን እንኳን ጠፋ፡፡ ሁለቱም ባል መሆን አማራቸው፡፡ ያውም ብልጥ ባሎች፡፡ ለዚህ ነው በሰርጋቸው ዕለት ፍቺው የተፈፀመው ባይ ነኝ ወዳጄ፡፡ በምዕራቡ ዓለም ቢሆን እኮ ሁለቱም ወንዶች ቢሆኑም ችግር የለውም፡፡ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ይፈቀዳላ! እዚህ አገር ግን ይህ ሃራም መሆኑን እያውቁም ሁለቱም አባወራ መሆን ፈለጉ፡፡ በአንድ ጎጆ ጣራ ስር እንደር ተብሎ ሁለት አባወራ እንዴት ይሆናል? አንድ አባወራና አንድ እማወራ እንጂ። በጣም የሚያሳዝነው ግን … ለአገራቸው ወይም ቆመንለታል ለሚሉት ህዝባቸው ብለው እንኳ አንዳቸው የእናትነት ሚናን ሊወስዱ አልወደዱም፡፡ ሁለቱም የቤት አስተዳዳሪ፣ ሁለቱም ፈላጭ ቆራጭ አባት፣ ሁለቱም አባወራዎች ለመሆን ነው የፈለጉት፡፡ በአንድ ጎጆ ግን ሁለት አባወራዎች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ (በአንድ ሰማይ ሁለት ፀሐዮች ይወጣሉ እንዴ?)
ይሄውላችሁ … ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ አገርም ብትሆን በአንድ ጊዜ ሁለት አባወራ ሊኖራት አይችልም፡፡ በአንድ ጊዜ አንድ ብቻ ነው! አንድ አባወራ! አንድ መሪ! አንድ ገዢ ፓርቲ! አንድ ጠ/ሚኒስትር! አንድ ፀሐይ ብቻ ነው የሚቻለው… ይሄ ሁሉ ተቃዋሚ እንዲህ የሚተራመሰው በዚህ ትውልድ ሥልጣን ላይ እፈናጠጣለሁ ብሎ ከሆነ አለቀልን በሉት፡፡ (የስልጣን ቅዠታቸውን ቢገቱት ይሻላቸዋል!) ለነገው ትውልድ ስልጡን የፖለቲካ ባህልና ሥርዓት ለመፍጠር ከሆነ ግን  ያስኬዳል፡፡ (“ሞኝህን ፈልግ” እያሉኝ እንደሆነ ይገባኛል!)
በነገራችሁ ላይ … ጋብቻቸውን በፍቺ የቋጩት አንድነትና መኢአድ ብቻ እንዳልሆኑ ጉደኛው ታሪካችን ሹክ ይለናል፡፡ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ “20 ዓመት ሙሉ ያልሰመረው የተቃውሞ ጎራው ውህደትና ጥምረት” በሚል የቀረበው ሰፊ ዘገባም የከሸፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጋብቻዎች ነው በዝርዝር የሚያሳየው፡፡ የ97ቱ ቅንጅትም እኮ የቱንም ያህል ከፍተኛ ድጋፍ የነበረው ፓርቲ ቢሆንም በችኮላ ጋብቻ መስርቶ በችኮላ ፍቺ የፈፀመ ግዙፍ “ህዝባዊ ፓርቲ” ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ይሄ ፓርቲ እንዴት ጋብቻው ፈርሶ ሁሉም ፓርቲዎች ወደ እናት ክፍላቸው እንደ ተመለሱ ቁርጥ ያለ መልስ እስካሁን አለመገኘቱ ነው፡፡ ልብ በሉ! ይሄን ጥያቄ ለመመለስ ያልተፃፈ መፅሐፍ የለም። ያልተደረገ ቃለ ምልልስ (ኢንተርቪው) የለም፡፡ (ያውም from the horse’s mouth!) ከየትኞቹም ግን እቅጯን መልስ  አላገኘንም፡፡ ይልቅስ ሰሞኑን በፓርቲዎች ውህደት መክሸፍ ዙሪያ ተጠይቀው መልስ የሰጡት የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ አበባው መኃሪ ትንሽ ፍንጭ ሰጥተውናል፡፡ “በውህደት ስም ፓርቲ እስከመውረስ የደረሱ…” እንዳሉ ነው የተናገሩት፡፡ አያችሁልኝ… ፓርቲዎች ለካ የሆኑ ግለሰቦች ንብረት ናቸው፡፡ (ኩባንያም ልትሏቸው ትችላላችሁ፡፡)
እኒህ ፓርቲዎች እምብዛም የገንዘብ ምንጭ ባይሆኑም የስልጣን ጥም ማብረጂያ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሥልጣን ጥመኞችም ለፓርቲ ጋብቻ በፍቺ መፈፀም ምክንያት መሆናቸው መነገሩ እንዳይረሳ፡፡ እቺን እንኳን እኛም እናውቃታለን! ኢህአዴግን በስልጣን ጥመኛነት እየወነጀሉ ላለፉት 20 ዓመታት የፓርቲ ፕሬዚዳንትነትን የሙጥኝ ያሉ ተቃዋሚ አመራሮች ለእኛ ብርቃችን አይደሉም፡፡ እናላችሁ … የተቃዋሚ ጎራው ለምንድነው በህብረት ወይም በጥምረት ለመስራት ዳተኛው የሆነው ብለን ስንጠይቅ መልስ የማናገኘው አምርረን መልስ ስለማንፈልግ እንጅ መልሱ አፍንጫችን ስር ይመስለኛል፡፡ (በጥናት ሳይሆን በግምት!) ከዚያ በፊት ግን የተቃዋሚ ጎራው መቼ መቼ ነው የህብረትና የጥምረት ጥያቄ የሚያነሳው የሚለውን በወጉ እንመልስ፡፡
እዚህች አገር ላይ ሁሌ ምን ግርም እንደሚለኝ ታውቃላችሁ? ተቃዋሚዎችም ሆኑ ገዢው ፓርቲ ህዝባቸው ትዝ እሚላቸው ምርጫ ሲቃረብ መሆኑ ነው! እስቲ ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ የምርጫ ጊዜያትን አስታውሱ፡፡ ኢህአዴግ ብዙ ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ውይይቶችን የሚያደርገው የምርጫ ሰሞን እኮ ነው! ከምሬ ነው …. አውራ ፓርቲው ከህዝብ ጋር ፍቅር የሚይዘው ምርጫ ደረሰ ሲባል ብቻ ነው፡፡ የአምስት ዓመት የህዝብ ችግርና ብሶት በአንድ ሰሞን ውይይት ሊፈታ መከራውን ይበላል፡፡ በተግባር ስለማይቻል ነው እንጂ ኢህአዴግ በምርጫ ሰሞን የህዝቡን ችግር ሁሉ ፈትቶ ቢገላገል ደስታው ነበር፡፡ (ህዝቡ የሚኖረው በአምስት ዓመት አንዴ መሰለው እኮ!)
ተቃዋሚዎችም ዳያስፖራን ለመቀስቀስ የሚነቃቁት ምርጫ ሲቃረብ መሆኑን አሳምረን እናውቃለን፡፡ ፋይናንስ የሚያሰባስቡትም ምርጫው ጥቂት ወራት ሲቀሩት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ፖለቲካን የሙሉ ሰዓት ስራቸው (Full-time job) የሚያደርጉት እንኳን ምርጫ መጣ ሲሏቸው ነው፡፡ (ከዚያ በፊትማ part-time job ነው) ከሁሉም የሚብሰው ግን ምን መሰላችሁ? ተቃዋሚዎች “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” የሚለው ዕድሜ ጠገብ አባባል ትዝ የሚላቸው ከፊታቸው አገራዊ ምርጫ ድቅን ሲልባቸው ብቻ ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው የማይተዋወቁ ፓርቲዎች ሁሉ ድንገት እየተነሱ የጋብቻና የቅልቅል ጥያቄ (Proposal) የሚያቀርቡት፡፡ በቅጡ ሳይተዋወቁ ወይም ሳይጠናኑ ጋብቻ ለመፈፀም ማቀድ ደግሞ እንደሰሞኑ የአንድነትና የመኢአድ ሁኔታ ሳይጋቡ መፋታትን ያመጣል፡፡ (Disaster ይሏል ይሄ ነው!) እንደኔ ምልከታዊ ትንታኔ ከሆነ ኢህአዴግ የምርጫ ሰሞን ከህዝቡ ጋር ፍቅር የሚይዘው ሥልጣኑን ስለሚወድ ብቻ ነው (ህዝቡ በድምፁ እንዳይቀጣው ይሰጋላ!) የተቃዋሚው ጐራም ምርጫ ሲቃረብ ጥምረትና ውህደትን የሚያነፈንፈው ለሌላ ሳይሆን ሥልጣን ፍለጋ ነው፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በሚለው ጥንታዊ ብሒል ለስልጣን ያነጣጥራል፡፡ ወዳጆቼ … ሥልጣንን መፈለግ ሃጢያት ነው እያልኩ አይደለም፡፡
በአምስት ዓመት አንዴ እየተነሱ ጋብቻና ቅልቅልን የሙጥኝ ማለት ግን ሌላ ትርጉም የለውም።
እልም ያለ የስልጣን ጥመኝነት እንጂ! እናላችሁ … ለአዲሲቱ ጦቢያ ያፈጠጠ የስልጣን ጥመኝነት እንደማይረባት የህይወት ልምዳችን አስተምሮናል። ለአገራችን የሚያስፈልጉት ሥልጣን የሙጥኝ የሚሉት ሳይሆኑ ከስልጣን ውጭ የሚያስቡ ፓርቲዎች ወይም ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ (ከስልጣን ወንበር ውጭ የሚያስቡት!) ከምሬ እኮ ነው… ስለዲሞክራሲ ሥርዓት ማበብ፣ ስለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጐልበት፣ ስለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ስለ ነፃና ገለልተኛ የፍትህ ስርዓት መጠናከር እንዲሁም ስለ ስልጡን የፖለቲካ ባህል መዳበር አስበውና አልመው፣ እውን ለማድረግም የሚታትሩቱ ናቸው የሚያስፈልጉን!!
ከስልጣን ውጭ የሚያስቡ ፓርቲዎች… ከጥንቱ ኋላቀር ልማዳዊ አስተሳሰብ የወጡትን ነው በእጅጉ የምንናፍቀው፡፡ እኔ ስማርት ፓርቲዎች ብያቸዋለሁ፤ የስማርት ፎን ዘመን የገባቸው! ወጌን ከመቋጨቴ በፊት ለገዢው ፓርቲ፣ ለተቃዋሚዎችና ለምርጫ ቦርድ አንድ አንድ ማስታወሻዎች ጣል ላድርግ፡፡
ለተቃዋሚዎች - ኢህአዴግን ለማሸነፍ አንድ ወር ይበቃናል የሚለውን አጉል ትምክህት ትታችሁ በቅጡ ተዘጋጁ (የ2007 ምርጫ ከ97 ምርጫ ይለያል!)
ለኢህአዴግ - ምርጫ በመጣ ቁጥር ከተቃዋሚዎች ጋር የስነምግባር ኮዱን ካልፈረማችሁ የሚል ውዝግብ ትዝብት ላይ ከመጣል ያለፈ ትርፍ የለውም!
ለምርጫ ቦርድ - የቦርዱ ሃላፊ በአንድ ምርጫ ወቅት ፓርቲዎችን ሁሉ እንደልጆቼ ሳላበላልጥ ነው የማየው ያሉትን እንዳይዘነጉ (እሳቸው ቢረሱትም እኛ አንረሳውም!)

No comments: