Monday, April 1, 2013

ይሓ

በቅድመ አክሱም ታሪክ የይሓን ሥልጣኔ በ100 ዓመት ወደፊት የሚያስቀድም 2 ሺሕ 800 ዓመት ዕድሜ ያለው ጥንታዊ ሕንፃ በቁፋሮ መገኘትን ያበሰሩት ኢትዮጵያውያንና ጀርመናውያን ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ያገኙትም በይሓ አካባቢ ግራት በዓል ግብሪ በተሰኘ ስፍራ ነው፡፡ እንደተመራማሪዎቹ ግኝቱ በኢትዮጵያና በየመን መካከል ቀድሞ በነበረ ግንኙነት  የሚናገሩ መላምቶችን የሚቀይርና የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያድስ ይሆናል፡፡

ከአክሱም ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 56 ኪሜ ርቆ የሚገኘው ይሓ ከጥንታዊው የአክሱም ሥርወ መንግሥት በፊት የነበረው የደአማት ሥርወ መንግሥት መቀመጫ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል በይሓ አሁንም ድረስ ፍራሹ ቆሞ የሚታየው ምኩራብ አለ፡፡ ምኩራቡ ‹‹አልሙቃህ›› ለተባለ የጨረቃ አምላክ አምልኮት ይፈጸምበት እንደነበረ በጥናት ተረጋግጧል፡፡

የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ አንድ ሕትመት እንዳሳየው፣ ይሓ የጥንታዊው የደኣማት መንግሥት መቀመጫ ማዕከል ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፣ መንግሥቱም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከስምንተኛ እስከ ሦስተኛ ክፍለ ዘመን እንደቆየ ጥናቶች ያወሳሉ፡፡ ይሓ በወቅቱ የንግድ፣ የእርሻ፣ የሥነጥበብና የአስተዳደር ማዕከል ሆኖ በማገልገሉ በላቀ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር የሚያሳዩ አሻራዎች እስካሁን ይታያሉ፡፡



በይሓ ሁለት ታላላቅ ሕንፃዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው ግራት በዓል ግብሪ በሚባል ቦታ የሚገኘው ቤተ መንግሥት የነበረ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በ200 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ጥንታዊው የይሓ ምኩራብ እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ ምኩራቡ ከ2,800 ዓመታት በፊት የታነፀና አልሙቃህ እንዲመለክበት የተሠራ መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ስሪቱ ያላንዳች ሲሚንቶ፣ አሸዋና ጭቃ ትላልቅ ድንጋዮችን ብቻ በማነባበር የተገነባው ሕንፃ 18 በ15 ሜትር አካባቢ ስፋት እና 13 ሜትር ቁመት አለው፡፡ 12 ዓምዶች እንደነበሩትም በምኩራቡ የሚታዩ ምልክቶች በግልፅ ያሳያሉ፡፡

ጣራ አልባ የሆነው ይኸው ግንብ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ተጽእኖዎችን ተቋቁሞ እስከ አሁን ዘመን መድረሱ በብዙዎች ዘንድአድናቆትን በማሳደር ላይ ይገኛል፡፡ ከ1960ዎቹ ወዲህ በተካሄዱ የአርኪዮሎጂ ምርምሮች በርከት ያሉ ከአለት ተወቅረው የተሠሩ 17 ያህል መቃብሮች፣ የሳባውያን ጽሑፍ የያዙ የተጠረቡ ድንጋዮችና የእጣን ማጨሻ፣ ከመዳብ የተሠሩ ማሕተሞችን ጨምሮ በርከት ያሉ የእርሻና የሕንፃ መሳርያዎች ተገኝተዋል፡፡

ይሓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ታላቅ ገዳም የሚገኝበትም ነው፡፡ ገዳሙን የመሠረቱትም ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ አፍጼ ናቸው፡፡ ቦታው የበርካታ አርኪዮሎጂያዊ ቁፋሮዎች መገኛ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አርኪዮሎጂ ተቋም ከ1944 ዓ.ም. የጀመረው የምርመራ ሥራ በዘመነ ደርግ ቢስተጓጎልም ከ1985 ዓ.ም. ወዲህ በፈረንሣይ የአርኪዮሎጂ ቡድን መቀጠሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

No comments: