Friday, June 19, 2015

ከሳሙኤል ወዲያስ ( ሄኖክ የሺጥላ )

ሳሙዔል

 ጩህ ላለው ጉሮሮ 
አልቅስ ላላው ካንጀት 
ይበቃ ነበረ የ-የኔ ሰው ገበሬ
 በሳት አሮ መሞት !

 በደል ለበቃው ሕዝብ
 መናቅ ለመረረው
 የባልቻ መታረድ ፣ ምን ሲል አስፈለገው ? 
የስክንድር መታሰር
 የርዮት እንግልት
 ያስነሳን ነበረ ፣ ሰው ብኖሆን ባንድነት ።

 የሸዋስ ፣ ተመስገን ፣
 አንዷለም ሀብታሙ
 ስለምን ታሰሩ ፣ 
ስለምን ስለ-ማን 
የመከራ ገፈት ዛሬም ይቀምሳሉ? 
 ብለን የምንጠይቅ ሰዎች ሆነን ቢሆን
 ህሊና ቢኖረን ፣
 እንደሰው ብናስብ 
በምኑም በምኑም ሰበብ ባንሰበስብ
 ይህ አይሆንም ነበር የኛ ታሪካችን
 ቀና ብለን ነበር እኛም ባገራችን ።


 የሸዋስ ሲታሰር ፣ አንዷለም ሲገረፍ
 መስከረም ጠብቶልን ፣ ዓመት ዓመት ስንድረስ 
ቃላት ስንደረድር ፣ ስብሰባ ስንጠራ
 እንደ የኪስ ሌባ ተገርፈን ስንገባ
 ሰብስበው ሲያንጫጩን 
እርስ በርስ ሲያጋጩን 
በጎሳ ና በዘር እንደ አርማታ ድንጋይ
 ለማነስ ስያፋጩን ፈልገን ነው እንጂ ፣
 መረገጥ ወዶልን ቢሻለን ነው እንጂ ፣ 
መዋረድ ሰምሮልን ይበቃን ነበረ ፣
 በቃን ብለን ብንል ። 

 ዘጠና ሚሊዮን አፉ ተለጉሞ 
ነብሱ የጭንቀት ጏዳ 
ደሙ "ብርክን " ወልዳ 
አያልቅም ፍርሃቱ ቢቀዳ ቢቀዳ 
አይ ያበሻ ዕዳ!!!

 ጏደኞቹን ቀብሮ 
እናትና እህቱን ዛሬም አሳስሮ
 ከአምናው ፍርሃቱ ዘንድሮም ተምሮ
 በታመቀው ድምጹ ራሱን አፍኖ
 ይኖራል ሀበሻ በማነሱ ገኖ !

 ሳሙዔል ቢገደል ፣ ሐበሽ ቀባሪ ነው 
ድንኳኑን ሰባሪ 
ካርታ እየፐወዘ ፣ ተረት ተረት አውሪ !

 አንድ ሳጥን ኮካ ፣ አንድ ድስት ምንቸት
 የዝን ነው ጥይቱ ፣ ለሞተው ወንድሙ ወንዱ የሚቆጭበት! 
ገደሉት እያለ ከንፈር መምጠጥ እንጂ 
በለቅሶ መፈንዳት ፣ እሪ ማለት እንጂ
 የሀበሻ መዳፎች ረስተዋል ፈንጂ ! 

ይልቅስ ያወራል 
የአከሌ ቀብር ላይ እኔም ነበርኩ እኮ 
አፈር ካለበሱት ፣ አንዱ እኔ ነኝ እኮ 
" ቀበር አትሄድም ወይ !?" 
ይልሃል ሀበሻ 
ለቅሶ አትደርስም ወይ 
ይልሃል ሀበሻ 
ቀብር እና ለቅሶ ሆኖ የሱ ጥሻ ! 

ታዲያ ሳሙዔል ቢሞት ፣ ምኑ ነው እሚገርመው 
ወንድሙ በደሉ ፣ ሞቱ ካላመመው ። 

እስክንድር ቢታሰር ፣ አንዷለም ቢሰቃይ 
የሀበሻ ወንድ ልጅ ፣ ተደፍኖበት ሰማይ 
ባህር የቧጥጣል ፣ ሊወጣ ወደላይ ! 

ታዲያ ምኑ ይገርማል ፣
 ምርጫው ቢጭበረበር 
ምኑ ነው የሚገርመው ፣ 
ሀብታሙ ቢታሰር 
ሞቶም " መኖር ደጉ " እያለ ለሚኖር
 ለእንደዚህ አይነት ሕዝብ ፣
 ምኑስ ነው የሚገርም ?

 ከሳሙኤል ወዲያስ ከሞቱ ባሻገር
 ካለፈላት ሀገር
 ከሞተለት ፍቅር 
 ከሱ ወዲያ ምንድን 
ምንም ካልተሰማን ፣
 ካልተነሳን በቀር አንገት ለመቆልመም ፣ 
ነብስ ለመቀርቀር ከሆነ ድንኳኑም ፣ 
መቀበሩም ይቅር !

 ከሳሙኤል ወዲያስ 
ስንት ወጥተን እንቅበር 
ስንቱን እናሳስር
 ስንቱን እናስገድል? 
ለስንቱስ እናልቅስ 
ስንቱንስ እንቅበር ?
 ካልበቃን ፣ ዘንድሮ ባንድ ላይ ካልሞትን 
ባንድ ላይ ባንድነት ፣ 
ሄኖክ የሺጥላ
ሞት ጋልተጋፈጥን የጀግና ሰው ሞቱ ፣ 
የዜና ማድመቂያ የውይይት መድረክ ፣ 
ድንኳንን ማሞቂያ የሚሆን ከሆነ 
ከሳሙኤል ወዲያ ፣ 
ሞቱ የማይከፈል ሺ ሳሙዔል አለ !
 ስለዚህ ጥያቄው

 ከሳሙኤል ወዲያስ ምን መሆን አለበት አንገቶች ይቃኑ ፣
 ከተመሸጉበት ድምጾች ድምጽ ይሁኑ
 ከተዳፈኑበት ጉልበቶች ይበርቱ ፣ 
ክንዶች ይፈርጥሙ ሳሙዔል ይነሳ ፣ ይሁን ዲበ- ኩሉ !

 ከሳሙኤል ወዲያ ምንድን ነው ዕጣችን የሚለው ነገር ነው ፣
 የኛ ፈተናችን ትልቁ ጥያቄ ፣ 
ትልቁ ጭንቃችን ደፍረን ካልመለስነው ዙሮ ዙሮ ያው ነው !

 ከሳሙኤል ወዲያስ ( ሄኖክ የሺጥላ )



ሄኖክ የሺጥላ/Henoke Yeshetlla 


No comments: