ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
"የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል"
ያባላል ድሮም ይባላል
ይዘለዝላል ይከትፋል
ብቻ እስከምጨርስ ድረስ፤ ሆድ ለሆድ ጊዜ ይሰጣል
ወተት አንጀት ነጥፎ ሲላብ
ሆድቃ ደርቆ ሆድ ስራብ
ተሟጦ አንጀት ላንጀት ስሳብ...........
የጣር ቀጠሮ ስንት ነዉ
ለሰዉ ልጅ ሰዉ ለምንለዉ
ላይችል ሰጥቶት ለምያስችለዉ
ስንት ቀን ነዉ ? ስንት ለት ነዉ ?........
የማዕዱ ወዝ ሳታጥጥ
አድባሩ አብዳ ሳትፈረጥጥ
ጥንብ ሳይተርፍ ሜዳ አይጥ
የቤት ድመት ሳታማምጥ
በእመቤቷ አስከሬን ብካይ
እሷም ዋይ ዋይ
ዉሻም በጌታ ስጋ ላይ
ቸነፈር በጣለዉ ስ ሳይ
አይ!...............
ስንት ቀን ትሁን የረሃብ አዋይ?.......
እስቲ እናንተ ተናገሩ፤ተርባችሁ የምታዉቁ
ከቸነፈር አምልጣችሁ፤ተርፋችሁ እንድሁ ሳታልቁ
ትንፋሽ ቀርቷችሁ እንድሆን፤ ያስችላችሁ እንደሆን ጥቂት
ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?.
ስንት ምልዓት? ስንት ለሊት?
ጥንብ አንሳዉ ሳይወርድ በፊት፤ ሳይሞዠርጣችሁ ጥፍሩ
በጣረ ሞት አክናፋቱ፤አንዣቦ በመቅሰፍት እግሩ
አንደበት ተርፍዋችሁ እንድሁ ሳትነግሩ ከምትቀሩ
ካስቻላችሁ ተናገሩ።
ቆሽት ሲቃዉ ላያጣጥር፤ሰቀቀኑ ሳያጋግል
እስትንፋስ ስልምልም ሳትል
ቀጠሮ ይሰጣል ረሃብ ለስንት ቀን ለስንት ያህል
ስንት ስዓት ነዉ የረሃቡ አቅሙ?
ለ'ኔ ብጠማ ትርጉሙ
የሁለት ፊደል ድምጽ ነዉ ራብ የሚሉት ከነስሙ
እንጂ የ'ኔ ብጠዉማ
የት አዉቆት ጸባዩንማ
ብቻ ሲነገር ይሰማል
ይህን ሁለት ፊደል ቃል.............
ቃሉማ ያዉ በዘለማድ፤ ይነገራል ይለፈፋል
ይተረካል ይዘከራል
ይደጋግማል ይተቻል
እንጂ እንኳን ጠባዩን፤ የራብ ዕድሜዉን የት ያዉቃል..........
እና እምታዉቁት ንገሩን፤እዉነት ራብ ስንት ቀን ይፈጃል?..........
በጣር አፋፍ ላይ ያልህ ሰዉ፤ ራብ እንደት ነዉ እምያዛልቅ
ለስንት ቀን ቀን ይሰጣል፤አንደበትክን ላይሸመቅቅ
ሸረሪት በልሳንህ ላይ፤ የድር ትብትቡን ሳይሰራ
ቁራና ቀበሮ በቀን፤ ከቀየህ ድባብ ሳይደራ
ጥንብ አንሳ ልጭር ሳይመጣ፤ቅምቡርስ ከጎጆህ ጣራ
እንደፍካሬ ኢየሱስ ቃል፤ በጣር ምጽዓት ሳትጣራ
አንደበት ሳለህ ተናገር
የምታዉቅ የራብ ነገር
አስከረንክ ከየጥሻዉ፤ተርፎ እንድሁ ሳይቀረቀር
ስንት ደቂቅ ስንት ፋታ፤ ቀጠሮዉ ስንት ትንፋሽ ነበር
ቆሽት አርሮ ሳይፈረፈር
ትናጋህ በድርቀት ንዳድ፤ ጉሮሮህ ሳይሰነጠር?........
የሆድ ነገር ስንት ያቆያል
ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?.
ስንት ምልዓት? ስንት ለሊት?
ስንት ስዓት ነዉ ሰቆቃዉ፤ስንት ደቂቃ ነዉ ጭንቁ
እስቲ እናንተ ተናገሩ፤ተርባችሁ የምታዉቁ
ስንት ያቆያል ስንት ያዘልቃል?..........
እዉነት ራብ ስንት ቀን ይፈጃል?
ጸጋዬ ገብረ መድህን
ጥር ፲፱፻፷፭
ዋልዲያ
ተርበዉ ለምያቁ ትሁንልኝ
No comments:
Post a Comment