
- ኢትዮ-ቴሌኮም በኖኪያ ቁጥጥር ስር የነበሩ የኔትዎርክ ወረዳዎችን ነፃ አወጣ!
- አንድነት እና መኢአድ ሳይጋቡ በመፋታት ሪከርድ ሰብረዋል
- “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ትዝ የሚላቸው ምርጫ ሲቃረብ ነው
የአፍሪካ አንድነት የሰላም አስከባሪ ኃይልን የተቀላቀለው የአገራችን መከላከያ ኃይል ሶማሊያ ውስጥ አልሻባብ ተቆጣጥሯቸው የነበሩትን ቦታዎች ማስለቀቁን በኢቴቪ ዜና እወጃ ላይ ሰምቼ ደስ ብሎኝ ነበር (ኢትዮጵያዊ ሆኖ ድል የማይወድ አለ እንዴ?) በነጋታው ነው መሰለኝ … ሌላ የምስራች ደግሞ ሰማሁ፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም በኖኪያ ቁጥጥር ስር የነበሩትን አየር ጤና፣ ቄራና ዓለም ባንክ አካባቢዎች ነፃ ማውጣቱ ተነገረ-በዜና ሳይሆን በተባባሪ ወሬ፡፡ እናላችሁ …. ሁለቱ አካባቢዎች አሁን ኔትዎርካቸው ያለመቆራረጥ እየሰራ ነው፤ ተብሏል (ኢንተርኔትና ፌስቡክም ያለችግር ማግኘት ችለዋል) ኢትዮ-ቴሌኮምን የማሳስበው ግን በዚህ የድል ብስራት ተኩራርቶ ሌሎቹን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የኔትዎርክ ወረዳዎች ነፃ ከማውጣት እንዳይዘናጋ ነው። ያለዚያ እኮ የሦስቱ አካባቢዎች ነፃ መውጣት ትርጉም የለውም (ተመልሰው በ“ጠላት እጅ” ሊወድቁም ይችላሉ!) እናላችሁ … ሌሎች የመዲናዋ አካባቢዎችም ከ “ባዕድ እጅ” ነፃ ሲወጡ ነው እነ ዓለም ባንክ ነፃነታቸውን በቅጡ የሚያጣጥሙት፡፡ እስከዛ እኮ እርስ በርስ ብቻ ነው ኮሙኒኬሽኑ!