ዛሬ የምንጓዘው ከስታዲየም ወደ ጎተራ መስመር ነው። ምድርና ሰማይ እንደተጠፋፉ ዘመዳማቾች በዝናብ ወሬያቸውን እንደተያያዙት ነው።
ነዋሪው ከቦይ ተርፎ በሚፈስ ጎርፍ ውስጥ እየተንቦጫረቀ ታክሲ ይጠብቃል። ድንገት ተራ አስከባሪው መጥቶ፣
‹‹ተሠለፉ በዝታችኋል!›› ብሎን ዘወር ከማለቱ፣ ‹‹ወይ ትዕዛዝ ብንሠለፍ ለራሳችን ምን ይቆጣናል?›› ብሎ አንዱ
ተናገረ። ‹‹ይገርማል! መቼም ሐበሻ አዲስ ነገር መቀበል ሞቱ ነው። ቆይቶ ግን የትናንቱን አዲስ በታላቅ
መስዋዕትነት ይጠብቀዋል። ሰው ትናንት ለምን እንሰለፋለን ብሎ እሪ እንዳላለ አሁን በውዴታ!?›› ብሎ ሌላው
ግርምቱን ይተርካል። ‹‹ምን እናድርግ ታዲያ? ወደን መሰለህ? ‘ወዳ አይደለም እኮ ቅጠል ስትበጠስ የምትበሰብሰው’
ሆኖብን እንጂ!›› ስትል አንዲት ሴት ትመልስለታለች።
ካፊያው እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው። ምሬታችን ካፊያውን ይከተለዋል። ካፊያው ዶፍ ሲሆን ግን እኛ ያው እኛው ነን። ‹‹ምን እናድርግ ታዲያ?›› ይላል አንድ ጎልማሳ በሠልፉ መሀል፣ ‹‹የመጣ የሄደው ትውልድ አገር እያፈረሰ አገር ሠራሁ ባለ ቁጥር እኛ እስከመቼ ሆ እንበል?›› ሲል አንድ ቄስ ቀበል አድርገው፣ ‹‹አሁን እንኳ መፍትሔው ከላይ ነው። እሱ በቃ እስኪለን መጠበቅ ነው እንጂ የሰው ነገር የበቃን ይመስለኛል፤›› ብለው አስተያየታቸውን ሰነዘሩ። ጥበቃችን በረታ። ደመናው ይበልጥ እየጠቆረ ቀኑ የሚጨልም ይመስል ጀመር። ቆመናል ታክሲ ጥበቃ። ጥበቃችን ግን ታክሲ ብቻ አይደለም። መፍትሔም ጭምር ነው። ‹‹ለብዙ ሠልፎች መፍጥሔ ያጣ ሕዝብ ጎዳናው ላይ አለ። ምናልባት የማያሳይ መስታወት ባለው ካዲላክ መንገድ አዘግተው የሚወጡ የሚገቡ ባለሥልጣኖቻችን አላየው ብለው ይሆን?›› በማለት ጥያቄ መሰል አሽሙር የሚሰነዝርም አለ፡፡
ለእኛ ያላት ታክሲ ከብዙ ቆይታ በኋላ ከተፍ አለች። ደግነቱ ዝናቡ ብዙም አልጎዳን። ዲስኩር እንጂ ተግባር ሕልም እንደሆነበት ደካማ የፖለቲካ ፓርቲ እየተስለመለመ ደመናው ይበተን ጀምሮ ነበር። ፀደይ በካፊያ ድግስ በሐሴት አብዳለች። ንፁህ አየር በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ይነፍሳል። ነዋሪው ዘግይታም ቢሆን መልስ በሰጠችው ተፈጥሮ እፎይ ብሏል። በሰው ሠራሹ ነገር ግን እንደጎበጠ ነው። ታክሲያችን ውስጥ ተራ ጠብቀን እየገባን ነው። ከአቅም በታች ለማሰብና ለመኖር የሚገደደው በርክቷል። ‹‹የስንት አኩሪ ታሪክ እናት አገር፣ የስንቱ ጀግና መወለጃ፣ ለስንቶች ፅናት አርዓያ የሆነች አገር እስከመቼ እየዳኸች እንደምትኖር እንጃላት፤›› ይላል ጎልማሳው በሹክሹክታ። አጠገቡ ተቀምጦ የነበረ ወጣት፣ ‹‹ይህን የልማቱ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት ነው፤›› ይለዋል። ቀና ብሎ ጎልማሳው ወጣቱን ሲያየው ይተዋወቃሉ። ‹‹ኧረ አንተ ነህ እንዴ? እኔ እኮ እንዴት ያለ ዓይን ያወጣ ነው እንዲህ የሚለኝ ብዬ ደንግጫለሁ፤›› ብሎት ሰላምታ መለዋወጥ ጀመሩ።
ሾፌሩ፣ ‹‹ኧረ በፈጠረህ እነሱንም አጠጋግተህ ጫናቸው። በዚህ ዝናብ ትርፍ አልጭንም ትላለህ?›› እያለ ወያላውን በገዛ ራሱ የዘወትር ተግባር ይወነጅለዋል። ወያላው የዘጋውን ተንሸራታች መዝጊያ ከፈተና ‹‹ኑ እሺ ግቡ!›› ብሎ ይጭን ገባ። ጠጋ ጠጋ ማለት ተጀመረ። ‹‹ሁለት የነበርነው በሦስት ተገመድን፤›› ስትል አንዲት ልጅ እግር፣ ‹‹ፈጥነን መበጠስ አለመበጠሳችንን ግን እንጃ?›› ትላለች ጓደኛዋ እያሾፈች። ‹‹እኔምለው ባለፈው መሥሪያ ቤታችሁ መጥቼ የሆንኩትን ብነግርህ?›› ብሎት ንግግሩን ገታ ወጣቱ። ‹‹ለምን ጉዳይ?›› ጠየቀ ጎልማሳው። ‹‹መብራት ሲጠፋ ጠቅላላ ኮምፒውተሮቼ መቃጠላቸውን ነግሬህ አልነበር? ኋላማ ማን በቅጡ ያናግረኝ? እንደ ዜጋ የሚቆጥረን እኮ ጠፋ? እንዲያው መጨረሻችንን ብቻ አይቼው?›› እያለው ቀጠለ። ‹‹ኧረ በምርጫ ሰሞን እንዲህ አይወራም፤›› ይላል አጠገቤ የተቀመጠ ጎረምሳ የቀልድ አስመስሎ። ወያላው ‹‹ሳበው›› እያለ ነው። እስከ መጨረሻ መጓዝ የሕይወት ግዴታ ነውና ታክሲዋ ተንቀሳቀሰች፡፡
ታክሲያችን በፍጥነት ስታዲዮምን ለቃ ስትፈተለክ የኳስ ወግ ቀድሟት ጀምሮ ነበር። ‹‹ዋሊያዎቻችን ወደዱም ጠሉም ለዓለም ዋንጫ ማለፍ አለባቸው፤›› አለች በሦስተኛነት ሦስተኛው መቀመጫ ላይ የተደረበችው ትርፍ ተሳፋሪ። ‹‹እሰይ! ምን ነው እንዲህ ግዴታ አደረግሽባቸው?›› አለቻት ጎማው ላይ የተቀመጠች ጓደኛዋ። ‹‹እንዴ! አላየሽም እንዴ ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፉ እንዴት ኑሯችንን ረስተነው እንደነበር? ስለአሠላለፍ ስናወራ ታክሲ መሰለፍ ትዝ አይለንም ነበር እኮ! ማን ቋሚ ተሠላፊ መሆን እንዳለበትና ማን መሆን እንደሌለበት ስናወራ የኑሮ ውድነቱን እርስት አድርገነው ነበር። በድጋፍ ሰበብ ማታ ወጥተን አንድ አንድ ስንል በኑሮ ሩጫ ምክንያት የረሳነውን ማኅበራዊ ሕይወት እንዴት እንዳደስነው አታስታውሽም?›› እያለች ስትቀጥል ፈገግ ታሰኘን ጀመር።
‹‹እና አንቺ ብሔራዊ ብድናችንን ብራዚል ላይ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ማየት የናፈቅሽው በእነዚህ ምክንያቶች ብቻ ነው?›› ብሎ አንድ ወጣት ቢጠይቃት፣ ‹‹ታዲያ! ኀብረ ብሔራዊነት በብሔር አስተሳሰብ በተተካበት ዘመን ለየትኛው ብሔራዊ ስሜት ብዬ መስሎህ ኗሯል?›› ብላ ጥያቄውን በጥያቄ ስትመልስለት ዝም እንዳለ አያት። ‹‹የእኔ ጥያቄ ግን ምን መሰለሽ?›› አላት በመስኮቱ በኩል ተጨናንቆ ተቀምጦ ያስጠጋት ተሳፋሪ። ዞር ብላ አየችውና ቀጥል ስትለው፣ ‹‹በአምስት ዓመት አንዴ እየመረጥን በአራት ዓመት አንዴ ኑሮን ከመርሳት ለምን በየቀኑ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ትንታኔ ዕለታዊ ኑሮን መርሳት አይሻልም?›› ሲላት አውራ ጣቷን አሳይታ ‘ጫር’ አለችው። እነሱ በእጅ ሲጭሩ እኛን በሐሳብ አስጫሩን፡፡
ከአፍታ የጥሞና ጊዜ በኋላ የሰሞኑ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ጉዳይ ተነስቶ ሰውን ያነጋግረው ጀመር። ወያላው ሒሳብ ሰብስቦ ከተቀመጠ ቆየት ብሏል። ‹‹ኧረ ሳትነግረኝ! ጋዜጣው ላይ ስምህን አገኘህ?›› ብላ ከኋላ መቀመጫ የተቀመጠች ተሳፋሪ ጓደኛዋን ስትጠይቀው፣ ‹‹ወይ ማግኘት እኔስ መመዝገቤን እስክጠራጠር ድረስ ነው ዕጣ ሳይወጣልኝ መቅረቱ ሊገባኝ ያልቻለው፤›› ብሎ መለሰላት። ‹‹አይዞህ! እውነት እናውራ ከተባለ በአሁኑ ጊዜ ቤት ኖረህ አልኖረህ ምን . . .›› ብላ ሳትጨርሰው የታክሲው ተሳፋሪዎች በሙሉ በኅብረት ‹‹ምን አልሽ?›› ብለው ጮኹባት። ‹‹አባባሌ በዚህ ኑሮ . . .›› ብላ አሁንም ሳትጨርስ፣ ‹‹ተይ! ተይ! ተይ! ‘መጀመሪያ የመቀመጫዬን’ አለች ጦጣ። መጀመሪያ ከኪራይ ኑሮ እንገላገል እስኪ፤›› አለ አንዱ። ሌላውም ይቀባበል ጀመር። ‹‹አዎ! መጀመሪያ እስኪ ቤት አለኝ እንበልና ከዚያ የሚሆነውን እንይ። በዚህ ጊዜ. . . እንዴ! ምን ማለትሽ ነው?›› እያለ ሰው ትችቱን አዝንቦባት እንደጨረሰ የኪራይ ቤት ገጠመኝ ይንሸራሸር ጀመር።
አንድ ተሳፋሪ እንዲህ ያወራ ጀመር። ‹‹ሰሞኑን የቤት አከራዬ ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው? ብዙ ጊዜ ፊልድ ስለምወጣ ቤት አለመቀመጤን አይተው ከትናንት ወዲያ ጠሩኝ። ‘እኔ ቤቱን ያከራየሁህ እንድትኖርበት እንጂ ዘግተኸው እየከረምክ የመጋኛ መሰባሰቢያ እንድታደርገው አይደለም። ስለዚህ የሚሻለውን ምረጥ፤ ወይ አንተ ሳትኖር ሳትኖር ቤቱን ለአንድ ቀን አዳር እንደ ቤርጎነት እንድጠቀምበት ፍቀድ ወይ ልቀቅ። የቱ ይሻልሃል?’ አይሉኝ መሰላችሁ?›› ከማለቱ አሳዝኖንም አስቆንም፣ ‹‹ምን አልካቸው ታዲያ?›› አልነው፡፡ ‹‹እኔ አልጋ ላይ ነው እኔ ሳልኖር ሌላ ሰው የሚያድርበት? ስላቸው ‘የለም እኔ አልጋ ላይ ነው’ ብለው አላገጡብኝ፡፡ እናም ቤቱን ትናንት ለቀቅኩላቸው፤›› ሲል ያን ያህል የምሩን አልመሰለንም ነበርና ቅፅበታዊ ድንጋጤ ውስጣችንን ሰረሰረው። ‹‹አንዳንዱ ተገዶ ለሽንፈት ሲፈጠር፣ በጥቅሻ ይወድቃል እንኳንስ በጠጠር፤›› አለ ገጣሚው። ኧረ ጉድ ነው ዘንድሮስ፡፡
ዝምታ ሰፈነ። አንዳንዴ እንዲህ ያለውን ዝምታ ከንግግር በልጦ ይደመጥና ውስጥን በቁጭት፣ በንዴትና በፀፀት ያብላላዋል። ዝምታው በረዘመ ቁጥር መዳረሻችን እየተቃረበ መጣ። ከመውረጃችን በፊት ሁለት አዛውንቶች ታክሲ ውስጥ ሳይተያዩ ተቀምጠው ቆይተው ኖሮ ሰላም መባባል ጀምረዋል። ‹‹አንተ አለህ?›› ይላሉ አንደኛው እጃቸውን አፋቸው ላይ ጭነው። ‹‹እኔስ አለሁ አገሩ ነው እንጂ የሌለው። አታይም ያ ያደግንበት ሜዳ ታርሶ የለ የተሽሎከለክንበት ሠፈር ሕንፃ ተሠርቶበት። አሁን ማን ያውቅሃል? ሰውም በዛ። እዚያ ቦታ ላይ እንዴት ያለ ታሪክ ሠርተን እንዳለፍን አሁን ማን ያውቅልሃል?›› ብለው ምስኪኑ ለወዳጃቸው ይመልሳሉ። ‹‹ልናገርስ ብትል የአሁን ትውልድ ‘እኔ ምን አገባኝ’ ብሎህ ይሄዳል እንጂ መቼ ቆሞ ያደምጥሃል?›› ይሏቸዋል ጓደኛቸው። ሁለቱም ረጂም ዕድሜ ያዩ ናቸው።
ከሁለቱ ሴት ጓደኛማቾች አንደኛዋ፣ ‹‹አሁን እኛ ይኼን ያህል ዕድሜ እንኖር ይመስልሻል?›› ስትላት ጓደኛዋን፣ ‹‹ይናፍቅሻል! ዕድሜ ለ‘ፌስቡክ’ ቆይ አሁን ስናረጅ ታያለሽ፤›› ብላት ትስቃለች። ‹‹ለመሆኑ እነእከሌ የት ደረሱ?›› ብለው የኋለኛው ተናጋሪ አዛውንት የፊተኛውን ይጠይቋቸው ጀመር። ‹‹አዬ እነሱማ በልማት ስም ተነስተው መቼ እንገኛለን?›› ብለው መለሱለቸው። ‹‹ሞት ይሻላል በቁም እንዲህ ከመራራቅ፤›› አሉ ትንሽ ቆዩና ጠያቂው አዛውንት እንባቸው ቅርር እያለ። ‹‹አዬ! ምን ታደርገዋለህ ለታሪክ፣ ለሰው፣ ለአገርና ለወገን ግድ የሌለው ትውልድ መጣብን። ጊዜ ነው ትለዋለህ እንጂ ምን ታደርገዋለህ? ‘እነሱስ ማን አላቸው?’ ብሎ የሚያስብልን አጣን። ሁሉም ለራሱ ነው ወዳጄ። ሁሉም ለራሱ!›› ብለው ሁለቱም ፀጥ አሉ። ወያላው ታክሲዋ ስትቆም ‹‹መጨረሻ›› ሲለን የአዛውቶቹ ‘ደህና ሁን!’ ‘ደህና ሁን!’ ስንብት አንጀታችንን በላው። ብዙ ዓመት እንደምናውቃቸው ሲለዩን ከበደን። ‹‹አይ ዕድሜ እንዴት ምቀኛ ነው ግን? በዚህ ጊዜ አገናኝቶ ደግሞ ያለያያል፤›› እየተባባለ ተሳፋሪው ተበታተነ። እኔ ጆሮ ውስጥ ግን አንደኛው አዛውንት፣ ‹‹ሁሉም ለራሱ!›› ያሉት አባባል ደጋግሞ እየደወለ ነው። በየቦታው ብሶት ሞልቷል፡፡
ታክሲ ውስጥ ደግሞ የገነፈሉ ብሶቶች ይሰማሉ፡፡ ብሶት እየገነፈለ ነው፡፡ አድርባይነትና ራስ ወዳድነት በገዘፈበት በዚህ ዘመን ‹‹ሁሉም ለራሱ›› ብቻ ማሰቡ ይከብዳል፡፡ የታክሲ ጉዟችን እንዲህ ባያጥር ኖሮ ብሶት እንዴት ያደርገን ነበር? የማይቀር ነውና በነገው ጉዞም ሌላ ብሶት ይገጥመናል፡፡ ከሃያ አንድ ዓመታት በፊት በድል አዲስ አበባ የገባው ኢሕአዴግስ ‹‹ብሶት የወለደኝ ነኝ›› ብሎ አልነበር? ዳሩ ምን ያደርጋል ዛሬም ብሶት አለ፡፡ የሚንተከተክ ብሶት፡፡ አጠገቤ ተቀምጦ የነበረው ከጎኔ እየተራመደ፣ ‹‹ብሶት ሲበዛ ደግ አይደለም፡፡ አንድ ቀን መገንፈሉ አይቀርም…›› እያለ ሲነግረኝ እኔ ደግሞ በሐሳብ ጭልጥ ብዬ ነበር፡፡ ለካ ሐሳብም ራሱን የቻለ ጉዞ ነው፡፡ መልካም ጉዞ!

No comments:
Post a Comment