Monday, April 1, 2013

ሃሎ ክቡር ሚኒስትር?

-    ሃሎ ክቡር ሚኒስትር?
-    እንዴት ነህ ደህና ነህ?
-    ወሩን ሙሉ’ኮ ተጠፋፋን፡፡
-    እንግዲህ መጀመርያ አራታችንም የየራሳችን ጉባዔ ስናካሂድ ነበር፡፡ ከዚያም የኢሕአዴግ ጉባዔ በባህር ዳር ተካሂዶ እዚህም እዚያም ስል አልተመቸኝም፡፡
-    በቃ አሁን አዲስ አበባ ስለመጡ እንገናኝና ያቺን ጉዳይ እንጨርሳት፡፡
-    እ - - - ?
-    ስልኩ አይሰማም ክቡር ሚኒስትር?
-    እ - - - ?
-    በቃ አይሰማም ክቡር ሚኒስትር - በአካል ቢሮዎ እመጣለሁ፡፡
-    አትምጣ ቆይ እኔ እደውልልሃለሁ፡፡
-    ጊዜ የለማ - ሰዎቹ ሁሉንም ነገር አዘጋጅተዋል፡፡ የት እናስገባው እያሉ ናቸው፡፡ ዛሬ እንጨርስ እያሉ ናቸው፡፡ ማታ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ፡፡ ዕድሉ እንዳያመልጥዎ ቢቀበሉዋቸው ጥሩ ነው፡፡ ካልናቸው እጥፍ ነው ያዘጋጁት፡፡ ያውም በውጭ ምንዛሪ፡፡
-    በቃ በቃ በስልክ አታውራ፡፡ ለምሳ እኔ ቤት እንገናኝ፡፡
-    እሺ - ቤት እመጣለሁ፡፡
[ቤት ተገናኙ ወሬ ቀጠሉ]

-    ምነው ድምፅዎ ተቀየረብኝ፡፡ እርስዎ አጠገብ ሰው ነበር እንዴ? በስልክ ማውራት አልፈለጉም ነበር ልበል?
-    በአሁኑ ጊዜ ጠንቀቅና ቆጠብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
-    ምን አዲስ ነገር ተገኘ?
-    በጉባዔው አንዳንዱ ሰው የቡድን ሙስናን መዋጋት አለብን እያለ ማካረር ጀምሯል፡፡
-    ታዲያ እንደኛ ዓይነቱን ልማታዊና የቅርብ ወዳጅ ላታስጠጉ ነው እንዴ? እኔ እንዲያውም በእንግድነት ጉባዔው ውስጥ መገኘት ነበረብኝ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደ ባለሀብት ማለቴ ነው፡፡
-    ተው ተው እንኳን አንተ ልትጨመር ሌሎች ሰዎች እዚያ በመገኘታቸው ከፍተኛ ቅሬታና ጥያቄ ተነስቷል፡፡
-    ምን የሚል ቅሬታ?
-    ጉባዔው ላይ ምን ሊያደርጉ መጡ? ማን ጋበዛቸው? ብለው አንዳንዶቹ ከፍተኛ ቅሬታ አሰምተዋል፡፡
-    ክቡር ሚኒስትር ካሉስ በቴሌቪዥን ምሥላቸውን ያየ እዚህ ያለው ሕዝብም በጣም አዝኗል፡፡
-    አዝኗል?
-    አዎን አዝኗል ክቡር ሚኒስትር፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ አምስቱ የኢሕአዴግ ድርጅቶች ተሰባሰቡ እያሉ ይቀልዱ ነበር፡፡ በመገኘታቸው ብቻ ሳይሆን በአቀማመጣቸው ፕሮቶኮልም ያልተገረመና ያላበደ የለም፡፡
-    ለመሆኑ ሕዝቡ ይከታተል የነበረው ኳሱን ነው ፖለቲካውን?
-    ኳሱም’ኮ ፖለቲካ ሆኖ ነበር፡፡ እዚያም እንዴት ነው ነገሩ ያሰኘ ፕሮቶኮል አይቶ ገርሞታል አዝኗል፡፡
-    ለምን ያዝናል?
-    ያየውን አይቶ ቢያዝን ምን ይገርማል? ባለሥልጣኑ ሁሉ ምን ሆነ? አያሳፍረውም? አይከብደውም? እያለ ነው ያመሸው፡፡ የኳስ ፍልሚያው የፖለቲካ ፍልሚያ አስከትሎ ነበር፡፡ በተለይም ያን አይቶ እንደገና ይህን ሲያይ ‹‹የበላይ አካሉ ማን ነው?›› የሚል ወሬ እንዲዛመት አድርጓል፡፡ ብቻ ክቡር ሚኒስትር ወደ መጣሁበት አጀንዳ እንግባ፡፡
-    የመጣህበት አጀንዳም’ኮ የፖለቲካ ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡
-    ለእርስዎም ለቤተሰብዎም የሚጠቅም ትልቅ ዕድል’ኮ ነው፡፡ የሕይወት ዋስትና አገኙ ማለት ነው፡፡ ብዙ ነው በቂ ነው፡፡ ይጨርሱላቸው፡፡
-    እነዚያ ሙስናን እንዋጋ የሚሉ ሰዎች እንዳይከታተሉን ፈርቼ እኮ ነው፡፡ የባለሥልጣንን ኪራይ ሰብሳቢነት እንዋጋ የሚል ኃይል ተፈጥሮአል፡፡ ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
-    ልዩ ጥንቃቄውም ይሁን፡፡ የሚደረግልዎት እዚህ ከሚሆን ውጭ አገር ይሁን፡፡ በእርስዎም በባለቤትዎም ከሚሆን በሌላ ዘመድ ይሁን፡፡ በዶክመንት ከሚደገፍ በመተማመን ይሁን፡፡
-    እኔ’ኮ ነገሩ እየተካበደ መሆኑን ልንገርህ ብዬ ነው እንጂ ይቅርብኝ ማለቴ አይደለም፡፡ ይህም ሳይቀርብን ለጥቃትም ሳንጋለጥ እንዴት እንሥራው ማለቴ ነው፡፡
-    እሱን ለእኔ ይተውት፡፡ እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ፡፡
-    በል እንግዲያውስ ሁሉንም ነገር በዚህ ሳምንት እንጨርስ፡፡
-    እሺ ክቡር ሚኒስትር ሁሉንም በዚህ ሳምንት፡፡
-    ቻው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሰዓት በኋላ ቢሮ እንደገቡ አንድ የውይይት መነሻ ሐሳብ የሚል ሰነድ እንደታሸገ ጸሐፊያቸው ሰጠቻቸውና ካነበቡ በኋላ ደወሉ]
-    አቤት ክቡር ሚኒስትር?
-    ከጽሕፈት ቤቱ የተላከ ነው የሚል አንድ ረቂቅ ዶክመንት አይቼ ነው፡፡ ከእናንተ ነው የተላከው?
-    አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡ የተወሰኑ የሥራ አስፈጻሚ አካላት ተሰባስበው ያወጡት ሙስናን መዋጋት ያስችላል የሚል ረቂቅ ሐሳብ ነው፡፡ በኋላ ውይይት ይደረግበት ብለው ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል፡፡
-    እ - እሺ፡፡
-    አይተውታል አይደለም በደንብ?
-    አይቼዋለሁ፡፡ ከግለሰቦች በስጦታም ሆነ በሌላ መንገድ ከአንድ መቶ ብር በላይ መቀበል ክልክል ነው ይላል፡፡
-    የሕክምናውንስ አዩት?
-    አዎን አይቼዋለሁ፡፡ መንግሥት በጀት ስለመደበ ከመንግሥት ገንዘብ ወጭ ከግለሰቦች ገንዘብ፣ ስጦታም ሆነ መጓጓዣና መታከሚያ መቀበል ክልክል ነው የሚልም አለበት፡፡
-    እሱን አላስተዋልኩትም ነበር፡፡
-    አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡ በሰው ገንዘብ ልጆች ውጭ አገር ልኮ ማስተማር፣ ራስን በነፃ በየሆቴሉ በሰው ገንዘብ ማዝናናት፣ ለዕረፍት መሄድ፣ ወዘተ ክልክል ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ በመንግሥት ይሸፈናል ይላል፡፡
-    እ - - - ?
-    ከበደዎት ክቡር ሚኒስትር?
-    እ - እኔ ንፁህ ነኝ ችግር የለብኝም፡፡
-    እንትኑንስ አዩት ክቡር ሚኒስትር?
-    ምኑን?
-    በሚኒስትር መሥርያ ቤቶች የተወሰኑ ውሳኔዎች ከሙስና የፀዱ መሆናቸውን መገምገም፣ ማጤንና ሪፖርት ማቅረብ የሚለውን፡፡
-    ቆይ ቆይ በዚያ ዓይን አላየሁትም ነበር፡፡ የወደፊቱን ነው ያለፈውንም?
-    ለወደፊቱ በጭራሽ የተለከለከለ ነው ይላል፡፡ ያለፈው ሪፖርት ደግሞ ይቅረብ ይላል፡፡
-    እ - እሺ፡፡
-    ሁሉም በዚህ ተስማምተዋል ማለት ነው?
-    ገና ነው’ኮ አንዳንዱ እንዲያውም ቅር ያለው አለ፡፡ ነገር ግን አገር በሙስና ስለተዘፈቀ ሕዝብንና አገርን ማገልገል ካለብን ራሳችንን ማፅዳት የግድ ነው የሚሉ ወገኖች እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
-    እ - እሺ - ቻው፡፡
[በአንድ በኩል በዚህ ሳምንት ጉዳዩን ጨርሰው ስለሚያገኙት ገንዘብ እያሰቡ፣ በሌላ በኩል ስለተፈጠረው ፀረ ሙስና እንቅስቃሴ እያሰቡ እንደተረበሹ ቤት ገቡ፡፡ ባለቤታቸው ጥያቄ አነሱ]
-    ምነው ፊትህ?
-    ምን ሆነ ፊቴ?
-    በሐሳብ የተወጠረ ይመስላል፡፡ በግልጹ ንገረኝ፡፡ ባለፈው ሰሞን አንድ ትልቅ ተስፋ ይዘህ ትልቅ ገንዘብ እንደምናገኝ ነግረህኝ ነበር፡፡ የት ደረሰ? ከሸፈ እንዴ?
-    አልከሸፈም፡፡ በዚህ ሳምንት ያልቃል፡፡
-    ጐሽ - እዚያው በእኔ ስም ይግባ፡፡
-    እስቲ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
-    የምን ጥንቃቄ?
-    እንዳይከታተሉን፡፡
-    እነማ?
-    ሙስናን እንዋጋለን! ሙስናን እናጠፋለን! ኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ጠላታችን ነው! የሚሉ፡፡
-    ማን ናቸው?
-    ምን ማን ናቸው?
-    አባላት ወይስ መላዕክት?
-    እኔ ጨንቆኛል አንቺ ትቀልጂያለሽ፡፡
-    ለምን ይጨንቅሃል? የጀመርከውን ጨርስ ይጠቅምሃል፡፡
-    መጨረሻውስ?
-    እንዴት መጨረሻውስ? አልገባኝም?
-    ተከታትለው ከያዙን መጨረሻችን ቃሊቲ ሊሆን ይችላል፡፡
-    አይዞህ ተከታትለው የሚያውቁትና ተከታትለው የሚያመጡት ነገር አይኖርም፡፡ ምን እንደተደረገም ፍንጭ አያገኙም፡፡
-    ስላለፈው ሁሉ ሪፖርት አቅርቡ ተብለናል፡፡
-    ታዲያ ሪፖርት አቅራቢው አንተ ራስህ ስለሆንክ ምን ችግር አለ? እንደሚጥምህ ሪፖርቱን አቅርብ፡፡
-    ይቻላል?
-    ምን ማለትህ ነው ይቻላል ስትል?
-    ስንቱ ተደብቆ ይቻላል ማለቴ ነው?
-    ምነው ተግደረደርክ ጠንከር በልና ያን ነገር አምጡ በላቸው፡፡
-    እሱንማ መቀበሉን ፈራሁ እንጂ አምጥተውታል፡፡ አዘጋጅተውታል፡፡ ያ የምታውቂው ሰውዬ ተከታትሎ እያስጨረሰው ነው፡፡
-    እሱን ሰውዬ አልፈልገውም፡፡ ባለፈው ጊዜ አሥር ሚሊዮን ለራሱ ወስዷል፡፡
-    እንዴት አወቅሽ?
-    ውጭ ይገባላችኋል ከተባለው ገንዘብ አሥር ሚሊዮን ጐድሎ ለምን ብዬ ስጠይቅ የአገናኘኋችሁ ክፈለን ስላለ አሥሩን ለእሱ ሰጥተናል አለኝ፡፡
-    አላወቅኩም ነበር፡፡
-    ያለፈው አልፏል፡፡ አሁን አታስጠጋው፡፡
-    ይሻላል?
-    በቃ አንፈልገውም እኔ ራሴ አለሁ፡፡ ከእኔ ጋር ይገናኙ፡፡ ግማሹን የሚወስድበት ምክንያት የለም፡፡ ገባህ?
-    እሺ፡፡
-    ገባህ? አታቅርበው አታስጠጋው፡፡ እጅህን አውጣ በለው፡፡
-    እሺ፡፡
[የሚስታቸውንም፣ የሰውዬውንም የድርጅታቸውንም ነገር እያሰቡ ሳይተኙ አድረው ነበር በጠዋት ቢሮ የገቡት፡፡ ጸሐፊዋ ወዲያው ገባች]
-    እሺ?
-    አንድ ሰውዬ ስልክ ብደውል ብደውል አላነሳ ስላሉ ለእሳቸው የሚጠቅም ጉዳይ ነው አስገቢኝ ብለው ጨቀጨቁኝ፡፡
-    አስገቢው (ገባ)፡፡
-    እንዴ አንተ ነህ እንዴ?
-    ምነው ከትናንት ማታ ጀምሮ ብደውል ብደውል አላነሳ አሉ? አንድ ሚሊዮን ዶላሩን አዘጋጅተዋል፡፡
-    በቃ አንተ ከዚህ ነገር ውጣ ተወው፡፡
-    እንዴት ተወው ክቡር ሚኒስትር?
-    ባለፈው አሥር ሚሊዮን ብር ወስደሃል አሉ፡፡
-    ድሮስ በነፃ ነው ወይ የምሠራው?
-    አንተ ባለሀብት አይደለህም ወይ?
-    ባለሀብት ብሆንም’ኮ ሀብቱ የመጣው በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ነው፡፡
-    ያለፈው አልፏል፡፡ በቃ አሁን ውጣ ተወው፡፡
-    ገንዘቤስ?
-    የምን ገንዘብ?
-    ከአንድ ሚሊዮን ዶላሩ ግማሹን!
-    አይመለከትህም፡፡
-    በቃ ክቡር ሚኒስትር እኔ ውጭ አገር እሄዳለሁ፡፡ እዚያ ሆኜ በዶክመንት አስደግፌ ለመንግሥት እልካለሁ፡፡
-    እኔን ለማጋለጥ! ለማስጠቃት! ለማሳሰር!
-    ምርጫው የእርስዎ ነው፡፡ ወይ ጥቃቱን ወይ ግማሹን፡፡
[በመሀል ስልክ ተደወለ]
[ከባለቤታቸው ነበር]
-    ነገርከው?
-    ምን?
-    ከዚህ ጉዳይ እጁን እንዲያስወጣ፡፡ አሁንም ግማሹን ልውሰድ ሊል ነው?
-    እንደዚሁ በቀላሉ አትይው፡፡
-    ስማኝ!
-    እየሰማሁ ነኝ ውድ ባለቤቴ፡፡
-    ምረጥ!
-    ምን ልምረጥ?
-    ወይ እኔን ወይ እሱን!
[በመሀል ሌላ ስልክ ተደወለ]
-    አቤት?
-    ደህና አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
-    ደህና፡፡
-    ከጽሕፈት ቤቱ ነኝ፡፡ ሪፖርቱን አዘጋጁ፡፡ በአስቸኳይ ነው የሚፈለገው፡፡
-    የምን ሪፖርት?
-    በመሥርያ ቤትዎ በኩል እስካሁን የተፈጸሙ ሙስናዎች ግምገማ ሪፖርት፡፡
-    እኔ ማዘጋጀቱ አልታየኝም፡፡
-    ግዴታ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ ሙስናን ለመዋጋት የመንግሥት ሁኔታን መገምገም አለብን፡፡
-    እ - - - ?
-    ስሙኝ ክቡር ሚኒስትር የረቂቅ ደንቡ ውይይት በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል፡፡ ሪፖርቱ ከዚያ በፊት ያስፈልጋል፡፡
-    በዚህ ሳምንት ለሕክምና ውጭ እሄዳለሁ፡፡
-    ሊሄዱ አይችሉም፡፡ የመንግሥት በጀት መቼ ተለቀቀለዎትና?
-    የምን በጀት?
-    ለሕክምና የሚሆን፡፡ ከአሁን በኋላ መንግሥት ነው የሚሸፍነው፡፡ ከባለሀብት ክልክል ነው፡፡
-    እና?
-    እናማ ክቡር ሚኒስትር ሪፖርት ያቅርቡ፡፡ ለስብሰባው ይዘጋጁ፡፡ እንደሚናፈሰው በጥብቅ ከሚገመገሙት ባለሥልጣናትና ተቋማት አንዱ የእርስዎ መሥርያ ቤትና እርስዎ ይሆናሉ፡፡
-    ምነው አማራጭ የሌለን አስመሰልከው?
-    አማራጭማ አለዎት፡፡ የሚያምር አማራጭ አይሆንም እንጂ?
-    ምንድን ነው አማራጩ?
-    ወይ ክብር ወይ እስር!

No comments: