Tuesday, April 16, 2013

የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና!

በዓለማችን ውስጥ የሚገኘው አጠቃላይ የምግብ ክምችት በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን በሙሉ ማጥገብ ይችል ነበር፤ ነገር ግን አብዛኛው የዓለማችን ሃብት በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ስር በመውደቁ ጥቂቶቹ የቅንጦት ኑሮ ሲኖሩ አብዛኛው ደሃ ህዝብ ግን በረሃብ አለንጋ ይገረፋል፤ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ባለመኖሩ፤ በማለት ማርክሲስቶች እኩልነት ደሃና ሃብታምን እኩል በማድረግ ማረጋገጥ እንደሚቻል ያስተምራሉ፡፡ በሌላ በኩል የካፒታሊዝም መስራቾች የግል ሃብት የማፍራት መብትን በማረጋገጥ የሃብታሞችና የድሆች መደቦችን በመፍጠር፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ማስፈን እንደሚቻል ወይም እኩልነትን በሃብት መበላለጥ ማምጣት እንደሚቻል ይሞግታሉ፡፡ የካፒታሊዝም ሆነ የሶሻሊዝም መስራቾች ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልንና እኩልነትን ይሰብካሉ፡፡

ታዲያ ሁለቱም እኩልነትንና ፍትህን የሚሰብኩ ከሆነ አሜሪካ መራሽ ካፒታሊስቶችና ሩሲያ መራሽ ሶሻሊስቶች ዓለምን ለሁለት ከፍለው ከአርባ አመታት በላይ ቀዝቃዛውን የሞቀ ጦርነት ለምን አካሄዱ? የካፒታሊዝም ፍልስፍና ኢ-ሥነምግባራዊ ነው? ሶሻሊዝምስ? ነገሩ ወዲህ ነው! ሁለቱም የኢኮኖሚ አስተሳሰቦች የሚያቀነቅኗቸው የምጣኔ ኃብት አስተሳሰቦች እርስ በርሳቸው በተቆላለፉ እጅግ በጣም ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ሥነ-ምግባራዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበረሰባዊ ፍልስፍናዎች የታጠሩ ናቸው፡፡ የዛሬው ጽሁፌ ዓላማ በካፒታሊዝም የኢኮኖሚ አስተሳሰብ የሚመራ ማህበረሰብ ወዶም ይሁን ተገዶ እየተመራበት ስለሚገኘው የኑሮ ፍልስፍና ሐተታ ማቅረብ ነው፡፡ ካፒታሊዝም በዲሞክራሲያዊ መርህ ላይ በተመሰረተ እኩልነት ይመራል፡፡
የዴሞክራሲ ስርዓት ሊያስከብራቸው ከተቋቋመበት ዓላማዎች ዋና ዋናዎቹ የመኖር፣ የነጻነት እና ንብረት የማፍራት (right to property) መብቶችን ማስከበር ነው፡፡ የካፒታሊዝም ኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ፍልስፍና መነሻቸው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ነው፤ በተለይም ደግሞ የግል ሀብት (private property) የማፍራት መብት፡፡ የዘመናዊው የካፒታሊዝም ምጣኔ ሀብት ፍልስፍና ጀማሪ ስኮትላንዳዊው ፈላስፋና የምጣኔ ሀብት ሊቅ አዳም ስሚዝ An Inquiry into the Nature and Causes of the Wealth of Nations በተባለውና በ1776 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፉ፣ በካፒታሊዝም ውስጥ የሚገኝ የሀብት ክፍፍል ደመወዝ፣ ኪራይ፣ ትርፍ በተባሉ ምጣኔ ሀብታዊ ጽንሰ ሃሳቦች ሊመነዘር እንደሚችልና ይህም ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት በሚደረግ ነጻ ገበያ (free market) ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
እንደ ስሚዝ እምነት፣ ለካፒታሊዝም ህልውና ወሳኝ የሆኑት ሦስት ሃሳቦች የግለሰቡ ፍላጎት (self-interest)፣ የግል ሀብት የማፍራት መብትና (private property) ውድድር (competetion) ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በካፒታሊስቶች አስተሳሰብ የግለሰቡ ፍላጎት (self-interest) ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ተብሎ ሲታሰብ፣ ማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የሚገኝ ሀብት ላይ ገንዘቡንና ጉልበቱን አፍስሶ፣ የራሴ የሚለው ሀብት የማግኘትና የማከማቸት መብት አለው የሚለውን መርህ የሚያጎላ ነው፡፡ የካፒታሊዝም ፍልስፍና የግለሰብ ፍላጎት ከማህበረሰብ ወይም ከሀገር ፍላጎት እንደሚበልጥ በገሃድ የሚታይበት አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህም ማለት ካፒታሊስቶች “በእኔ ባዮች” (egoists) የሥነ-ምግባር ፍልስፍና የሚመሩ ሲሆኑ ይህም ሰው በተፈጥሮው ራስ ወዳድ ስለሆነ፣ የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ ለአድራጊው ግለሰብ ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡
የዚህ ፍልስፍና ሁለተኛው መርህ፣ግለሰቡ በፈቀደው መንገድ የሰበሰበውን ሀብት የማከማቸት (accumulation) እና ባሻውና ያረካኛል በሚለው መንገድ የማውጣት መብትም የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ አንዱ ነጋዴ ከሌላው ነጋዴ፣ ተወዳድሮ ያሻውን ምርት ሊያመርትና ያዋጣኛል በሚለው ዋጋ በመሸጥ ትርፋማ ሊሆን ይችላል፡፡ የግል ሃብትን የማከማቸት መብት (the right to property) የካፒታሊዝም ኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች የተሳሰሩበት የጋራ መድረክ ነው፡፡ አንድ ሃገር የዴሞክራሲ ስርዓትን የሚከተል ከሆነ የካፒታሊዝምን ፍልስፍና መቀበል ይኖርበታል፤ ለካፒታሊዝም ህልውና ደግሞ የዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ጥበቃና ድጋፍ እስትንፋስ የግድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ለካፒታሊዝም ምጣኔ ሃብታዊ ፍልስፍናና ለአሜሪካ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው የእንግሊዙ ፈላስፋ ጆን ሎክ፤ ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ ያገኙት ሃብት ላይ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በማፍሰስ፣ የግል ሃብት የማካበት ተፈጥሯዊ መብት እንዳላቸው መሞገቱ የግል ሃብት መብት ምን ያህል ቁልፍ ቦታ እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሦስተኛው የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና መርህ፣ ውድድር (competetion) ነው፡፡ በእኔ ባይ የሥነ-ምግባር ፍልስፍና የተቃኘው የካፒታሊዝም የውድድር ፍልስፍና፣ ከትብብር በእጅጉ የራቀ ስለሆነ በሀብታምና በደሃ መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ጥቂት የአለማችን ሃብታም ግለሰቦች በርካታውን የምድራችንን ሃብት የሚይዙበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
በአሜሪካን ሀገር በኒዮርክ ከተማ በመስከረም በ2011 ዓ.ም ተነስተው የነበሩት የ Occupy the Wall Street (OWS) ሰልፈኞች “ዘጠና ዘጠኝ በመቶው የዓለም ህዝብ እኛ ድሆቹ ነን! We are the 99 percent!” የሚለው ካፒታሊዝምን በመቃወም ያሰሙ የነበረው መፈክር ለዚህ በአብነት የሚቀርብ ነው፡፡ ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚካሄደው የካፒታሊዝም የነጻ ገበያ ፍልስፍና ከውድድር፣ ከሃብት ክምችትና ከሉላዊነት መርሆዎች ጋር ተዋህዶ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች፣ በግብይት ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ታዳጊ ሃገሮች ውስጥ የሚመረተውም ምርት፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አብዛኛው ዜጎች ተወዳድረው መሸመት ስለማይችሉና ምርቱን አቅም ያላቸው የውጪ ሀገር ነጋዴዎች በፍጥነት ስለሚረከቡት፣ በሃገር ውስጥ ምርቱ ተመርቶ (supply) እያለ የዜጎችን የሸቀጥ ፍላጎት (Demand) ማሟላት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ በካፒታሊዝም የህይወት ፍልስፍና ውስጥ ውድድር እጅግ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ ውጤታማነት ማለት በማንኛውም መልኩ፣ በየትኛውም መንገድ ከሌላው በልጦ መገኘት ነው፡፡
በጀርመናዊው የምጣኔ ሃብትና ማህበረሰብ ሳይንስ ሊቅ ማክስ ዌበር (Max Weber) Formal Rationality መርህ ላይ የተመሰረተው የካፒታሊዝም የውድድር ፍልስፍና፣ በወጪ ቀሪ (cost benefit) ስሌት የተቀመረ ነው፡፡ በመሆኑም ግለሰቡ በስሌቱ መሰረት ድርጊቱ ሌላውን ለመብለጥ የሚያስችል፣ ከኪሳራው ትርፉ ከበለጠ ወይም አዋጭ መስሎ ከታየው ማንኛውንም ሃላፊነት የጎደለውና ህገ ወጥ የመበልጸጊያ መንገዶችን ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ ይህንንም ጀርመናዊው ፈላስፋ፣ ሰዎችን እንደሰዎች (life world) ሳይሆን እንደ ሸቀጥ የሚያወርድ፣ ራስን ያማከለና ሌሎችን ያላገናዘበ ገንዘብ ተኮር (impersonal) የኑሮ ፍልስፍና ነው ይላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ዌበር The Protestant Ethic and the spirit of Capitalism (1905) እና The Religions of the East (1920) በተባሉት ስራዎቹ ካፒታሊዝም በምዕራቡ ዓለም በቀላሉ ለመስፋፋት የቻለውና በምስራቁ እንዳይስፋፋ የሆነበት ምክንያት የማህበረሰቡ ስነምግባራዊና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ብርቱ ተጽዕኖ ስለነበራቸው ነው ይላል፡፡
በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና፣ ሰዎች በውድድር መንፈስ ውስጥ ስለሚኖሩ እርካታን የሚጎናጸፉት የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማሟላት ወይም በማድረግ ሳይሆን የሚፈልጉትን ነገር በማድረግ ነው፡፡ የሚፈልጉት ነገር ደግሞ በውድድሩ ውስጥ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በድረገጾች ላይ በማስታወቂያ ቋንቋ ተውበው የሚቀርቡትን ወይም በኢኮኖሚያቸው ወይም በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው የክብር ስፍራ ላቅ ብለው የሚታዩ ግለሰቦችን ምርጫ አብነት በማድረግ የሚመነጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ምቾት ያለው ወይም ጥሩ ኑሮ እየኖረ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው፣ ሰው ገንዘቡን ለሚያስፈልገው ነገር (for necessiety) የሚያወጣ ሳይሆን ከቢጤዎቹ ጋር ተወዳድሮ በልጦ ለመታየት ለሚያበቃው ነገር በከፍተኛ ደረጃ የሚያወጣ ነው፡፡ ይህም ፋሽን ልብሶችና ጫማዎች በመከተል፣ የመኪና ሞዴሎችን በመቀያየር፣ እንዲሁም ሌሎች የቅንጦት እቃዎችን በመግዛት የሚገለጽ ነው፡፡
በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና፣ የአንድን ሸቀጥ ዋጋ ለመተመን በጣም አስፈላጊው ጉዳይ ሸቀጡ የሚሰጠው አገልግሎት፣ ብዛት ወይም ጥራት ሳይሆን ህብረተሰቡ ለሸቀጡ ያለው ስነልቡናዊ እሴት (value) ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ቱርክ ውስጥ የተመረተ ጫማ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመረተው አንጻር የተሻለ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ጫማው ካለው ጥንካሬ ወይም ከተሰራበት ጥሬ ዕቃ ወይም ከዲዛይኑ ማማር የተነሳ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ስነልቡና ከአፍሪካውያን ምርት ይልቅ የአውሮፓውያን (brand) ተሻለ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚወሰድና ዋጋውም የበለጠ ስለሆነ፣ በተመልካች ዘንድ የተለየ የክብር ቦታ ያሰጣል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተቦጫጨቀና የተጣጣፈ ጂንስ ሱሪ በውድ ገንዘብ ገዝቶ መልበስ እንደ ፋሽን ተይዟል፡፡
ለመሆኑ ፋሽን ምንድን ነው? ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት የሚገባው ለምን ዓይነት ልብስ ነው? ለዚያ ለተቀዳደደ ልብስ በምን አይነት አመክንዮ ያን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ለማውጣት ወሰኑ? በርግጥ ዲዛይነሮቹ በአውሮፓ ወይም በአሜሪካን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳደደውንና የተጣጣፈውን ልብስ ሲያቀርቡ ዲዛይኑን ላዘጋጁለት የተለየ ማህበረሰብ አንዳች ትርጉም እንዲሰጥ አድርገው፤ ወይም ከአንድ ሁነታ (event) ጋር አስታከው ሰርተውት ይሆናል፤ ለእኛ ለኢትጵያውያንስ…?! በእኔ አስተሳሰብ በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና ከሌሎች መወዳደርና እኩል ሆኖ ወይም በልጦ መታየት ታላቁ የውጤታማነት የኑሮ ፍልስፍና (life success) ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ ማንኛውም ሸቀጥ ታላቅነት የሚለካው በሚሰጠው አገልግሎት ብዛትና ጥራት ሳይሆን በሚያወጣው የገንዘብ መጠን ከፍተኛነት ነው፤ ምክንያቱም ፍልስፍናው ከሌሎች በልጦ ወይም ተመሳስሎ መገኘት ነውና፡፡
የሚገርመው ነገር ጥሩ ወይም የሚያምር የሚባለው ልብስ እንኳ የሚለየው ከብራንዱ ወይም ከተከፈለበት ከፍተኛ ዋጋ አንጻር ነው፡፡ በካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና በጭፍን የሚመሩ ግለሰቦች አንድ ሸቀጥ ስሪቱ ጥሩም ይሁን መጥፎ ምርጫቸው ዋጋው ከፍተኛ የሆነው ብቻ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አንድ ተመሳሳይ ዕቃ ሁለት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከትርፍና ኪሳራ ስሌት ውጪ በሆነ እጅግ በጣም የተራራቀ ዋጋ ሲሸመት መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ አሁን አሁንማ ይባስ ብሎ ሸቀጦችን ተገቢ በሆነ ዋጋ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች የሸቀጦቻቸው ዋጋው ዝቅተኛ ስለሆነ ብቻ ጥራት እንደሌለው ተደርጎም እየታሰበ ነው፡፡ የካፒታሊዝም የኑሮ ፍልስፍና፣ የግል ሀብት ማከማቸትን ስለሚያበረታታና የሃብት አሰባሰቡና አጠቃቀሙ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በግለሰቡ ፍላጎትና በውድድር ላይ የተመሰረተ ስለሆነ፣ በግለሰቦች መካከል ከትብብር ይልቅ የፉክክር ስሜትን ይፈጥራል፡፡ የግል ሃብትን የማከማቸት ጥማት በራስ ወዳድነት (egoistic) የስነምግባር ፍልስፍና መመራትን የግድ ይላል፡፡ በራስ ወዳድነት የተቃኘ የሃብት ሽሚያ ወይም ስግብግብነት ደግሞ ለሀገር ፍቅር ስሜት መቀዝቀዝ፣ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር ይዳርጋል፡፡
ሃገራችን በልማት ጉዞዋ ላይ ዛሬ የተጋደመባት ጋሬጣም ይኸው ነው፡፡ በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ሲመደቡ የሚያስጨንቃቸው የትኛውን የትምህርት ዘርፍ ብመርጥ ለወገን ብሎም ለዓለም የሚተርፍ የምርምር ውጤት አበረክታለሁ ሳይሆን በየትኛው መስክ ብሰማራ ከሌሎች የተሻለ ገንዘብ አገኛለሁ የሚለው ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በምርቃታቸው ዋዜማ ውይይታቸው ተመርቄ እንዴት ሃገሬን አገለግላለሁ ሳይሆን በየትኛው አቋራጭ ተጠቅሜ በአጭር ጊዜ እበለጽጋለሁ የሚል ነው፡፡ በመጨረሻም የካፒታሊዝምን ፍልስፍና አስከፊ ገጽታ አስቀድሞ መመልከት የቻለው ካርል ማርክስ፣ የካፒታሊዝምን ስርኣት ገርስሶ በሶሻሊዝም ብሎም በኮሚውኒዝም ስርአት መተካት ብቸኛው መፍትሄ እንደሆነ ከጓደኛው ፍሬዴሪክ ኤንግልስ ጋር በአንድነት ባሳተመው The Communist Manifesto በተባለው መጽሀፉ በዝርዝር አስረድቷል፡፡
ከዚህም አልፎ ምዕራቡ ዓለም ካፒታሊዝምን የሙጥኝ ባለባቸው ዘመናት፣ ምስራቁ ዓለም የማርክስን ፍልስፍና በተግባር ለመተርጎምና የቀረውን ዓለም በማርክሲስት ፍልስፍና አጥምቆ የሃብት እኩልነትን በማረጋገጥ፣ ዓለምአቀፋዊ ትብብርን ለማስፈን የሞት ሽረት ትግል አካሂዶ ነበር፤ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት፡፡ ይህም ውጥረት ከቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት መበታተን በኋላ ተዳፍኖ ለየት ባለ መልኩ በኩባ፣ በተወሰኑ የላቲን አሜሪካ ሀገሮች እንዲሁም በቻይና በዝቅተኛ ደረጃ በመተግበር ላይ የሚገኝ ቢሆንም ካፒታሊዝምን በሶሻሊዝም መተካት ግን ለካፒታሊዝም የስነምግባር ዝቅጠት የተሻለ መፍትሄ መሆን እንደማይችል ከታሪክ ተምረናል፡፡
እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ አርዌል የእንስሳት እድር (Animal Farm) በተባለው ዘይቤያዊ ድርሰቱም አሳይቶናል፡፡ ይሁንና ባለንበት ዘመን በርካታ ሃገሮች ይህንኑ የካፒታሊዝም ኢ-ሥነምግባራዊ አስተሳሰብ በመገንዘብ ከካፒታሊዝምና ከሶሻሊዝም ፍልስፍና በጎ በጎው ተውጣጥቶ የተሰናዳ ቅይጥ ኢኮኖሚ (Mixed Economy) የሚባል የምጣኔ ሃብት ፍልስፍና በመከተል ላይ ይገኛሉ፡፡ ጀርመናዊው ፈላስፋ ሃቤርማስ (Jurgen Habermas) ደግሞ በበኩሉ ለምዕራባውያን የካፒታሊዝም ፍልስፍና የስነምግባር ዝቅጠት ዋነኛ ምክንያት በወጪ ቀሪ (cost benefit) ስሌት የተቀመረው የማክስ ዌበር Formal Rationality መርህ ስለሆነ መፍትሄው በምዕራባውያን የኢንዱስትሪ ዲሞክራሲ፣ የሰው ልጆችን ዓለም (life world) በሸቀጥ ደረጃ አውርዶ፣ በሂሳብና በገንዘብ የሚተምነውን ፍልስፍና communicative action በተባለው የሃቤርማስ ፍልስፍና መንገድ መተካትና ዜጎች ከመንግስታቸው ጋር እንደ ካፒታሊዝም ባሉ ስነምግባራዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በአመክንዮ ተወያይተው እንዲተማመኑ ማድረግ ነው ይላል፡፡ እርስዎስ ታዲያ ምን ይላሉ?

No comments: