Monday, April 1, 2013

‹‹የአገሬ ፕሬዚዳንት መሆን እችላለሁ ብዬ መናገሬ በራሱ ትልቅ ነገር ነው›› ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ የፓርላማ ብቸኛው የግል ተመራጭ

‹‹የአገሬ ፕሬዚዳንት መሆን እችላለሁ ብዬ መናገሬ በራሱ ትልቅ ነገር ነው›› ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ የፓርላማ ብቸኛው የግል ተመራጭ

የቀድሞው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ በምርጫ 2002 ዓ.ም. ተወዳድረው በማሸነፍ በፓርላማ ብቸኛ የግል ተመራጭ ናቸው፡፡
በፓርላማው ውስጥም የሳይንስ፣ የመገናኛና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮ ጀርመን ወዳጅነት ኮሚቴን በምክትል ሊቀመንበርነት ይመራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል ሲሆኑ፣ በወቅታዊ አገራዊና አኅጉራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የማነ ናግሽ ዶ/ር አሸብርን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2002 ዓ.ም. በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ ተቀናቃኝዎን አሸንፈው የፓርላማ አባል ከሆኑ ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ፓርላማው በአግባቡ እየሠራ አይደለም ይባላል፡፡ በተለይ ደግሞ የሳይንስ፣ የመገናኛና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢነትዎን እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር አሸብር፡- እንደ ምክር ቤቱ አባል ፓርላማው በአግባቡ እየሠራ ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ በእኛ ቋሚ ኮሚቴም ተጠሪነታቸው ለእኛ የሆኑት ሚኒስትር መሥርያ ቤቶች ለእኛ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ እንደ የኢትዮጵያ ጨረር መከላከያ፣ ደረጃ መዳቢዎች፣ አዕምሮአዊ ንብረት የመሳሰሉት ተጠሪነታቸው ለእኛ ነው፡፡ የእነሱን ሪፖርት እናዳምጣለን፡፡ ዕቅዳቸውንም እናያለን፡፡ መሻሻል ያለበትን እንጠቁማለን፡፡ የሩብ ዓመት፣ የስድስት ወራት እንዲሁም የአንድ ዓመት ክንውናቸውንም እንገመግማለን፡፡ ግብረ መልስም እንሰጣቸዋለን፡፡ ጠርተን እናነጋግራቸዋለን፡፡ አንዳንዴም ‹‹ሰርፕራይዚንግ ቪዚት›› (ድንገተኛ ጉብኝት) እናደርጋለን፡፡ መደበኛ ሥራም እንሠራለን፡፡ ሌላም በምክር ቤት ደረጃም መደበኛም አስቸኳይ ስብሰባዎችም አሉን፡፡ ይኼ እንግዲህ ዕቅድ ተይዞለት ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ ምክር ቤቱ ሥራውን እየሠራ ነው፡፡


ሪፖርተር፡- ምክር ቤቱ በአግባቡ እየተሰበሰበ አይደለም፡፡ መሰብሰብ ካለበት 18 ስብሰባዎች ስድስት ጊዜ ብቻ ነው የተሰባሰበው የሚባል ነገር አለ፡፡

ዶ/ር አሸብር፡- ይኼ የራሳችን ጥፋት ነው፡፡ የሠራነው ሥራ ለሚዲያ በወቅቱ ስለማናሳውቅ ሚዲያዎች በምክር ቤቱ ላይ የተሳሳተ ጽሑፍ የሚያቀርቡበት ሁኔታ አለ፡፡ አንድ ጊዜ ለምሳሌ አንድ ሚዲያ ምክር ቤቱ 18 ስብሳባዎች ማካሄድ ሲኖርበት ስድስት ጊዜ ነው የተሰበሰበው ብሎ ገልጿል፡፡ ጥፋቱ ከሚዲያው ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምከንያቱም ሚዲያ ያገኘውን ነው የሚያቀርበው፡፡ የእኛ ሥራ ስብሰባ ብቻ አይደለም፡፡ በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ መስክ ላይ የሚሠራ ሥራ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርላማው ከ2002 ምርጫ ጀምሮ እንደበፊቱ ክርክር የሚደረግበትና የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት አይደለም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጥያቄዎችን ታነሳላችሁ፡፡ ነገር ግን ከፓርላማ የሚጠበቀውን ያህል ሕዝቡ በጉጉት የሚጠብቀው ነገር አላገኘም፡፡

ዶ/ር አሸብር፡- እኔ እሱ አይደለም የሚያሳስበኝ፡፡ ሕዝቡ የመሰለውን መርጧል፡፡ ፓርላማውም መሥራት የሚገባውን እየሠራ ነው፡፡ እኔ የሚያሳስበኝ የወደፊቱ ነው፡፡ የእኛ አገር ተቃዋሚዎች ያኔ በ2002 ምርጫ ከተሸነፉበት ጊዜ ጀምረው ጠንክረው መሥራትና ሕዝቡንም ከጎናቸው ማሰለፍ፣ ዓላማቸውን ማስረዳትና ከገዥው ፓርቲ የተሻለ ጠንካራ የሆነ ዓላማ እንዳላቸው ማሳወቅ የሚገባቸው እነሱ ናቸው፡፡ እንግዲህ ምርጫ ከተደረገ ሁለት ዓመት ተኩል አልፏል፡፡ በዚህ ዓመት ውስጥ ጠንካራ ዝግጅት እያየሁ አይደለም፡፡ ገዥው ፓርቲም ‹‹አውራ›› እንዲሆን እያደረገ ያለው የተቃዋሚዎች ድክመት ነው፡፡ ችግርም ቢኖር ተቋቁመው መሄድ አለመቻል ነው፡፡

ይኼ ሁኔታ ደግሞ ገዥውን ፓርቲ ብቻ እያጠነከረ የሚሄድ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት የሚሆነው በምርጫ 97 አዲስ አበባ ላይ በተገኘው መቶ በመቶ ድል ተጠቃሚ አለመሆናቸው ነው፡፡ ያንን አንፈልግም ብለው መተዋቸው ነው የሚመስለኝ፡፡ አንዱን ትልቅ ዕድል ካጣህ መልሰህ ለማግኘት ከባድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ወደፊት ምን መሆን አለበት በሚለው ራሳቸው ተቃዋሚዎች ካልሠሩ ለእነሱ ማንም አይሠራም፡፡ ይኼ እንግዲህ በአሁኑ ወቅት የደረስንበት የፓርቲዎች የኃይል ሚዛንና አሠላለፍ ነው፡፡

በተረፈ ግን ወደ ምክር ቤት ስትመጣ ምክር ቤቱ ውስጥ ክርክር የለም የሚለው እኔን አይመስለኝም፡፡ ክርክር አለ፡፡ ግን ሰው አንዳንዴ ሚዲያውን ከመከታተል ይልቅ ገና ለገና ምን ክርክር አለ ብሎ መደምደሙ ችግር የሚፈጥር ይመስለኛል፡፡ የፓርቲ አባላት እርስ በርሳቸው ሳይቀር ክርክር ያነሳሉ፡፡ አስፈጻሚው አካል እንደበፊቱ ተጨበጭቦለት የሚሄድ አይደለም፡፡ ሪፖርት ሲቀርብ መስተካከል ያለበትና ስህተትም ከሆነ በገዥው ፓርቲም፣ በተቃዋሚም፣ በግልም የሚነገርበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ መደምደሙ ነው ትልቅ ችግር እየፈጠረ ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርላማ ውስጥ መሻሻል አለባቸው የሚሏቸው የታዘቧቸው ነገሮች የሉም?

ዶ/ር አሸብር፡- እውነቱን ለመናገር ብዙ ጊዜ የምክር ቤቱ በጀት ውስን ነው፡፡ የአገራችንን አቅም መሠረት አድርጎ ነው የሚቀርበው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የምክር ቤቱ አባላት በአብዛኛው እንደሌላ አገር ሰዎች ገንዘብ የሚገዛቸው አይደሉም፡፡ 200 ዶላር እየተከፈላቸው የሚሠሩና ለአገር የሚቆረቆሩ እኔ የምከብረው አገር ሲከብር ነው በማለት የሚሠሩ የፓርላማ አባላት ናቸው፡፡ ኬንያ ብትሄድ  አንድ የፓርላማ አባል ደመወዙ እስከ አሥራ አምስት ሺሕ ዶላር ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው የኢትዮጵያ ምክር ቤት ችግር ውስጥም ሆኖ ከዜጋው እኩል እየተቸገረ የሚሠራ አባል ነው ያለው፡፡ በምንም ደረጃ ቢመዘን ደመወዙ አነስተኛ በመሆኑ ለልጅ ትምህርት ቤት ተከፍሎ፣ ለትራንስፖርትና ቤተሰብን አስተዳድሮ የሚቻል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በምርጫ 2002 ለፓርላማ ሲወዳደሩ በካፋ ዞን ከፍተኛ የልማትና የአስተዳደር ችግር እንደነበር ሲናገሩ ነበር፡፡ አሁን ያ ችግር ተቀርፏል ማለት እንችላለን?

ዶ/ር አሸብር፡- በዚያን ጊዜ በአካባቢው ሥር የሰደደ የልማትና የአስተዳደር ችግር ነበር፡፡ የአካባቢው ምሁርና ነጋዴ የሚታሰርበትና የሚሰደብበት ጊዜ ነበር፡፡ ገበሬው ማሳውን ተነጥቆ ለባለሥልጣን ዘመድ የሚሰጥበት ጊዜ ነበር፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ በአንድ ስልክ ጥሪ ከሥራ ገበታ የሚፈናቀልበት ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሳይቀር እርስ በርስ ሲተራመሱ ነበር፡፡ ወጣቱና ሴቱ ሥራ ያጣበት ጊዜ ነበር፡፡ እጅግ አስቸጋሪ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ ያንን የካፋ ሕዝብ ፍፁም የሚረሳው አይደለም፡፡ አሁን ግን ከዚያ ሁሉ ችግር ሙሉ ለሙሉ ተላቋል ባይባልም ከሞላ ጎደል የሥርዓቱ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ በወቅቱ አንድ ባለሥልጣን በገባበት መሸታ ቤት ከአርባና ከሃምሳ በላይ ፖሊሶች እየጠበቁት ከተማው ያለጥበቃ የሚያድርበት ጊዜ ነበር፡፡ እንደዚያ የሚያደርግ አሁን ምንም ዓይነት አምባገነን ባለሥልጣን እዚያ አካባቢ የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ሕዝቡም አይቀበለውም፡፡

ምርጫውን አሸንፌ ፓርላማ ከገባሁ በኋላ ዋና ሥራዬ የውክልና ሥራ ነው፡፡ ሕዝቡ ያለበትን የልማት ችግር ካነጋገርኩ በኋላ መጥቼ ለምክር ቤቱ አነሳለሁ፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው መፍትሔ እንዲያገኙ እጥራለሁ፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ በየአካባቢው እየሄድኩ ሕዝቡን አነጋግራለሁ፣ ግብረ መልስም እሰጣለሁ፡፡ የተገኘውን ውጤት ለሕዝብ አቀርባለሁ፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በዓመት ሁለት ጊዜ እንሄዳለን፡፡ ነገር ግን በማናቸውም ጊዜ ሄደን የወከልነውን ኅብረተሰብ መጠየቅና ማየት የሚከለክለን የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ከተቀናቃኝዎ ከአቶ ብርሃኑ አዴሎ ጋር ከፍተኛ የምርጫ ትኩሳት ውስጥ ነበራችሁ፡፡ ከምርጫ በኋላ በሥራ አጋጣሚ ተገናኝታችሁ ታውቃላችሁ?

ዶ/ር አሸብር፡- እኔ በመርህ የማምን ሰው ነኝ፡፡ አቶ ብርሃኑንና እኔን ያገናኘን አንድም የአካባቢው ልጆች በመሆናችን ሁለትም በምርጫ ነው፡፡ በእኔ እምነት ተለያይተን መለያየት የለብንም ነው የምለው፡፡ ምርጫውን በተመለከተ ከግንቦት 15 በኋላ የምርጫው ስሜት ማብቃት አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡ ሕዝቡም ይመሰክራል፡፡ በሌላ ወገን ያ ስሜት አለ የለም የሚለውን አሁንም የአካባቢው ሰዎች የሚመሰክሩት ነው፡፡

በሚገርም ሁኔታ ግን እኔና እሳቸው በሥራ ሁኔታ እንገናኛለን ብዬ አስቤም ገምቼም አላውቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን አጋጣሚ ሆኖ አቶ ብርሃኑ የሚሠሩበት መሥሪያ ቤት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥር የአዕምሮአዊ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ደግሞ ተጠሪነቱ እኔም ለምመራው ቋሚ ኮሚቴ ነው፡፡ እናም በዚህ ወቅት አቶ ብርሃኑ ሲመጡ ሪፖርታቸውን አዳምጣለሁ፡፡ ኮሚቴውን ሰብስቤም እሳቸውም ባሉበት ሪፖርታቸውን አዳምጣለሁ፤ ግብረ መልስም እሰጣለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት የዚህ አጋጣሚ ተገላቢጦሽ ሆኖ ይመጣል ብዬም አስቤም አላውቅም፡፡ ከዚሁ ሁሉ የተረዳሁት በዚህ ሰዓት አንተ ሕግንና ሥርዓትን አክብረህ የምትሄድበት፣ ሕገ መንግሥቱን ጠንቅቀህ ካወቅክና ታማኝ መሆን ከቻልክ፣ ሥልጣን እነደሆነ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንዳሉት ‹‹የዛፍ ላይ እንቅልፍ›› ነው፡፡ ሥርዓቱ ሕጉን ስታከብር ሥልጣን የሚሰጥ፣ ከዚያ ወጣ ስትል ደግሞ በድንገት ወድቀህ የምትገኝበት መሆኑን ነው ያወቅሁት፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በቅርቡ ሥልጣናቸውን ለተተኪው ሰው እንደሚያስረክቡ ይጠበቃል፡፡ እርስዎ በፓርላማ ብቸኛ የግል ተወካይ ነዎት፡፡ ዶ/ር አሸብር ፕሬዚዳንትነቱን ይይዛሉ ተብሎ በስፋት እየተወራ ነው፡፡ ሳይነገራቸውም አልቀረም ይባላል፡፡ አሁን አዲስ ፕሬዚዳንት የምናይበት ጊዜ ከመቃረቡ አንፃር ምን ይላሉ?

ዶ/ር አሸብር፡- እንዳልከው የግል ተመራጭ ነኝ፡፡ ፕሬዚዳንት ትሆናለህ ወይ የሚል ጥያቄ እሰማለሁ፡፡ ‹‹ተነግሮሃል ወይ›› ለሚለው የምሰጠው መልስ ባይኖርም፣ ከሕዝቡ የሚሰማውም የግል ተመራጭ በመሆኔና የፓርቲ አባልም ፕሬዚዳንት መሆን አይችልም ከሚል የተነሳ ነው፡፡ ለእኔ ግን ዋናው ቁም ነገር እሱ አይደለም፡፡ በፊት ፓርላማ ለመግባት አስቸጋሪ የነበረው ጊዜ አልፏል፡፡ ዛሬ እንደ አንድ ዜጋ የአገሬ ፕሬዚዳንት መሆን እችላለሁ ብዬ መናገሬ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በዚህ አገር ውስጥ ፕሬዚዳንት የመሆን መብት እንዳለው፣ ያ ሥርዓት እንደተገነባ፣ ብሔር ብሔረሰቦች የሥልጣኑ ባለቤት መሆን መቻላችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ የሕዝቡ ንግግርና መነሻውም ሕገ መንግሥቱንና ሥርዓቱን መሠረት ያደረገ ነው፡፡

ስለዚህ አሸብርም ሆነ ሌላ ሰው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ወይም ሌላ የትልቅ ሥልጣን ባለቤት ሊሆን እንደሚችል መታሰቡ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ አሁን ሌላው ሰው እንደሚጨነቀው ገዥው ፓርቲ የሚጨነቅበት ወቅት ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም ኢሕአዴግ ባህሉን ሳጠና አይቸኩልም፡፡ ለረዥም ጊዜ ወደፊት የሚያስብና የሚያቅድ መንግሥትና ፓርቲ ነው፡፡ እናም ምርጫ 2002 ሲደረግ እንዴት ነው የወደፊት ፕሬዚዳንት የምንመርጠው? እንዴት ነው የምናስተካክለው? ብሎ ሳያቅድና ሳይወስን እዚህ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህም የገዥውን ፓርቲ ውሳኔ መጠበቅ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በምርጫ 2002 አካባቢ ከዚሁ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መተካት የለባቸውም በማለት ‹‹መለስን ማጣት ለኢትዮጵያ ከአቅሟ በላይ ነው›› ብለው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሞት ተለይተዋል፡፡ ከእሳቸው በኋላ የተደረገው የሥልጣን ሽግግርና መተካካቱን እንዴት ይመለከቱታል?

ዶ/ር አሸብር፡- እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ቀድመው ከተረዱ ሰዎች አንዱ ነኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡ እኔ ጥረታቸው ሁሉ ይገባኝ ነበር፡፡ ለምን እንደሚደክሙ፣ ለቤተሰባቸው ለምን ምንም ጊዜ እንደሌላቸው፣ ቀን ከሌሊት እንደተቃጠሉልን በጣም ይገባኝ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የሞቱ ጊዜ አባቴ ሞቷል፤ ወንድሜም አርፏል፡፡ ከዚያ በላይ ሁሉ ነው ሐዘኑ የሆነብኝ፡፡ በጣም ነው ውስጤን ያቃጠለኝ፡፡ የዚህ ዓይነት ሰው በምድር ላይ ደጋግሞ የሚመጣ አይደለም፡፡ ምሉዕ ሰው ናቸው፡፡ የማያውቁትና የማይዳስሱት ጉዳይ የለም፡፡ በሕክምናው ብትሄድ እንደሐኪም ይናገራሉ፡፡ ኢንጂነሪንግ ዘንድ ብትሄድ እንደ ኢንጂነር ያወራሉ፡፡ ፍልስፍናውም ጋ ስትሄድ እንደዚሁ፡፡ በአስተዳደርም እንደዚሁ፡፡

በሁሉም ዘርፍ ላይ ዕውቀት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሌም እየተለቀሰላቸው የሚኖሩት ሁሉን አክባሪ ስለሆኑ ነው፡፡ በአፍሪካም በዓለምም የተናቅንበት ጊዜ ነበር፡፡ ረሃብተኞችና ለማኞች ተብለን የተሰደብንበት ጊዜ ነበር፡፡ ያን ሁሉ አስቀርተው ሌላ መልካም አቅጣጫ አስይዘው ያለፉ ሰው ናቸው፡፡ ለዚህ ነው እሳቸውን ማጣት ከባድ ነው ያልኩህ፡፡ ምክንያቱም ትንሽ በሕይወት ቢቆዩ ኖሮ የበለጠ ጠቃሚ ነበር፡፡ እንግዲህ ሰው ናቸው፡፡ ሁላችንም ቢሆን ወደ እሳቸው እንሄዳለን እንጂ እሳቸው ወደ እኛ አይመጡም፡፡ የእሳቸውን ዕጣ ፈንታ ነው የምንከተለው፡፡ ከዚህ አኳያ በወቅቱ መተካካቱ ነው የታየኝ እንጂ የዚህ ዓይነት ቅጽበታዊ ሞት ይገጥማቸዋል ብዬ ጠብቄም አስቤም አላውቅም፡፡ ለዚያ ነው ሐዘኔ መሪር የነበረው፡፡ ለአገሪቱም፣ ለዓለምም፣ ለአፍሪካም ትልቅ ሰው ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ ‹‹ሳናውቅ የጠላንህ ስናውቅ የተለየኸን›› ብሎ ሲያለቅስና ሲማረር የነበረው፡፡

አሁን እንግዲህ ያ አልፏል፡፡ አሁን ቦታው ላይ ያለውን ሰው ማገዝ፣ መተባበር፣ ወደ እሳቸው ደረጃ እንዲበቃም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉ ሰው እንደ አንድ ሰው ሆኖ መሥራት ያለበት ወቅት ነው፡፡ በእርግጥ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መጥፎ ጅምር አይደለም ያላቸው፡፡ በአጋጣሚም የአፍሪካ መሪዎችን ስብሰባ ሲመሩ እንዳየሁት ትልቅ አቅም እንዳላቸው ያሳዩበት መድረክ ነው፡፡ የሕዝቡ ድጋፍ ታክሎበት የበለጠ እየጠነከሩ ይሄዳሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከድህነት ለመውጣት የተማረና ጤነኛ የሆነ ዜጋ መፍጠር፣ ጠንክሮ መሥራት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳይተውን አልፈዋል፡፡ እንግዲህ ድህነት ተመልሶ የሚመጣበት አጋጣሚ አይኖርም፡፡ ዜጋም አይቀበልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የራሳቸው ሰብዕና አላቸው፤ የራሳቸው ይዘውት የመጡት ዕውቀትም አላቸው፡፡

 ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተማሩት ደግሞ ይኖራል፡፡ ብዙ ዕውቀት ሰጥተዋቸዋል፡፡ ራሳቸው ደጋግመው እንዳሉትም የመለስን ራዕይ ለማስፈጸም ያዳግታቸዋል ብዬ አላስብም፡፡ የራሳቸው ዕውቀትና ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያገኙት ልምድ ተዳምሮ ትልቅ ነገር መሥራት ይችላሉ፡፡ ሌሎች አጠገባቸው ያሉ ሚኒስትሮችም ቀላል ሰዎች አይደሉም፡፡ 

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ኢሕአዴግ የረዥም ጊዜ ሊቀመንበሩና ዋና መሥራቹ በሌሉበት ጉባዔ ያካሂዳል፡፡ እንደ አንድ የግል የፓርላማ አባል ከዚህ የገዥው ፓርቲ ጉባዔ ምን ይጠብቃሉ?

ዶ/ር አሸብር፡- እንዲህ የተጀመረው ትልቅ የለውጥ አቅጣጫ አለ፡፡ የአገሪቱ ገጽታ ተቀይሯል፡፡ ፓርቲው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሌሉበት ያንን ይዞ መቀጠል መቻል አለበት፡፡ ለሕዝብ አለኝታ መሆን አለበት፡፡ በተለይ በታች የሥልጣን ተዋረድ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ሕዝብን አክብሮ አለመሄድን ማስወገድ መቻል አለበት፡፡ ገዥው ፓርቲ ለሕዝቡ የማይመቹ አመራሮችን ፈጥኖ ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ የሕዝቡን ጥያቄ መርምሮ ፈጣን ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ በዚህም በሕዝቡ ያለውን ተቀባይነት ጠብቆ መሄድ አለበት፡፡ ጉባዔው ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሚካሄድ በመሆኑ ፓርቲው ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡

 በእውነት መለስን ይኼ ፓርቲ ተክቷል? እውነት ይኼ አመራር መለስን ተክቷል ወይ የሚለው በአሁኑ ጉባዔ ነው የሚታወቀው፡፡ የአሁኑን ጉባዔ ሕዝቡ በጣም ስለሚከታተል፣ ገዥው ፓርቲ ሚዛኑን ለመድፋት በጣም ተጠንቅቆና ዕውቀት በተሞላበት መንገድ የሕዝብ ስሜትን ጠብቆ መሄድ አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በጣም የሚያዝና የሚጨበጥ ተደርጎ የማይታይ ነበር፡፡ ግን ሽግግር መፍጠር የሚቻልበት ፍንጭ አሳይቷል፡፡ እስካሁን የታዩትን ጥንካሬዎችና ድክመቶች በትክክል ገምግሞ ለወደፊቱ የሚያስቀጥልበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት፡፡

ሌላው በአሁኑ ወቅት የኑሮ ሁኔታ ሕዝቡን እየተፈታተ ነው ያለው፡፡ ከዚህ አኳያ መፍትሔዎችን የሚያስቀምጥ ፓርቲው ነው የሚሆነው፡፡ ለሕዝቡም ደግሞ ችግሩ ይኼ ነው መፍትሔውም ይኼ ነው ብሎ በግልጽ የሚያሳይበት አጋጣሚ ነው፡፡ መለስ ከጎናችን ባይኖርም አይዞህ እወጣዋለሁ ብሎ መልስ የሚሰጥበት ጉባዔ መሆን አለበት ነው የምለው፡፡

ሪፖርተር፡- በፓን አፍሪካ ፓርላማ ኢትዮጵያን ወክለው አባል ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ ፓርላማው ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር አሸብር፡- ለአንድ ዓመት ተኩል  የፓርላማው አባል ነኝ፡፡ ፓርላማው በአሁኑ ወቅት ውሱን ሥራዎችን ነው እየሠራ ያለው፤ የማማከር ሥራ፡፡ ይህ ደግሞ የአፍሪካ መሪዎች የሰጡት ገደብ ነው፡፡ በዚህ መሀል ብዙ ሥራ ለመሥራት አመቺ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ፓርላማው ባደረጋቸው ተደጋጋሚ ስብሰባዎች ወደ ሕግ አውጪነት እንዲቀየር የሚያስችል ሥልጣን እንዲሰጠው ጥናት ተካሄዶ በጉባዔ ውስኖ ለመሪዎች ጉባዔ ቀርቧል፡፡ ሆኖም ብዙም የተሳካ ነገር የለም፡፡ ጥፋቱ የማን ነው ብዬ ራሴን ስጠይቅ  የፓርላማ አባላት ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የአፍሪካ ፓርላማ አባላት የሄድነው ከብሔራዊ ፓርላማዎች ተወክለን ነው፡፡ መጀመርያ የእያንዳንዳችንን አገር መሪዎች ማሳመን ይኖርብናል፡፡  መሪዎቹ ጉዳዩን በአግባቡ ያስረዳቸው አካል ያለ አይመስለኝም፡፡

ምክንያቱም የፓን አፍሪካን ፓርላማ ሥራ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ነው እየሠራው ያለው፡፡ ለምሳሌ በጀትን ብንወስድ ኮሚሽኑ ራሱ ያወጣል፣ ራሱ ያፀድቃል፡፡ ሕግም ራሱ ያወጣል፣ ራሱ ያፀድቃል፡፡ የቁጥጥር ሥራም ራሱ ነው እየሠራ ያለው፡፡ ክፋቱ ከመሪዎቹ አይመስለኝም፡፡ እነሱ እያዩ ያሉት ሥራው መሠራቱን ነው፡፡ ማን ምንድን ነው መሥራት ያለበት ለሚለው ግን በእያንዳንዱ አገር ያለው ፓርላማ የሚሠራውን ሥራ ነው እሱም መሥራት ያለበት፡፡ ስለዚህ በግምገማችን ጥፋቱ የእኛ የራሳችን መሆኑን ነው የተስማማነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የፓርላማው አባላት ያለማሳመን ድክመት እንዳለ ሆኖ ግን መሪዎቹ የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ አላቸው? ምናልባትም የጥቅም ግጭት ያለ አይመስለዎትም?

ዶ/ር አሸብር፡- የጥቅም ወይም የሥራ ግጭት የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ይህንን በአግባቡ ለመሪዎች ማስረዳት ያለብን እኛ ነን፡፡ ፓርላማ ሕግ ባያወጣ የሚጠቀሙት ነገር የለም፡፡ ሕግ ቢያወጣ ግን ብዙ የሚጠቀሙት ነገር አለ፡፡ ሥርዓት ለማስያዝም ትልቅ ፋይዳ ነው ያለው፡፡ መሪዎቹ ምንም አላደረጉም፡፡ የአባል አገሮች መሪዎች የአገራቸው ፓርላማ ባወጣው ሕግ እየተመሩ ሲፈልግ ይሾማቸዋል፣ ሲፈልግ ያዋርዳቸዋል፣ ይቆጣጠራቸዋል፡፡ ቢያንስ በመርህ ደረጃ ያንን ተቀብለው ነው እየሠሩ ያሉት፡፡ ፓርላማ ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀው ነው የሚያውቁት፡፡ በአፍሪካ ኅብረትም ላይ የዚሁ ተቋም አስፈላጊነት የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደዚያ ከሆነ በአሁኑ ወቅት ለምሳሌ የኅብረቱ መሪነት በኢትዮጵያ እጅ ነው ያለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ናቸው የኅብረቱ ሊቀመንበር፡፡ ከዚሁ አንፃር ፓርላማው የሕግ አውጪነት ሥልጣን እንዲኖረው ምን ዓይነት ሚና መጫወት ይችላሉ?

ዶ/ር አሸብር፡- ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በላይ ሥራው ሊኖር የሚገባው በአባላቱ አማካይነት ነው፡፡ ከእያንዳንዱ አገር አምስት አምስት ተወካዮች አሉት፡፡ እያንዳንዱ ተወካይ መሪውን ማስረዳትና ማሳወቅ አለበት፡፡ እኛም ለራሳችን መሪ ጉዳዩን በአግባቡ ቀርበን ልናስረዳ ይገባል፡፡ በተረፈ ግን እንደየወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነታቸው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የራሳቸው ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡

 በእሳቸው ዘመን የዚህ ዓይነቱን ነገር ሥርዓት ማስያዝ መቻሉ ታሪክም ነው፡፡ እንደ ሰብሳቢነታቸው ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡ በዋናነት ግን ሥራውን እያንዳንዱ የፓርላማ አባል ከሠራና መሪውን ማስረዳትና ቤቱ ውስጥ መተማመን ከተቻለ ይኼ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥራ ካልሠራን ግን ፓርላማው ምን ትርጉም አለው? እያንዳንዱ አገር ነው ያን ሁሉ ወጪ እየሸፈነ ያለው፡፡ ያን የሚያደርገው ይኼ ውክልና ጥቅም ያስገኛል ብሎ ነው፡፡ መሪዎቹ የሚገናኙት በዓመት አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ነው፡፡ መጥተውም ፓርላማውን አይደለም የሚያገኙት ኮሚሽኑን ነው፡፡ ኮሚሽኑ አካባቢ ደግሞ ያለመረዳት አለ፡፡ ያ ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ እስከሚለምዱት ማወያየትና ማነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ መሪዎች ሕጉ የት ነው? ምን ይላል? ብለው ፖለቲካዊ ውሳኔ ማሳለፍ አለባቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡  

ሪፖርተር፡- እናንተ የኢትዮጵያ ተወካይ ቡድን በመሆናችሁ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ስለጉዳዩ ተነጋግራችሁ ታውቃላችሁ?

ዶ/ር አሸብር፡- በዚህ ዙርያ እስካሁን አላነሳንም፡፡ በአፍሪካ ፓርላማ ደረጃ ግን ቀደም ሲል የነበሩት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ለመረዳት ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንደ የወቅቱ ሊቀመንበርነታቸው ይህንን ነገር መስመር ያስይዛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡

No comments: