የመንግሥትም ሆነ የግሉ ሚዲያ የኢሕአዴግ ጉባዔ ዜናዎችን በማሰራጨት ተጠምደዋል፡፡ በተለይ አራቱ
የግንባሩ አባል ድርጅቶች በበላይነት የሚመሩባቸው ክልሎች ዋና ከተሞች ላይ የየራሳቸው ጉባዔያቸውን እያካሄዱ
ነበር፡፡
በአንዳንድ አባል ድርጅቶች ጠንካራ አመራሮችን ለማስወገድ፣ በሌሎች ደግሞ የቀድሞውን አመራር ለማጠናከር ጥቅም ላይ ውሏል በሚል እያነጋገረ ነው፡፡ ድርጅቱ ከ20 ዓመታት በፊት በ1981 ዓ.ም. በሕወሓት ፊታውራሪነት ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በበላይነት የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የፓርቲው ቀጥሎም የመንግሥት ከፍተኛ ሥልጣናቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አያውቅም፡፡ የሕወሓትንና የኢሕአዴግን የፓርቲ የውስጥ የፖለቲካ አጀንዳ ብቻም ሳይሆን የአገሪቱን የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ የሚወስን አቅጣጫ የሚያስይዙ፣ የፖለቲካውም፣ የኢኮኖሚውም፣ የውጭ ግንኙነቱም መሐንዲስ ሆነው ቆይተዋል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ‹‹ዲሞክራሲያዊነታቸው›› በብዙዎች ዘንድ አከራካሪ ቢሆንም፣ ሥልጣንን የመጠቅለል ችሎታቸው፣ ተፎካካሪያቸውን በዕውቀትና በንግግር ብልጠት ክህሎታቸው ልቀት ግን ለጭፍን ደጋፊዎቻቸውም ለአክራሪ ጠላቶቻቸውም የሚያጠያይቅ አልነበረም፡፡ ይህ ከፍተኛ የአመራር ብቃታቸው፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕውቀታቸውና ተናግሮ የማሳመን ክህሎታቸው ከፓርቲም ከአገርም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስመስክረው አልፈዋል፡፡ ምናልባትም በመጨረሻ የሥልጣን የሕይወት ዘመናቸው በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪው ሰው ሆነው ነበር፡፡
በውጭ መሪዎችም ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ድህነት ቀባሪ፣ የልማት አብሳሪ፣ የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ጠባቂ፣ የአፍሪካ ቃል አቀባይ፣ የዓለም የድሆች ተሟጓች የሚሉ ቅጥያ ስያሜዎችን እንደሰጡዋቸው በሕልፈተ ሕይወታቸው ወቅት የተስተናገዱ የተለያዩ ጽሑፎች ያመለክታሉ፡፡ ቡድን 20 እና ቡድን ስምንትን ጨምሮ የዓለምን ፖለቲካ ብሎም የአፍሪካና የተቀረውን ዓለም ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት የመወሰን ከፍተኛ ሚና ባላቸው ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የሚሳተፉ ብቻ ሳይሆን፣ በእያንዳንዱ አጋጣሚ አንዳች አነጋጋሪ ሐሳብ በማቅረብና በመሞገት የሚታወቁ ሰውም ነበሩ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበለፀጉ አገሮች በተለይ ደግሞ በቀድሞ የአፍሪካ ቅኝ ገዥዎች የተከፈተ ጦርነት ያስመሰሉበት የአየር ንብረት ለውጥ ፖለቲካ፣ የዓለም መሪዎች የሚሉት እስኪጠፋቸው አንዳንዶቹም ስብሰባ ረግጠው እንዲወጡ ያስገደደው የአቶ መለስ የካሳ ጥያቄ፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠር ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለአፍሪካ እንዲሰጥ ግፊት አድርጓል፡፡ በተቃዋሚዎቻቸው ስማቸው በአንባገነንነት የሚነሳ ቢሆንም፣ በአንዳንዶቹ ታዋቂ ጸሐፊዎች ‹‹አንባገነንነት በዓለም ተቀባይነት እንዲኖረው ያደረጉ ብቸኛ መሪ›› የሚል ስያሜም ያገኙ ናቸው፡፡
በከፍተኛ የመሪነት ብቃታቸውና በኢኮኖሚ ዕውቀታቸው፣ ከዚህ የተነሳም በፓርቲ መሪነታቸውም ሆነ በአገር መሪነታቸው ጥያቄ ያነሳ ሰው በአጠገባቸው አልነበረም፡፡ ይህንን ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን በድርጅታቸው ውስጥ የማይተኩ ብቸኛ መሪ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡
የመተካካት መሐንዲስ
በተለይ የ97ቱ አወዛጋቢ ምርጫ ያስከተለውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ቢቢሲን፣ አልጄዚራን፣ አሶሼትድ ፕሬስን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋዜጠኞች ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አንድ ሳያነሱት የማያልፉት ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ሥልጣን መቼ ይለቃሉ?›› የሚል፡፡ በዚህ ጋዜጣም አቶ መለስ ‹‹የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይባሉ ይሆን?›› በሚል የተጻፈው ዘገባም ይታወሳል፡፡ በፓርቲ ሥልጣን በበረሃ የነበሩት ተቀናቃኞቻቸውን እነ ግደይ ዘርአፅዮንና አረጋዊ በርኼን በተለያዩ ጊዜያቶች ሞግተው በፖለቲካ ልዩነት ከድርጅቱ እንዲወገዱ በማድረግ ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰላሳ ዓመታት ደገማ የሕወሓት ሊቀመንበር በመሆን፣ ኢሕአዴግን ከ20 ዓመት በሚበልጥና አገርን ደግሞ ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በላይ ለ20 ዓመታት መርተዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያቶች የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ከፖለቲካ ጨዋታ ውጪ ማድረግ ቢችሉም፣ እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ ሥልጣን የግላቸው አልነበረም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ላይ ሆነው የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉ ሰውም አልነበሩም፡፡ በወቅቱ የሕወሓት መሰንጠቅን ተከትሎ የድርጅቱ ርዕዮተ ዓለም ቁንጮ (አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም) የወታደራዊ ስትራቴጂ ባለቤት (የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃ)፣ የፕሮፓጋንዳ ኃላፊው (የቀድሞ የትግራይ ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አስራት) እና ሌሎች የድርጅቱ ከ10 በላይ ከፍተኛ አመራሮች መወገድን አስከትሏል፡፡ የእነዚህ የድርጅቱ ወሳኝ ሰዎች መወገድን ተከትሎ በመንግሥትም ሆነ በፓርቲ ሥልጣናቸውን የተደላደለና ምንም የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሌላቸው ሰው መሆን የቻሉበት ጊዜ ነበር፡፡ የፈለጉትን ሕግ ማውጣት ያልፈለጉትን የመደቆስ ሥልጣኑም ጉልበቱም ነበራቸው፡፡
በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች አመለካከት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የራሳቸው የግል ሰብዕና ፈጥረው ሲያበቁ ነበር ‹‹ሥልጣን እለቃለሁ›› የሚል ጥያቄ ያነሱት፡፡ ሥልጣን የሚለቁት ግን ሌሎች በአጠገባቸው ያሉትን ባለሥልጣናትም አብረው እንዲለቁ የሚያስገድድ ሐሳብ ይዘው በመምጣት ነበር፡፡ የመተካካት መርህ የሐሳቡ አመንጪና በድርጅቱ ምክር ቤት አስወሳኝ መሆናቸው የሚነገርላቸው ሲሆን፣ በተለይ ከትጥቅ ትግል ጊዜ ጀምሮ አመራር ላይ የነበረው የቀድሞው አመራር በአዲስ ትውልድ የመተካት ጉዳይ ነው፡፡
ለመተካካት መርሁ መነሻም መድረሻም ድርጅቱን ሥልጣን ላይ ማቆየትን መሠረት ያደረገ መሆኑ አመላካቾች አይጠፉም፡፡ ለዚህም ድርጅቱ እንደ ሞዴል መነሻ ያደረገው አንድ ፓርቲ ለሃምሳና ለስልሳ ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆየባቸውን ጃፓንና ቻይናን ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ሕዝቡ ለኢሕአዴግ ድምፁን የነፈገበትን ሁኔታ ይተነትናሉ፡፡ ሥልጣን ላይ ለብዙ ጊዜ መቆየት ለብዙ ተንታኞች የዲሞክራሲ ምልክት ተደርጎ የሚታይ ባይሆንም፣ ለሃምሳና ለአርባ ዓመታት ሥልጣን ላይ መቆየት ለአቶ መለስና ለኢሕአዴግ አምባገነንት አይደለም፡፡ በ97 ምርጫ ሕዝቡ በአመራሩ ላይ የተመዘዘ ‹‹ቢጫ ካርድ›› ነው ብሎታል፡፡ የድርጅቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ርዕዮተ ዓለም ትንተና የሚደረግበት አዲስ ራዕይ መጽሔት የሐምሌ-ነሐሴ 2001 ዕትም እንደሚያብራራው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወነው የአመራር መተካካት በኢትዮጵያም ተግባራዊ እየሆነ መምጣቱንና በምርጫ ኢሕአዴግ አሸናፊ እየሆነ መቆየቱን ያትታል፡፡ ‹‹ይሁንና . . . ለማንም ግልጽ እንደሚሆነው ኢሕአዴግ ስህተቶችን ካላረመ ምን ሊከተል እንደሚችል የ97 ዓ.ም. ምርጫ አመላክቷል፡፡ ምንም እንኳን እስከዛሬ ኢሕአዴግ ከመንግሥት ኃላፊነት በቀይ ካርድ ባይባረርም፣ በ97 ምርጫ ቢጫ ካርድ ተሰጥቶት እንደነበር የማይካድ ነው፤›› (ገጽ 6) ይላል፡፡ የድርጅቱ የመተካካት መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለመደው የምርጫ ዲሞክራሲ የማይፃረር ነገር ግን ‹‹ከልማታዊ ዲሞክራሲያዊ አቅጣጫ›› ምልከታ ከተለመደው ዲሞክራሲያዊ አሠራር በላይ የተካሄደ የድርጅቱ የምክር ቤት ውሳኔ ነው፡፡
ያ የሆነበት ምክንያት የድርጅቱ ልዩ ባህሪ አስገዳጅ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግል የመጣ ነው፡፡ ሌላው ላለው የኪራይ ሰብሳቢነት ፈተና በተደጋጋሚ የተጋለጠ መሆኑ ነው፡፡ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በቁልፍ የአመራር ቦታ የቆየ አንድ ኃይል መኖሩም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ይኼው ኃይል በአንድ በኩል ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ የሚያበረክት፣ በሌላ በኩል ከጥቅም ውጪ ከመሆኑ በፊት በተደራጀና በአስተማማኝ ሁኔታ የአመራር መተካካቱ ሥራ የሚከናወንበት ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ነው፤›› (ገጽ 8)፡፡
በተለመደው ዲሞክራሲያዊ አካሄድ አባላቱ በነባሩ አመራር ኃይል ላይ ጠንካራ እምነት ስላለው በሒደት አመራሩ በተፈጥሮአዊ ምክንያት ተዳክሞና ውጤት ማምጣት ተስኖት እምነት እስኪያጣበት ድረስ በተከታታይ ሊመርጠው ይችላል የሚለው የድርጅቱ አቋም ነው፡፡
በመሆኑም በዚሁ የድርጅቱ መጽሔት እንደተብራራው፣ ኢሕአዴግ የመተካካት መርህ ያስፈለገው የቀድሞው አመራር በተለመደው የሕዝብ ምርጫ ሊስተናገድ ሰለማይችል የተለየ አሠራር ማስፈለጉን ነው፡፡ በመሆኑም የመርሁ አፈጻጸም በሁለት መንገድ ነው፡፡ በአንድ በኩል የአዲስ ትውልድ አመራር ማብቃት ነው፡፡ ተተኪ አመራር፡፡ በሌላ በኩል ነባሩን አመራር ደረጃ በደረጃ ወደ ደጋፊ ኃይልነት ማሸጋገር ይሆናል፡፡ እውነት አዲስ አመራር እንዲበቃ ተደርጓል? የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
የከሸፈው መተካካት
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሥልጣን ዘመናቸው ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የፓርቲውንም ሆነ የአገሪቱን የፖለቲካ አጀንዳ በቁጥጥራቸው ማድረግ ችለው ነበር፡፡ የመተካካት መርሁንም ይዘውት የመጡት ሥልጣን መልቀቅ መፈለጋቸውን ተከትሎ ስለመሆኑ አነጋጋሪ ነበር፡፡ የመተካካት መርሁን ተግባራዊ ለማድረግ ግንባር ቀደም ሆነው የፓርቲንም የመንግሥትንም ሥልጣን መልቀቅ እፈልጋለሁ ማለታቸው በፓርቲው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አንድም መተካካት የሚለው የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ባሥልጣናት በአዲስ አመራር የመተካት ስትራቴጂ ይዘው ከመጡ በኋላ ነው፡፡ ሒደቱ የበላይ አስፈጻሚ ያስፈልገዋል፡፡
ሁለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠቃላይ የፖለቲካ ምኅዳሩንና አጀንዳውን ተቆጣጥረው ቆይተው ፓርቲው አዲስ ሊቀመንበር ባላዘጋጀበት ሁኔታ ነው፡፡ በመሆኑም ሒደቱ እንዲጠና ተደርጎ ሁለትና ሦስት ውሳኔዎች ተወስነዋል፡፡ አንደኛ የሥልጣን የዕድሜ ጣርያ 65 እንዲሆን፣ የመተካካት ሒደቱ በሦስት ደረጃ በዱላ ቅብብሎሽ መርህ እንዲከናወን፣ ሦስተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይዘውት የመጡት አመራርን የማደስ ሒደት በበላይነት ራሳቸው እንዲመሩት፣ ራሳቸው አጨብጭበው የመጨረሻው ሦስተኛው ተተኪ ረድፍ በሚቀጥለው የምርጫ ዘመን ዋዜማ ይዘው እንዲወጡና አመራሩ በአጠቃላይ በአዲስ አመራር እንዲተካ ነበር፡፡ ሒደቱ እንዲጠናቀቅ የታሰበው ካለፈው ምርጫ 2002 እስከ ሚቀጥለው ምርጫ በአምስት ዓመት ውስጥ ነው፡፡
በፌስቡክ ድረ ገጽ ኢሕአዴግን በተለይ ደግሞ የሕወሓትን ወቅታዊ ሁኔታዎችን እየተከታተለ አዳዲስ መረጃዎችን በማስነበብና በመተንተን የሚታወቀው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ወጣት አብርሃ ደስታ ግን፣ የመተካካት ሒደትን ከመነሻው ጀምሮ እንደ መርህ አይቀበለውም፡፡ እንደ እሱ እምነት፣ መተካካት የሚል መርህ ብቅ ያለው በትጥቅ ትግል የመጣው የገዥው ፓርቲ አመራር እንዳለ ሥልጣን መቆጣጠሩ በሕዝቡ መወቀስ ሲጀመር ነበር፡፡ ታጋዮች ብቻ አመራሮች ሆነው በመቀጠላቸው ከሕዝቡ የቀረቡበት ከፍተኛ ወቀሳና ቅሬታ ወደሌላ ደረጃ እንዳይሸጋገር ለመቀልበስ ነው፡፡ ‹‹አይዞህ ሥልጣን ለብቻችን ተቆጣጥረን አንኖርም፤ አዲስ አመራር እንፈጥራለን የሚል ነው፤ ሲቪል አመራር፤›› ይላል፡፡ የመተካካት ሒደቱ ግን በምን መስፈርት፣ በዕድሜ ይሁን በብቃት ማነስ፣ ወይም ከፍተኛ ሥልጣን ላይ በመቆየት ግልጽ የሆነ ሥዕል እንዳልነበረው ያስረዳል፡፡ ይኼም የተደረገበት ሁኔታ አላስፈላጊ የሆነ አመራር ቀስ በቀስ ከሥልጣን ለማስወገድ ዓላማ ያደረገ ነው በማለት ያስረዳል፡፡
በመጀመርያው ሒደት አቶ ስብሐት ነጋንና አቶ ሥዩም መስፍንን (ከሕወሓት)፣ አቶ አዲሱ ለገሰና አቶ ተፈራ ዋልዋን (ከብአዴን) የመሳሰሉ አንጋፋ የድርጅቱ አመራሮች እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ በተለይ በሕወሓት ውስጥ አንድም የወጣት አመራር ወደ ከፍተኛ አመራር የመጣበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ አቦይ ስብሃትን ተክተው የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሆኑ የተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ቅሬታ መነሳቱ ይነገራል፡፡ የትግራይ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ፀጋይ በርኸም በዕድሜ ከእሳቸው ይበልጣሉ ተብለው በሚገመቱ በአቶ አባይ ወልዱ ነበር የተተኩት፡፡
በብአዴን ውስጥ የመተካካት ሒደቱ የተሻለ ጅምር ነበረው፡፡ ሁለቱም አንጋፋ መሪዎች በአዲስ ትውልድ አመራሮች ተተክተዋል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበርም አቶ ደመቀ መኮንን (በትጥቅ ትግል ያልነበሩ) እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ በኦሕዴድ የመተካካት ሒደትም በወቅቱ ብዙም ያልታየ ሲሆን፣ ደኢሕዴን በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ያልተሳተፈ በመሆኑ እምብዛም ሒደቱ እንዲሠራ አይጠበቅበትም፡፡
ዘንድሮ በ9ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ኢሕአዴግ ሁለተኛው የመተካካት ደረጃ በተሳካ ሁኔታ ያደርጋል ተብሎ ነበር የተጠበቀው፡፡ የሆነው ግን ለየቅል ይመስላል፡፡ ከተደረጉ ለውጦች አኳያ መተካካት (አብረሃ ደስታ እንዳለው) አንድም ከመነሻው የታለመለት ዓላማ እንደተባለው አዲስ አመራር ወደ ላቀ ደረጃ ለማምጣት አይደለም፡፡ ሁለትም መተካካት ኢሕአዴግ እንደሚለው የድርጅቱን አመራር ለማደስ ከሆነ የከሸፈበት ይመስላል፡፡ ለዚህም ሦስት ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡
አንድ መተካካት በድርጅት የውስጥ ፍላጐት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡንም ፍላጎትና ነባራዊ ሁኔታ ግምት ያስገባ እንዲሆን የተቀመጠ ነበር፡፡ ሆኖም አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በተለይ በሕወሓት ውስጥ ሁለት የተለያዩ ቡድኖች የተፈጠሩ መሆናቸውን፣ አንዱ ሌላውን ለማጥቃት መሣርያ መሆኑ ሲወራ ሰንብቷል፡፡ ክፍፍሉ በአንድ በኩል እነ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ አባይ ወልዱና ወ/ሮ አዜብ መስፍን ያሉበት መሆኑን፣ ይኼ ቡድን ጉባዔተኛውን በበቂ ሁኔታ ያደራጀና የተቆጣጠረ ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል በአብዛኛው በአዲስ አበባ የሚገኙትና እነ አቶ አርከበ ዕቁባይ፣ ደ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ የሚገኙበት መሆኑ፣ አንዳንድ የሕወሓት አንጋፋ አመራሮችም የአስታራቂነት ሚና ሲጫወቱ እንደነበር በስፋት ሲወራ ከርሟል፡፡
ያም ሆነ ይህ በአንዳንድ ሰዎች ቀድሞ እንደተገመተው አንድ ቡድን በሌላው ቡድን ላይ የበላይነቱን በማሳየት አብዛኛው ሕዝብ ከጠበቀው ውጪ በተለይ የአቶ አርከበ ዕቁባይና የአምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ በፓርቲው ከፍተኛ ቦታ ይሰጣቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ መሰናበታቸው አስደንጋጭ መሆኑም ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል በዕድሜም በአመራርም ደክመዋል ተብሎ የሚታመንባቸው እነ አቶ አባይ ወልዱና አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ ሥልጣን ይለቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ በከፍተኛ ሥልጣን እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ብዙዎችን ያስገረመው ግን የአቶ አባይ ወልዱ (የሕወሓት ሊቀመንበርና የወቅቱ የትግራይ ፕሬዚዳንት) ባለቤት ወ/ሮ ትርፏ ኪዳነ ማርያም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው መመረጥ ይመስላል፡፡ አንዳንድ የክልሉ ተወላጆች በተለይ ደግሞ የፓርቲው አባላት ሆነው በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች በዚህ ድርጊት የተበሳጩ ይመስላል፡፡ የፆታ ውክልናውን የሚደግፉ ሌሎችም አንድም ወ/ሮ ትርፏ ታጋይ በመሆናቸው የእሳቸው ወደላይኛው እርከን የመተካካት ሐሳብ የሚቃረን ነው በሚል፣ ሁለትም ለዚሁ ቦታ የሚበቃ የፖለቲካም ሆነ የትምህርት ብቃት የላቸውም የሚል ተቃውሞ በስፋት እየተሰማ ነው፡፡
ይህ አካሄድ በአብዛኛው በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አባሎች የዝምድና ትስስር መኖሩ ግልጽ የወጣ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስንና የቀድሞ የትግራይ ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋይ በርኸም በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚነት ከእነባለቤታቸው የነበሩ በመሆኑ ቤተሰባዊ ትስስሩ እየተለመደ መምጣቱ ይነገራል፡፡ አንጋፋ መሪዎችን ተከትለው ወደ ሥራ አስፈጻሚም ሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴ የገቡ ሰዎች ከአሸናፊው ቡድን ጋር ቅርበት ያላቸው በሚል ቅሬታ እየተነሳ መሆኑን መምህር አብርሃ ደስታ ለሪፖርተር አረጋግጧል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ከማዕከላዊ ኮሚቴም ሆነ ከሥራ አስፈጻሚ የተሸኙ ሰዎችን ተክተዋል የተባሉ ሰዎች አንዳንዶቹ ታጋዮች ባይሆኑም በዕድሜ ከወጡትም ይበልጣሉ የሚል ነው፡፡
ባለፈው ጉባዔ በመጀመርያ የመተካካት ደረጃ መልካም ፍንጭ ያሳየው ብአዴን አሁን ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ነው፡፡ ድርጅቱ በመተካካት ሒደት ብዙም ግምት ያልተሰጣቸው የፍትሕ ሚኒስትሩን አቶ ብርሃን ኃይሉና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚነት ዝቅ በማድረግ በድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አባልነት እንዲቀጥሉ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህም በላይ ቀደም ሲል በክብር የተሸኙት አቶ አዲሱ ለገሰን መልሶ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ማድረጉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በብአዴን ውሰጥ የታየው ስውር የሆነ የመሸጋሸግ ሒደት በሌሎች አባል ድርጅቶች ጥርጣሬ መፍጠሩ በስፋት እየተነገረ ሲሆን፣ በጉባዔተኞች መካከል ከፍተኛ ቅሬታ መስተዋሉን ጉባዔውን ከተከታተሉ አባላት ማወቅ ተችሏል፡፡ እንደተባለው ከሆነ የብአዴን አንጋፋ አመራሮች ለቀረበላቸው ጥያቄ በመከላከል ላይ የተመሠረተ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በድርጅቱ ጉባዔ እየተሳተፉ የነበሩት (አቦይ ስብሃትን ጨምሮ) የሕወሓት አንጋፋ ተሰናባች አመራሮች ግን ጉዳዩን ከሰዎች መቀያየር በላይ እንዲታይ በማለት ተተኪውን አመራር ማብቃት ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
በዚሁ የመተካካት ሒደት ሕወሓት አራት አንጋፋ አመራሮቹን ከሥራ አስፈጻሚነት በክብር ሲያሰናብት፣ ዘጠኝ ታጋይ አመራሮቹን ከማዕከላዊ ኮሚቴ ሸኝቷል፡፡ ከሕወሓት ቀጥሎ የመተካካት ሥራ መሥራቱ የተነገረለት አባል ድርጅት ኦሕዴድ ግን አቶ አባዱላ ገመዳና አቶ ኩማ ደመቅሳን ከሥራ አስፈጻሚነት ሸኝቷል፡፡ ከሕወሓት ውጪ የተቀሩት አባል ድርጅቶች የማዕከላዊ ኮሚቴ ቁጥር ከ45 ወደ 65 እና 81 ከፍ ያደረጉ ሲሆን፣ መተካካቱ አዲስ ወጣቶችን በማካተት ለማሳየት የተፈለገ ይመስላል፡፡
ድምዳሜ
የኢሕአዴግ የመተካካት ስትራቴጂ ግልጽ የሆነ መስፈርትና አሠራር አልተከተለም የሚሉ አሉ፡፡ በመሆኑም ከአንድ አባል ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ የተለያየ ገጽታ የተስተዋለ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ በአንዳንዶቹ ለመቧደን በሌሎች ደግሞ ሽግሽግ ለመፍጠር ጥቅም ላይ የዋለ ይመስላል፡፡ አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ሕወሓት ውስጥ ውስጥ ለውስጥ ተፈጠረ የተባለው መከፋፈል እንዳለ ሆኖ የመተካካት ሒደቱን ግን በግልጽ ታይቷል፡፡ ብአዴን ውስጥ የተከሰተው በክብር የተሸኙት የአቶ አዲሱ ተመልሶ መምጣት ግን ግርምትን ፈጥሯል፡፡ ከሁሉም አጋጣሚዎች ውጭ ግን መተካካቱ በአባል ፓርቲዎች የሚደረግ በመሆኑ የፓርቲዎቹ አመጣጥ፣ የሚያስተዳድሩት ሕዝብ ባህልና ጂኦግራፊያዊ ስፋት በመለያየቱ የማይጠበቅ አይደለም ይላሉ፡፡
በአጠቃላይ የመተካካት ሒደት ቀያሽ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በድንገት በማለፋቸው ሒደቱ ለአደጋ መጋለጡን አመላካች መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አዲስ አመራር (ተተኪ) ማብቃት የተባለው በአብዛኛው አባል ፓርቲዎች ያልሠራ ሲሆን፣ ብቃት ያላቸው አንዳንድ ወጣት አባላትም የቀድሞውን አመራር ሲተኩ አልተስተዋለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መተካካትን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ኢሕአዴግ ራሱ ማደስ ካልቻለ ከፍተኛ የመበስበስ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል አመልክተው የነበረ ሲሆን፣ እሳቸውን ተክቶ ሒደቱን ሊያሳካ የሚችል ጠንካራ አመራር ስለመኖሩ ጥርጣሬ ነግሷል፡፡ በጉባዔው ላይ የመተካካት ሒደቱ በሚገባ ሁኔታ መካሄዱ ቢነገርም፣ ብዙዎች ግን ሒደቱ ሳንካ ገጥሞታል በማለት ይሞግታሉ፡፡
No comments:
Post a Comment