Monday, April 1, 2013

ሲም ካርድ ከቴሌ ኔትወርክ ከእኛ?

ሰላም! ሰላም! ለመሆኑ ‹‹እየሄዳችሁ ነው?›› በማለት ብጠይቃችሁ አደናግራችሁ ይሆን? ለማንኛውም የሰማ ላልሰማ እንዲያሰማ የሰሞኑ የሰላምታ ፋሽን ይኼ መሆኑን ለመናገር እወዳለሁ።
ኑሮ በጠና ይዞን ጤና በጠፋበት ጊዜ ጤና ይስጥልኝ መባባል ከነትናንት ጋር እያለፈበት የሄደ ይመስላል። ጨዋታዬን ስጀምር ሁሌም በሰላምታ ነው። ከሰላምታውም ጋር ተያይዘው አንዳንድ ወጎችም ቁምነገሮች እንዳጫውታችሁ ይገፋፉኛል።

ታዲያላችሁ የዚህ ጥያቄ (‘እየሄዳችሁ ነው?’ የሚለው ማለት ነው) ምንጩን ለማጣራት ሞከርኩ። እንደነገሩኝ ከሆነ ‹‹ራብ ክፉ ሰው ነህ ከቶ አንጀት የለህም፣ ስሄድ ያዘኝ እንጂ ቆሜስ አልቆይህም፤›› ከሚል ባህላዊ የቁጭት ግጥም የመጣ መሆኑን ነገሩኝ። ‹‹ሁሉም ሰው በሕይወት መስመሩ ተስፋ መቁረጥን አስወግዶ ቢያንስ እየሄደ እንዲታገል ለማደፋፈር የታሰበ የሰላምታ ዓይነት ነው፤›› ብሎ ማን ያስረዳኛል ባሻዬ። የዘንድሮን ፍልስፍናና ፈጠራ ግን ታዩልኛላችሁ? ወይ ትራንስፎርማሽን!

 እንግዲህ እኔም ይኼን ስሰማ መጠርጠር ልማዴም አይደል? የምርጫ ዋዜማ ስለሆነ ‹‹የገዢው ፓርቲ ስትራቴጂ ይሆን እንዴ ይኼ ነገር?›› ብዬ አሰብኩ። ‹‹ያገኛችሁትን ከጤፍ ጋር ቀላቅላችሁ ብሉ ያለን መንግሥት ‘በባዶ እየታገላችሁ ኑሩ’ ለማለት ምን ይከብደዋል?›› የሚለኝ ደግሞ የዘወትር ወዳጄ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። ወሬው ሁሉ ሄዶ ሄዶ ከመንግሥት ጋር ሲጋጭ ሳይ እገረማለሁ። እጀግ በጣም የምገረመው ግን ይኼን ሁሉ ስሞታና ሐሜት የሚሰማው መንግሥታችን ስለምናወራው ነገር ምንም ነገር እንደማይገባው መታወቁ ነው። አሁን አሁንማ ዝም ብለን ስናስበው፣ በቃ መንግሥታችን ምንም ነገር ሊገለጽለት እንዳልቻለ ይሰማናል። ድሮ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ሳለን (ስሙ ይቅርና) አንዳንድ አስተማሪዎች ስለሚያስተምሩት ነገርም ምንም የማይገባው ጓደኛ ነበረን። አንድ ቀን የአማርኛ መምህራችን፣ ‹‹አንተ ላይህ ላይ ትምህርት ቤት ቢሠራብህም አይገባህም!›› ቢሉት፣ ‹‹ጥያቄውን ድገሙልኝ›› ያለው ትዝ አላለኝ መሰላችሁ? ሳያውቁ ወይስ እያወቁ ማጥፋት? እስኪ ምን ይሉታል?

አነሰም አደገም ከፋም ለማም ደግነቱ ይኼው እየሄድን ነው። ‘ወዴት?’ ከሆነ ጥያቄያችሁ መልሱ ወደፊት! ነው። ቢሞላም ባይሞላም ወደፊት ብለናል ለጊዜው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን  አንድ ትልቅ ጉባዔ አልነበር? ለነገሩ በእኛ አገር ስብሰባ ያልኖረበት ቀን መቼ አለ? ‹‹እኛ አገር ሁሌ የሌለው ፋሲካ እንጂ ስብሰባ አይደለም፤›› እስኪባል ድረስ እኮ ነው የማወራችሁ። ደግነቱ ገዢው ፓርቲያችን በስብሰባ ነዋሪውን፣ ሠራተኛውን፣ ተማሪውን እንዳሰለቸ ሲገባው ስሙን ግምገማ ብሎ ከቀየረው ቆይቷል። ‹‹በተለይ ለሐበሻ በጣም ተስማሚው ቃል የተገኘለት…›› አለኝና የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ገዢው ፓርቲን ቢያንስ በዚህ ልናመሰግነው ይገባል፤›› ብሎ አጨበጨበ። እኔም በጭብጨባው ደንግጬ አልፎ ሂያጁን ገልመጥ እያልኩ ሳስተውል ቆየሁና ‹‹እንዴት?›› ስል ጠየኩት።

‹‹አንበርብር? ይኼንንም እንዳስረዳህ ትፈልጋለህ? እስኪ ዝም ብለህ ሁለቱን ቃላት አነጻጽራቸው። ‘ስብሰባ’ ሲባል አንድ ሐሳብ ላይ ለመድረስ በአንድ ወይም በተወሰኑ አጀንዳዎች ዙሪያ ለአዲስ ነገር መወያየት ማለት ነው። ‘ግምገማ’ ሲሆን ግን ቀጥታ የግለሰብን ገመና ገላጭ ነው። ምንም እንኳ ሥራው መነሻ ቢሆንም ማብቂያው ወይም መደምደሚያው ሥራውን ሲሠራው  የነበረው ግለሰብ ነው። ይኼ ደግሞ ለሐሜትና ለሹክሹክታ አሪፍ አጋጣሚ ያስገኛል። ያኔ እንዲሁም እንዲሁ ነን ማን ሥራ ሊሠራልህ ትፈልጋል?›› ሲለኝ ነገሩ ገባኝ። አገሪቷ ራሷ በድህነት ተቆራምዳ ተቀምጣ የሰረቀችን ዕድሜ አንሶ እልፍ ያለ ነገር ላንሠራ ዕድሜያችን በስብሰባ ማለቁ በእውነት ያንገበግባል። ‹‹ለነገሩ ሥራ ማለት ሕግና ደንብ በሳምንት በሳምንት እየቀያየሩ ሕዝብን ማሰልቸት በሆነበት አገር ስብሰባ ባይበዛ ይገርመን ነበር፤›› የሚለው ደግሞ አንድ ደላላ ወዳጄ ነው። አቤት በየተቋማቱ ያለ የቢሮክራሲ ምሬት፡፡ የሚቻለውን አይቻልም የሚለው ጥቃቅን ሹመኛ መብዛቱ ነው ምክንያቱ፡፡

ይኼውላችሁ ስለመተካካትና ስለሰሞኑ የኢሕአዴግ ጉባዔ አወራለሁ ብዬ ሌላ ነገር እቆሰቁስ ጀመር። ይሁን ግድ የለም፤ የምንገናኘው የሆድ የሆዳችን ለመጫወትም አይደል? ይኼ ኢሕአዴግ ‹‹መተካካት›› እኛ ደግሞ ‹‹መጠጋጋት›› የምንለው ነገር ሰሞኑን በርካታ ሰዎችን ብዙ ሲያስብላቸው እታዘብ ነበር። ይህ በዚህ እንዳለ ግን ስልኬ ጠርታ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ በተቆራረጠ ድምፅ ባለሦስት ፎቅ መኖሪያ ቤት እንደሚሸጥ እንደተነገረኝ ልንገራችሁ። ወደዚያው ቤቱን ለማየት መጓዝ ጀመርኩ። ቤቱ የሚገኝበት አካባቢ ስደርስ ባለቤቶቹን ደወልኩላቸውና መጥተው እየመሩ ወስደው እስኪያሳዩኝ በተለመደችው አቋቋም (በፎቶ እንደምታዩት) ቆሜ እጠባበቅ ጀመር። እንዲህ አላፊ አግዳሚውን ሳጠና ነበር ገዢው ፓርቲን የተመለከቱ ወሬዎች ሲንሸራሸሩ የታዘብኩት። አንዱ ‹‹አገር የግለሰብ ትመስል ፓርቲ ሳይተካ ግለሰብ ቢቀያየር ምን ይጠቅመናል?›› እያለ እጁን ያወናጭፋል። ሌላው፣ ‹‹መቼ ነው ከፖለቲካቸው በላይ ስለሕዝብና ስለአገር አንገብጋቢ ጉዳይ ብቻ አውርተው የሚለያዩት? ዘለዓለም ፖለቲካ!›› እያለ እንዲሁ ይነጫነጫል።

ወዲያው አንድ መንገድ ዳር ተኝቶ የነበረ ወፈፍ ያደረገው ጎልማሳ ትኩር ብሎ እያየኝ ወደኔ ይመጣ ጀመር። እየተጠጋኝ በመጣ ቁጥር ጫት እየቃመ መሆኑን ማየት ችያለሁ። አጠገቤ ሲደርስ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ባይኖር እኔን እንዲህ አምሮብኝ አታየኝም ነበር፤›› አለኝ። መሳቅ እየቃጣኝ፣  ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹አንደኛ፣ እኔን የመሰለ ያራዳ ልጅ የእናቴን ቤት ወርሼ መሀል ከተማ እየኖርኩ ሳለሁ ‘ለልማት ስለምፈልገው’ በማለት አስነስቶ ጎዳና ስለጣለኝ። ሁለተኛ፣ የምበላው አጥቼ በምግብ አምሮት ስሰቃይ ጫት የሚባል አፍዛዥ አደንዛዥ እፅ በአደባባይ እንዲወሰድ በመፍቀዱ ረሃቤን ስላስታገሰ፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹መሀል አዲስ አበባ መኖ ቢቸግረኝ ጫቴን እየበላሁ በሙድ ተከብቤ እውልልሃለሁ። ይኼም መተካካት ነው አንድ አሥር ብር ጣል አድርግ እስኪ አሁን!›› ብሎ አፈጠጠብኝ። መተካካት በአንድም በሌላም ይኼው እዚህ ደረሰ፡፡   

 የሚሸጠውን ባለሦስት ፎቅ ቤት ካየሁ በኋላ ገዢ ለማፈላለግ መባከን ጀመርኩ። በዛሬ ጊዜ እንኳን ወዲያ ወዲህ ብላችሁ እንዲሁም የምታዩት ጉድ በዝቶ አይደል? እናላችሁ ጥድፍ ጥድፍ እያልኩ በአንድ ምግብ ቤት ደጃፍ (በኋላ አተኩሬ እንዳየሁት ‘በርገር’ ቤት) ሳልፍላችሁ ከወትሮው ለየት ያለ አለማመንና ለማኞች አጋጠሙኝ። በኋላ ሳስበው እኔ አጋጠምኳቸው ልበል እንጂ እነሱስ ሳይለምዱት የቀሩ አይመስልም። ለማኝ ተብዬዎቹ  ዩኒፎርም ለባሽ ሕፃናት ተማሪዎች ናቸው። የሚለምኑት ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ‘በርገር’ ነዋ ሌላ ምን ይሆናል ብላችሁ ነው በ‘ፋስት ፉድ’ ዘመን! እጄን ባፌ ላይ ጭኜ በማየው ነገር በጣም እየተገረምኩና እያዘንኩ እንዳለሁ፣ አንዳንድ አስተያየቶች ለማኝ ተማሪዎች ላይ ሲወርዱባቸው ማዳመጥ ጀመርኩ።

‹‹እናት በእልህ ተምሮ ትልቅ ደረጃ ይደርስልኛል ትላለች እነኝህ መንገድ ለመንገድ ልመና፤›› ይላሉ አንድ እናት እንደማሽሟጠጥ እያሉ። ‹‹ምናለ እንዲህ ‘ፋስት ፉዱ’ ላይ የምትነቁትን ያህል ትምህርቱ ላይ ብትበረቱ?›› ይጠይቃል ሌላው መንገደኛ። ‹‹እኛ ስለትምህርታችሁ ጥራት ከመንግሥት ጋር እንነታረካለን፣ እናንተ እዚህ የልመናን ሀሁ ትቆጥራላችሁ። ምንታደርጉ . . .››  ትላለች አንዲት ተመጋቢ። ይኼን ጊዜ በዘንድሮ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ምርጫ ላይ ብሳተፍ ኖሮ ስል ተቆጨሁ። ‹‹እንደማታሸንፍ እያወቅከው እንዴት አሰብከው?›› አለኝ የባሻዬ ልጅ የሆነውን ሁሉ አጫውቼው ሳበቃ። ‹‹አይምሰልህ ዋናው የፖለቲካ ጨዋታ ያለው ልዩ ምልክትህ ላይ ነው፤›› አልኩት። እሱም፣ ‹‹እሺ ተወዳድረህ ቢሆን ኖሮ ልዩ ምልክትህ ምን ይሆን ነበር?›› ሲለኝ መልሴን ቀድማችሁኝ ሳትሉት አትቀሩም ብዬ አስባለሁ።  ‘በርገር’! ምን በመሰለ የ‘በርገር’ ፎቶ ሆዱን ሳጮህለት እንኳን የዘንድሮ ወጣት ኢሕአዴግ ራሱ አይመርጠኝም ብላችሁ ነው? 

ለሽያጭ የተባለው ቤት ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት ባለቤቶቹ ሐሳባቸውን ስለቀየሩ እንዲከራይ ተፈርዶበት ቻይናዎች በግሩፕ ተከራዩት። እኔም ድርሻዬን ተቀብዬ ላጥ አልኩ። ለአንድ የቤት ኪራይ ሥራ የወጣች የምትመስለው ጀንበር ፈጥና ማቆልቆል ስትጀምር ወደ ቤቴ ጉዞ ጀመርኩ። መንገድ ላይ ሸማቹን፣ ለዋጩን፣ ነጋዴውን፣ ተማሪውን፣ አዛውንቱን፣ ወጣቱን ለመኖር ሲታገል እያስተዋልኩ እራመዳለሁ። አንዳንዴ የዚህ ሁሉ ልፋት ትርፉ ሳይገባን የመሮጣችን ሚስጥር እየገረመኝ፣ አንዳንዴ ደግሞ ከድካማችን ፍሬ (ምንም እንኳ ኑሮ እንዲህ መናሩ አግባብ ባይሆንም) የዕለት ጉርሳችንን ሸፍነን ስናደር ማየቴ እርካታ ይሰጠኛል። ባይሆን በዚህ በዚህ እንካስ እንጂ!

ቤት እንደደረስኩ ማንጠግቦሽ አፈፍ ብላ ተነስታ፣ ‹‹በል እኮ አንተን አይደል እንዴ የምጠብቀው? ምናምን ደረብ አድርግ ጎረቤት ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ የምንለው ሰው አለ፤›› አለችኝ። ፊቷ የተረበሸ ይመስላል። ‹‹ምን ተገኘ? ለመሆኑ ማን ነው እሱ?›› ብዬ ስጠይቅ ‘ኮንዶሚኒየም’ ዕጣ የደረሰውን አንድ ጎረቤታችንን የምሥራች እንዴት አልሰማህም ብላ ትወርድብኝ ጀመር። ሰው ሆኖ ምኞት መቼም አይከለከልም። ማንጠግቦሽም ዕለት ተዕለት የቤት አምሮቷ የምግብ አምሮቷን እየተሻማው ስለመጣ እንዲህ የምትሆነው ወዳ አይደለም። የሚገርማችሁ የምናውቀው ሰው ሁሉ መንግሥት ዕጣውን ተሳስቶም ይሁን አውቆ ባወጣለትና ባለቤት ባደረገው ቁጥር ትዳራችን ሥራው መበጥበጥ ሆኗል። አመሏን ስለማውቀው እንዳለችኝ ካፖርቴን ደርብ አድርጌ ስሄድ የእንኳን ደስ አለህ ‘ፓርቲ’ ተዘጋጅቶ ጠበቀኝ። ባሻዬም የባሻዬ ልጅም እዚያው ባገኛቸው፣ ‹‹ኧረ የት ልተንፍሰው?›› ስለው የነበረውን ጉድ ለማውራት ቸኮልኩ። ማንጠግቦሽ በዚህ ዙር የ‘ኮንዶሚኒየም’ ቤቶች ዕጣ ዕድለኛ ባለመሆኔ የእኔ ጥፋት እንደሆነ ሁሉ እንዳኮረፈችኝ እያጫወትኳ ቆየሁና፣ ‹‹እኔምለው ድግሱ ግን ያን ያህል አስፈላጊ ሆኖ ነው?›› ብዬ ባሻዬንም ልጃቸውን ጠየኳቸው። ሁለቱም እንደተመካከሩ ሁሉ ‹‹የዘመኑ ሰው ‘በልተን እንሙት’ ያለበት ዘመን ነው!›› ብለው አንድ ላይ መለሱልኝ። ወይ ‘በልተን እንሙት!’

ከድግሱ ቤት ወጥተን ቤታችን ደርሰን ለመተኛት ስንዘጋጅ የሞባይል ስልኬ ጮኸ፡፡ በዚህ ምሽት ማነው የሚደውልልኝ ብዬ ቁጥሩን ሳየው አላውቀውም፡፡ ለማንኛውም ብዬ ‹‹ሐሎ›› ማለት ስጀምር ስልኬ እንደ ማሽን ይጮህ ጀመር፡፡ ደንግጬ ዘጋሁት፡፡ እንደገና መደወል ሲጀምር ሳነሳው እንደ አውሎ ንፋስ ያለ ድምፅ ተሰማኝ፡፡ ‹‹ሐሎ፣ ሐሎ…›› ብል ድምፅ የለም፡፡ ቢቸግረኝ ባትሪውን አጥፍቼ አስቀመጥኩት፡፡ ማንጠግቦሽ እየሳቀች፣ ‹‹የተባለውን አልሰማህም እንዴ?›› አለችኝ፡፡ ‹‹ደግሞ ምን ተሰማ?›› ስላት፣ ‹‹ስለቴሌ ነዋ!›› ብላ ሳቀች፡፡ ከንዴቴ በረድ ብዬ፣ ‹‹ስለቴሌ ምን ተሰማ ደግሞ?›› ማለት፡፡ ‹‹እንዲህ በሞባይል መገናኘት አለመቻል ያስመረራቸው ሲም ካርድ ከቴሌ ኔትወርክ ከእኛ ማለት ጀምረዋል፤›› ስትለኝ ወደው አይስቁ አልኩኝ፡፡

No comments: