- ፊያሜታ
አነበብኩት፡፡ ደግሜ አነበብኩት፡፡ መላልሼ አነበብኩት፡፡ ለምን
እንደሆነ አላውቅም ያነበብኩትን ነገር ለማመን አቃተኝ፡፡ ሉጫ ፀጉራቸው እርስ በርሱ ተገማምዶ ጀርባቸው ላይ
የወደቀ፣ ወዝ የጠገበ ላመነት ያገለደሙ፣ እህል የራቀው አንጀታቸውን በሰንሰለት ሸብ ያደረጉ፣ ፂማቸውን ያንዠረገጉ፣
ከአለም ተነጥለው በራቸውን የዘጉ…እንዲህ ያሉ መናኝ ---- በአሉ ግርማን ማሰብ አቃተኝ፡፡ “አበቃ” ብሎ በዘጋው
ጦሰኛ ስራው ሰበብ፣ የእሱም ነገር እንዳበቃ ከተነገረለት፤ ከዚያኛው በአሉ የቀጠለ ሌላ በአሉ አልመጣልህ አለኝ፡፡
ከተቋጨ ደራሲነትና ጋዜጠኝነት የቀጠለውን የበአሉ መናኝነት ማሰብ ተሳነኝ፡፡ ባለፈው ሰኞ ምሽት አንድ ወዳጄ
በፌስቡክ የላከልኝ “ጉድ” “በአሉ ግርማ በጣና ደሴት ገዳማት የመናኝ ህይወት እየገፋ ተገኘ” የሚል ነበር፡፡ ይህን
“ጉድ” ለማመን ቸግሮኝ ጥቂት እንደተወዛገብኩ፣ ነገርዬው “የሚያዝያ ልግጥ” (April the fool) ሊሆን
እንደሚችል ገመትኩ፡፡
ይሄን ጉድ ለላከልኝ ወዳጄ አጭር ምላሽ ላኩለት፡፡ “ወሩን ሙሉ
“አፕሪል ዘ ፉል” አለ እንዴ?” በማለት፡፡ የወዳጄ ምላሽ ፈጣንና የበለጠ ግራ አጋቢ ነበር፡፡ “እውነቴን ነው
የምልህ…አገር ምድሩ የሚያወራው እኮ ስለዚህ ነው፡፡ በአሉ ግርማ በህይወት ተገኝቷል” አለኝ፡፡ የወዳጄ እርግጠኝነት
ችላ ብዬው የነበረውን ከመሸ የመጣ “ወሬ”፣ ከፍፁም ቅጥፈት ቆጥሬ እንዳላልፈው አስገደደኝ፡፡ “ጉድ ሳይሰማ
ማክሰኞ አይጠባም” በሚል ሌሎች ወዳጆቼ ስለ ጉዳዩ ያውቁ እንደሆነ በዚያው በፌስቡክ ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ “አልሰሜን
ግባ በለው” አለኝ አንዱ፣ እስከዛሬ ስለ ጉዳዩ አለመስማቴን በሽሙጥ እየገለፀ፡፡ “ጀለሴ አፕሪል ዘ ፉል ነው”
ሌላኛው ቀጠለ፡፡ “እኔ እኮ በ1997 ዓ.ም ነው ይሄን ነገር የሰማሁት” ይህቺኛዋ ሴት ናት፡፡ “እውነት
ነው?...እባካችሁ የምታውቁ ንገሩኝ” ባህር ማዶ ያለ አብሮ አደጌ፡፡ የሚያሾፉ፣ የሚደሰቱ፣ የሚገረሙ፣ የሚደነግጡ፣
ተስፋ የሚያደርጉ…እንዲህና እንዲያ ያሉ ምላሾች አገኘሁ፡፡
ማክሰኞ ማለዳ… ሳብሰለስለው ያደረኩትን የበአሉ ጉዳይ በተመለከተ
መረጃ ሊኖራቸው ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ሁሉ መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ አብዛኞቹ ስለ ነገሩ ከሰሙ ቀናት ማለፋቸውን
ነበር የገለፁልኝ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን አንዳቸው እንኳን ከ’ወሬ’ነት ያለፈ ተጨባጭ መረጃ አልነበራቸውም፡፡ “ወሬ
ይሮጣል” እንዲል በዕውቀቱ ስዩም፣ የበአሉም ጉዳይ በፍጥነት አገር ምድሩን ማዳረስ ያዘ፡፡ እንደዋዛ ከቤቱ ወጥቶ
የውሃ ሽታ ሆኖ የቀረው በአሉ ግርማ፣ ‘ተፈፀመ’ ተብሎ ከተነገረለት ከአመታት በኋላ፣ እንደገና መቀጠሉ ተወራ፡፡
ድሮም ሞቱም ሆነ አሟሟቱ እንቆቅልሽ ነበርና፣ ብዙዎች ‘አልሞተም’ የሚለውን ፍፁም ላለማመን ምክንያት
አልነበራቸውም፡፡ ተድበስብሶ ያለፈውን የበአሉ ሞትና አሟሟት በተመለከተ እርግጠኛ ሆኖ በሙሉ ልብ የሚናገር ሰው
ባልተገኘባት አገር፣ የሰሞኑን ወሬ በግማሽ ልብም ቢሆን ለማመን የፈቀዱ ብዙዎችን ማግኘት ላይገርም ይችላል፡፡ ችግሩ
ግን እንደ ‘ሞቱ’ ሁሉ ‘መኖሩ’ንም በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ሰው መታጣቱ ነው፡፡ “በአሉ ግርማ በህይወት
ተገኘ!” የሚለው ወሬ የሁሉም መነጋገሪያ ሆነ፡፡ “ነገርዬው ‘አፕሪል ዘ ፉል’ ነው፣ እባካችሁ ተወት አድርጉት”
በማለት ህዝብን ከውዥንብር ለመታደግ የሞከሩ ቢኖሩም፣ አብዛኛው ሰው ግን ድሮም የበአሉ ነገር ያልተፈታ እንቆቅልሽ
ሆኖበት ነበርና “አይሆንምን ተተሽ…” በማለት ጆሮ ነፈጋቸው፡፡ የተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆችን በመጠቀም መምጫው
የማይታወቀውን ድንገተኛ ወሬ በየአቅጣጫው የሚነዙ በረከቱ፡፡ የፌስቡክ ገፆች ስለ “በአሉ ግርማ” በህይወት መኖር
በሚያትቱ ወሬዎች ተጣበቡ፡፡ ወሬውን የሰሙም የተሰማቸውን አስተያየት መሰንዘር ያዙ፡፡ ተስፋ ያደረጉ የደራሲው
አድናቂዎች፣ “ምናለ እውነት በሆነና የናፈቅነውን ብዕሩን መልሶ ባነሳልን!!... ምናለ ሌላ ኦሮማይ፣ ሌላ ከአድማስ
ባሻገር፣ ሌላ ሀዲስ በፃፈልን” ብለዋል፡፡
የበአሉ ሞት ሳይዋጥለት የኖረ ሌላ አድናቂውም፣ ‘ሊኖር ይችላል’
የሚል ጭለማ ተስፋው ጊዜ ጠብቆ እውን ሊሆን መስሎት ክፉኛ በጉጉት ልቡ ተሰቀለ፡፡ “ልክ ጉዳዩን ስሰማ ምን ትዝ
እንዳለኝ ታውቃላችሁ?... ስብሃት ገ/እግዚአብሔር በአንድ ወቅት ስለ በአሉ ሞት የተናገረው!” አለ ይሄው ተስፈኛ
የበአሉ አድናቂ፡፡ (ስብሀት በአሉን ደርግ አስገድሎታል ብሎ እንደማያስብ መናገሩን ልብ ይሏል)፡፡ ለሰሞንኛው
“ወሬ” ልቡን የሰጠ ሌላ የፌስ ቡክ ደምበኛ ደግሞ፣ ስለ በአሉ መኖር እናውቃለን ያሉትን የፌስ ቡክ አባላት ቅንጣት
ታህል አልተጠራጠረም፡፡ “በጣም …እጅግ በጣም ደስ የሚል ዜና ነው!...በአሉ በህይወት መኖሩን ከመስማቴ በላይ፣
የመንጌን ንፁህነት ማረጋገጤ አስደስቶኛል” ይላል የዚህ ሰው አስተያየት፡፡ ወሬው ይሮጣል… ከአፍ ወደ አፍ፣
ከፌስቡክ ወደ ፌስቡክ፣ ከትዊተር ወደ ትዊተር እየተሸጋገረ ይጋልባል፡፡
ይሄኛው ከዚያኛው ተቀብሎ በፍጥነት ለባለተራው እያሻገረ፣ ያልሰማ
መስማቱን፣ የሰማ ማሰማቱን ተጋበት፡፡ ወሬው በህዝቡ ዘንድ እየፈጠረ ያለው ውዥንብር ያልጣማቸው አንዳንዶች፣ “ኧረ
ደግ አይደለም” ለማለት ቢሞክሩም ሰሚ አልነበራቸውም፡፡ መሰረተ ቢሱ አሉባልታ በደራሲው ቤተሰቦች ላይ የሚፈጥረውን
የስነ ልቡና ተጽእኖ ቀድመው በመረዳት “ላልተጨበጠና ለማይታመን ወሬ ጆሮ አንስጥ” ለማለት የሞከሩም ነበሩ፡፡
ይሄም ሆኖ ግን ከእነዚህኞቹ ይልቅ እነዚያኞቹ የወሬው አቀጣጣዮች ነበሩ የተሰሙት፡፡ የጉዳዩን እውነትነት ለማጣራትና
እርግጥም በአሉ ግርማ ገዳም ውስጥ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ጊዜ ያጡ ፌስ ቡከኞች፣ የደራሲውን የቀድሞ ጉርድ
ፎቶግራፍ በመለጠፍ “ሆድ ማንቦጭቦጭ” ቀጠሉ፡፡ ከፎቶግራፉ ግርጌም እንዲህ ሲሉ ፃፉ- “የማይታመን፣ ግን እውነት
የሆነ ነገር” ይህን መረጃ (?) አይተው የማይታመነውን ለማመን የዳዱ ቢኖሩም፣ አንዳንዶች ግን “ሙድ መያዛቸው”
አልቀረም፡፡ “በአሉ ግርማ ገዳም ገባ” ላሏቸው ወዳጆቻቸው፣ “ፍሬንዶቼ…ሰውዬው እኮ ኮሚኒስት
ነበር!...ወይስ…የኮሚኒዝም ርዕዮተ አለም መጨረሻው ምናኔ ነው ተባለ?” የሚል የሽሙጥ መልስ በመስጠት፡፡ “በአሉ
ገዳም ውስጥ ተገኘ” በሚል የተጀመረው የሰሞኑ ወሬ ቀስ በቀስ ዘርዘር እያለ መጣ፡፡ “ነገሩ ወሬ ብቻ አይደለም”
የሚል አቋም ያላቸው አንዳንዶች፣ “ወሬ”ን ወደ “ዜና” ለማሳደግ ሞከሩ፡፡
“የትኛው ገዳም” ለሚለው የህዝቡ ጥያቄ፣ “የጣና ደሴቱ ደጋ
እስጢፋኖስ” የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ ይሄን ተከትሎ ብዙ ጆሮዎች ወደ ባህርዳር አቅጣጫ ተቀሰሩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ
ብዙ ጆሮዎች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ እግሮች አባይን ተሻግረው ወደ ጣና ገዳማት ሊዘልቁና መናኙን በአሉ ሊያገኙ ወረፋ
መያዛቸው ተወራ፡፡ “ይቅርታ “ተዘገበ” ነው የሚባለው አይደል?” “ተወራ” ብሎ ማለፍ፣ የድረ - ገፁን የዘጋቢነት
ሚና ለማንኳሰስ መሞከር እንዳይሆን ስለሰጋሁ ነው፡፡ “አምሃሪክ ቲዩብ” የተባለው ድረ - ገፅ በወሬ ደረጃ ይናፈስ
የነበረውን ጉዳይ በ”ዜና” ደረጃ አሳድጐ ነው ለአንባቢያን ያደረሰው፡፡ ድረ - ገፁ በዜና አምዱ ስር “በአሉ ግርማ
ባህርዳር ውስጥ ተገኘ” በሚል ርዕስ የዘገበው መረጃ፣ ደራሲው አለም በቃኝ ብሎ በመመንኮስ ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም
ውስጥ እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ እንደሚገኝ “አረጋግጧል”፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ የበአሉ ግርማን የድርሰት
ስራዎች ለሚናፍቁ፣ ባለመሞቱ ተደስተው “ከአሁን በኋላስ ይጽፍ ይሆን?” ብለው ለሚጠይቁ የዋህ አንባበያን ሌላ
ተጨማሪ የምስራች እነሆ አለ፡፡
በአሉ ገዳም ከገባ በኋላም ድርሰት መፃፍ አለማቋረጡን ጠቅሶ፣
ከቅርብ አመታት ወዲህ በአንድ ወጣት ደራሲ ስም እየታተሙ ለንባብ የሚበቁትና በመቶ ሺህ ኮፒዎች እየተሸጡ ያሉት
መጽሐፍት በሙሉ የበአሉ ግርማ ፈጠራዎች መሆናቸው መረጋገጡን (የፈረደበት “መረጋገጥ”) ይፋ አድርጓል፡፡ ድረ -
ገፁ በአሉ ግርማ የፃፋቸውና በወጣቱ ደራሲ ስም ለንባብ የበቁ መሆናቸውን ጠቅሶ የአራት መጽሐፍትን ርዕስ
ቢዘረዝርም፣ (ዘገባውን በትኩስነቱ ለህዝብ ለማድረስ ከመነጨ ጉጉት በተፈጠረ ስህተት ይመስላል) ከተዘረዘሩት
የመጽሐፍት ርዕሶች መካከል አንደኛው፣ ሌላኛው መጽሐፍ ላይ የሚገኝ ገፀ - ባህሪ ስም ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህች
ትንሽ ስህተት ምክንያት የድረ ገፁን ዘገባ ዋጋ ማሳጣት ያልፈለጉ አንዳንድ ቅን አንባቢዎች ታዲያ፣ “በዘገባው እንደ
መጽሐፍ ርዕስ ሆኖ የተጠቀሰው ስያሜ፣ ወጣቱ ደራሲ በበአሉ ስራዎች ባገኘው ገንዘብ ያቋቋመው “ሆቴል” ስም በመሆኑ
እንደ መጽሐፍ ቢቆጠር ችግር የለውም” ብለዋል፡፡ እዚህ ላይ የአንድ ወዳጄን ገጠመኝ ማንሳት ይኖርብኛል፡፡
ወዳጄ ከላይ የተጠቀሰውን ወጣት ደራሲ አላደንቅም ባይ ነው፡፡
መጽሐፍቱንም ደጋግሞ ሲተች አውቀዋለሁ፡፡ ሰሞኑን ታዲያ ይሄው ድረ ገጽ መጽሐፍቱ በበአሉ ግርማ እንደተፃፉ
ማረጋገጡን ሲያውጅ በደስታ ሰክሮ “እነዚህ መጽሐፍት የበአሉ ግርማ ናቸው ተባለ እኮ” አለኝ፡፡ ደራሲውን ሲያጣጥል
መጽሐፍቱን እያደነቀ መሆኑ አልገባውም፡፡ ለሳምንታት ያህል የዘለቀው ሯጭ ወሬ ውቅያኖስ ተሻግሮ ለመዝለቅ ጊዜ
አልፈጀበትም፡፡ አባይን ተሻግሮ የወሬውን እውነትነት ለማረጋገጥ የሞከረ ሰው ስለመኖሩ ሳልሰማ ነበር፣ ወሬው ራሱ
ውቅያኖስ ተሻግሮ አሜሪካ መግባቱን ያወቅሁት፡፡ መቀመጫውን በአትላንታ ያደረገውና ዘወትር ቅዳሜ የተለያዩ የመዝናኛ
ፕሮግራሞችን በአማርኛ ቋንቋ የሚያቀርበው “አድማስ ሬዲዮ”፣ ዛሬ ማታ ከደራሲ በአሉ ግርማ ሴት ልጅ ጋር በጉዳዩ
ዙሪያ ቃለ ምልልስ ሊያደርግ ቀጠሮ ይዟል፡፡ ወደ አካባቢው በመደወል ነገሩን ለማጣራት የሞከሩ ግለሰቦች
አጋጥመውኛል፡፡ ወደ ጣና ደሴቶች አምርቶ የዳጋ እስጢፋኖስን ገዳም የአስተዳደር አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸውን
በማነጋገር እውነታውን ለማጣራት የሞከረው ወጣቱ ጋዜጠኛና ገጣሚ ደመቀ ከበደ፣ ከትናንት በስቲያ የሙከራውን ውጤት
እነሆ ብሏል፡፡ ያነጋገራቸው ሁሉ እርግጠኛ ሆነው የሰጡት ምላሽ እንዲህ የሚል ነው፤ “ከመናኞች መካከል ይህ
የምትሉት ሰው የለም” ኦሮማይ (?)
No comments:
Post a Comment