ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና ያልተጠኑ የበርካታ ጥንታዊ
ሥነጽሁፎች ባለቤት ናት፤ ማጥናት አቅቶን ሌሎች አጥንተው የቅጂ መብቱን ከመውሰዳቸውና የታሪክ ክፍትት ተፈጥሮ
በመጪው ትውልድ ተወቃሾች ከመሆናችን በፊት የዘርፉ ምሁራን ጥናትና ምርምር በማካሄድ፣ ዩኒቨርስቲዎች ጉዳዩን
የምርምር አቅጣጫቸው ውስጥ በማስገባት፣ ዜጎችም ጥንታዊ የጽሁፍ ሃብታችንን አስፈላጊነት ተገንዝበን ከዘራፊዎች
በመጠበቅ ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠሩ ሥነቃላዊና የጽሁፍ ፍልስፍናዎች ባለቤት
ናት፡፡ ከአስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ መልኩ በርከት ያሉ የፍልስፍና
ስራዎችን በመስራት በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፤ በጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ ከተጻፉት የፍልስፍና ስራዎቿ መካከል
ከፊሎቹን በትውልድ ካናዳዊ፣ በምርጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነው ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ
በመተርጎም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ ሲያደርግ፤ ሌሎች በርካታ በግዕዝና በአረብኛ ቋንቋዎች የተጻፉ የጽሁፍ
ስራዎች በጥንታዊ ቤተእምነቶችና ቤተመዛግብት ውስጥ ተቀምጠው ክላውድ ሰምነርን የመሰሉ ፈላስፎችንና የጥንታዊ ጽሁፎች
ተመራማሪዎችን (philologists) እይታ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ፍልስፍና በጥቅሉ የተጻፉትንና በቃል ከትውልድ ትውልድ
የሚተላለፉትን የጋርዮሽ የማህበረሰብ ወጎች፣ ልማዶች፣ጥበቦች፣ የእውቀት ዘርፎችንና አስተሳሰቦችን፤ በጠባቡ አተያይ
ደግሞ በግለሰብ ፈላስፋዎች በአንድ ዘመን ተሰርተው በጽሁፍ የተላለፉትን ስራዎች ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ በቃል
ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ማኅበረሰባዊ ፍልስፍናዎች በተረትና ምሳሌ፣ በምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በዘይቤዎች፣
በቅኔዎችና በወጎች ሊገለጡ ይችላሉ፡፡ ስለ ጾታ ልዩነት፣ እድሜ፣ ፖለቲካ፣ ስነምግባር እንዲሁም ስለ ህጻናትና
አረጋውያን ያለውን ነባር ፍልስፍና ማህበረሰቡ ባሉት የሥነቃል መከወኛ መንገዶች ያቀርባል፡፡ ለዚህም ነው ምሳሌያዊ
አነጋገሮች የረዥምና ውስብስብ ማሳመኛዎች አጭር መገለጫዎች ናቸው የሚባለው፡፡
እነ ዶክተር ክላውድ ሰምነር እና ወርቅነህ ቀልቤሳ በሥነቃላዊ
መንገድ የተላለፉትን የኢትዮጵያውያንን ፍልስፍና ከኦሮሞ ህዝብ ቋንቋና ባህል ውስጥ አውጥተው ያሳዩባቸውን ስራዎች
በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቀደምት አባቶቻችን መላው አፍሪካ ባልሰለጠነበት ዘመን ቀድመው ባህላችንንና ታሪካችንን
በድንጋይ ቀርጸውና በብራና ጽፈው ስላስተላለፉልን ኢትዮጵያ ከስነቃላዊ ፍልስፍና ባሻገር በጽሁፍ ፍልስፍናም ተጠቃሽ
ስራዎች አሏት፡፡ ምንም እንኳን በዘመናዊነት ስም ጥንታዊ ባህላችንንና ቋንቋችንን ረስተን የጽሁፍ ሃብታችንን
ሳንመረምር፣ በርካታ ዘመናትን የራሳችንን ስናንቋሽሽ፣ የምዕራባውያንን ስናደንቅ ብናሳልፍም፣ ጉዳዩ ያብሰለሰላቸው
በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና በርካታ ምዕራባውን የቻሉትን ያህል ለማሰባሰብ፣ ለማጥናትና ለዓለም ለማስተዋወቅ
ችለዋል፡፡
በዚህ ረገድ እነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ታደሰ ታምራትና
ስርግው ሃብለሥላሴ ከሃገር ውስጥ እንዲሁም ፕሮፌሰር ፓኦሎ ማራሲኒ፣ አሌሳንድሮ ባውዚ፣ ሪቻርድ ፓንክረስትና ክላውድ
ሰምነር ከውጪ ሃገር ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ካናዳዊው ክላውድ ሰምነር Classical Ethiopian
Philosophy በተባለው መጽሐፉ ከግዕዝ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጉሞ ያሳተማቸው የፍልስፍና ስራዎች- መጽሐፈ
ፊሳልግዎስ፣ አንጋረ ፈላስፋ፣ የስክንድስ ህይወትና አባባሎቹ፣ ሀተታ ዘርዓያዕቆብ እና ሀተታ ወልደ ህይወት ናቸው፡፡
እነዚህ ስራዎች በተለይ አፍሪካውያን የጽሁፍ ፍልስፍና ስለሌላቸው ፍልስፍና በአፍሪካ ውስጥ የለም በሚል ባለፉት
ሶስት አስርት ዓመታት ሲሞግቱ ለነበሩ ምዕራባውያን፤ የማያዳግም መልስ በመስጠት ለአፍሪካ የፍልስፍና ታሪክ ብርሃን
የፈነጠቁ ናቸው፡፡
የዛሬው ጽሁፌ ዓላማም እነዚህን የፍልስፍና ስራዎች በአጭሩ
ማስተዋወቅ ይሆናል፡፡ የጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ፍልስፍና፤ የውጪ የጥበብ ስራዎች ውርስ ትርጉምና ወጥ
(original) የፍልስፍና ስራዎች በመባል ይከፈላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሥነጽሁፍና ታሪክ ውስጥ በመጀመሪያው ክፍል
እንደተጻፈ የሚነገርለት የመጀመሪያው የፍልስፍና የጽሁፍ ስራ መጽሐፈ ፊሳልግዎስ (physiologus) ይባላል፡፡
ይህ የፍልስፍና ስራ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚነገርለትን የጥበብ ስራ ከግሪክ ወደ ግእዝ ቋንቋ
በመተርጎም የተሰራ ሲሆን ትርጓሜውም ተራ ሳይሆን ከኢትዮጵያ የባህልና የቋንቋ አውድ ጋር በማዛመድ የተሰራ ነው፡፡
ፊሳልግዎስ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ወይም አጋማሽ አካባቢ ከፍተኛ የመጽሐፍ ክምችት በሚገኝበት ምናልባትም
በግብጽ ሀገር በሚገኝ ገዳም ውስጥ በሚኖር ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ እንደተጻፈ ይገመታል፡፡ ፈላስፋው ሰምነር የጥንታዊ
ድርሳናት ተመራማሪው (philologist) ፍሪትዝ ሆሜል (Hommel) በ1877 ዓ.ም በለንደን፣ ፓሪስና ቬና
ቤተመዛግብት ውስጥ የሚገኙ የግእዝ ብራና ፊሳልግዎስ መጻህፍትን ከጀርመንኛ ትርጓሜው ጋር በማገናዘብ ካዘጋጀው
የተስተካከለ ቅጽ (critical edition) ላይ የተረጎመው ሲሆን ከካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ የ1951 ጣልያንኛ
ትርጉም ጋርም አመሳክሮታል፡፡ ፊሳልግዎስ ለመጽሐፉ ደራሲ የተሰጠ ስያሜ ሲሆን ይህም እንስሳትን፣ ዕጽዋትናና
የማዕድናትን ምንነት የሚገልጽና በተምሳሌት (symbolism) የሚያስቀምጥ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የስነጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠውና
ሁለተኛው ክፍለ ዘመን በመባል በሚታወቀው የአጼ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግስት (1434-68) ፤ መጽሐፈ ፈላስፋና
የስክንድስ ህይወትና አባባሎቹ የተባሉ ሁለት የፍልስፍና መጻህፍት ወደ ግእዝ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡ ምናልባት እነዚህ
ትርጉም ስራዎች እንዴት የኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚል ስያሜ ሊሰጣቸው ቻለ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ ሰምነር
እንደሚለው፤ ምንም እንኳ ስራዎቹ ትርጉም ቢሆኑም ኢትዮጵያውያን የራሳቸው የሆነ ወጥ የአተረጓጎም ስልት ስላላቸው
ኢትዮጵያዊ አሻራ ይይዛሉ “Ethiopians never translate literally: they adapt,
modify, add, subtract. A translation therefore bears a typically
Ethiopian stamp” (ኢትዮጵያውያን በትርጉም ሂደት ላይ ከራሳቸው ባህልና አውድ ጋር ለማዋሃድ ሆነ ብለው
የመጨመር፣ የመቀነስና የማሻሻል ባህል ስላላቸውና ፍጹም ኢትዮጵያዊ አሻራ አንዲኖረው በማድረግ ስለሚተረጉሙ ነው፡፡)
መጽሐፈ ፍልስፍና፤ አንጋረ ፈላስፋ ወይም የፈላስፎች አነጋገር በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከ1510-1522 ዓ.ም አባ
ሚካኤል በተባለ ኢትዮጵያዊ ከአረብኛ ቋንቋ ወደ ግእዝ የተተረጎመ ነው፡፡
መጽሐፉ መጀመሪያ በግሪክ እንደተጻፈና በ809 ዓ.ም አካባቢ
ሁናይን ኢብን ኢስሐቅ በተባለ የሜሶፖታምያ ተወላጅ ወደ አረብኛ ቋንቋ የተተረጎመ ነው፡፡ መጽሐፈ ፈላስፋ በ1953
ዓ.ም በሊቀመዘምራን ዕቁበጊዮርጊስ አንጋረ ፈላስፋ በሚል ወደ አማርኛ ቋንቋ የተተረጎመ ሲሆን በውስጡም ከጠቢቡ
ሂቃር ጥበብ ጀምሮ፤ የቅድመ ሶቅራጠስ የግሪክ ፈላስፎችን የሶቅራጠስን፣ የአሪስቶትልን (አሪስጣጣሊስ) በተለይ ደግሞ
የፕሌቶንና (አፍላጦን) የፕሌቶን ተከታዮች አነጋገሮች አካቶ የያዘ የፍልስፍና ስራ ነው፡፡ ሦስተኛው
የኢትዮጵያውያን የፍልስፍና መጽሐፍ የስክንድስ ህይወትና አባባሎቹ በሚል ርዕስ የተጻፈው ነው፡፡ በጀርመን ሀገር
ከሚገኘው የግእዝ ብራና መጽሐፍ ላይ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የተመለሰው ይህ መጽሐፍ፤ የሲግመንድ ፍሮይድ
(Oedipus complex) ንድፈ ሃሳብ የተመሰረተበትን ታሪክ በጽሁፍ ይዘው ከተገኙት አምስት የዓለማችን ቋንቋዎች
(ግሪክ፣ ላቲን፣ ሲራይክ፣ አረቢክ እና ግእዝ) መካከል አንዱ መሆኑን ይናገራል፤ ክላውድ ሰምነር። ከአረብኛ ቅጂ
ላይ የተተረጎመው መጽሐፉ በሶስት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል የስክንድስን ህይወት ታሪክ፤
ሁለተኛው ክፍል ሃያ አምስት ጥያቄዎችና መልሶቻቸውን፤ እንዲሁም ሦስተኛው ክፍል ደግሞ አንድ መቶ ስምንት የፍልስፍና
ጥያቄዎችንና ጠቢቡ ስክንድስ የሰጣቸውን ምላሾች ይዟል፡፡
የመጨረሻዎቹ ሁለት የፍልስፍና መጻህፍት ከላይ ከቀረቡት ሦስት
ስራዎች በእጅጉ የተለዩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የጽሁፍ ፍልስፍና ከጥበብ (wisdom) ስራዎች ወደ አመክኖአዊ
(rational)፤ ከውርስ ትርጉም ወደ ወጥ (original) ስራነት ለመሸጋገሩ ህያው ምስክሮች ናቸውና -
የዘርዓያዕቆብ (ወርቅዬ) እና የተማሪው የወልደ ህይወት (ምትኩ) ሐተታዎች፡፡ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን
(1599-1692) የህይወት ታሪኩንና የፍልስፍና ስራዉን ብራና ዳምጦ፣ ቀለም በጥብጦ፣ በመፃፍ ያቆየልን ኢትዮጵያዊ
አመክኗዊ (rational) ፈላስፋ ዘርዓዕቆብ፤ በሃይማኖተኝነቱ፣ በስነጽሁፍ ስራዎቹና በብርቱ አስተዳደሩ
ከሚታወቀው የአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን (1434-68) ኢትዮጵያዊ ንጉስ አጼ ዘርዓያዕቆብ የተለየ መሆኑን ልብ
ልንል ይገባል፡፡ ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ፤ አጼ ዘርዓያዕቆብ ካለፈ ከ1.5 ምዕት ዓመት በኋላ በአጼ ሱስንዮስ
የንግስና ዘመን እ.ኤ.አ በ1626ዓ.ም የተነሳ ፈላስፋ ሲሆን ሐተታ የተባለውን ፍልስፍና የሰራውም ለሁለት ዓመታት
ያህል ለብቻው ዋሻ ውስጥ ተደብቆ በቆየባቸው ጊዜያት ነበር፡፡የዘርዓ ያዕቆብና የተማሪው ወልደህይወት ሐተታዎች፤
በይዘታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ “ሐተታ” የተባለው የፍልስፍና መንገድ አንድን ጉዳይ ደረጃ
በደረጃ እየጠየቁ ጥልቅ ወደ ሆነ ምርምር የመግባትና በዚህም አንድ እውነተኛ እውቀት ላይ የመድረስ ሂደትን
ያመለክታል፡፡
ዘርዓያዕቆብ በጥንታዊት ኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት፤ በንባብ
ቤት፣ በዜማ ቤትና በቅኔ/ሰዋስው ቤት ያለፈ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ፈላስፋ ሲሆን እርሱ በነበረበት ዘመን የነበሩ
ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ሥነምግባራዊ አስተሳሰቦችን በአመክኗዊ ሐተታ (rational inquiry)
በመታገዝ ይመረምርና ይተች ነበር፡፡ የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና የፈጣሪ ህግን ከሰው ህግ፣ የተፈጥሮ ሥርዓትን ከሰብዓዊ
ሥርዓት፤መለየትንና በአንድ አምላክ አማኞች ሃይማኖት ውስጥ የሚገኙ ተገቢ ያልሆኑ የሰው ሥርዓቶችን አስወግዶ
በእውነተኛው የተፈጥሮ/የፈጣሪ ህግ ብቻ መመራት ላይ ያተኩራል። በተፈጥሮ ህግና በምክንያታዊነት መነጽር በመታገዝ
ስለሃይማኖት መከፋፈል፣ስለሙሴና ነቢዩ መሀመድ ህጎች፣ ሐሰተኛ እምነትን ስለመለየት፣ ስለአምላክና ስለሰው ህግ፣ስለ
እውነተኛ እውቀት ምንጭ እንዲሁም ስለጋብቻና ምንኩስና ተፈላስፏል፡፡ በአፍሪካ የጽሁፍ ፍልስፍና መገኘት የውስጥ
እግር እሳት የሆነባቸው ምዕራባውያን፤ የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና የኢትዮጵያውን ስራ አይደለም ሲሉ ሞግተዋል፡፡
ለምሳሌ ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ ስራው የGiusto d’Urbino ነው
ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ክላውድ ሰምነር ለዚሁ ሙግት መልስ ለመስጠት በጻፈው Ethiopian Philosophy
(Vol,II) መጽሐፍ ላይ ጊስቶ ዲ አርቢኖ ከጻፋቸው ደብዳቤዎችና ሌሎች ስራዎች፣ ሐተታው ከተጻፈበት የቅኔ ባህል፣
እንዲሁም በጉስቶ ትዕዛዝ ስለተገለበጠው ሐተታ ጸሐፊ የግዕዝ ቋንቋ እጥረት አንጻር የማያዳግም ምላሽ ከሰጠ በኋላ
የሚከተለውን ድምዳሜ አስቀምጧል፤ “MODERN PHILOSOPHY, in the sense of a personal
rationalistic critical investigation, BEGAN IN ETHIOPIA with Zara’yaecob
at the same time as in England and in France.” (በግለሰብ ፈላስፋ ደረጃ የሚካሄድ
ዘመናዊ የአመክንዮ ፍልስፍና በኢትዮጵያ ተጀምሯል፤ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ሀገር በተጀመረበት በተመሳሳይ ጊዜ
እንደማለት) ዘመንፈስቅዱስ አብርሃ፤ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ጥበብ ለአሁኑ ትውልድ ለማሳወቅና ለወደፊቱ ለማስተላለፍ
ከነበረው ምሁራዊ ሃላፊነት አንጻር ልዩ ልዩ የጥበብ ስራዎችን ከግዕዝ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በማሳተም ለንባብ
አብቅቷል፡፡ ሐተታ ዘርዓያዕቆብ ወልደህይወትንም እ.ኤ.አ በ1955ዓ.ም በፈረንሳይ ሃገር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ግእዝ
ብራና መጽሐፍ ላይ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ አሳትሟል።
ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ኪሮስም፤ የፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነርን መንገድ
ተከትሎ የዘርዓያዕቆብን ፍልስፍና ከፈረንሳዊው የአውሮፓ ዘመናዊ ፍልስፍና መስራች ሬኔ ዴካርት (Rene
Descartes) ሥራ ጋር በማነጻጸር፣ ኢትዮጵያ በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የነበራትን ሚና ለተቀረው ዓለም አጉልቶ
አሳይቷል፡፡ የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና ዛሬ ሊታወቅ የቻለው ካናዳዊ ዜግነት ባለው ሰምነር አማካኝነት ነው፡፡ የውጪ
ሰዎች የኛን ጥንታዊ መጻህፍት ለማጥናት ይህን ያህል ከተጉ እኛ ኢትዮጵያውንማ…፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና ያልተጠኑ
የበርካታ ጥንታዊ ሥነጽሁፎች ባለቤት ናት፤ ማጥናት አቅቶን ሌሎች አጥንተው የቅጂ መብቱን ከመውሰዳቸውና የታሪክ
ክፍትት ተፈጥሮ በመጪው ትውልድ ተወቃሾች ከመሆናችን በፊት የዘርፉ ምሁራን ጥናትና ምርምር በማካሄድ፣ ዩኒቨርስቲዎች
ጉዳዩን የምርምር አቅጣጫቸው ውስጥ በማስገባት፣ ዜጎችም ጥንታዊ የጽሁፍ ሃብታችንን አስፈላጊነት ተገንዝበን
ከዘራፊዎች በመጠበቅ ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል እላለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment