Monday, April 1, 2013

ከትዝታ እስከ ሻላዬ

የታወቀው ስታር ባክስ ቡና ቤት ቁጭ ብሎ በጣዕሙ ጠንከር ያለውንና ሽታው የሚያውደውን ይርጋ ጨፌን ቡና መጠጣት በምዕራቡ ዓለም የተለመደ ነው፡፡
ጥያቄው ግን ከቡናው ጀርባ ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው? ይኼንን ቡና የሚያመርቱት ገበሬዎቹስ ምን ዓይነት ሕይወት አላቸው? ሙዚቃቸውስ ምን ዓይነት ነው? የሚለውን ጥያቄ የሚጠይቀው ምን ያህል ሰው ነው፡፡

ውጭው ዓለም የሚኖሩ ሰዎችን ተወት እናድርጋቸውና ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ናቸው ከዚህ ከሚጥም ቡና ጀርባ ያሉ ሰዎችን የአኗኗር ዘዬ የሚያውቁ በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ውስጥ የምትገኘው ይርጋ ጨፌ በቡና ታዋቂ ብትሆንም በሕዝቧ አኗኗር ወይም በሙዚቃ አትታወቅም፡፡ እንደ ሌሎች አካባቢዎች የተመዘገበ ታሪክ ወይም ሙዚቃ ስለሌለ ይሔንን ለማወቅ ቦታው ላይ መሔድ ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ዓለም ባህላቸውን ወይም ዘፈናቸውን አወቀላቸው አላወቀላቸው ግድ ባለመስጠት ከአዲስ አበባ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ለምና አረንጓዴ ቦታዋ ይርጋ ጨፌ ሕፃናት በአዲስ ዓመትና መስቀል ‹‹አና ዴስኮ›› የሚል ዘፈን እየዘፈኑ ያድጋሉ፡፡ ዘፈኑ በይርጋ ጨፌ ብቻ ሳይሆን በዲላ ከተማ እንዲሁም በጌድኦ ዞን ታዋቂ ነው፡፡ አብርሃም በላይነህ ቦታውን ከጐበኘ በኋላ ዘፈኑና ዜማው አዕምሮ ውስጥ ተቀርፆ ቀረ፡፡ እናም አንድ ነገር ለማድረግ ወሰነ፡፡ ይሔንን ዘፈን የራሱን ነገሮች ጨምሮ ታዋቂ የሆነውን ሻላዬ (ቆንጅዬ) የሚለውን ዘፈን አወጣ፡፡

አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው አብርሃም ከቅርብ ጓደኛው ስለ አካባቢው የሰማቸው ታሪኮችም በጥሩ መልኩ ተፅዕኖ እንደፈጠሩበት አይደብቅም፡፡ አካባቢው ሲሔድም ዘፈኖቹ የማይረሳ ትዝታን ስለጣሉበት በስልኩ ቀርፆ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ እናም ይሔንን ዘፈን እንደ ጉዞ ማስታወሻ አድርጐ ሠራው፡፡

ሻላዬ (ቆንጆ) በሚላት አንዲት ሴት ውስጥ የማኅበረሰቡን አኗኗር፣ ወግ እንዲሁም ፍልስፍና ለመግለጽ ሞክሯል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ማኅበረሰቡ የራሳቸውን ያልሆነ ነገር ምንም ያህል ጠቃሚና ውድ ቢሆንም አያነሱም፡፡ ይሔንንም የመኪና ቸርኬ አግኝተው ባስቀመጡት አሳይቷል፡፡

ዘፈኑ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች የሚሰማና ታዋቂ ቢሆንም አድማጭ ጆሮ በሰፊው እንደዚህ ለመድረስ አሥራ አንድ ወራት ያህል ወስዶበታል፡፡ ዘፈኑ ከዝነኝነት ጣራ ላይ ከማስቀመጡም በላይ የተለያዩ የመዝፈን ዕድሎችን እንዲሁም ውጭ ሀገርን ጨምሮ የሙዚቃ ዝግጅቶችን  አስገኝቶለታል፡፡ በተለይም በይርጋ ጨፌና ዲላ በነበሩት ባዛሮች ላይ መዝፈኑ ለእሱ ለየት ያለ ትርጉም ነበረው፡፡ ማኅበረሰቡ በዘፈኑ መደሰቱንና ተቀባይነቱን ሲያገኝ ደስታው ከልብ የመነጨ ሆኗል፡፡

አብርሃም እንደሚያምነው ለዚህ ዘፈን የራሱን ፈጠራዎች አዲስ ዓይነት ድምፅ  በመጨመር እንዲሁም የተለያዩ ባህላዊ ዘፈኖችን አንድ ላይ በማጣመር መዝፈኑ ተቀባይ እንዳደረገው ያምናል፡፡ ማቀናበሩን የሠራው አማኑኤል ይልማ ሲሆን ከበሮና ቤዝ ጊታር በብዛት ተጠቅሟል፡፡

‹‹በተቻለው መጠን ዋናውን ባህል ባልለቀቀ መልኩ ዘፈኑን ተጫውቼዋለሁ፡፡ የገለጽኩት ግን በራሴ መንገድ ነው›› ይላል አብርሃም፡፡

የዚህን ዘፈን ተቀባይነት የዞኑ አስተዳደር ከተመለከተ በኋላ ሌላም ዘፈን እንዲሠራ ጠይቀውት በገንዘብና በሌሎችም ቁሳቁሶች አስተዋጽኦ እያደረጉለት መሆኑን ተናግሯል፡፡

‹‹ሙዚቃ ምንም ዓይነት ልዩነቶችን ማለፍ የሚችልና ሕዝቦችን ማገናኘት የሚያስችል ነገር ነው›› ይላል አብርሃም፡፡

ለዘመናት ኢትዮጵያ ስትባል በሰሜነኛው ባህል፣ ሙዚቃ፣ ታሪክ ወይም የኑሮ ዘዬ ነው የምትገለጸው፣ ለዚህም ለዘመናት የነበረው የኃይል ሚዛን ሚና ተጫውቷል፡፡

ብዙዎች እንደሚናገሩት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ባህል እንዳልታየ እንዲሁም በሰሜነኛው ታሪክና ባህል እንደተዋጠ ነው፡፡ በታሪክ ብቻ ሳይሆን ለዘመናትም አራቱ ቅኝቶች ማለትም አምባሰል፣ ባቲ፣ አንቺሆዬና ትዝታ ቅኝቶች የሙዚቃውን የበላይነት ተቆጣጥረው ለዘመናት ተሻግረዋል፡፡

አማርኛ ዋነኛው ሆኖ ትግርኛ፣ ኦሮምኛ እንዲሁም ጉራጊኛ ቋንቋዎች የተለመዱ የሚዘፈንባቸው ቋንቋዎች ሆነዋል፡፡ ምንም እንኳን የማኅበረሰቡ የባህል ዘፈኖች በዕለት ተዕለት ኑሯቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚዘፈን ቢሆንም ለገበያ የሚውሉ ወይም የተቀረጹ ሥራዎች በጥንት ጊዜ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡

እነዚህ ለዘመናት የተተውትን የደቡብን ሙዚቃና ታሪክ ላይ አንዳንድ ሙከራዎች እንዲሁም ምርምር ያደረጉ አንዳንድ ምሁራን ነበሩ፡፡

ለሁለተኛው ዲግሪ ማሟያ ስሜነህ በትረዮሐንስ የጻፈው ‹‹ሚዩዚክ
ኤንድ ፖለቲክስ ኢን ትዌንቲዝ ሴንቸሪ ኢትዮጵያ ኢምፓየር ሞደርናይዜሽን ኤንድ ሪቮሉሽን›› የሚል ርዕስ በሰጠው ጽሑፉ የመጀመሪያውን ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ስለመሠረተው ግብፃዊው አቀናባሪ ሀሊም ኤል ዳብ ምርምሮችን ጽፏል፡፡

በ1957 ዓ.ም. አካባቢ ነው አርባ ያህል ከተለያዩ የብሔር ብሔረሰብች የተውጣጡ የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ተጨዋቾችን እንዲሁም ሙዚቀኞችን በማሰባሰብ የመጀመሪያው ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን አቋቋመ፡፡ እነዚህን የተለያዩ ሙዚቀኞች አንድ ላይ ማምጣት ከባድ ሥራ ሆኖበት ነበር፡፡ የተለያዩ ምርምሮችን የደቡብ ሙዚቃ ላይ ያደረገ ሲሆን ዘፈኖቹንም በመቅረጽ ለትውልድ አስተላልፏል፡፡

የደቡብ ሙዚቃ ሲነሳ የታዋቂው አቀናባሪ ሙላቱ አስታጥቄ ሥራዎች ይነሳሉ፡፡ የጃዝ ሙዚቃ ሥረ መሠረቱ አፍሪካ ነው፣ የሚለው ሙላቱ የደራሼንና የሱርማን ሙዚቃ ከጃዝ ጋር በመቀላቀል የተለየ ሙዚቃ ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ ይኼም ሥራው ሌሎች ሙዚቀኞች እንዲሁም ብዙ በሮችን ለመክፈት ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በደርግ አገዛዝ ጊዜ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሥር መዋቀሩ በተለያየ ብሔር ብሔረሰብ ለተውጣጡ ሙዚቃዎች መድረክን ከፍቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በደርግ ጊዜ ብዙ የኪነት የሙዚቃ ቡድኖች የተቋቋሙ ሲሆን እነሱም የኢትዮጵያን ባህል ከማርክሲዝምና ሌኒንዝም እሴቶች ጋር አጣምሮ የያዘ ዓላማ ነበረው፡፡ ይኼም ቡድን ለተለያዩ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞችና ሙዚቃ ዓይነቶች መድረክን ፈጥሯል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የጊሼ ዓባይ ኪነት ሲሆን ከጉሙዝ፣ ከአገውና ከኩናማ የተውጣጡ አርቲስቶችንም በአባልነት ይዞ ነበር፡፡ ከኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ ጋር ተያይዞ የመጣው ብሔር መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ለተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ መደመጥ ሰፋ ያለ ቦታ እንደሰጠው ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ለዘመናት በብቸኝነት ሲደመጡ የነበሩትም የአማርኛ ዘፈኖች በሌሎች ቋንቋ ለሚዘፈኑ ዘፈኖች ቦታ እየሰጡም ነው፡፡

በእነዚህ በሁለት አሥርታትም ውስጥ ብዙ ዘፋኞች ለየት ካሉ ዘፈኖቻቸው ጋር በመምጣት አዳዲስ ድምፆችን ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ እነዚህ አብዛኛዎቹ ዘፈኖች የዳንስ ሙዚቃ ሲሆኑ፣ ምታቸውም ብዙዎችን ከመቀመጫቸው አስነስቶ የማንቀሳቀስ ባሕርይ አላቸው፡፡ በተለያዩ አዲስ አበባ ክለቦችም ውስጥ እነዚህን ዘፈኖች መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የብርሃኑ ተዘራ ‹‹ያምቡሌ›› እና ‹‹ኤሌኤሌአባ›› የቴዲ አፍሮ ‹‹ሰለሜ››፣ የቶክቻው ‹‹ጨምበላላ››፣ የአብርሃም በላይነህ ‹‹ሻላዬ››፣ የስንታየሁ ‹‹ኢቦንጐ›› የሚጠቀሱ ሥራዎች ናቸው፡፡

የደቡብ ሙዚቃዎች ብቻ ሳይሆን በሰቆጣ  የሚዘፈነው የአገውኛው ‹‹ሶራ›› ቪዲዮ ክሊፕ መለቀቅ በኋላ አዲስ የእስክስታ ዓይነት እንዲሁም ዜማው ገበያውን ለመቆጣጠር ችሏል፡፡

ከአገውኛ ዘፈኖች በተጨማሪ የኩናምኛ ዘፈኖችም መምጣት በዚህ አሥር ዓመት ውስጥ ከሰሜኑ በኩል ያልተሰሙ ሙዚቃዎች እንዳሉ ማሳያ የሆነ ሥራ ነው፡፡ አንዳንዶችም የሰሜኑም ክፍል በደንብ አልታየም የሚሉም አሉ፡፡ ብዙዎቹ እነዚህ ሙዚቃዎች የቱባውን ባህል ወይም እንደወረዱ ሳይሆን የሚሠሩት ከሌሎች የሙዚቃ ዓይነቶች ጋር በመቀላቀል አዲስ ዓይነት የከተሜ ድምፅም በመስጠት ነው፡፡

ብዙዎቹ እነዚህ የባህል ሙዚቃዎች ያልተነካና ሀብታም የሆነ ባህል ያላቸው ሲሆኑ ብዙዎቹም ከልጅነት፣ ጉልምስና ጋብቻና ሞት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የልጆች ዘፈኖች አብዛኛውን ጊዜ ከእረኝነት ጋር እንዲሁም በተለያዩ በዓላት የሚዘፈኑ ናቸው፡፡ ሽለላ፣ ፉከራ፣ ጀግኖችን ማወደስ፣ ሠርጎች ላይ ያሉ ዘፈኖች በብዙ ማኅበረሰብ ዘንድ የተለመዱ ናቸው፡፡

ብዙዎች የእነዚህን ሙዚቃዎች መሰማት እንደ ጥሩ ነገር የሚያዩት ሲሆን፣ የቅንብሩንም ሥራ አንድ አቀናባሪ ማለትም ካሙዙ ካሣ  ተቆጣጥሮታል፡፡ ብዙዎችም በክለብ፣ ቲቪ፣ ሬዲዮ ላይ የሚሰሙት የርሱ ሥራዎች ናቸው፡፡

የእነዚህ ዓይነት ሙዚቃዎች መምጣት ለየት ያለ ምት ኢትዮጵያ ውስጥ መምጣት እንደቻለም ያምናል፡፡ ወላይታ ተወልዶ ያደገው ካሙዙ ዓለም አቀፍ ታዋቂዎቹ የሙዚቃ ስልቶች እንደ ዳንስ ሆል ያሉት አዲስ አይደሉም፡፡ ለአካባቢው የተለመዱ የሙዚቃ ስልቶችም እንደሆኑ ይናገራል፡፡

‹‹እነዚህ በዓለም ዝናቸው የናኙ የሙዚቃ ስልቶች ምታቸው ከጥንት ጀምሮ ወላይታ ስንሰማው ነው ያደግነው›› በማለት ካሙዙ ይገልጻል፡፡

እነዚህ የደቡብ ሙዚቃዎች ለየት ያለና አዲስ የሆነ ድምፅ ማስተዋወቅ እንደቻሉ ካሙዙ ያምናል፡፡ በየክለቦቹ መደመጣቸውና መወደዳቸውም ታዋቂ እንዳደረጋቸውም ይናገራል፡

የእነዚህ ከፍተኛ ድምፅና ምት ያላቸው ዘፈኖች ገበያውን ሰብሮ መግባትና መታወቅም በደቡብ ውስጥ ያሉትን ቀስ ያሉ ዘፈኖችንና ዜማዎችን እንዲረሱና እንደሌሉ እንዳደረጋቸው ካሙዙ ያምናል፡፡ ገበያውንም በአንድ አቅጣጫ እየመራው እንደሆነም ያስረዳል፡፡ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ሀድያና ጌድኦ በጣም ከሚሰሙት የሙዚቃ ዓይነቶች ሲሆኑ ዘፈኖቹም የሚሠሩት ለክለብ ዓላማ እንደሆነም ካሙዙ ጨምሮ ያስረዳል፡፡

እነዚህ ዘፈኖች አብዛኛውን ጊዜ የክለብ ዘፈኖች እንደመሆናቸው መጠን በከበሮ የታጀቡ ናቸው፡፡ ‹‹ወደ ጋሞ ጎፋ አንድ ሰው ቢሄድ ለሰስ ባለው ድምጽ ዜማና ቅንጅት ይገረማል፤ የየምም ሙዚቃ እንዲሁ›› ይላል ካሙዙ፡፡

እነዚህ ሙዚቃዎች በገበያው ምክንያት እንደ ፋሽንም እየታዩ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ዘፈኖቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚሠሩበት መንገድ ከችክችካ ጋር በመቀላቀል ሲሆን በተቻለም መንገድ የሙዚቃ መሣሪያዎችንም ለማጥናት ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡

‹‹የተለያዩ ምቶችን እንዲሁም የሙዚቃ መሣሪያዎችን አጠናለሁ፡፡ እናም የራሴን ፈጠራዬን እጨምርበታለሁ፡፡›› ይላል ካሙዙ፡፡

ሙዚቃዎችን ከወላይታ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ፣ ኮንታ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና የስልጤ ዘፈኖችን አቀናብሯል፡፡ ብዙ የተቀዱ ሙዚቃዎችን የማዳመጥ ዕድል የሚያገኘው ካሙዙ አካባቢው ላይ በቀጥታ የተቀዱ ድምፆችንም በቀጣዩ ሥራዎቹ ለማካተት የሚያስብ ሲሆን፣ ይሔም ሙዚቃዎቹ ቱባ የሆነውን ባህልና ሙዚቃም እንዳይታጣ ያደርጋል፡፡

ብዙዎቹ የሚሠሩት ዘፈኖች ነጠላ ዜማ ሲሆኑ፣ አልበም መሥራት በተለያዩ ምክንያቶች እንደ ገንዘብ እጥረት፣ የሕገወጥ ቅጅና የአልበሞች ሽያጭ መውደቅ ጋር ተያይዞ አልበምን መሥራት ከባድ እንዳደረገው ካሙዙ ያስረዳል፡፡

አሁንም ቢሆን ስቱዲዮው ፋታ ያላገኘው ካሙዙ የተለያዩ ሙዚቀኞች ስቱዲዮው እየመጡ የደቡብ ዘፈን ብቻ ሥራልን እንደሚሉት ካሙዙ ገልጿል፡፡ የደቡብ ክልላዊ መንግሥት የደቡብ ክልልን ለሚያስተዋውቁ ሙዚቀኞች የተለያዩ ሽልማቶችን እንደሚሰጥ ብዙዎች ቢናገሩም እስካሁን ድረስ ምንም ነገር እንዳልተሰጠው ካሙዙ ተናግሯል፡፡

የደቡብ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቅርቡ ከአምሳ ለሚበልጡት ብሔር ብሔረሰቦች አልበም እንዲሠራ ተነጋግረው አልበሙን በማሠራትም ላይ ይገኛል፡፡ የዘፈኖቹ ተወዳጅነትና ተደናቂነት አንዳንዴ የሚያስገርመው ሲሆን፤ በተለይም ክለብ ሲወጣ የሰውን ስሜት ለማየት ያስችለዋል፡፡ የተለያዩ ዲጄዎችም ምን ያህል ሙዚቃዎቹን ለማጫወት አመቺ እንደሆነና በተለይም ዳንስ ለሚፈለጉ አድማጮች ጥሩ ተመራጭ ሆኗልም ይሉታል፡፡ ከእነዚህ ከፍተኛ ድምፅና ምት ከተቀላቀለባቸው ዘፈኖች ለየት ባለ መልኩ ለስለስ ያለና ልብን የሚመስጥ ሙዚቃ የሆነው የኩናምኛ ዘፈን ለከተሜው አዲስ ድምፅን መስጠት ችሏል፡፡

እግሩ ላይ ቆርኪ አድርጐ የመሬቱን ወለል ረገጥ ገረገጥ እያደረገ የሚዘፍነው ኪዳነ ኃይሌ  ነው፡፡ አዘፋፈኑም ሆነ ሙዚቃው ከማሊዎቹ የቱዋረግ ሙዚቃ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡

ለ13 ዓመታት ራሚድ ባንድ ጊታርና ክራር የተጫወተው ኪዳነ ለማህሌት ገብረ ጊዮርጊስ፣ ሶፍያ አፅብሐና ተስፋዬ ታዬም ኩናምኛ ግጥሞችን ሰጥቷል፡፡ ብዙዎቹ ዘፈኖቹ የፍቅር ዘፈኖች ሲሆኑ፣ ከዚህም በተጨማሪ ኩናማ ውስጥ ስለሚኖሩት አራቱ ማኅበረሰቦችም ይዘፍናል፡፡ ‹‹ኪሾመን መንቲታ›› የሚል ዘፈን ያለው ሲሆን፣ ይህ ዘፈንም ምን ያህል ርቀት ፍቅሩን እየጐዳው እንደሆነ የሚያሳይ ሥራ ነው፡፡

በዘፈኖቹም  ድንበር የሚዋሰኑ ማኅበረሰቦችን ማገናኘት ችሏል፡፡ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ኩናማዎችን ሺራሮና ሁመራ እንዲሁም በየመሀሉ የሚገኙ ኩናማዎችን ዘፈኑ ነክቷቸዋል፡፡ በኤርትራ ውስጥም ዘፈኖቹ ታዋቂ ሆኗል፡፡

ሙዚቃ የማኅበረሰቡ የልብ ምት እንደመሆኑ መጠን በየዕለቱ እንቅስቃሴያቸው ይዘፍናሉ፡፡ በእርሻና በዝናብ ወቅት እንዲሁም በተለያዩ ወቅቶች አብረው ይዘፍናሉ፡፡ ከሥራ ሲመለሱ አብረው ቁጭ ብለው ጠላቸውን እየጠጡ ‹‹ኮታና›› የሚለውን ዜማ ያንጐራጉራሉ፡፡ ሲቀመጡ ብቻ ሳይሆን መንገድም ላይ ‹‹አሻ›› የሚል ዘፈን እየዘፈኑ ይራመዳሉ፡፡ በፋሲካ ጊዜም ‹‹ኩንዳን›› ይዘፍናሉ፡፡

ዘፈኑንም ሲሠራ ከክራርና ከከበሮ በተጨማሪ ባለ ሁለት ክር የተሠራው ‹‹አባንጋላ›› የሚባል የሙዚቃ መሣሪያ እንዲሁም ከቆርኪ የሚሠራው ‹‹ሾካ››ንም ለማስተዋወቅ ችሏል፡፡

የሕወሓት ኪነት አባል የነበረው ኪዳነ በትግልም ወቅት ኩናምኛ ይዘፍን ነበር፡፡ እሱ ዘፈኑን ካወጣ በኋላ የተለያዩ ጥናታዊ ፊልሞች ስለማኅበረሰቡ መውጣት ጀመሩ፡፡ ዘፈኖቹም የማኅበረሰቡ አኗኗር ዘዬ ነፀብራቅ ለመሆን ችለዋል፡፡ ይኼም ሁኔታ ያስደስተዋል፡፡

ግሩም ግዛው የመለከት ባንድ አባል ሲሆን በመካኒሳና ጃዝ አምባ ሙዚቃ ትምህርት ቤቶችም ያስተምራል፡፡ አሁን በከተማው የሚሰሙት የደቡብ ዘፈኖች ምታቸውም ሆነ ዳንሳቸው ከምዕራብ አፍሪካ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ዩኒክ ናቸው በማለትም ይገልጻል፡፡

ባንዱም ያንን ሰፊና ያልተነካ ባህል በፔንታቶኒክ ስኬልና ከጃዝ ጋር በመቀላቀል ይጫወታል፡፡ ግሩም እንደሚያምነው የሙላቱ አስታጥቄ ሥራ ለብዙዎች ሥራዎች በር ከፋች ሆኗል፡፡ ‹‹ይሔ የደቡብ ዘፈን ላይ ያለው የመደጋገም (ጠሪ ቃል) በጣም ደስ የሚያሰኝ ድምፅ አለው፤›› ይላል ግሩም፡፡

ግሩም እንደሚለው ብዙዎቹ ለገበያ ተብለው የሚሠሩ ሥራዎች ቱባ የሆነውን መልኩን እያሳጣው ሔዷል፤ በተለይም ያ ለየት ያለው የአዘፋፈናቸው ስልትና የድምፅ አወጣጥ ብዙ ከተሜዎቹ ዘፋኞች ላይ አይታይም፡፡

‹‹ብዙዎቹ ከተማ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ዘፋኞች የአንድን ማኅበረሰብ ባህል በትክክል ማምጣት ይከብዳቸዋል፡፡ በተለይም የድምፅ አወጣጥ ላይ ችግር ይታያል፡፡›› ግሩም እሱ እንደሚለውም ይሔ ጠለቅ ያለ ዜማ ያላቸው ዘፈኖች ወደ ገበያ ሲመጡ መልካቸውን ቀይረው ነው፡፡ ባንዱ ዘፈኖችን ከጋምቤላ፣ ከጌድኦ እያመጣ ከተለያዩ ስልት ጋር በመቀላቀል ይጫወቱታል፡፡

ብዙዎች እንደሚከራከሩት የዘፈኖቹ ቅንብር በተለይም ከሌላ ስልት የተቀላቀሉበት መንገድ ጥሩ አለመሆኑን ነው፡፡ እንደ ዶክተር ውቤ ካሣዬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤዱኬሽንና ቢሄቪየራል ሳይንስ ዲፓርትመንትና መምህርና ለብዙ ዓመታት ሙዚቃ ያስተማሩ ሲሆን፣ ገበያው ሙዚቃውን የሚመራበት መንገድ እንደሚያስፈራቸውም አልደበቁም፡፡

‹‹የከተማው የኑሮ ዘዬ ሌላውን የአገሪቷ ክፍል ይመራል፣ እናም በየአካባቢው የሚወለዱት ታዋቂ ዘፋኞች ሰለሚከተሉ ባህሉ እንዲጠፋ ያደርገዋል፡፡›› ይላሉ፡፡

አንዳንዶች እንደሚሉት፣ የከተማ ሙዚቀኞች ለማኅበረሰቡ ሥነ ልቡናዊ ቅጥ (ሳይኮሎጂካዊ ሜካፕ) እንዲሁም ለባህሉ አዲስ በመሆናቸው የማኅበረሰቡን የልብ ምት ሊያገኙት አልቻሉም፡፡

ከዚህ በተለየ መልኩ ባህል አንድ ቦታ አይቆምም፣ ባህል ተራማጅ ነው፣ እንዲሁም የመቀላቀሉ ሥራ የፖስት ሞደርኒዝም እንቅስቃሴ ነው የሚሉም አልታጡም፡፡ የደቡብ ሙዚቃም አንዲሁም ከሌሎቹ ጋር መቀላቀሉ የዚህ እንቅስቃሴ መገለጫ ነውም ይላሉ፡፡

No comments: