Monday, April 1, 2013

‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ!›› በታሪክ አጻጻፍ ስልትና የተዛቡ የሁነቶች ትንታኔ ላይ የተሰጠ ሙያዊ ሒስ

በሳሙኤል ኪዳነ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ
እውን ግን ታሪክ ይከሽፋል?
የዚህ ጽሑፍ ዋና መነሻ የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመባል የሚታወቀውን ተቋም በጂኦግራፊ የትምህርት ዓይነት በአስተማሪነት ሞያ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ፣ በአሁኑ ወቅት በጡረታ የሚገኙት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ታኅሳስ 2005 ዓ.ም. ላይ
‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚል ርእስ ለሕትመት ባበቁት መጽሐፍ ላይ በተነሱት ታሪካዊ ጉዳዮች ላይ ያለኝን የግል አስተያየት መሠረት በማድረግ መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ላይ መረጃን ብቻ መሠረት ያደረገ ሙያዊ ሒስ ለመስጠት ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ማን ናቸው? ለሚለው ጉዳይ ብዙ ማብራርያ ለመስጠት ባልደፍርም ሆኖም ግን እሳቸው በሙያቸው ያበረከትዋቸው ሥራዎች ግን ምንድን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ለዚህ ጽሑፍ አንባብያን ይረዳ ዘንድ በ2003 ዓ.ም. ራሳቸው ካሳተሙት ‹‹አገቱኒ ተምረን ወጣን›› በሚለው መጽሐፋቸው ተዘርዘረው የሚገኙትን ነጥቦች ማየቱ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡


እዚህ ላይ የምናነሳው ስለታሪክና የታሪክ አጻጻፍ ስልቶች ነው፡፡ በዚህም መሠረት በፕሮፌሰር መስፍን የተቀመጡትን ታሪካዊ ሁነቶች በታሪክ አጻጻፍ ስልት መነጽሮች ሲታዩ ምን ያህል አውነት ናቸው? ምን ያህልስ ተኮላሽተዋል? የሚለውን ፍርድ የአንባቢውን ብቻ መሆን ስላለበት ነው፡፡

በታሪክ አጻጻፍና አተረጓጎም ላይ መሠረት ያደረጉ በርከት ያሉ ጽሑፎች በመጻፍ የሚታወቁ በሙያው አንቱታን ያተረፉ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት፣ የታሪክ ትምህርት  ጣዕም በአንድ ተመሳሳይ ርእሰ ጉዳይ ላይ የታሪኩን ምንጭ (Source) ለመተርጎምና ሙያዊ ትንታኔ ለመስጠት ትኩረት ባደረጉ ግብረገብነት የተሞላቸው ክርክሮችና ሒሶች በሚከፍቷቸው አዳዲስ የአስተሳሰብ ሐዲዶች፣ ሰዎች ለበለጠ ዕውቀት ፍለጋ የሚገፋፉ ሁኔታዎች የሚፈጥሩ በመሆናቸው ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ የታሪክ ትምህርት ምሁራን ጸሐፊዎች እምነት ከሆነ ታሪክ እንደ ልብወለድ ጽሑፍ አልያም እንደ ሌላ የፈጠራ ጽሑፍ መቸት እያጣጣምክ የመሰለህን እያስገባህ የማይጥምኸን ነገር ግን እውነተኛ ክዋኔ እየቆረጥክ የምትጽፈው ጽሑፍ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ‹‹አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ በማለት ያስረዳሉ፡፡

‹‹የታሪክ ትምህርት ግን የሚጠቅም የእውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲሆን ነው፡፡ እውነተኛንም ታሪክ ለመጻፍ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የሚከተሉትን ሦስት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ያስፈልጋልና፡፡ መጀመርያ ተመልካች ልቦና የተደረገውን ለማስተዋል፤ ሁለተኛ የማያዳላ አእምሮ በተደረገው ለመፍረድ፤ ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማሳወቅ፡፡ ያገራችን የታሪክ ጸፎች (ፀሐፊዎች) ግን በእነዚህ ነገሮች ላይ ኃጢአት ይሠራሉ፡፡ በትልቁ ነገር ፈንታ ትኒሹን ይመለከታሉ፤ ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጠባሉ፣ አጻጻፋቸውም ድብልቅልቅ እየሆነ ላንባቢው አይገባም፡፡››

ታሪክ በግብዝነትና በማን አለብኝነት የሚጻፍ ጉዳይ ሳይሆን እጅግ በረቀቀ አኳኋን እውነተኛ ጭብጥ የያዘ ጭብጡ ከተጻፈበት ሁነት በመንፈስ ያልተለየ መሆን አለበት፡፡ ይህን ካልን እንግዲያ አንድ ሁነት በታሪክ መዝገብ ሊጻፍ የሚችልበት የተለያዩ መንገዶች አሉ፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ሁነት ሲጻፍ በተለያዩ ወቅቶች ማለትም ድርጊቱ በተፈጸመበት ቀን፣ ሰዓት፣ ዓመት ወይም ድርጊቱ ከተፈጸመ ከአጭር ወይም ከረጅም ዓመታት በኋላ ሊጻፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው ምንጭ እስካለው ድረስ ብቻ ነው፡፡

በአንጻሩ ግን የአንዲት አገር ወይም ሕዝቦች ታሪክ በግብዝነትና በማን አለብኝነት የተጻፈ እንደሆነ በይዘት ደረጃ ሊያካትታቸው የሚገባቸውን ነጥቦች በማጣመም ወይም በመሸራረፍ በትውልድ ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ አሻራ እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አለቃ ታዬ ገብረ ማርያም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ›› የሚለውን መጽሐፋቸው የጻፉበትን ዋና ምክንያት ወይም ዓላማ እንዲህ በማለት ያብራራሉ፤ ‹‹ይህንንም ታሪክ ስናወጣው ከልብ አንቅተን ከሕሊና አውጥተን ልብ ወለድ የጻፍነው አይደለም፡፡››

ከዚህ አንጻር ሲታይ የመጀመሪያዎቹ በአማርኛና ሌሎች ቋንቋዎች የተጻፉትን ታሪክ ቀመስ ጽሑፎች ላይ የሚታዩ በርከት ያሉ ችግሮች ሲኖሩዋቸው ከችግሮቹ ውስጥ ለአንድ ሃይማኖት ብቻ ማዳላት፣ አንድ ብሔርን ብቻ ተኮር ያደረገ ታሪካዊ ይዘት ያለውን ጽሑፍ መሆን፣ የራስን ሃይማኖት ወይንም ብሔር እንደ ዋነኛ ተዋናይ በመቁጠር የሌሎች ሕዝቦች ታሪክ ሕዝቦቹ ራሳቸው ከሚያስቡበት አቅጣጫ በተቃራኒው መዘገብ፣ ከብዙዎቹ በኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ ላይ የሚታዩ ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ከቀደምት ፀሐፊዎች ግንባር ቀደም ተወቃሽም ተወዳሽም ሲኖሩ በእኔ እምነት አሁን የዚህ ጽሑፍ መነሻ ምክንያት የሆኑትን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በዚሁ ረድፍ ያሉ የሕዝብ ታሪክ አጻጻፍ ስልት አራማጅ ተብለው ሊገለጹ ይችላሉ፡፡

በአጠቃላይ በእሳቸው የተጻፉትን ‹‹የታሪክ›› መጻሕፍት ልብ ብሎ ለሚያነብ አንባቢ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች የነበረውን በሽታ እሳቸው ላይ ያየዋል፡፡ ምን ዓይነት የታሪክ ድግግሞሽ አልያም መገጣጠም እንደሆነ ባላውቅም እኔም ብሆን ገብረሕይወት ባይከዳኝ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች ባየበት መነጽር ፕሮፌሰር መስፍንን ሳያቸው ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከ100 ዓመት በፊት ከጻፈውና ከሥር እንደሚከተለው እንደተገለጸው ልዩነት አላገኘሁባቸውም፡፡

‹‹የታሪካችንም ጻፎች ሁለት ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ አንዱ ዓይነት የቤተ መንግሥት ሊቃውንት ይባላሉ፣ ማለት እንጀራን ሲፈልጉ ከቤተ መንግሥት ተጠግተው ንጉሡ ያዘዛቸውን የራሱን ውዳሴ ታሪክ ብለው ጽፈው ለኋላው ትውልድ የሚያስቆዩ አቆላማጮች፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ግን መነኮሳት ናቸው፡፡ እነሱም የሚጽፉት ታሪክ አድልዎ ይበዛበታል፣ የራሳቸውን እንጂ የሕዝቡን ጥቅምና ጉዳት ከቶ አያቃጥሩምና፣ ስለዚህ የልባቸውን የሚፈጽምላቸው ንጉሥ ቅዱስ ቅዱስ ይሉታል፣ ከዱንቁርናቸው ወጥቶ ከፍ ባለ ሕሊና ተመርቶ ስለዜጎች ልማት የሚጥር ግን ርኩስ፡፡››

በነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ዘንድ ቀደም ሲል ተጽፎ እንደምናገኘው ‹‹ዝቅ ብሎ ጠፍቶ የነበረው መንግሥታችን ባባ ታጠቅ ቴዎድሮስ ሲታደስ፣ በወሬሳው ካሳም ሲወሃድ እንዴት እንደነበር፣ ባባ ዳኘው ምኒልክም እንዴት አርጎ ሰፍቶ እንደረጋ ገልጾ የሚያወጋን የታሪክ ጸሐፊ ከቶ መቼ ይወጣ ይሆን›› እንደተባለው ሁሉ በጣም የሚገርመውና ለአንባቢም ለመቀበል የሚከብደው ነጥብ ግን አፄ ዮሐንስ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የሠሩትን ሥራ በሙሉ ብቻቸውን አይወጡትም ነበር ተብሎ በተጠቀሰው ነጥብ ላይ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አንድነት የተደረገውን ትግል የንጉሠ ነገሥቱን ዋጋ በሚያሳጣ መልኩ በንጉሠ ነገሥቱ ሥር ሲተዳደሩ የነበሩትን አካላት ከፍ ለማድረግ የተጠቀሙበት አካሄድ ትዝብት ውስጥ ሳይከታቸው እንደማይቀር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

እንደ አብዛኛዎቹ የታሪክ ጸሐፊዎች እምነት በርከት ያሉ ታሪካዊ ክስተቶች ለመለየት እጅግ በሚያስቸግር መልኩ ተመሳሳይ ባሕርያት ይዘው በተለያዩ ወቅቶችና ቦታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥናት ለሚያካሂዱ ምሁራን ይህንኑ የአሁኑ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ራሳቸውን ከቀደምት የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊያን በተለይም ከጦቢያው ደራሲ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረየሱስ ለይቶ ለማየት በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ለአብነት ያህል ፕሮፌሰር አፈወርቅ በገብረሕይወት ባይከዳኝ በሚከተለው መልኩ ይተቻሉ፡፡

‹‹ያ ከአቶ አፈወርቅ እጅ የታተመ ታሪክም ቢሆን ሙሉ አይደለም፡፡ ብዙውን ነገር በጨለማነት ይተዋል፣ ብዙውንም ነገር ያሳምራል፣ በየዋሁ በጠንካራውም የትግሬ ነገድ ይልቁንም በንደ ወሬሳ ካሳ ያለ አርበኛ ከማንም ሰው እንጂ እንደ አቶ አፈወርቅ በሊቅነት ከተጠራ ሰው እጅና አፍ ሊወጣ የማይገባው የስድብ ቃል ይገኝበታል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክን ለማመስገን ዳግማዊ (አራተኛው ዮሐንስ ማለታቸውን ነው) ዮሐንስን መስደብ የሚያስፈልግ ይመስላል፡፡››

በሌላው መልኩ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከተነሱ ‹‹አጨቃጫቂ›› ነጥቦች አንዱ በትግራይ ነበር ስለሚባለው የሽፍተኝነት ጉዳይ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ሽፍተኝነት የብሔረ ትግራይ የተለየ ‹‹የሥራ መደብ›› አድርገው ማቅረባቸው፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በርእሱ ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር ያደረጉት እንደ R.A. Caulk ያሉ ምሁራን ከፈር የለቀቀ ትንታኔ ነው፡፡ እሳቸው አዳዲስ ሐሳብ ይዘው ቢመጡ ባልከፋ ነበር፣ ዳሩ ግን ያልነበረውን ተቀጥያ በመስጠት ከእውነት ሊያንሸራትት የሚችል ሐሳብ ሆነ እንጂ፡፡ እስካሁን በርእሰ ጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አብዛኛዎቹ እስከ አሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ ወደ ሥልጣን የወጡ ነገሥታት የኋላ ታሪካቸውን የታየ እንደሆነ ከሽፍተኝነት የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ለአብነት ያህል አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ተብለው እስከተሾሙበት ጊዜ እሳቸውን ጨምሮ በርካታ በሰሜን፣ በሸዋ፣ በቤጌምድር (ጎንደር)፣ በወሎና በትግራይ የሽፍተኝነት ኑሮ የቀመሱ ሽፍቶች በኋላ ነገሥታት ሆነው ብቅ ብለዋል፡፡ ለዚህ አባባላችን ማሰሪያ ይሆን ዘንድ R.A. Caulk ይህንን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ጽፎ እናገኘዋለን፡፡

“Everywhere in the Christian empire in the nineteenth century, government troops, tax assessors, and all travelling on official business to and from the court or the residences of provincial governors lived off the country side. Booty supplied the bounty by which lords bound retainers. Outlawry was an avenue to office frequently pursued by neglected members of the office-hoding families… The most renowned shefta have been malcontents from the local office-holding families who made up the provincial gentry in the Christian highlands. Some of these families had such wide ranging connections by marriage as to form a provincial nobility.”

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ የአፄ ምኒልክ ጸሐፌ ትዕዛዝ በመሆን የአፄ ምኒልክን ዜና መዋዕል የጻፉትን ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ አፄ ምኒልክ በድኅረ መተማ ንጉሠ ነገሥት ተብለው ከመጠራታቸው በፊት በተለያየ መልኩ በአፄ ዮሐንስ 4ኛ በሚመራው ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ሲያምጹ ወይም ሲሸፍቱ እንደነበር የሚያመላክቱ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ሽፍተኝነት ብለው ከጠቀስዋቸው ሥራዎች በመንፈስ በፍፁም የማይለዩ ተግባራት እናያለን፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም መጽሐፍ ውስጥ ያልተካተተው የምኒልክ የሽፍተኝነት ኑሮ በጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ በእንዲህ መልኩ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡

‹‹አፄ ቴዎድሮስ በ1860 ዓ.ም. ከሞቱ በኋላ ግን ንጉሥ ምኒልክ ሸዋንና ወሎን በግዛት ይዘው በንጉሠ ነገሥትነት ስም እየተጠሩ ለ10 ዓመት ያህል ቆዩ፣ የዚያን ጊዜ ማኅተማቸውም ‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ምንይልክ ንጉሠ ነገሥት› የሚል ነበር፡፡›› እንዲሁም ‹‹በ1874 ዓ.ም. ግንቦት 30 ቀን እምባቦ ላይ ከጎጃሙ ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር ተዋጉ በዚህም ጊዜ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ድል አድርገው ማረኳቸው፡፡››

በእነዚህ ሁለት ነጥቦች መሰመር ያለበት ዋና ጉዳይ ንጉሥ ምኒልክ አፄ ቴዎድሮስ ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ አፄ ተክለ ጊዮርጊስና አፄ ዮሐንስ 4ኛ ወደ ሥልጣን እስከመጡት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ንጉሡ ምኒልክ በሁለቱም ላይ ለተከታታይ አሥር ዓመታት አልገባም ብለው ሲሸፍቱ እንደነበር የማይካድ እውነት እንደሆነ፤ በተጨማሪም የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አፄ ዮሐንስ ገብተው እያለ እሳቸው በጦር መውጋቱ በእጅ ዙር አፄ ዮሐንስ 4ኛ ሲወጉ እንደነበር የሚያመላክቱ የሽፍተኝነት ተግባራት ናቸው፡፡

እዚህ ላይ በጣም የሚገርመው ግን የትግራይ ሕዝብ የሽፍተኝነት ኑሮ አንገሽግሾት አፄ ቴዎድሮስ በግዛታቸው ሲያደርጉት የነበረ አረሜናዊ ሥራዎች የከፋ ቢሆንም አፄው የትግራይን ሕዝብ ከውቤና ከአገው ንጉሥ ስለታደጉዋቸው ለማዕከላዊ መንግሥት እጅግ የከበረ ምስጋና እንደነበራቸው ደብተራ ፍስሃ ጊዮርጊስ ዓብየዝጊ ወይንም በብዕር ስማቸው አለቃ ዘወልድ ‹‹ታሪኽ ኢትየጵያ›› በሚል በትግርኛ በተጻፈው የመጀመርያው የታሪክ መጽሐፋቸው ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በሌላ መልኩ ግን እንደ R.A. Caulk አገላለጽ፣ አብዛኛዎቹ የሽፍተኝነት የታሪክ ሁነቶች በተለይም ከደገኞቹ በግብርና የተሰማሩ የክርስቲያን ነገሥታት ይዞታዎችና አጎራባቾቻቸው ከነበሩ ወደ ቀይ ባሕር የተጠጉ የሙስሊም ይዞታዎች በሚገኙ ቦታዎች ውጭ የሽፍተኝነት ታሪክ በተገቢው መልክ ለታሪክ ጸሐፊዎች እንደ ግብዓት ሊሆን በሚችል መልኩ ተጽፈው አናገኛቸውም፡፡

ሌላው በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም መጽሐፍ የተካተተው ርእሰ ጉዳይ በአፄ ቴዎድሮስ እና በካሳ ምርጫ በኋላ አፄ ዮሐንስ መካከል የነበረውን ፀብ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን የእነዚህ ሁለት ገዢዎች የተለያየ ባሕሪ ለአንባቢ ሳያስነብቡ በቀጥታ ዘለው የሚገቡት የግጭቱን ምንጭ በመተው ወደ ግጭቱ ሒደትና ውጤት ነው፡፡

 ይህ ለአንባብያን ወደ ፍፁም ጨለምተኝነት የሚያሸጋግር አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመሠረቱ የመይሳው ካሳ እና የካሳ ምርጫ ግጭት መታየት ካለበት በወቅቱ የነበሩትን ሦስት ዓበይት ነጥቦች ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በወቅቱ የነበረውን ዓለም አቀፍ ሁነት፣ የመይሳው ካሳ የባህሪ ለውጥና ያስከተለው የሕዝብ ቁጣ እንዲሁም በወቅቱ ካሳ ምርጫ ልክ እንደ ወላጃቸው የሚያይዋቸውን የእንደርታው ገዢ ደጃች አርአያ ድምፁን በመይሳው ካሳ መቅደላ ላይ ተወስደው መታሰር የተፈጠረው ቁርሾና የበቀል ስሜት ናቸው፡፡ በተለይም ከሦስተኛው ነጥብ በኩል የነበረውን የትግራይ መኳንንት ስሜት በወቅቱ የዓለም የሽርክና ዲፕሎማሲ ትስስር መሠረት የነበረውን ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው፣ የወዳጄ ጠላትም ጠላቴ ነው›› የሚለውን አስተሳሰብ በተገቢውን ቦታ ሊያስተናግድ የሚችልበትን ሁነት እንዲፈጠር አስችሎታል፡፡

ከላይ ከጠቀስነው ነጥብ በተቃራኒ አፄ ቴዎድሮስ ትግራይን እጅግ ይወድዋት እንደነበር በተለያየ መልኩ ይገልጻል፡፡ እንደ ታሪክ ጸሐፊዎች ዘገባ ከሆነ ግን የአፄ ምኒልክ ስሜት ከተመለከትን በተቃራኒው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ እንዲህ በማለት ጽፈው እናገኛቸዋለን፤

‹‹ትግሬ በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ፈጽሞ ጠፍተዋል፡፡ የትም የትም ብትሔድ በዚያች አገር የለማ መንደር አታገኝም፡፡ ሰው ከሚኖርባቸው ጎጆዎች ይልቅ የድሮ ልማትዋን የሚመሰክሩ ፍራሾችዋ ይበዛሉ፡፡ የትግሬም ጎበዝ በዛሬ ዘመን ባባቱ አገር አይገኝም፣ አውራ እንደሌለው ንብ ድርሻው ሳይታወቅ ወደ አራት የዓለም መዓዘኖች ተዘርተዋል እንጂ፡፡ ባገሩም ላይ ድህነት ሰፍታለች፣ የሌሎች ወገኖች መተረብያ እስክትሆን ድረስ፡፡ ሁሉም መሬት በሰላም ሲኖር ምስኪኒቱ ትግሬ ግን ሽፍታና ወንበዴ አልተለያትም፡፡››

በፕሮፌሰር መስፍን አፄ ምኒልክ ቂም የለሽ ደግ መሪ ነበሩ ተብሎ የተጻፈው አፄ ምኒልክን ለመካብ እንዲሁም እሳቸው የተጓዙበትን የአስተሳሰብ ሐዲድ በእሳቸው ዘመን እንደ ቅጽበት የተፈጠረ ተደርጎ ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ አውነታው ግን አፄ ምኒልክ እጅግ የከፋ ቂመኛና በቀለኛ እንደነበሩ የሚገልጹ ጽሑፎች አሉ፡፡ ለአብነት ያክል ጸሐፌ ትዕዛዛቸው አለቃ ገብረ ሥላሴ እንደጻፉት የሸዋ ሰው ከጎጃሞችም በተዋጉ ቀን እየገደሉ ሲሰልቡ እንደነበር፤ እንዲሁም በዓድዋ ጦርነት ወቅት ለኢጣልያ ገብረው የጠላት ወታደር በመሆን የተዋጉትን ኤርትራውያን እጅና እግራቸው መቁረጣቸውን ከዚያም በላይ እጅግ የሚዘገንን ነው፡፡

ግን የአፄ ምኒልክ ሠራዊት ወደ ትግራይ በዘመተበት ወቅት ትግራይ ላይ ያደረሰውን ውድመት በአብዛኛዎቹ የታሪክ ፀሐፊዎች ለምን ተቆርጦ እንደሚተው ባላውቅም በጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ የተጻፈውና ከዚህ በታች የተዘረዘረውን አንባቢ እንዲያውቀው ማድረጉ ህሊናን ይፈታተናል የሚል እምነት የለኝም፡፡

‹‹የሠራዊቱም ብዛት ልክ መጠን የለውም ነበርና ተከፍሎ እንዲጓዝ ንጉሡ ከዚያው ውሎ አድርገው ራስ ሚካኤልንና ራስ ወሌን ቱርክ ባሻ ታምሬን ደጃች መኩርያዬን ፊታውራሪ ተክለ ማርያምን ደግሞ ሌሎች መኳንንት ተጨምረው ቀድመው ተጓዙ፡፡ አፄ ምኒልክ ግን በየካቲት መባቻ በ16ኛው ቀን መቀሌ ከአፄ ዮሐንስ ከተማ ገቡ፡፡ ከዚህ በኋላ በየካቲት 25 ቀን ተነስተው አብርሃ አጽብሐ ሰፈሩ፣ በ27 ውሎ ሆነ፡፡ አገሩ ሁሉ ገብሮ የሚዘረፍ ታጥቶ ሠራዊቱ ተርቦ ነበር፡፡ በ29 አጽቢ ዕዳ ሥላሴ ሰፈሩ፡፡ የባላገሩ ብዙ እህል ተገኝቶ ነበርና ሠራዊት ስንቁን አነሳ፡፡››

እዚህ ላይ አንባቢ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ሠራዊቱ መብዛቱ ብቻ ሳይሆን ያገኘውን ሁሉ እየቀማና እየዘረፈ መሔዱ ሳያንሰው፣ ለዘመናት ሳይደፈሩ የኖሩትን ከተከታታይ የእሳት ቃጠሎ ፍርድ የተረፉትን አድባራትና ቤተ ክርስቲያናት መዘረፋቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግንባር ቀደም ተጎጂ የሆነው የአብርሃ ወአጽብሃ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው፡፡

በፕሮፌሰር መስፍን ምኒልክን የሥልጣኔ መሪና በመቻቻል የሚያምኑ ተደርጎ ለተቀናበረው ሐሳብ በተቃራኒው ያለው እውነት የሚያሳየው ግን አፄ ምኒልክ የመንግሥታቸውን አጠቃላይ አሠራር ምን ያህል ከድሮው የአስተሳሰብ ድር ጋር ተሳስሮ እንደቀጠለ ገብረሕይወት ባይከዳኝ እንዲህ በማለት ገልጸዋቸዋል፤

‹‹አጤ ምኒልክ በእውነት የሸዋ ሰውና አቶ አፈወርቅ እንደሚሉት አዲስ ሕግጋት አውጥተዋልን፣ ትምህርትስ ገልጸዋልን፣ እውነት አይደለም፣ ይህማ ቢሆን ይህን ያህል ጊዜ በሰላም እንጀራቸውን አይበሉም ነበር፡፡ የሸዋው ንጉሥ ግን ለሕዝባቸው ያባቱን ልማድ መረቁለት፣ አዲስ ነገር እንዲቀበላቸውም አልተከራከሩትም፡፡››

ከዚህ ነጥብ እንኳን ብንነሳ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያ በአፄ ቴዎድሮስ ፊታውራሪነት የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ በተጀመረበት ፍጥነት እንዳይቀጥል ያቅማቸውን መሥራታቸውን ያሳየናል፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ ሕዝቡና አገሪትዋን ለረጅም ዓመታት የሚቆይ ቁርሾ ‹‹Land Concession›› ተብሎ ወደሚታወቀው የፖለቲካ ቁማር ነበር የገቡት፡፡ ይህም ጉዳይ የመክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ዋና አርእስት ሳይሆን መቅረቱ ሾላ በድፍኑ እንደሚባለው ዓይነት ያስመስለዋል፡፡

ሌላው ጉዳይ ስለቂም ከተነሳ ፕሮፌሰር መስፍን እንዲህ በማለት አስነብበውናል፡፡
‹‹በትረ መንግሥት ከአፄ ዮሐንስ ወደ አፄ ምኒልክ ሲተላለፍ አንዳንድ ለውጦችን አስከትሎአል፤ በመጀመርያ የአፄ ዮሐንስን ተከታዮችና ዘመዶች ማስኮረፉ ከቴዎድሮስ ጀምሮ ብዙ መስዋዕት የተደረገበትን አንድነት አደጋ ላይ ጥሎታል፤ በትግራይ መሳፍንትና መኳንንት መካከል በአንድ በኩል በአደረባቸው የሥልጣን ምኞት፣ በሌላ በኩል በኢጣልያኖች በሚደረገው በገንዘብና በመሳሪያ የመደለል ዘመቻ ሰፊ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር፡፡››

በዚህ ረገድ በቁጥር በርከት ያሉ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ሟሟያ ጽሑፎች ተጽፈው እናገኛለን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የቀድሞው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የነበረው አቶ መኮነን ብርሃነ የጻፈውን ጽሑፍ ውስጥ የተካተቱ አበይት ቁም ነገሮች ጋር የሚጋጭ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሠረቱ አፄ ምኒልክ በትግራይ ሲከተሉት የነበረውን ፖሊሲ በራሱ ሲተነተን ከፋፍለህ ግዛ ከሚለው የቄሳራውያን ኃይሎች ፖሊሲ ምንም ዓይነት መሠረታዊ ልዩነት የለውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አንባብያን የበለጠ መረጃ ይኖራቸው ዘንድ የአፄ ምኒልክ መንግሥትና የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በደጃች ጉግሳ አርአያ ሥላሴና በራስ መንገሻ ዮሐንስ እንዲሁም ቆይቶ በደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳና በራስ ሥዩም መንገሻ ላይ ሲያራምዱት የነበሩትን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲዎችን ማጤን ተገቢ ጉዳይ መሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ ይህንን ካላደረግን ግን ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ይሆንና ድሮ ሲነገረን እንደነበረው የሰምና ወርቅ ምሳሌ ግጥም
‹‹ውላሞ ሲል አቤት አቤት
ሲዳሞ ሲል አቤት አቤት
ጋሞ ሲል አቤት አቤት
ትግሬ ጎረበጠኝ የጣልያን ጎረቤት›› ትርጉሙ ሳይገባን መክረማችን ግድ ይለናል፡፡
እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ የአፄ ምኒልክን ታሪክ ከመጀመሪያው ጀምረን በምናነብበት ወቅት ያሉትን አጠቃላይ ሁነቶች ከቂምና ከተንኮል የጸዱ ናቸው ብለን ብናስተምር የዋህነታችንን በአደባባይ እንደመግለጽ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን ስህተት ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፍም (ገጽ 141) በዚህ መልኩ ተደግሞ እናየዋለን፡፡

‹‹የአፄ ምኒልክ ዘመን የምንመለከተው ከአሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት መጀመርያ አንስቶ በመላ ኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን ትልቅ ትርምስ በዚህም ሳቢያ ማዕከላዊው መንግሥት ተዳክሞ በዘመነ መሳፍንትና በአምባገነኖች ኃይል አገሪቱ ወደ መከፋፈል ደረጃ ተቃርባ እንደነበር በመገንዘብ ነው፡፡››

በፕሮፌሰር መስፍን ዘንድ ከተጠቀሱት ነጥቦች አንዱ አፄ ዮሐንስ ከእንግሊዝ ሠራዊት ጋር የመሠረቱት ጥምረት አፄ ዮሐንስ ሲኖሩበትም ሲገዙትም በነበረው አካባቢ ወገን ማስጠቃት የተለመደ ተግባር ነበር ተብሎ የተጻፈው ነጥብ እጅግ መኮነን ያለበት ብቻ ሳይሆን ሌሎች የዋሆች ‹‹እውነት ነው›› በሚል የዋህ አእምሮ ተሳስተው እንዳይደግሙት መረጃን አጣቅሶ መኮነን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ እውነቱ መነገር ካለበት በመክሸፍ እንደ ኢትየጵያ ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ በዋቢ መጻሕፍት ሥር ከተዘረዘሩት በጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ ‹‹ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› የተጻፈውን በመኳንንቱ መካከል የነበረውን ግልጽና ተጨባጭ የመጠቃቃት ተግባራት እንደሚከተለው ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡

አፄ ምኒልክ በ1880 ታኅሳስ 28 ደርቡሽን ለመውጋት አምባ ጫራ እንደዘመቱ በሚያትት የጽሑፋቸው ርእስ ላይ ፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹አፄ ምኒልክም መተማ አጠገብ ድረስ በያገሩ ቀለብተኛውን ምሪት አግብተው ከማህል ሰፋሪና ከዘበኛ ጋር በ17 ቀን አምባጭራ ሰፍረው 22 ቀን ተቀምጠው ከዚህ በኋላ ደርቡሽ ከምሽጉ የማይወጣ ቢሆን፣ አፄ ዮሐንስም ከሰሐጢ ተመልሰው መቀሌ ከከተማዋ ገባሁ ብለው ቢልክብዎ ወደ ሸዋ ለመመለስ በግንቦት 11 ቀን ተጉዘው ሚካኤል ደብር ሰፈሩ››

በዚህ ነጥብ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወገን ማስጠቃት ብለው ለገለጹት አባባል ምናልባትም አፄ ምኒልክ ከደርቡሽ ጋር ላለመዋጋት የወሰዱትን ዕርምጃ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ምኒልክ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የደርቡሽን ኃይል ሳይዋጉት ተመልሰዋል፡፡ እነሱም፤

1ኛ አፄ ዮሐንስ ወደ ሰሓጢ ያደረጉትን ዘመቻ በለስ ያልቀናቸው እንደሆነ ምኒልክ ከመተማ ወደ ትግራይ ለሚያደርጉት ጉዞ ሠራዊታቸውን እንደተጠበቀ እንዲቆይላቸው ከነበራቸው ፍላጎት፣
2ኛ አፄ ዮሐንስ ጣልያንን ሰሓጢ ላይ ድል አድርገው እንደሆነ በአንጻሩ ግን ንጉሥ ምኒልክ በደርቡሾች ከተሸነፉ በሁለቱም በኩል የነበረውን ባላንጣነት በንጉሥ ምኒልክ ሠራዊት መዳከም ምክንያት እንዲሁም አፄ ዮሐንስ ሰሓጢ ላይ ባገኙት የማሸነፍ ወኔ አፄ ምኒልክን ጠቅልለው ሊያሸንፍዋቸው የሚችሉበትን ዕድል ሊኖር ስለሚችል በሚሉ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ከዚህ አንጻር የነበረውን ሁነት በማይቀይር መልኩ ትክክለኛ ታሪካዊ ምልከታ ወይም ቅኝት ቢሰጠው ወገንን ለማስጠቃት በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ሰሓጢ ላይ ሲፋለም የነበረው አፄ ዮሐንስና የትግራይ ሠራዊት ነው፣ ወይስ መተማ አፋፉ ላይ ሠራዊቱን የሰልፍ ትርዒት እንዲያሳይ ሲያደርግ የሰነበተው በንጉሥ ምኒልክ የሚመራው የሸዋ ሠራዊት ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የትኛው ነው የሚያሻማው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ የዚህ መጽሐፍ ይዘት በተወሰነ መልኩ ለመቃኘት እንደተሞከረው በይዘትም በታሪክ ሁነቶች አቀራረብም እጅግ ከፈር የወጣ ከመሆኑም በላይ ለአንድ ንጉሠ ነገሥት በማድላት እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት በሕዝቦች ፈቃድ ሳይሆን በነገሥታት ችሮታ ብቻ የሚመነዘር ጉዳይ ተደርጎ ማቅረቡን፤ ከምንም በላይ ግን ጸሐፊው በአፄ ዮሐንስና በብሔረ ትግራይ ላይ ያላቸውን ጨለምተኛ አመለካከት በአደባባይ እንዲታይ ማስቻሉን አንባብያን የመሰላቸውን ፍርድ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል፡፡ በመጨረሻም በጸሐፊው ስለ አፄ ዮሐንስ አሟሟት የተገለጸው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‹‹ahistory›› ተብሎ የሚገለጽ ጉዳይ ቢሆንም የጸሐፊው የኋልዮሽ ጉዞ ግን ወዴት እያመራ አንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ ‹‹History shall remember kings but not soldiers›› በሚለው አባባል ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ በጻፉት ጽሑፍ ጽሑፌን አጠቃልላለሁ፡፡

‹‹የአገራችንም የታሪክ ጻፎች ውዳሴ ከንቱን፣ ስድብ እውነተኛውን ታሪክ አይተው የማይመስለውን ተረት የሚወድ ባይሆን ምንም ባልጎዳነም ነበር፡፡ መጽሐፋቸውንም እንኳ እውነቱን መርምሮ ለማግኘት አእምሮ ላለው ሰው ባላስቸገረው ነበር፡፡ እጅግ ያሳዝናል እስካሁን ድረስ ያበሾች ታሪክ በጨለማ ተሸፍነዋልና፡፡››

ከአዘጋጁ፡- ይህ ጽሑፍ ለ117ኛው የዓድዋ የድል በዓል የካቲት 22 ቀን 2005 ዓ.ም. በዓድዋ ከተማ በዘ አዘር ፌስስ ኦፍ ኢትዮጵያ አስተባባሪነት በተዘጋጀው መድረክ ላይ የቀረበ ነው፡፡ ፀሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው bazen.axum@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

No comments: