*ኢህአዴግ - “ቀፎ ከእኔ፤ ማር ከእናንተ!” እያለ ነው
*መንገድ ትራንስፖርት - “መንገድ ከእኔ፤ ትራንስፖርት ከናንተ!” ይላል
ሁልጊዜ
ምን እንደሚገርመኝ ታውቃላችሁ? የኢህአዴግ ነገር! አልሳካ ብሎት እንጂ ሁላችንንም እንደቀለበት መንገድ ጥፍጥፍ
አድርጐ በአንድ ቅርፅ ቢሰራን ደስታውን አይችለውም፡፡ (ከፍቅሩ የተነሳ እኮ ነው!) በተለይ ተቃዋሚ
ፓርቲዎችንማ---ሁሉንም በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ቢያጠምቃቸው እፎይ ብሎ እንቅልፉን በለጠጠ ነበር፡፡ ግን
እኮ አምባገነንነት አምሮት አይደለም (ኧረ ሲያልፍም አይነካው!) በነገራችሁ ላይ … በአምባገነኖች ላይ ባደረግሁት
Formal ያልሆነ “ባህላዊ ጥናት”፤ አብዛኞቹ አምባገነኖች የእግዚአብሔርን ስም ደጋግመው መጥራት እንደሚወዱ
አረጋግጬአለሁ፡፡ (ማጭበርበርያ እኮ ነው!) ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት በካንሰር ህመም የሞቱት የቬንዝዌላው የቀድሞ
ፕሬዚዳንት ሁጎ ቻቬዝና የቀድሞው የኡጋንዳ ፕሬዚደንት ኢዲ አሚን ተጠቃሽ ናቸው - የፈጣሪን ስም በመጥራት፡፡
አሚንማ ከእግዚአብሔር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አደርጋለሁ ባይ ነበሩ፡፡
በዚህ ጥናት መሰረት ታዲያ የጥንቱ ሶሻሊስት “ነፍሴ ኢህአዴግ”
አምባገነን አለመሆኑን ደርሼበታለሁ (የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ አያቅማ!) እናላችሁ --- ኢህአዴግ የአገሩን ህዝብ
ጥፍጥፍ አድርጎ መሥራት የሚመኘው ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት አገራዊ ራዕይ እንዲኖረው ከመፈለግ ብቻ ነው! ሌላ
ሌላውን ዝባዝንኬ ትቶ ልማት ላይ ብቻ እንዲተጋለት! (እንደኢህአዴግ ከልማት ጋር በፍቅር የወደቀ ፓርቲ አይቼም
ሰምቼም አላውቅም) በሌላ አነጋገር አንድ ልማታዊ ህዝብ ለመፍጠር ነው! በደርጉ ዘመን One people one
country (አንድ ህዝብ አንድ አገር እንደማለት!) እንደተባለው ግን አይደለም፡፡ በሁለቱ መካከል የሰማይና
የምድር ያህል ልዩነት መኖሩን እንዳትዘነጉ፡፡ አያችሁ--- የደርግ መነሻው ትምክህት ነው (ኢህአዴግ እንደነገረን)
የኢህአዴግ ግን ልማት ነው - ድህነት ተረት ማድረግ! (አሁንም ኢህአዴግ እንደነገረን) ለዚህ እኮ ነው ኢህአዴግ
ተቃዋሚዎች “ድብር” የሚሉት፡፡
“ልማታዊ ተቃዋሚ” ቢሆኑለት እልል ባለ ነበር፡፡ በነገራችሁ ላይ
ኢህአዴግ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ቢጠናከር እኮ ደስታው ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ቢበራከቱም አይጠላም፡፡ እሱ የሚጠላው
ተቃውሞ ነው (የማይቃወሙ ተቃዋሚዎች የሉም እንዴ?) ምን መሠላችሁ? ተቃውሞ ፈርቶ እኮ አይደለም! ሌላ ሌላውን
ቢቃወሙ እኮ ግድ የለውም፤ ልማቱን ሲቃወሙበት ግን … ባለ ሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገቱን (ለጊዜው ድምፁን
ቢያጠፋም) አንቀበልም ሲሉት ግን … ለኑሮ ውድነቱና ለዋጋ ግሽበቱ ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው ሲሉ ግን …
ድምጥማጣቸውን ቢያጠፋቸው በወደደ! ግን አድርጎት አያውቅም፡፡ ለምን? ኢህአዴግ በስሜት የሚነዳ ፀብ ጫሪ ፓርቲ
አይደለማ - ያመዛዝናል፡፡ ስላመዛዘነም ይኸው ዛሬም ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር ይተጋል፡፡ እንዲያ ባይሆንማ
ለምርጫው ሥራ ማስፈፀሚያ ተብሎ ከተሰጠው ሚሊዮኖች ብር ቆንጥሮ ለምስኪኖቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አይለግስም ነበር፡፡
(ለካስ ኢህአዴግ ሳይታወቅበት “ቸር ፓርቲ” ነው) ችግሩ ግን
ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ ጠባይ እንደሌለው ሁሉ እድልም የለውም - የመመስገን! (ደግነቱ ሶሻሊስት በዕድል
አያምንም!) ግን እስቲ አስቡት -- 2 ሚሊዮን ብር ተካፈሉ ብሎ የሰጠ ፓርቲ እንዴት ምስጋና ይነሳል? ገንዘቡ
በምርጫው ለሚሳተፉ ፓርቲዎች ብቻ ነው የሚሰጠው የሚል መስፈርት ስላወጣ ብቻ “ደግነቱን” አፈር ድሜ አስበልተው
“እቺቺማ እጅ ጥምዘዛ ናት ---- አንቀበልም!” አሉ - አንዳንድ ተቃዋሚዎች፡፡ ደርግ ቢሆን ኖሮ እኒህን
ተቃዋሚዎች ምን እንደሚላቸው ታውቃላችሁ? “ወርቅ ሲያነጥፉላቸው ፋንድያ ነው ይላሉ!” እርግጥ ነው ኢህአዴግ ይሄን
ገንዘብ የለገሰው ደግነቱን ለማሳየት አልነበረም - ይልቁንም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ምን እንደሚመስል ትንሽዬ ሙከራ
ቢጤ ለመሥራት አስቦ ነው፡፡
እኔ የምለው ግን ---ከ97 ምርጫ በኋላ የኢህአዴግ ልሳን
በሆነው አዲስ ራዕይ መፅሄት ላይ ስለተቃዋሚዎች ምን ተፅፎ እንደነበር ታውቃላችሁ? ኢህአዴግ ፤ ተቃዋሚዎች ዳግም
እንዳያንሰራሩ በትጋት እንደሚሰራ ገልፆ ነበር (ደንግጦ ነዋ!) ግን እኮ አላደረገውም፡፡ አድርጐታል እንዴ?
በፍፁም! ለምን ይመስላችኋል? የፓርቲው ዲሞክራሲያዊ ባህሪ አይፈቅድለትማ! በእርግጥ አንዳንድ ኢ-ዲሞክራት የፓርቲው
አመራር ወይም አባላት አሊያም ፅንፈኛ ካድሬዎች የተቃዋሚዎችን አለማንሰራራት አይፈልጉትም ማለት አይደለም፡፡
(ፓርቲው የመላዕክት ስብስብ እኮ አይደለም) እንዴ … የ “97ቱ የምርጫ ናዳ” ሌላም ያሳስባል እኮ! አንድ
ኢህአዴግ ወዳጄ ምን እንዳለኝ ታውቃላችሁ? “ምርጫ ሲመጣ ፍርሃት ፍርሃት ይለኛል!” አያችሁ … የምርጫ ፎቢያ መሆኑ
እኮ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ የምርጫ ፎቢያ ያለባቸው ኢህአዴጎች አሁን አሁን ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ እኔ እኮ
አንዳንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ምርጫ ሲቃረብ ድንገት ተነስተው ተቃዋሚዎችን ሲሳደቡና ሲዛለፉ “የምን
እንደሰፈር ልጅ ነገር ፍለጋ ነው” እያልኩ እቀልድባቸው ነበር፡፡
ለካስ እነሱ ተቸግረው ነው - በምርጫ ፎቢያ!! እስቲ አስቡት …
ያኔ እኮ (በ97 ምርጫ ማለቴ ነው) ኢህአዴጐች ከሥልጣን ተወርዶ በህይወት የሚኖር ሁሉ አይመስላቸውም ነበር፡፡
ይሄኔ ነው (ነፍሳቸውን ይማረውና) የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “መተካካት” የሚል ስራቴጂ የቀረፁት፡፡
አያችሁ--- አሁን ኢህአዴግ እንደ 97 ዓይነቱ የምርጫ ናዳ ቢወርድበት (የሰይጣን ጆሮ አይስማው---ብያለሁ)
እንደዚያ ጊዜ አይርበደበድም፡፡ ለምን አትሉም ---ከግማሽ በላይ አመራሩ ሥልጣን ኦክስጂን እንዳልሆነ
ተገንዝቦታል፡፡ ዕድሜ ለመተካካት! አያችሁ --- አሁን የኢህአዴግ አንጋፋ አመራሮች በኢቲቪም ሳይቀርቡ መኖር
እንደሚችሉ በተግባር አይተውታል፡፡ (እንደገና መወለድ አትሉትም!) ጠ/ሚኒስትሩን በዚህ ከልቤ አመሠግናቸዋለሁ፡፡
ፈጣሪ ትንሽ እድሜ ቢሰጣቸው ኖሮ -- ኢትዮጵያ ያለ ኢህአዴግም መኖር እንደምትችል ያሳዩን ነበር (በ3ሺ ዘመን 3ሺ
መንግስት ያየች አገር እኮ ናት!) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግ ለ30 እና 40 ዓመት ሥልጣን ላይ መቆየት እፈልጋለሁ
የሚለውን “ምኞቱን” አሁንም ካልቀየረ የግድ “የሥልጣን እፎይታ” ያስፈልገዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ (የግብር
እፎይታ እንደሚባለው) ምን ችግር አለ … ትንሽ እረፍት አድርጎ ወይም ትንፋሽ ወስዶ ይመለሳል፡፡
ያለዚያ እኮ ይታክተዋል፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን እንደያዘ ሰሞን
አንዳንድ የትጥቅ ትግል የሚያራምዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፓርላማ ወጥተው ሲያስቸግሩት ምንድነው ያለው? ይዋጣልን እኮ
አላላቸውም! “እኛ ጦርነት ሰልችቶናል!” ነበር ያላቸው፡፡ ምናልባት አይመስለን ይሆናል እንጂ ሥልጣንም እኮ
እንዲሁ ይሰለቻል፡፡ (ማርም ሲበዛ ይመራል ነው ነገሩ!) የአፍሪካ አምባገነኖች ከ40 ዓመት በላይ ሲገዙ ለምን
አልሰለቻቸውም … ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ልክ ናችሁ - ግን ደግሞ ኢህአዴግ አምባገነን አይደለማ! ቢያንስ በመርህ
ደረጃ “ዲሞክራሲያዊ” ፓርቲ መሆኑን እናውቃለን! ስለዚህ ዝም ብለን ለረዥም ጊዜ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ካደረግነው
አንድ ቀን ሳንዘጋጅ “ ሥልጣን ሰልችቶኛል፤ ተረከቡኝ!” እንደሚለን ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ (ያኔ ጉድ ነው!)
እውነቴን እኮ ነው … ኢህአዴግ “ሥልጣን በቃኝ” ቢለን ወንበሩ ላይ ማንን ልናስቀምጥበት ነው! በእርግጥ ይሄ ሁሉ
ተቃዋሚ (ያኔ ደግሞ ይጨምራል) የማንን ጎፈሬ ያበጥራል ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ሁሉም ለሥልጣን የሚታገል መሆኑ እኔስ
መች ጠፋኝ፡፡
እኔን የሚያሳስበኝ እንደ ኢህአዴግ “ልማታዊ ፓርቲ” ከየት
እናመጣለን የሚለው እኮ ነው፡፡ (“ብቸኛ አማራጭ እኔ ብቻ ነኝ” ያለው እኮ ወዶ አይደለም!) እንግዲህ “ልማታዊ
ፓርቲ” ከጭቃ ተጠፍጥፎ አይሰራ ነገር! አልገባንም እንጂ---- ኢህአዴግ በተቃዋሚዎች ብግን የሚለው እኮ ለዚህ
ነው፡፡ (ሥልጣን ይጋሩኛል በሚል ስጋት እንዳይመስላችሁ) አንድ ቀን ሥልጣን ቢታክተኝ ማነው እቺን አገር የሚረከበኝ
ብሎ ሲያስብ ስጋት ይገባዋል (አርቆ አሳቢ ነዋ!) እውነቱን እኮ ነው! የጀመረውን ግድብ፤ የመንገዱንና የተፋሰሱን
ሥራ፣ የኮንዶሚኒየም ግንባታ፣ የስኳሩን ፋብሪካ፣ የባቡር መስመሩን ዝርጋታ፣ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያውን … ወዘተ
ማነው የሚያስቀጥለው? (ራዕዩንማ መንገድ ላይ ጥሎ ሥልጣን አይለቃትም!) እንጂማ ተቃዋሚዎች ያሻቸውን ፖሊሲ ቢቀርፁ
እሱ ምን ተዕዳው! ኢህአዴግን ሁሌም የሚያሰጋው “ሥልጣን በቃኝ” ስል የትኛው ፓርቲ ነው የሚረከበኝ የሚለው ጉዳይ
ብቻ ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው አንድ አይነት ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው ህዝብ መፍጠር የሚሻው። ይኸውላችሁ… ባለፈው
ጊዜ የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሬድዋን “ተቃዋሚዎች በምርጫው ተሳተፉም አልተሳተፉም ትርፍም ኪሳራም
የላቸውም” ያሉት ለክፋት እኮ አይደለም፤ ወይም ደግሞ የተቃዋሚዎችን ጨጓራ ለመላጥ አስበው እንዳይመስላችሁ፡፡
“እንዴት--- ከኢህአዴግ ተምረው ልማታዊ ፓርቲ መሆን
ያቅታቸዋል” በሚል የመቆርቆር ስሜት ነው፡፡ (ይሄ የእኔ ቅዱስ ግምት ነው!) ሰሞኑን ደግሞ ምን አሉ መሰላችሁ?
ኢህአዴግ ሁሉን ነገር በሁለት መክፈል ይወድ የለ! (እንደ አራተኛ ክፍል የሣይንስ ትምህርት) ተቃዋሚዎችንም በሁለት
ከፍለው እንደሚያዩአቸው ተናገሩ - እናም በሚያዝያው አካባቢያዊ ምርጫ ላይ (በቂ አቅምና እጩዎች ባይኖራቸውም)
ለመሳተፍ ዝግጁ ለሆኑ ተቃዋሚዎች ሁሉ አድናቆታቸውን ካቀረቡ በኋላ ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉትን ሁሉ ነቅፈዋል፡፡
(ዝም ብለው ነው እንጂ መብታቸው እኮ ነው!) በመጨረሻ የተናገሩት ግን እንኳን ፓርቲዎቹን እኔንም አስደንግጦኛል፡፡
ምን መሰላችሁ ያሉት? “ሁሉም ተቃዋሚዎች ስለ ዲሞክራሲ ያላቸው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው” ብለው ሁሉንም በጅምላ
ደፍጥጠዋቸው አረፉ፡፡
እኔ የምለው--- ኢህአዴግ “ተናጋሪ አይውጣልህ” ተብሏል እንዴ?
ቆይ እስቲ… ልማታዊ ነኝ የሚል ፓርቲ ወዳጅ እንጂ ጠላት ማብዛት ምን ይጠቅመዋል? በዚህ አካሄዱ “ስልጣን
የደከመው” እለት ማን ሊያሳርፈው ነው? (ቀባሪ አታሳጣኝ እንደሚባለው ሥልጣን ተረካቢ እንዳያጣ!) እኔ የምላችሁ…
የምርጫ ቅስቀሳ ተጀምሯል አይደል! አደራ እንግዲህ (ለፓርቲዎች በሙሉ ነው!) ቅስቀሳውን ባህላዊ እንዳታደርጉብን፡፡
(የኢህአዴግን ቡናና ፈንዲሻ ማለቴ እኮ አይደለም) ለምን መሰላችሁ… ይሰለቸናላ! (ልክ ወደፊት ኢህአዴግ ሥልጣን
እንደሚሰለቸው!) አያችሁ… ቅስቀሳው ከሥልጣን ከወረደ 21 አመት ያለፈውን ደርግን እያነሱ የእርግማን መአት ማውረድ
ከሆነ “ድክሞ” ይሆንብናል፡፡
እኛ እንደ ህዝብ የምንፈልገው አሁን በእጃችሁ ያለውን ነገር ብቻ
ነው (ዋናው ይዞ መገኘት ነው ሲባል አልሰማችሁም?) ደርግማ የሚያወዳድመውን አወዳድሞ የታሪክ ዶሴ ውስጥ ገብቷል!
ባይገርማችሁ አንዳንድ የኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች ደርግን ብቻ ሳይሆን የንጉሱን ፊውዳላዊ ሥርዓትም እያነሱ
እርግማን ሊያወርዱ ይዳዳቸዋል (የንጉሱ መንግሥት ከተገረሰሰ 40 ገደማ ሊሆነው እኮ ነው!) እናም የፖለቲካ
ፓርቲዎች --- የራሳችሁን ጉዳይ ብቻ እንድትነግሩን አደራ እንላችኋለን! ሌላውን ሁሉ ለታሪክ ተውለት! በቃ እናንተ
የእናንተን ብቻ ንገሩን! አንዳንድ “መራጮች” በኢቴቪ ስለሚመርጡት ፓርቲ ሲናገሩ ሰምታችኋል? “እኔ የምመርጠው
ለአገር ልማትና እድገት የሚሰራውን ፓርቲ ነው” ይላሉ፡፡
ስሙን መጥራት እኮ ነው የቀራቸው! (የመራጮች ቅስቀሳ የሚባል
ነገር ተጀመረ እንዴ?) በተረፈ ምርጫው ሰላማዊ፤ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ሁሉም በትጋት ይፀልይ! የዛሬውን
ፖለቲካዊ ወጌን ከመቋጨቴ በፊት በቴሌኮሙ የSMS አገልግሎት ከአንድ ዳያስፖራ ወዳጄ የደረሰኝን መረጃ ላጋራችሁ
(Information is power ይሉ የለ ፈረንጆቹ!) ኢህአዴግ - ቀፎ ከእኔ፤ ማር ከናንተ! ኢቴቪ -
ፕሮፓጋንዳ ከእኔ፤ መዝናኛ ከናንተ! ውሃና ፍሳሽ - ቆጣሪ ከእኔ፤ ውሃ ከናንተ! መብራት ኃይል - ግድብ ከእኔ፤
መብራት ከናንተ! መንግሥት - የዋጋ ግሽበት ከእኔ፤ ኑሮ ከናንተ! ዳያስፖራ - ፖለቲካ ከእኔ፤ መስዋዕትነት
ከናንተ! መንገድ ትራንስፖርት - መንገድ ከእኔ፤ ትራንስፖርት ከናንተ! ትምህርት ሚ/ር - ት/ቤት ከእኔ፤ ትምህርት
ከናንተ! ፍትህ ሚ/ር - ህግ ከእኔ፤ ፍትህ ከናንተ! ተቃዋሚ - ተቃውሞ ከእኔ፤ አማራጭ ከናንተ! የሆቴል
ባለቤቶች - ህንፃ ከእኛ፤ መስተንግዶ ከናንተ! የግል ኮሌጆች - ፕሮሞሽን (ማስታወቂያ) ከእኛ፤ ብቃት ከናንተ!
እኔ ደግሞ ቴክስት ሜሴጁን አንብቤ ሳበቃ እንዲህ የምትል ሃሳብ መጣችልኝ… ለናንተ! “መረጃ ከእኔ፤ ጋዜጣ
ከናንተ!” በመጨረሻም መልካም የሰንበት ጊዜ እላችኋለሁ - “ምኞት ከእኔ - ሰንበት ከናንተ!”
1 comment:
የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.
Post a Comment