Wednesday, April 3, 2013

ከሚድሮክ ኢትዮጵያ ከ632 ሚሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ ይፈለጋል

ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከንግድ ትርፍ ግብርና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ከ632 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ በመንግሥት እንደሚፈለግበት የኩባንያው ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
ሚድሮክ ይህንን ክፍያ እንዲፈጽም የተነገረው ለባለኮከብ ሆቴሎቹ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኩባንያው ምንጮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በቅርቡ ለሚድሮክ ኢትዮጵያ በላካቸው ሦስት የትርፍ ግብር ውሳኔ ማስታወቂያዎች የተጠቀሰው ገንዘብ እንዲከፈል ጠይቋል፡፡


በዚህም መሠረት የመጀመርያው የውሳኔ ማስታወቂያ ከማንኛውም ንግድ ትርፍ ግብር ስለማስከፈል በወጣው አዋጅ ቁጥር 173/1953 ዓ.ም. መሠረት  እ.ኤ.አ. ከ1998 እስከ 2002 በጀት ዓመት ድረስ ተጨማሪ ግብር 95,789,968.58 ብር ሚድሮክ እንዲከፍል የተወሰነ መሆኑን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ በታክስ አመዳደቡ መሠረት ለተጠቀሰው ወቅት እንዲከፈል የታዘዘው ከንግድ ትርፍ ግብር (35 በመቶ) 50,417,772,94 ብር ሲሆን፣ መቀጫው 47,374,195.65 ብር መሆኑን ምንጮች አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም እ.ኤ.አ. ከ1998 እስከ 2002 በጀት ዓመት ድረስ ከማንኛውም ንግድ ትርፍ ግብር ስለማስከፈል በወጣው አዋጅ ቁጥር 286/1994 ዓ.ም. መሠረት 478,736,112.14 ብር ተጨማሪ ግብር እንዲከፈል መወሰኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይኼ በባለሥልጣኑ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተወሰነው የግብር ጥያቄ የንግድ ትርፍ ግብር (30 በመቶ) 126,772,352.88 ብር፣ ቀሪ ግብር 126,772,352.88 ብር፣ ወለድ 122,243,060.99 ብር፣ መቀጫ 229,420,698.27 ብር እንደሚያጠቃልል የሚድሮክ ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ሌላው ሚድሮክ ኢትዮጵያ የተጠየቀው የግብር ዓይነት የተጨማሪ እሴት ታክስ ሲሆን፣ ከ2003 እስከ 2004 በጀት ዓመትን ይመለከታል፡፡ በተጨማሪ እሴት ታክስ ውሳኔው ማስታወቂያ መሠረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ስለማስከፈል በወጣው አዋጅ ቁጥር 285/1994 ዓ.ም. መጠቀሱን ምንጮች ገልጸው፣ 58,375,206 ብር የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍል ሚድሮክ ታዟል፡፡

በአጠቃላይ በባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት የግብሩ አስተሳሰብና አመዳደብ መግለጫ በታክስ ኦዲት የሥራ ሒደት በተወሰነው የኦዲት ሪፖርት መሠረት፣ የግብር ውሳኔ በሰንጠረዥ ተዘርዝሮ ለሚድሮክ ኢትዮጵያ እንደደረሰው የኩባንያው ምንጮች አክለው አስረድተዋል፡፡ በአመዳደብ መግለጫው በተሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት ሚድሮክ ኩባንያ ለባለኮከብ ሆቴሎቹ እንዲከፍል የተወሰነበትን ግብር ማስታወቂያው በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ እንዲከፍል ማሳሰቢያ መስጠቱን ምንጮች ገልጸው፣ ካልከፈለ ግን እንደ እምቢተኛ ተቆጥሮ በሕጉ መሠረት እንደሚጠየቅ መገለጹን አስረድተዋል፡፡ ቅሬታ ካለውም ማቅረብ እንደሚችል መገለጹን እንዲሁ አክለው ገልጸዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በሚድሮክ ኢትዮጵያ ኩባንያ ሥር ያሉ ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ፣ ናሽናል ማይኒንግ ኮርፖሬሽን፣ ፋርማኪዩር ኩባንያ፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ኩባንያና ሚድሮክ የትምህርትና የሥልጠና ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2012 ድረስ የትርፍ ግብር ሪፖርታቸው ዜሮ የሚያሳይ መሆኑን የኩባንያው ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ሚድሮክ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአሥር ዓመታት በላይ መሥራታቸውን የሚናገሩ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተጠቀሱት ኩባንያዎች የትርፍ ግብር ሪፖርታቸው ዜሮ መሆኑ አስደንግጧቸዋል፡፡ በተለይ እንደ ሚድሮክ ጎልድ ያሉ ኩባንያዎች ሪፖርት ላይ ያዩት ዜሮ የሚለው አኅዝ ግራ እንዳጋባቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአገሪቱ ውስጥ በመሥራት ላይ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች በትርፍ ግብር መልክ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለመንግሥት ፈሰስ ሲያደርጉ እነዚህ ትላልቅ ኩባንያዎች አላተረፉም ሲባል ለመስማት ይከብዳል፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም በአነስተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለመንግሥት ተገቢውን ግብር ሲከፍሉና የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጡ፣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይጠበቅባቸዋል የሚባሉት እነዚህ ኩባንያዎች ዜሮ የትርፍ ግብር ሪፖርት ማቅረባቸው አሳሳቢ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

No comments: