Thursday, March 28, 2013

ተገኝወርቅ ጌቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊ ሆነው ተሾሙ


   
አዲስ አበባ መጋቢት 18/2005 ኢትዮጵያዊው ተገኝወርቅ ጌቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔና የጉባዔዎች ማኔጅመንት ረዳት ዋና ፀሐፊ ሆነው ተሾሙ። አቶ ተገኝወርቅ መቀመጫቸው በኒው ዮርክ፣አሜሪካ ሆኖ በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ በጄኔቫ፣በቪዬናና በናይሮቢ ከተሞች የሚገኙትን ሁለት ሺህ 200 ሠራተኞችን በበላይነት ይመራሉ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን ኃላፊነቱ የተሰጣቸው አቶ ተገኝወርቅ በዋና መሥሪያ ቤቱ ያሉትን አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠራተኞችን በቀጥታ
ያስተዳድራሉ። አቶ ተገኝወርቅ ክፍሉን በተጠባባቂነት ሲመሩ የነበሩትን ቤልጂያማዊውን ዣን-ጃኩዬ ግራዪሲን በመተካት ሥራውን እንደሚቀጥሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን የጠቀሰው የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል። ከነዚህም መካከል የኮሚቴ ፀሐፊዎች፣የተመራማሪዎች ረዳቶች፣የስብሰባ አዘጋጆች፣የፕሮቶኮል መኮንኖች፣አስተርጓሚዎችና አርታኢዎች፣የግራፊክ ዲዛይን ባለሙያዎች ይገኙባቸዋል። ተሿሚው በዋና መሥሪያ ቤቱ ባሳዩት በተግባር የተፈተነ ብቃትና ዕውቀትና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ውስብስብነት የተሞላባቸው ሥራዎችን መምራታቸው በአዲሱ ኃላፊነት መመደባቸውን ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ ያስረዳል። ላለፉት 30ዓመታት በብሄራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃዎች በልማት መስክ በመሰማራት ያስመዘገቡት ውጤት እንዲሁም በትምህርት በመንግሥትና በግል ዘርፎች ያከናወኗቸው ሥራዎች ተመራጭ እንዳደረጋቸውም አመልክቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቢሮ ረዳት ዋና ፀሐፊ ሆነው ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በመሥራት ላይ የነበሩት አቶ ተገኝወርቅ፣የፕሮግራሙ ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተርና በናይጄሪያ የፕሮግራሙ ተጠሪ ሆነውም ሰርተዋል። በኮሎምቢያ፣በሮቸስተርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎችና በሃንተር ኮሌጆችም ማስተማራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

No comments: