Monday, April 1, 2013

የወደቀችው ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት እ.ኤ.አ ከ1960 ወዲህ መረጋጋትን አስተናግዳ አታውቅም፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የተፈረካከሰች ግዛት ይላታል፡፡ በዓለም በዕድገታቸው ወደኋላ ከቀሩ አገሮችም ከመጨረሻው ሥፍራ ትመደባለች፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ አገሪቷ ሀብት አጥታ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን የባሕር በር ባይኖራትም በውኃና በማዕድን ሀብቷ አንቱ የተባለች ነች፡፡

ለግብርና ምቹ ሥፍራም ናት፡፡ ሆኖም በአገሪቷ ለረዥም ጊዜያት ተንሰራፍቶ የሚገኘው ሙስና የአገሪቷን የጣውላና የአልማዝ ኢንዱስትሪ አቀጭጮታል፡፡ ያልተነኩ የአገሪቷ የደን ሀብቶች በውስጣቸው የያዙዋቸው ዝሆንና ጐሬላ የአገሪቱ መገለጫዎች ቢሆኑም፣ አገሪቷ ከተፈጥሮም ሆነ ከሰው ሀብቷ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም፡፡ ይልቁንም ሕዝቧ በአገሪቱ በየጊዜው በሚያገረሸው ብጥብጥ ለሞትና ለስደት ተጋልጧል፡፡

ምሁራኑ ከተፈረካከሰች ግዛት የሚመድቧት ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት አስተናግዳለች፡፡ በአንድ ወቅት ራሳቸውን ንጉሥ አድርገው የሾሙት ዦን ቤደል ቦካሳ በፈረንሳይ አጋዥነት በዴቪድ ዳኮ በተመራ መፈንቅለ መንግሥት እ.ኤ.አ በ1979 ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ አገሪቷ የተለያዩ መሪዎችን ብታፈራርቅም አልሆነላትም፡፡ ግጭትን ማርገብ አልቻለችም፡፡ ሕዝቧ ከሽምቅ ውጊያ አልወጣም፡፡


የመፈንቅለ መንግሥት መሪው ዴቪድ ዳኮ ለሁለት ዓመት አገሪቷን ቢመሩም በሥልጣን ለመቀጠልም ሆነ አገሪቷን ከውጥረት ለማውጣት ዕድል አላገኙም፡፡ እሳቸውም በእንደር ኮሊኝባ ተወገዱ፡፡

በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሥርዓት የሚያምኑት ሚስተር ኮሊኝባ በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ነበር ከሥልጣን የወረዱት፡፡ በእሳቸው እግር የተተኩት አንቢ ፍሌክሲ ፖታሲ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1997 ለሕዝባቸውና ለአገሪቷ መረጋጋትን ማምጣት ተስኗቸዋል፡፡ ዜጐችም ለታጣቂዎች አመፅና ለዝርፊያ ተዳርገዋል፡፡

በወቅቱ በአገሪቷ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፈረንሳይ ወታደሮች አገሪቷን በመልቀቃቸው፣ ፈረንሳይ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች ሰላም አስከባሪ ኃይል በማቋቋም አገሪቷን ለመታደግ ሞክራለች፡፡ በወቅቱ የተቋቋመው ሰላም አስከባሪ ኃይል በአሁኑ ጊዜ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይልነት አድጓል፡፡

እ.ኤ.አ በ1999 ፖታሲ ከዘጠኝ ዕጩዎች ጋር ተወዳድረው የፕሬዚዳንትነቱን መንበር ቢጨብጡም፣ እ.ኤ.አ በ2003 በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ተወግደው ወደ ቶጐ ተሰደዋል፡፡

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተነፃፃሪ ሰላም የነበራት እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ነበር፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ በ2012 መነሻቸውን ከደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል አድርገው ጥምረት የፈጠሩት የሲሊካ ሽምቅ ተዋጊዎች ባለፈው እሑድ የአገሪቷን ፕሬዚዳንት በኃይል እስካስለቀቁበት ጊዜ ድረስ የአገሪቷ ዜጐች በጦርነት ተሰቃይተዋል፡፡ ቀድሞውንም በሕገወጥ የጦር መሣርያ ዝውውር ምክንያት መረጋጋትን ያጣችው አገሪቷ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የባሰ ውጥረት ውስጥ ገብታለች፡፡ 

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንሲስኮ ቦዚዚ አማፂያን ገፍተው ዋና ከተማዋን ባለፈው እሑድ ባንጉዊን ከመቆጣጠራቸው በፊት አገሪቷን ለቀው ወደ ጐረቤት ካሜሩን ተሰደዋል፡፡ የአማፅያን መሪዎች ቤተ መንግሥቷን እንደተቆጣጠሩ በፕሬዚዳንት ቦዚዚ ጊዜ የፀደቀውን የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አግደዋል፡፡ ፓርላሜንቱንም በትነዋል፡፡ አማፂዎቹን የሚመሩት ሚቼል ፍቶዲያ በአገሪቱ ተዓማኒነትና ግልጽነት ያለው ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ የሽግግር ጊዜ እንደሚኖር አሳውቀዋል፡፡ አያይዘውም በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ የሰላም ስምምነት እንዲደረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አማፂዎች የአገሪቱን ፕሬዚዳንት በኃይል ካባረሩ በኋላ የአፍሪካ ኅብረት በአማፅያኑ መሪዎቹ ላይ ማዕቀብ ጥሏል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት ለማድረግ ከተስማሙ በኋላ አምስት ሺሕ ያህል የአማፅያን ወታደሮች የአገሪቷን ዋና ከተማ ባንጉዊን መውረራቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ካለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ማብቂያ ጀምሮ መጣ ሄደት እያሉ የአገሪቷን መረጋጋት ሲያናጉ የከረሙት አማፅያን፣ ፕሬዚዳንት ቦዚዚ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ አላደረጉም ሲሉ ይወነጅላሉ፡፡ ሆኖም ከአፍሪካ ኅብረት ገደብ ማምለጥ አልቻሉም፡፡ አማፅያኑ ከተማዋን ከተቆጣጠሩ በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል አቋርጠዋል፤ ሦስት የኃይል ምንጮችን ተቆጣጥረዋል፡፡ ሕዝቡም በፍርኃት ተውጧል፡፡

ከአምስት ሚሊዮን የማይበልጥ ሕዝብ ያላት ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐቿ ወደ ቻድና ካሜሩን ተሰደዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ አገሪቷን ለመምራት ብቅ ያሉ ፕሬዚዳንቶችም የመፈንቅለ መንግሥትና የአማፅያን ሰለባ ሆነዋል፡፡ ተሰደዋል፡፡ አገሪቱ ፍፁም መረጋጋትን አጥታለች፡፡ አሁንም አገሪቷን የተቆጣጠሩት አማፅያን ምርጫ በሦስት ዓመት ውስጥ እንናካሂዳለን ቢሉም እርስ በርሳቸው ሳይበጣበጡ ለመቆየታቸው ማረጋገጫ የለም፡፡ ምክንያቱም አገሬው ሕገወጥ የጦር መሣርያ በገፍ ታጥቋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት አገሪቷን ለማረጋጋት የተቻላቸውን ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ አገሪቷ ልትረጋጋ አልቻለችም፡፡ ሕዝቡም ከአገሪቷ ዕምቅ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት፣ አልማዝ፣ ዩራንየም፣ ወርቅና የውኃ ሀብት መጠቀም አልቻለም፡፡ ይልቁንም የስደትና የሞት ሰለባ ሆኗል፡፡ አገሪቷ መቼ ትረጋጋ ይሆን? ለጊዜው መመለስ የሚከብድ ጥያቄ ነው፡፡ 

No comments: