Monday, April 1, 2013

ተማሪዎች ብሪትሽ ካውንስልና መንግሥትን ለመክሰስ ዝግጅት እያደረጉ ነው

ከእንግሊዙ ካምብሪጅ ኮሌጅ ዲግሪ ለማግኘት በማሰብ በአገር ውስጥ በትብብር ሥልጠናውን ይሰጥ ከነበረ ተቋም የተልኮ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩና የተመረቁ መንግሥትን ጨምሮ፣ ተቋሙንና የብሪትሽን ካውንስልን ፍርድ ቤት ለማቆም እየተዘጋጁ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡
ዘመን ዲቨሎፕመንት ኤንድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የተሰኘው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በድንበር ዘለል ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ዕውቅና ተሰጥቶት፣ 400 ያህል ተማሪዎችን ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ ሆኖም ካለፈው ታኅሳስ ወር 2005 ጀምሮ ዕውቅናው መሰረዙን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ውሳኔው ኤጀንሲው ምክንያት ያደረገው ከካምብሪጅ ኢንተርናሽናል ተሰጥቶኛል ያለውን የታደሰ የዕውቅና ማረጋገጫ፣ ዘመን ኢንስቲትዩት እንዲያቀርብለት ቢጠይቅም ሊቀርብለት ባለመቻሉ እንደሆነ አስታውቆ ነበር፡፡

ይሁንና ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ቢጽፍም ትምህርት ሚኒስቴር ግን የኤጀንሲው ውሳኔ እንዲፀና በማድረግ የትምህርት ተቋሙ የተጠየቀውን ዕውቅና እንዲያመጣ አሳስቧል፡፡ ይልቁንም ካምብሪጅ ኮሌጅ በእንግሊዝ አገር በማስትሬት ዲግሪ መርሐ ግብሮች ሥልጠና ለመስጠት ዕውቅና የተሰጠው ነው በማለት ምስክርነቱ ሰጥቶ የነበረው ብሪቲሽ ካውንስል ሁለት ጊዜ መሰል ማረጋገጫ መስጠቱ ስህተት እንደሆነ በመግለጽ ይቅርታ መጠየቁን የተገነዘበው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ተቋሙ በድንበር ዘለል ትምህርት ዘርፍ ሥልጠና እንዳይሰጥ ብቻ ሳይሆን መዝግቦ ሲያስተምራቸው የነበሩትንም ተማሪዎች ተመጣጣኝ ወደሆኑ ሌሎች ተቋማት እንዲያዛውር፣ በትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ የተወሰነበትን ውሳኔ አጠናክሮበታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በዘመን ኢንስቲትዩት ለተመረቁ ተማሪዎች ዕውቅና እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

እንዲዘጋ የተወሰነበት ዘመን ኢንስቲትዩት በምትኩ ብሪቲሽ ስኩል ኦፍ ቢዝነስ ኤንድ ፋይናንስ ከተባለ ተቋም ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን በማስታወቅ፣ ወደሌላ ተቋም እንዲያዛውራቸው የተባሉትን ተማሪዎች በዚህ ተቋም ዕውቅና በሚሰጠው አኳኋን ለማስተማር እንዲፈቀድለት ጠይቆም ውድቅ ተደርጎበታል፡፡

እነዚህን ውሳኔዎችና ሒደቶች ሲከታተሉ የቆዩት ተማሪዎች ግን ዕውቅና ከሌለው ተቋም ለተገኘ ዲግሪ ዕውቅና ይሰጠዋል በማለቱና በአግባቡ ዕውቅናውን ሳያጣራ የድንበር ዘለል ሥልጠና እንዲሰጥ ለዘመን ኢንስቲትዩት ዕውቅና በመስጠቱ ጭምር ኤጀንሲው መከሰስ እንደሚገባው በመመካከር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዘመን ኢንስቲትዩት ላደረሰባቸው የጊዜ፣ የገንዘብና የሞራል ኪሳራ በፍርድ ቤት እንደሚጠይቁ መወሰናቸው ሲታወቅ፣ ብሪቲሽ ካውንስልም ዕውቅና የሌለውን ተቋም ዕውቅና እንዳለው በማስመሰል ማረጋገጫ መስጠቱ፣ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ እንደሚሆን ከተማሪዎቹ መካከል ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡

ወደሌሎች የትምህርት ተቋማት እንዲዛወሩ የተባሉት ተማሪዎች በማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እንዲሁም በፕሮጀክት ማኔጅመንት በማስተር ኦፍ አርትስ ዲግሪ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል የተመዘገቡ በመሆናቸው፣ በእነዚህ ዘርፎች ውስጥ ከሚሰጡት ጥቂቱ ብቻ በሁለቱ ተቋማት እንደሚሰጡ በማረጋገጣቸው ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶቹም ከሁለቱ ተቋማት የሚገኘውን ዲግሪ ለማግኘት ሳይሆን ዓለም አቀፍ ዲግሪ ለማግኘት ብለው ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ሲማሩ እንደቆዩም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ መንግሥት እዚህ አገር በመስጠት ላይ ካሉ የአሜሪካ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ሊያስቀጥልላቸው ይገባ እንደነበር በመግለጽ ይወቅሳሉ፡፡  

No comments: