Thursday, March 14, 2013

መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች ...

“የጥናት ቡድኑ አስራ ሁለት የሚሆኑ የቀን ጭፈራ ቤቶችን ለመመልከት የበቃ ሲሆን ከጭፈራ በተጨማሪም ሲጋራ ማጨስ ፣መሳሳም ... ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደጉዋሮ በመውጣት ለወሲብ ክፍሎችን መከራየት... በወንበር ፣በአግዳሚ ወንበር፣ ሶፋ፣ መሬት ...ምንም ቦታ ሳይመርጡ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የየራሳቸውን ስሜት ለማርካት ወሲብ ይፈጽማሉ፡፡ በጭፈራ ቤቶች አካባቢ መኪና ውስጥ ጫት ይዘው የሚቀመጡ ወንዶች ሴት ሕጻናቶቹ ከጭፈራው ቤት ሲወጡ ጠብቀው ለወሲብ አገልግሎት ይዘዋቸው ይሄዳሉ” አቶ ስንታየሁ ደመቀ...የጥናቱ አስተባባሪ
መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች ...በወጣቶችና ሰቶች ላይ እያስከተሉት ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለይቶ ለማወቅ እንዲረዳን ተገቢው እርምጃ በሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እንዲወሰድ ለማስቻል የአዲስ አበባ ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ከሌሎች ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ጥናት አድርጎ ይፋ አድርጎአል፡፡
በዚህ እትም የለሊት እና የእራቁት ጭፈራ ቤቶችን
የማሳጅ አገልግሎትን እንደሽፋን በመጠቀም የሚሰሩ የወሲብ መስተንግዶዎችን እንዲሁም የጫት መቃሚያና ሽሻ ማጨሻ ቤቶችን ተግባር ታነቡ ዘንድ እነሆ ብለናል፡፡ ምንጫችን አቶ ስንታየሁ ደመቀ በአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ወጣቶችን የማሳተፍና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ መሪ እና የጥናቱ አስተባባሪ ናቸው፡፡
ኢሶግ፡ የሌሊት እና እራቁት ጭፈራ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል ይገኛሉ?
አቶ ደመቀ፡ የሌሲት ጭፈራ ቤቶችን በሚመለከት በአዲስ አበባ በአስሩም ክ/ከተሞች
ውስጥ እንደሚገኝ የጥናት ቡድኑ ተመልክቶአል፡፡ የጭፈራ ቤቶቹ በከፊል ሕገወጥ ስራ የሚሰሩ ሲሆን ...ለምሳሌ ወሎ ሰፈር አካባቢ ቡድኑ የተመለከተው ጭፈራ ቤት ገና ከበሩ መግቢያ ላይ በጣም ትልቅ በሆነ ከሰል ማንደጃ እሳት ተሞልቶ ተቀምጦአል፡፡ ወደውስጥ ሲገባም በእያንዳንዱ ጠረጴዛ ላይ ሽሻ ማጨሻ ለተስተናጋጁ ተዘጋጅቶአል፡፡ ምናልባትም ተስተናጋጆቹ በሙሉ ማለት ይቻላል ...ሽሻ የማይስብ የለም፡፡ ከዚያም ሙዚቃው ከባህላዊ እና ከታዋቂ ዘፋኞች ጀምሮ ቀስ በቀስ እየተቀየረ ይሄዳል፡፡ እንደሙዚቃው ሁሉ ጨፋሪዎቹም ቀስ በቀስ ልብሳቸውን እየቀየሩ በመሄድ ከሌሊቱ ስድስት ሰአት በሁዋላ ጭፈራ ቤቱ ሙሉ በሙሉ መልኩን ይለውጣል፡፡ በአንድ መድረክ እድሜያቸው ከ25-26 የማይበልጡ ቆነጃጅት እና ቁመናቸው ያማረ ሴቶች በአጭር እና ስስ ልብስ ይጨፍራሉ፡፡
ታዳሚዎቹ ሀብታም ነጋዴዎች ፣ጥቁር ዲፕሎማቶች ባለስልጣናት እና ለሎችም ገንዘብ ያላቸው ስለሆኑ ገንዘብ ሲሸልሙ ማንንም በሚያጉዋጉዋ መንገድ ልኩ ሳይታወቅ እያፈሱ ወደመድረክ ወይንም ወደ ተዘጋጀው ቦታ ይበትናሉ፡፡ እንደዚህ ያለው ልምድ የሀገራችን ሳይሆን ከውጭ የተወረሰ ነው፡፡ ሁኔታውም ጎጂ ጎን ያለው ሲሆን ሺሻ መሳብ ፣በአልኮሆል ሱስ መያዝና ልቅ ወደሆነ ወሲባዊ ድርጊት የሚመራ ነው፡፡ በጭፈራው ቤት የሚታደሙት ትልልቅ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ተማሪዎችም ጭምር ናቸው፡፡
የእርቃን ወይንም እራቁት ጭፈራ ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ምናልባት ከአስር አመት በፊት በነበረበት ሁኔታ ሳይሆን እጅግ ተስፋፍቶ የሚገኝ መሆኑን የጥናት ቡድኑ ታዝቦአል፡፡ በጣም ውስን በሆነ አቅምና ጊዜ ወደ ስድስት የሚሆኑ ጭፈራ ቤቶችን የተመለከተ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱ ማንም ሰው ያለብዙ ቁጥጥር የሚገባባቸው ናቸው፡፡ አንዱ ጭፈራ ቤት ደግሞ በጣም ድብቅ ሲሆን ሁለቱ በጣም ጥንቃቄ የተሞላባቸው ናቸው፡፡ ማንም ሰው መግባት ሲፈልግ የመኪናው ታርጋ በጥንቃቄ ታይቶ ተፈትሾ በአይነቁራኛ ተመርምሮ ወደውስጥ ይገባል፡፡
ከእራቁት ደናሾች መካከል አንዱዋ እንደሰጠችው እማኝነት ለዚህ ስራ ይመጥናሉ የሚባሉት ሴቶች የሚመለመሉት ከዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን መግፋት ያልቻሉ ወይንም ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፣የገንዘብ እጥረት ያለባቸው ወይንም ቤተሰባቸውን በገንዘብ መደጎም የሚፈልጉ ቆንጆና ቁመና ያላቸው ሲሆኑ ስልጠናው የሚሰጣቸውም ከሱዳን በመጣች የእራቁት ዳንስ አስተማሪ ነው፡፡
የእርቃን ዳንሱ ለስም ያህል ጡት መያዣና ሙታንታ ያደረጉ ሲሆን ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ሰውነትን ማየት የሚያስችል ስስ ልብስ ነው፡፡ ከተወሰነ ጭፈራ በሁዋላ ሌሊት ለይ ዳንሰኞቹ ከመድረክ እየወረዱ በወንዶች ጭን ላይ መቀመጥ አንዱ ተግባራቸው ሲሆን ምናልባት የሚቃወም እንኩዋን ከተገኘ ጎሽመውና ገላምጠው ትተው እንደሚሄዱ የጥናት ቡድኑ ለመመልከት በቅቶአል፡፡ እነዚህ ዳንሰኞች ከዳንስ ቤቱ ውጭ አቅሙ ወዳላቸው ሰዎች ቤት በቀጠሮ እየሄዱ የሚያዝናኑ ሲሆን በኮንትራት ወደ አረብ አገሮችም ለተወሰነ ጊዜ እየሄዱ የዳንስ ስራን ይሰራሉ፡፡ ይህ ድርጊት ትውልድን ወደየት እየመራው ነው ብለን ስንጠይቅ ...የጥፋት መድረክ ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ድርጊት ፈጻሚዎቹም ሆኑ ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡
ኢሶግ፡ የማሳጅ ቤቶች አገልግሎት በጥናቱ ሲፈተሸ ምን መልክ አለው?
አቶ ደመቀ፡ የማሳጅ ቤቶቹ ፈቃድ አውጥተው በትክክለኛው መንገድ የሚሰሩ የሚገኙ ሲሆን
አንዳንዶቹ ግን ከእስፖርታዊና ከጤና አገልግሎት ውጭ ወሲባዊ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ የማሳጅ ቤቶቹ አገልግሎት የሚሰጡት በቪላ ቤቶች፣ በኮንዶሚኒየም የጋራ መጠቀሚያ ቤቶች ጭምር ሲሆን የአንዳንዶቹ መስተንግዶ እጅግ በሚገርም ሁኔታ የወሲብ ግብዣ ነው፡፡ የጥናት ቡድኑ ሁኔታውን ለማረጋገጥ ቀጠሮ በመቀበልና ወደስፍራው በመሄድ መስተንግዶውን አይቶአል፡፡ በማሳጅ ቤቶች ውስጥ ...
መታሸት፣
የሚታሸው ሰው ከምታሸው /ከሚያሸው ጋር ...እየታሹ ማሸት፣
ወሲብ መፈጸም ... የሚባሉ የአገልግሎት ደረጃዎች አሉ፡፡
በቅድሚያ አገልግሎት ፈላጊው በምን መልክ ሊስተናገድ እንደሚፈልግ እንዲናገር ከተደረገ በሁዋላ በስምምነት ተግባሩ ይፈጸማል፡፡
የጥናት ቡድኑ ተሳትፎአዊ ምልከታ እንዲያደርጉ የተመደቡ ሰዎች ያሉት ሲሆን በማሳጅ ቤቱ ሁኔታውን እስከሁለተኛው ደረጃ ተሳትፈው ወደሶስተኛው ሳያመሩ አቋርጠው በመውጣት እውነታውን አረጋግጠዋል፡፡
ኢሶግ፡ ሽሻ መሳቢያ እና ጫት መቃሚያ ቤቶች አገልግሎት ምን ይመስላል?
አቶ ደመቀ፡ ሽሻ እና ጫት ቤቶች በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተማዎች በተለይም
በዩኒቨርሲቲዎችና በትምህርት ቤቶች አካባቢ በቀላሉ የሚገኙ ሲሆን ሴቶችና ወጣቶች በስፋት ይዝናኑበታል የሚባል ቦታ ነው፡፡ በአዲስ ከተማና በድሮ ቄራ እንዲሁም በቦሌና አንበሳ ጋራዥ አካባቢ ተስተናጋጆቹ ተማሪዎች ጭምር ሲሆኑ ተማሪዎቹ ከነዩኒፎርሞቻቸው ያለምንም መሳቀቅ ገብተው የሚዝናኑበት ነው፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጠውም ...
ለሚፈልጉ ሰዎች ለእራሳቸው እየቀነጠሱ መቃም ፣
በመቀጠል ደግሞ ሴቶች ከቃሚው አጠገብ ቁጭ ብለው እየቀነጠሱ በመስጠት እየቃሙ ማስቃም ፣
በስተመጨረሻ ለሚፈልጉ ሰዎች የወሲብ አገልግሎት መስጠት ...በሚል የተከፈለ አገልግሎት በጫት መቃሚያ ቤቶች ይሰጣል፡፡
የጫት መቃሚያ ቤቶች በየደረጃው መስተንግዶ የሚሰጡባቸው ቤቶች የተለያዩ ሲሆኑ ሰዎች እንደፈለጉ የሚሆኑባቸው የተለያዩ ክፍሎችም አሉዋቸው፡፡ ጫት እየቀነጠሱ የሚያስቅሙና እራሳቸውም የሚቅሙ ሴቶች አጫጭር ልብስ ወይንም ሰውነትን የሚያሳይ ስስ ልብስ የሚለብሱ ናቸው፡፡ ጫት ቤቶች እንደሚታሰበው በቀላሉ ጫት ብቻ የሚቃምባቸው ሳይሆኑ ተማሪዎች ፣ባለትዳሮች ፣የተለያየ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በገፍ የሚገቡባቸውና ብዙዎችን ወደተሳሳተ የህይወት መስመር የሚመሩ ናቸው፡፡
ኢሶግ፡ የኮንዶም አጠቃቀም ምን ይመስላል?
አቶ ደመቀ፡ በማሳጅ ቤቶቹ በሻማ ብርሀን ወይንም በደብዛዛው ክፍል ኮንዶም ተዘጋጅቶ
እንደሚጠብቅ ለመመልከት ተችሎአል፡፡ ነገር ግን የተጠቃሚዎቹ ማንነት ይወስነዋል፡፡ በቀን ጭፈራ ቤት የሚገለገሉት ሕጻናት ተማሪዎች ሲሆኑ እነዚህ ልጆች ወደስፍራው የሚሄዱት ለመጨፈር እንጂ ሌላ ነገር አስበው አይደለም፡፡ ወደወሲባዊ ግንኙነት የሚያመሩትም ብዙ ጨፍረው ፣አልኮሆል ወስደው ፣ሲጋራ አጭሰው ፣እራሳቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸውና ባገኙበት ቦታም ስለሆነ ኮንዶም ይጠቀማሉ የሚለውን ነገር ማሰብ ይከብዳል፡፡ ሌሎቹ ጭፈራ ቤቶችና ጫት ቤቶቹ ጋም ቢሆን የተስተናጋጆቹ ማንነት እና ጥንቃቄ የሚወስነው ጉዳይ ነው ፡፡ ስለዚህ በእንደዚህ ያሉ ቤቶች የሚዝናኑ ሰዎች ለአባላዘር በሽታ ለኤችአይቪና ሌሎችም ጉዳቶች ሊዳረጉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡
ኢሶግ፡ በጥናት የተገኙትን አስከፊ ድርጊቶች ለማረም ማ...ምን ያድርግ?
አቶ ደመቀ፡ በዚህ ድርጊት ተወቃሹ ማነው ቢባል ሁሉም ነው ይሆናል መልሱ፡፡ ተቋማት
የንግድ ፈቃድ ሲሰጡ አስፈላጊውን ክትትል የሚያደርጉበት መንገድ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሰዎች ቤታቸውን ለንግድ ስራ ሲያከራዩ ምን እንደሚፈጸምበት ማየት ግዴታ ይሆናል፡፡ ለጥናት ከተመረጡ ትምህርት ቤቶች መካከል በአንዱ ተማሪዎች ከያዙት ሞባይል 80ኀ ያህሉ የወሲብ ፊልም ተጭኖበት ለማየት ተችሎአል፡፡ ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው ገንዘብና ሞባይል እየገዙ መስጠት ብቻ ሳይሆን ምን እየተፈጸመበት ነው ማለት አለባቸው፡፡ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ለሚያዘጋጁዋቸው እንደ... የእብደት ቀን ...የቀለም ቀን የመሳሰሉትን ሁሉ ማስተካከል ይገባቸዋል፡፡ መገናኛ ብዙሀኑ የሚያስተላልፉዋቸውን መልእክቶች ...ፊልሞች ...ወዘተ ወጣቱን በተገቢው መንገድ ሊቀርጽ የሚችል መሆኑን መፈተሸ አለባቸው፡፡ የህጉ ቁጥጥርም መላላት የለበትም፡፡ በዚህ መልክ ሁኔታዎችን ማስተካከል ካልተቻለ አዝማሚያው አስከፊ ይሆናል፡፡

No comments: