Monday, May 25, 2015

ይድረስ ለኢትዮጵያ............

ዲዮጋን

ሰዉ ፍለጋ ከቤት ወጥቶ
እጅግ ብዙ ተንከራቶ
ተመለሰ ከቤቱ
ሰዉ ጠፍቶ ባገሪቱ።
                አዘርግ(2003 e.c)

ሌቱን ሙሉ ኣሰብኩ፣በጣም አሰብኩ፣ በመጨረሻም፣ከቤቴ ወጣሁ፣አዲስ አበባን በእግሬ እየኳተንኩ ቃኘዉ  አእምሮዬ ላይ የጥያቄ ክምር ተከማችቷል።መጠየቅ የምፈልገዉ ደግሞ ኢትዮጵያን ነዉ እናም ጀመርኩ.............

እኔማ ሰምቸ ነበር ይህች ኢትዮጵያ የምትባል ምድር እንኳን ለህዝቦችዋ በግዛትዋ የሚያልፍ አዉሮፕላኖች ይባረካሉ!

እኔማ ሰምቸ ነበር ዓለም ባንድ መሪ የምትመራበት ዘመን ይመጣል ! ያኔ በዓለም ላይ የበዛ ሰላም፣ የበዛ ጤና፣ የበዛ መተሳሰብ፣ የበዛ ፍቅር፣የበዛ አንድነት ይሆናል ጦርነት ፣ጥል ፣ጥላቻ ፣ዘረኝነት ፣ርሀብ ምቀኝነት ፣መነቋቆር  ይወገዳል!  ያ መሪ ደግሞ ከኢትዮጵያ ነዉ!

እኔማ ሰምቸ ነበር ቅድስትቷ ምድር በታላቁ መፅሐፍ ቅዱስና ቅዱስ ቁርዓን*  በርካታ ጊዜ በመጠራት ካለም አንደኛ ናት።ይህ ደግሞ ለምክንያት ነዉ። ምክንያቱም ያነ የኢትዮጵያ ዘመን ስመጣ ያለም ህዝብ ሁሉ የኢትዮጵያን ቋንቋን** ይናገራል።

እኔማ ሰምቸ ነበር ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግር ት ዘረጋለች  ያነ ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ ይሆናል፤ተራራዉ ሜዳ፤ደረቁ ለምለም፤ ችጋሩ ጥጋብ፤ለቅሶዉ ፌሽታ፣ሰላም ማጣት ሰላም ማግኘት ይሆናል!

እኔማ ሰምቸ ነበር ያነ ዘመን ለኢትዮጵያ ስመጣ በመላዉ ዓለም ዉስጥ ያሉ የኢትዮጵያን መሬት ለመርገጥ 24 ሰዓት ያልማሉ፤ይተጋሉ  ለፈጣሪያቸዉ 'ፈጣሪ ሆይ የኢትዮጵያን መሬት ሳልረግጥ አትግደለኝ' እያሉ ይፀልያሉ ፣ ይማልዳሉ!

እኔማ ሰምቸ ነበር እነ አክሱምን እነ ላሊበላን እነ ፋሲለደስን የገነቡት ጠቢቦች ወደፊት የዓለም ስልጣኔ መነሻ ምንጭ ይሆናሉ በመሬት ሆነ በህዋ የእድገት ማማ ላይ ይሰቀላሉ በሁሉ ነገር የበላይ ይሆናሉ። የኢትዮጵያ ባንዲራ በጨረቃ ላይ በማርስ ላይ ይሰቀላል፤ይዉለበለባል  አረንጓደ ፣ቢጫ ፣ቀይ አርማዉ ከፍ ይላል ወጥቶ ከማማዉ

እኔማ ሰምቸ ነበር ኢትዮጵያ በሥነ ጥበብ ሆነ በሥነ ህይወት ሆነ በኪነ ጥበብ የዓለም ቆንጮ ት ሆናለች!

እኔማ ሰምቸ ነብር ዓለም በየሁለት ዓመቱ ታላቅ የሀገሪቱ መሪዎችን የስልጣን ገደብ የምታስቀምጥ ብቸኛዋ ሀገር ት ሆናለች!

......ብዙ ሰምቻለሁ፤ነገር ግን........


እማማ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ የኔ መመኪያ !ግን ለምን ይሁን ወጣቶችሽ በሱስ ተተብትበዉ ዉጪ ሀገራትን የሚያልሙት ?
ለምን ይሁን እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባዮች የበዙት?
ለምን ይሁን ሁለ ችግር ጉስቁልና ምሳሌ የሚያደርጉሽ?
ለምን ይሁን በህዝቡ ዉስጥ ፍርሀት የነገሰዉ?
ለምን ይሁን አንዱ መሪ የጀመረዉ ቀና ነገር ሌላዉ መጨረስ አቅቶት ሁሌ ካዲስ የሚጀምሩ?
ለምን ይሁን ከራስ ወዳድነት እና ራስን ከማስቀደም በሽታ ወጥተን ታላቋን ኢትዮጵያ ሀገር ትቀድማለች ማለት ያቃተን?
ለምን ይሁን ከሰሜን ነኝ ስልጣን ለኔ ከደቡብ ነኝ ስልጣን ለኔ ይምንለዉ?
ለምን ይሁን ወጣቶችሽ የወጣትነት ዘመናቸዉን በሱስ የሚያጠፉት፣ታላላቅ ምሁራኖችሽ እዉቀታቸዉን ለፈረንጅ ሀገራት የሚገብሩት፣ሴት ወጣቶችሽ ጉልበታቸዉን ላረብ ሀገራት የሚገብሩት፣በመሪዎችሽ መሃከል ከልብ የመነጨ የጠበቀ አንድነት የሌለዉ?
ለምን ይሁን በምድርሽ ላይ ሰዉ ሲሞት ብቻ ክብር እንድሰጠዉ እንጂ በህይወት ዘመኑ  የሚያደርግ ባህል የሞላሽብን?
ለምን ይሁን በህዝቦችሽ ላይ ጥርጣሬ፣ግራ መጋባት፣ፍርሀት፣ቶሎ ተስፋ መቁረጥ፣ባዶ፣ባዶ፣ባዶ፣ባዶ፣ባዶ የሞላሽብን?
ለምን ይሁንሞራላችን ቦግ ብሎ ወዲያ ድርግም ሞቅ ብሎ ወዲያዉ ቅዝቅዝ እችላለሁ ብሎ ወዲያዉ በጥርጣሬ መሞላት ሲስቁ መሳቅ፣ሲያለቅሱ ማልቀስ፣ስያጨበጭቡ ማጨብጨብ፣ስቦጭቁ ሞቦጨቅ የ   መ   መ   ሳ  ሰ  ል  ባህልን ለምን ይሁን የሞላሽብን?
ለምን ይሁን ታዋቂዎች፣የሀገር ባለዉለታዎች፣የሀገር አረያዎች፣ታላላቅ ምሳሌዎች ሲሞቱ ለቀናት ከንፈር እንመጥና ፣ለቀናት የቃለ መሀላ ዉርጅብኝ እናደርግና፣ለቀናት ዉስጣችን ይነሳሳና፣ ለቀናት በታይታና መመሳሰል እንሞላና ልባችን በሀዘን ይሰበርና ....? ተይዉ ብቻ እማማ ኢትዮጵያ  የማያልቁ ጥያቄዎች ላንቺ ነበሩኝ ፈራሁኝ አትመልሽልኝም ብዬ ተጠራጠርኩ
አንቺ ራስሽ ነሽ የሞላሽብኝ  ስለዝህ እናት ሀገሬ ኢትዮጵያ ጠቢቡ
"ኢትዮጵያን የምትወዳት ከሆነ በብስጭት ትሞታለህ!"
እንዳለዉ ቶሎ መሞት አልሻምና የጥያቀዬን ክምር እንደያዝኩ ቤቴ ተመለስኩ፣ተኛዉ። መተኛትንም የተማርኩት ካንች ነዉ።
ግና በነጋታዉ ስነሳ አእምሮዬ ላይ
"ካልደፈረሰ አይጠራም ካልከረረ አይበጠስም!!"
የሚል ጥቅስ አንቃጨለብኝ በተስፋ ተሞላሁ
ተስፋ ማድረግን የመሰለ ምን ታላቅ ነገር አለና?

ያንቺዉ ታዛቢሽ ልጅሽ 
ጌታቸዉ ካሳሁን

ኢያርኮ 999(ገፅ 146-148)

*ከራሰ ያከልኩት  ነዉ ደራሲዉ መፅሐፍ ቅዱስን ብቻ ነዉ የጠቀሰዉ
**ይህንም ከራሰ ያከልኩት  ነዉ ደራሲዉ አማርኛ ቋንቋ ነበር ያለዉ

ኻዮሉማ/xayouluma

No comments: