ሰላም! ሰላም! አንድ ወዳጄ ‹‹ይኼን ሳምንት ‘ቢቢሲ’ ይዘንባል ብሎ ተንብዮአል፤›› ብሎ እንዲሁ አንጋጦ ውኃ ያዘለ የደመና ክምር ሲጠብቅ ሰነበተ።
ይገርማል ‘ኢቲቪ’ ተናግሮት ቢሆን ኖሮ እንኳን ከሰማይ ከቧንቧ ውኃ ባልጠበቀ ነበር። አፈር ልሁንለትና የዛሬ ስንት ዓመት ገደማ አንድ ጋዜጠኛ ጓደኛ ነበረኝ። ይህ ወዳጄ አብዝቶ ስለሙያው ክብርና ትልቅነት ያጫውተኝ ነበር። እና አሁን ሳስበው እንኳንም ቆሞ አላየ እላለሁ። ምኑን ካላችሁ መልሱ ‹‹ሁሉን!›› የሚል ነው። እንኳን እሱ ሌላውም ቢሆን። ጥቂቶች ሊባል በሚያስቸግር ሁኔታ ሆዳቸውን እንጂ የሙያ ክብራቸውና ግዴታቸውን የረሱና የስንቱን ሙያ ስም ክፉኛ ያጠፉ አሉም አይደል? ማለቴ አሁን ደላላ ሲባል ስሙንም ሰውዬውንም ማን ያምናል? እሱን እኮ ነው የምላችሁ። ታዲያ ፀሐይ ሰልችታው የ‘ቢቢሲ’ን ትንቢት ተስፋ ወደሚጠባበቀው ወዳጄ ስመለስ፣ ይኼው ወዳጄ አንድ ነገር አስታወሰኝ። እርሱም የአገራችን የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ ነው። እያደር እያሸማቀቀን እያደር ይፋዊና ሕጋዊ የወንጀል አደባባይ እየሆነ መምጣቱን ሳስብ ሥጋቴ ያይላል።
እኔስ ደላላ ነኝ፤ እንዲያው ግን እንደኔ ያውም ከእኔ በላይ ለኅብረተሰቡ መረጃን የማግኘት መብት የሚተጉ እውነተኛ ጋዜጠኞችን ሳስብ ሐዘኔ ለከት አይኖረውም። ‹‹ኧረ አሁንማ በአንድ ጣት የሚቆጠሩ ጋዜጦችና መጽሔቶች እኮ ናቸው የቀሩን!›› ይለኛል ከአንድ ስኒ ቡና ጋር ጋዜጣ ማንበብን በፍቅር የሚወደው የባሻዬ ልጅ። ፍቅሩ ምኞት ሆኖበት ሲተክዝ ብዙ ጊዜ ሳገኘው። (‘እንደተመኘኋት አገኘኋት’ የሚለው የድል ዜማ ለማዜም አልሆንልን ያለው በሚዲያ ነፃነቱ ብቻ አለመሆኑን ልብ ይሏል።) ብቻ ‘በዚህ ሉዓላዊነት ሁሉንም ነገር በሰከንዶች ውስጥ በሚያቀናጅበት ዘመን የእኛ እያደር እንዲህ መሆን ምን ይባላል?’ ብላችሁ ማንንም ሰው ብትጠይቁ መልሱ ‘ዝም’ ነው። ‘ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም!’ እኛም እዚህ ላይ ስለሚዲያ ማውራታችንን አቁመን ‘ዝም' ብንልስ!? ጨጓራችንን በሁዳዴ ፆም ለምን እናቃጥል?
‘ሚዲያ’ን አንስቶ ‘ፕሪሚየር ሊግ’ን መርሳት ልጅን ጠርቶ አባትን መዘንጋት ስለሚሆን ትንሽ ስለቴዎድሮስ ደመኛ አገር እንግሊዝና የእግር ኳስ ሊጓ መጨዋወት አለብን። ‹‹‘ገደልን እንዳይሉ ሙተው አገኟቸው፤ ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው፤ ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው፤ ለወሬ አይመቹም ተንኮለኞች ናቸው፤’ ባልንበት አፋችን በቪክቶሪያ አገር ኳስ መደበራችንን ተያይዘነዋል። ‹‹ለዚህ ደግሞ ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ያሉት ሚዲያዎቻችን በተለይ ‘ኤፍኤም’ ሬዲዮ ጣቢያዎች ውለው ይግቡልን፤›› ሲል ምፀተኛው ወዳጄ ሦስተኛው ወዳጃችን ሰማውና፣ ‹‹ታዲያ ስለምን ይንገሩን? መቼም አንዳንዱ ባለሥልጣን በሕዝብ ሀብት ምን እየሠራ፣ እየበላ፣ እየገዛ፣ እየጠጣ፣ ወዘተ ከሚነግሩን ይልቅ አንድ የእግር ኳስ ተጫዋች በላቡ ከሱፐር ማርኬት ‘አስቤዛ’ ሲያደርግ ስለሚያወጣው ዶላር ቢነግሩን ሰላማችን እንደተጠበቀ ሳንታወክ እናዳምጣቸዋለን፤›› ብሎ መለሰለት። ምድረ ሙሰኛ ታሪኩ ቢዘገብ አገር እንደምትፈርስ ስናስብ የኳሱ ወሬ ይበል ይቀጥል ለማለት አሰኘን። ‘የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ’ አሉ ባሻዬ!
ለማንኛውም እናንተ እንዴት ሰንብታችሁልኛል? የዋጋና የኑሮ ንረትስ እንዴት እያደረጋችሁ ነው? ‹‹አይ! ተው የኑሮንስ ነገር አትጠይቀኝ፤›› ይለኛል የሙያ አጋሬ ደላላ ወዳጄ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹ነጋ ብለኸው ሳትጨርስ በሚመሽበት በዚህ ፈጣን ጊዜ እንዴት ተደርጎ ነው ኑሮ የሚጠየቀው? እስኪ ራስህን ልጠይቅህ?›› ይልና ወደኔ ነገሩን ይመልሰዋል። እንዲህ ስንመላለስ እውነትም ቀኑ ይመሻል። ታዲያ የባሻዬ ልጅ ሁልጊዜ የሚላት ነገር ትዝ ትለኛለች።
‹‹ቀን የሚሆን እየመሰለን ስንሮጥ ሌት፣ በሐሳብ ታመን እንቅልፍ በዓይናችን ሳይዞር መልሶ እየነጋ መቼ መኖር ልንጀምር ነው?›› ሲል የምስቀው ይታወሰኛል። እውነት ለመናገር የምስቀው የተናገረው ‘ኮሜዲ’ ሆኖ ሳይሆን አለመኖራችንን እያሰብን መኖራችንን ማወቃችን በማሰቤ ነው። ‹‹እኔ ማውቀው . . .›› ይላል አንድ በቀንም በማታም መጠጥ ዘመዱ የሆነ የሠፈራቸን አውቆ አበድ። እኛም ‘እኔ የማውቀው አለማወቄን ነው!’ ይላል ብለን ስንጠብቀው፣ ‹‹እኔ የማውቀው እየኖርኩ አለመኖሬን ነው!›› ይልና ብቻውን ይስቃል። ሕመም የተሸከመ ሳቅ። ለነገሩ አትፈርዱም፤ መንግሥታችንም የ‘ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ሲባዝን የእኛን ኑሮ ድብን አድርጎ እየረሳው መጣ። ‹‹ግድ የለም ይርሳው ብሎ ብሎ በእኛ ‘ቢዚ’ ይሁን?›› ልጃቸው ማለቱን ባሻዬ ሲሰሙ፣ ‹‹አሁን ‘ቢዚ’ የሆነው በማን ሆኖ ነው ታዲያ?›› ብለው መስቀለኛ ጥያቄ ይጠይቁታል። እንግዲህ መስቀለኛ መንገድ በባህሪው የአራት የተለያዩ አቅጣጫ አውራ መንገዶች መገናኛ ነው። የባሻዬ ልጅ ግን አራት ጊዜ አባቱን ‹‹እንጃ!›› እያለ ይመልስላቸዋል። ከፈለጋችሁ አምስተኛ ‘እንጃ’ መጨመር ትችላላችሁ!
ይወራ ቢባል ነገሩ እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት ከሰው ልጅ የማያቋርጥ የመውለድ ሱስ ጋር የትየለሌ ሆኗል እኮ። በተቃራኒው ለማስረዳት የእኔና የእናንተ ጊዜ ብቻ ነው እያነሰ የመጣው። የብዙ ነገሮች ‘ኔትወርክ’ ባለመሥራቱ በየዕለቱ አላገናኘን ብሎ ይኼው በሳምንትም ለመተንፈስ አልበቃን ይላል። ምን ታደርጉታላችሁ? ለወር ያላችሁት ለሳምንት፣ ለዓመት ያላችሁት ለወር እየሆነ ካስቸገረ ቆየ። እናንተ እሱን ትላላችሁ? ሰው ሁሉ ለወሬና ለሐሜት ጊዜውን በሰፊው በመደበበት ዘመን የእኔና የእናንተ የሳምንት ሰዎች መሆን ይበልጥ አይደንቅም? እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ስላለኝ ላጫውታችሁ።
ሁለት የልብ ጓደኛማቾች በጣም እየተጠፋፉ መገናኘታቸውን በማስመልከት ሲገናኙ፣ ‹‹ወይ ጉድ! እንዲህ ትጠፋ እንዲህ እልም ትል?›› በመባባል ብዙ ሰዓት ያጠፉ ጀመር። በኋላ አንደኛው ከስንት ጊዜ አንዴ ለሚገናኙትም ጊዜያቸውን ‘እንዲህ እንጠፋፋ?’ በማለት እንደሚጨርሱት ታዝቦ፣ ‹‹ወዳጄ ምነው ቁም ነገር ብንጨዋወት? ስንት ጉዳይ እያለ ስለቤተሰብ፣ አገር፣ ፖለቲካና የኑሮ ሁኔታ መጨዋወት ስንችል . . .›› ብሎ ሳይጨርስ ወዳጁ አቋርጦት ‹‹ያው ነው እባክህ። ስላልካቸውም እናውራ ብንል ከአንድ ቃል ውጭ ሌላ አይኖረንም፤›› አለው። ‹‹ለመሆኑ ያ ቃል ምንድን ነው?›› ብሎ ሲጠይቀው ምን ያለው ይመስላችኋል? የእንግሊዝኛውን ሳይሆን (የእንግሊዝኛ ነገር የማይሆንላችሁ እንኳን የሰማችሁትን ያያችሁትን ሳይቀር በእንግሊዝኛ ለመረዳት ለምትጥሩ የተብራራ) የአማርኛውን ‹‹ጉድ!›› ጠርቶለት አረፈው። እውነት አይደል ታዲያ? ከላይ እስከታች ያልተሸከምነው ምን ‘ጉድ’ አለ?
ከሥራዬ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ያጋጠመኝን ልንገራችሁ ደግሞ። የዋጋ ንረት እንላለን እንጂ ለምዶብን የመሸጥ የመለወጡ ነገር ምንም የሚቀንስ አይደለም። በተለይ እንደ እኛ ሆናችሁ ስታዩትማ ይብሳል። እናማ ባለፈው ሰሞን የማውቀው ወዳጄ ‘አይሱዙ’ መግዛት ፈልጎ ወዲያ ወዲህ ስል ቆየሁና አግኝቼለት አስፈትሸን ስናበቃ ሊገዛው እንደሚፈልግ አሳወቀኝ። የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ የመኪናውን ‘ሊብሬ’ ስም ለማዛወር ውልና ማስረጃ አብረን ካልሄድን አለኝ። እኔም አንድም ወዳጄ ስለሆነ ሌላም ከኮሚሽኔ ውጭ ጭማሪ (ቅንጥብጣቢ እንዳልል ፆም ነው) ነገር አላጣም ብዬ ሄድኩላችሁ።
ጠዋት የቆምን እኩለ ቀን አልፎ ከሰዓት ሆነላችሁ። ‹‹እንዴ! ምንድን ነው ነገሩ?›› ይላል እንደኔው የተገረመ። ሠራተኞቹ የተቻላቸውን ያህል ቢሠሩም ሰው በላይ በላዩ ይነባበራል። ከአስተናጋጆቹ መሀል አንዳንዶች ሲጮሁ እንሰማለን። ‹‹ቀስ በያ! አንድ ነገር ሳይጣራ ቢያልፍና ስህተት ሆኖ ቢገኝ እኮ እስር ቤት ነው የምላከው!›› ሲሉ ይሰማሉ። ከተስተናጋጁ መሀል አብዛኛው እርስ በእርሱ ይንሾካሾካል። ‹‹ድንቄም ቅልጥፍና›› ሲሉ አንዲት አዛውንት፣ ‹‹ህም! መልካም አስተዳደር ብሎ ዝም! እንዴት አመናጭቆኝ እንደሄደ ታያላችሁ?›› ትላለች አንዲት ወጣት። ትርምሱ እየጋለ ሰው በጥበቃና በመታከት እየዛለ ተቀምጦና ቆሞ ተራውን ይጠባበቃል። ‹‹አዬ! እንዲህ ያለውን አሠራር እኮ ማንም መጣ ማንም ከዚህ በላይ ሊያሻሽለው የሚችል አይመስለኝም። ወንድም ወንድሙን ልጅ እናቱን ጉድ በሚሠራበት ዘመን እንዴት ብለው እነሱስ ቶሎ ቶሎ ይሥሩ?›› ይላል አንድ ጎልማሳ። ፖለቲካው፣ ማኅበራዊ ሕይወቱ፣ ኢኮኖሚው በሁሉም አንደበት እንደሁሉም እየተተነተነ ይቀጥላል። በጥበቃ ብቻ አንድ ቀን ከዕድሜ ላይ እየተቀነሰች ለጭውውት በር ትከፍታለች!
በሉ እስኪ እዚህ ላይ የሳምንት ሰው ይበለን። ከዚያ በፊት ግን ባሻዬ ሰሞኑን ሲያጫውቱኝ የነበረውን ነገር ላካፍላችሁና ይብቃን። ሁዳዴ ከገባ ጀምሮ ይኼው ሳምንታቸው ባሻዬ ፆማቸውን ውለው ቡና የሚጠጡት ከእኔ ጋር ሆኗል። ከዚሁ ከፆሙ ጋር በተያያዘ የቅበላ ቀን በአዲስ አበባ (ቦታው በውል የት እንደሆነ ተዘነጋኝ) የሥጋ ‘ኤግዚቢሽን’ ነበረ መባሉን አንስቼ ሳጫውታቸው ቆየሁ። ታዲያ እሳቸውም ትዝብታቸውን ያጫውቱኝ ያዙ። ‹‹እኔን እኮ የሚገርመኝ ሰው ለራሱ ብሎ ማድረግ የሚገባውን ነገር ግዴታ ሆኖበትና ይሉኝታ ይዞት ሲያደርገው የማየው ነገር ነው። እምነት ደግሞ ውስጣዊ ነገር እንደመሆኑ መጠን እኮ ልጅ አንበርብር፣ የልብ ፆም ነው ከሁሉ የሚበልጠው፤›› ብለውኝ ሲያበቁ ‹‹ኤድያ! አሁንማ ላይ ላዩን ሆነ ነገሩ ሁሉ፤›› ብለውኝ በረጅሙ ተነፈሱ። እኔም ዝም እንዳልኩ የውስጣቸውን እስኪተረትሩት መጠበቅ ያዝኩ። ባሻዬ ቀጠሉ፣ ‹‹ተማሪው ዩኒፎርሙ እንጂ ያለው የትምህርት ወኔው ተሰልቧል። አስተማሪውም ገቢውን እንጂ ሙያዊ ግዴታውን ረስቷል።
ሹማምንቱ ገጽታቸው እንጂ ሥራቸው የታይታ ብቻ ነው። ሰውም የሚጠበቅበትን ትቶና ሸሽቶ ለቁሳዊና ብልጭልጭ ነገሮች መንፈሱን ሸጦታል። እንዲው ምን ይሻለናል ብለህ ብትጠይቅ መልሱ ከቋጥኝ ከብዶልሃል፤›› ብለውኝ በዝምታ ተሸብበው ቡናቸውን ፉት አሉ። ነገሩን ሳብላላው ነገሩ በሙሉ ከላይ እስከ ታች ከአንገት በላይ ከሆነ መሰነባበቱን ተረዳሁ። ግን እስከ መቼ ከአንገት በላይ? የእኛስ ነገር የቁራ ጩኸት ሆኖ የሚቀጥለው እስከ መቼ? የባሻዬ ልጅ እየሳቀ፣ ‹‹‘ከአንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም’ የሚባለው ተረስቶ ከአንገት በላይ ሲኮን ችግር አለ፡፡ እስከ መቼ ከአንገት በላይ ብለን ደግመን ደጋግመን እንጠይቅ፤›› ሲለኝ፣ እኔም ወደናንተ አደረስኩት!
No comments:
Post a Comment